
የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢራን የተጣሉባት ማዕቀቦች በሙሉ የሚነሱላት
ከሆነ በከፍተኛ መጠን ያበለጸገችውን ዩራኒየም የጥራት ደረጃ ዝቅ ለማድረግ ልትስማማ እንደምትችል የአገሪቱ የአቶሚክ ኃላፊ መናገራቸውን
የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘገበ።
ኢራን ያቀረበችው ይህ ሐሳብ ከአሜሪካ ጋር
እያደረገችው ባለችው ድርድር በግልጽ አቋሟ የተንጸባረቀበት ተደርጎ ተቆጥሯል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የባሕር
ኃይላቸውን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ማሰማራቸውን ተከትሎ በዋሽንግተን እና ቴህራን መካከል ጦርነት ይነሳል የሚል ስጋት በርትቶ ቆይቷል።
ይህ ስጋት ማየሉን ተከትሎም የአሜሪካ እና ኢራን ዲፕሎማቶች ካለፈውሳምንት ጀምሮ በኦማን አደራዳሪዎች አማካኝነት ኦማን ውስጥ ንግግር
እያደረጉ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቋም ባለፈው
ዓመት ይፋ ያደረገው ግምት እንደሚያሳየው ኢራን ከ400 ኪሎ ግራም በላይ የሆነ ዩራኒየም አከማችታለች። የኢራን ዩራኒየም እስከ
60% የሚደርስ የጥራት ደረጃ እንዳለውም ተገልጿል።
ዩራኒየም ለጦር መሣሪያነት ደረጃ ደርሷል የሚባለው
90% ጥራት ሲኖረው ሲሆን የኢራን ክምችት እዚህ ላይ ለመድረስ አንድ እርምጃ ብቻ የቀረው እንደሆነም ተቋሙ አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ
የአየር ድብደባ የፈጸመችው አሜሪካ፤ ይህን የዩራኒየም ክምችት እንድትተው ትፈልጋለች።
የኢራን የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ኃላፊ መሐመድ
ኢስላሚ፤ "60 በመቶ የበለጸገውን ዩራኒየም የመበረዝ (diluting) አማራጭ... በምላሹ የተጣሉብን ሁሉም ማዕቀቦች
ይነሳሉ ወይስ አይነሱም በሚለው ላይ የተመሰረተ ነው" ብለዋል።
እስካሁን ድረስ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር በተደረገው
ንግግር የኢራንን የበለጸገ ዩራኒየም ወደ ሌላ አገር የመላክ ሐሳብ እንዳልተነሳም ኃላፊው መናገራቸውን የኢራን የዜና ወኪል አይኤስኤንኤ
ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ
አሊ ኻሜኒ የቅርብ አማካሪ እና የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊ የሆኑ አሊ ላሪጃኒ፤ ከአሜሪካ ጋር ድርድር እየተደረገባት ወዳለችው
ኦማን እንደሚጓዙ ተዘግቧል።
"በዚህ ጉዞ [ላሪጃኒ] ከኦማን ከፍተኛ
ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ስለ ወቅታዊው ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች እንዲሁም ስለ ሁለትዮሽ ትብብር ይመክራሉ"
ሲል ከፊል ይፋዊ የዜና ወኪል የሆነው ታስኒም ዘገባ አመልክቷል።
ቀጣዩ ዙር የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር የሚካሄድበት ጊዜ እና ቦታ እስካሁን አልታወቀም።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን፤ ቀጣዩ ዙር ንግግር "ለዚህ
ጉዳይ ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ መፍትሄ ለማግኘት የሚያስችል ተገቢ አጋጣሚ ነው" ብለዋል።
አሜሪካ ከፍተኛ ጫናዎችን ከማሳደር ከተቆጠበች
እና ቃሏን የምታከብር ከሆነ ተፈላጊው ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻልም ገልጸዋል።