አሜሪካ በዓለም ትልቁ የጦር መርከቧን ከቬንዙዌላ የባሕር ዳርቻ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አንቀሳቀሰች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ በዓለም ካሉ ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች ትልቁ የሆነውን እና ወደ ቬንዙዌላ የባሕር ዳርቻ አሰማርታው የነበረውን የጦር መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲያቀና አዘዘች።
አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው ዩኤስኤስ ጄራርድ ፎርድ የተባለው ግዙፍ የጦር መርከብ “ከካሪቢያን ባሕር ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲጓዝ” ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።
የዜና አገልግሎቱ ከአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ምንጭ ጠቅሶ እንዳመለከተው “ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል ባሉት መሠረት” የጦር አውሮፕላን ተሸካሚው መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተንቀሳቅሷል።
በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ሦስት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ “ጄራርድ ፎርድ የጦር መርከብ እና አጋዥ መርከቦች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል” በማለት ዜናውን አረጋግጧል።
እጅግ ዘመናዊ የሆነው ይህ አውሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ የጦር መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሲያመራ ከሳምንታት በፊት ወደ አካባቢው የተሰማራውን አብርሃም ሊንከን የተባለውን ሌላ ተመሳሳይ መርከብን በመቀላቀል ከፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ይጠብቃሉ።
አሶሺየትድ ፕሬስ እንዳለው አሁን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲጓዝ የታዘዘው ጄራርድ ፎርድ የጦር መርከብ ባለፈው ጥምት ወር ነበር ከሜዲትራኒያን ባሕር ተነስቶ ቬንዙዌላ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ወደ ካሪቢያን የደረሰው።
አሁን ደግሞ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲያቀና የታዘዘው አሜሪካ እና ኢራን የሚያደርጉት ድርድር ውጤት የማያስገኝ ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ በኢራን ላይ እንደሚወስዱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተናገሩት መሠረት ጫና ለመፍጠር ሊሆን እንደሚችል ዎል ስትሪት ጆርናል ከሁለት ዘግቦ ነበር።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ባለፉት ቀናት ተጨማሪ የጦር መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንደሚያሰማሩ እና “ፕሬዝዳንቱ ሁሉንም አማራጮች እንደሚጠቀሙ” ገልጸው፤ ነገር ግን ቅድሚያ የሚሰጡት ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ መድረስ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters





















