ማርኮ ሩቢዮ አሜሪካ ዓላማዎቿን በማሳካቷ ኢራን ላይ የከፈተችው የማጥቃት ዘመቻ “አብቅቷል” አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ማክሰኞ ዕለት በዋይት ሐውስ በሰጡት መግለጫ ዩናይትድ ስቴትስ ዓላማዎቿን በማሳካቷ በኢራን ላይ የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ “መጠናቀቁን” ገለጹ።
አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ነበር።
ሩቢዮ በዋይት ሐውስ በሰጡት በዚህ መግለጫ “ኦፕሬሽን ኢፒክ ፉሪ ተጠናቅቋል። የዘመቻውን ዓላማዎቻችንን አሳክተናል፤ . . . የሰላም መንገድን እንመርጣለን። ፕሬዚዳንቱ ከስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ሩቢዮ አሜሪካ ሰኞ ዕለት አዲስ የጀመረችው ዘመቻ ዓላማ የሆርሙዝ ወሽመጥን ማስከፈት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ አነስተኛ መጠን ያለው ዘመቻ ከመጀመርያው ወታደራዊ ዘመቻ የተለየ መሆኑን በመግለጽ አሜሪካ “ካልተተኮሰባት በስተቀር” ወታደራዊ ምላሽ እንደማትሰጥ ተናግረዋል።
አሜሪካ በኢራን ኣለይ ጦርነት የከፈተችበት አንዱ ምክንያት የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳታመርት ለመከላከል ነው።
አሜሪካ የኢራንን በከፍተኛ ደረጃ የበለጸገ 408 ኪሎ ግራም ዩራኒየም ማውጣት እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመርከቦች እንቅስቃሴ ክፍት ማስደረግ እስካሁን ድረሰ አልቻለችም።

የፎቶው ባለመብት, Amirhosein Khorgooi/ISNA/WANA (West Asia News Agency) via REUTERS
ሩቢዮ በመግለጫቸው ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ መንቀቀሳቀስ ላልቻሉ መርከቦች መንገዱን ለማስከፈት የተጀመረው ዘመቻ ከ87 አገራት የተውጣጡ የ23ሺህ ሰዎችን ሰቆቃ የሚያስቆም ነው ብለዋል። በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ባለው ግጭት ምክንያት እስካሁን ድረስ 10 ባህረተኞች መሞታቸውን ተናግረዋል።
“ተነጥለው ነው ያሉት፤ እየተራቡ ነው፥ ተጋላጭ ናቸው። ቢያንስ 10 ባህረተኞች በዚህ የተነሳ ሞተዋል፤ ሲቪል ባህረተኞች” ብለዋል።
ሩቢዮ ሞቱ ስላልዋቸው ባህረተኞች ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሩቢዮ ከበርካታ መርከቦች ጋር የሆርሙዝ ወሽመጥን አቋርጦ ስለመውጣት በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ሩቢዮ አሁን ጊዜው ቴህራን “የሁኔታውን እውነታ የምትቀበልበት ነው” በማለት የአሜሪካ ልዑካን የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነር የዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ መፈለጋቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።
ሩቢዮ አክለውም መፍትሄው ኢራን “የሆነ ስፍራ የደበቀችውን የኒውክሌር ቁስ ይመለከታል” ሲሉ ተናግረዋል
"ፕሬዚዳንቱ የድርድር ሂደቱ አካል የበለጸገው [ዩራኒየም] ብቻ ሳይሆን የሆነ ስፍራ የቀበሩትን ቆፍረው ማውጣት ከቻሉ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ግልጽ ነው " ብለዋል።
ሩቢዮ በሁለቱ አገራት መካከል እየተካሄደ ነው ስለሚባለው ውይይት ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
“ይህ በጣም ውስብስብ ነው፤ በጣም ቴክኒካዊ ነው። ነገር ግን እነሱ ለመደራደር ፍቃደኛ ስለሆኑባቸው ርዕሰ ጉዳዮች እና እነዚያን ንግግሮች ጠቃሚ ለማድረግ በግንባር ቀደምትነት ሊያደርጉት ስለሚችሉት መጠን በጣም ግልፅየሆነ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ሊኖረን ይገባል" ብለዋል።





















