አሜሪካ ጦርነቱን ለመቋጨት የኢራንን ምላሽ እየጠበቀች ሳለ ነዳጅ የጫነች መርከብ በሆርሙዝ በኩል አለፈች

አሜሪካ ላቀረበችው የሰላም ዕቅድ የኢራንን ምላሽ እየጠበቀች ሳለ ለፓኪስታን የተፈጥሮ ጋዝ የጫነች የኳታር መርከብ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማለፏ ተገለፀ። አል ካራይቲያት የተባለችው ይህች መርከብ ከኳታር ራስ ላደፋን ተነስታ ወደ ፓኪስታን ቃሲም ወደብ እያመራች መሆኗ ተገልጿል። የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የኳታር መርከብ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ሲያልፍ ይህ የመጀመርያው ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ከአሜሪካ እና ኢራን ተኩስ ልውውጥ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    ነዳጅ የሚቀዳ እጅ

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

    አሜሪካ እና ኢራን በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ተኩስ መለዋወጣቸው ከተሰማ በኋላ አርብ ሌሊት የእስያ ገበያ ሲከፈት የነዳጅ ዋጋ ጨምሮ ታየ።

    የአሜሪካ ጦር “ትንኮሳ ሳይኖር” የተሰነዘሩ ያላቸውን የኢራን የሚሳዔል፣ ድሮን እና የአነስተኛ ጀልባ ጥቃቶችን ማክሸፉን፤ በምላሹም የራስ መከላከል ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    ከዚህ ጥቃት በኋላ፤ የዓለም የነዳጅ ዋጋ መለኪያ የሆነው ብሬንት ዋጋው በ1.5 በመቶ ጨምሮ በበርሜል 101.60 ዶላር ተሽጧል። በአሜሪካ ገበያ የሚሸጠው ነዳጅ ደግሞ ዋጋው በ1.1 በመቶ አድጎ 95.87 ዶላር ሆኗል።

    በአውስትራሊያ ጀምስ ኩክ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጂያጂያ ያንግ እንደሚናገሩት፤ የነዳጅ ዋጋ በድጋሚ የጨመረው በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚወሰደው ወታደራዊ እርምጃ በስትራቴጂካዊው የንግድ መስመር የሚጓጓዘው የኤነርጂ አቅርቦትን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ስጋት በመጨመሩ ነው።

    በሲንጋፖር ናሽናል ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ተመራማሪ የሆኑት ሁይፌንግ ቻንግ በበኩላቸው፤ አሜሪካ እና ኢራን ውጥረቱን ለማርገብ እየሞከሩ ቢሆንም እንኳ ነጋዴዎች ተኩስ አቁሙን “በቀላሉ የሚጣስ” አድርገው ስለሚመለከቱት አካሄዳቸውን በዚያው ልክ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

    ከእስራኤል ጋር በመሆን በየካቲት ወር ጦርነት የከፈተችው አሜሪካ፤ ግጭቱን ለመቋጨት ከኢራን ጋር ለምታደርገው ድርድር የሚሆን የስምምነት ማዕቀፍ እያዘጋጀች መሆኑን አስታውቃለች። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦርነቱ "በፍጥነት ያበቃል" ሲሉ በዚህ ሳምንት ተናግረዋል።

    ጥቃት የተከፈተባት ኢራን በአጸፋው ቁልፍ የነዳጅ እና ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን ሆርሙዝ ወሽመጥ እንደምትዘጋ ከዛተችበት ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ የኤነርጂ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ከዓለም የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦት ውስጥ አንድ አምስተኛው የሚያልፈው በዚህ የባሕር መስመር ነው።

  2. የጀርመኑ ሚኒስትር በአገራቸው ለተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የትራምፕን “ኃላፊነት የጎደለው ጦርነት” ተጠያቂ አደረጉ

    የጀርመን የፋይናንስ ሚኒስትር ላርስ ክሊንግቤል

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የጀርመን የፋይናንስ ሚኒስትር የአሜሪካው ፕሬዝዳንትን እያካሄዱት ያሉት “ኃላፊነት የጎደለው ጦርነት” በአገሪቱ ሊሰበሰብ ታስቦ የነበረው የታክስ ገቢ በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ ማድረጉን ተናገሩ።

    ሚኒስትሩ ላርስ ክሊንግቤል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እርምጃዎች በቀጣናው “ዓለም አቀፍ የኤነርጂ ቀውስ” እንዲፈጠር ማድረጉን በማንሳትም ወቅሰዋል።

    የጀርመን ባለሥልጣናት ከ2026 እስከ 2030 ለመሰብሰብ አስቀምጠውት የነበረውን የታክስ ገቢ ዕቅድ በ82 ቢሊዮን ዶላር ቀንሰዋል። ይሄ የእቅድ ቅነሳ “በኢራን የሚደረገው ጦርነት ምን ያህል ኢኮኖሚያችንን እየጎዳ እንደሆነ ያሳያል” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    ከሳምንታት በፊት የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ ዋይት ሃውስ በኢራን ተደራዳሪዎች “እየተዋረደ ነው” የሚል ንግግር ማድረጋቸው ትራምፕን አበሳጭቶ ነበር። በዚህ ንግግር የተነሳም ትራምፕ በጀርመን በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሠፈሮች ከሰፈሩ ወታደሮች ውስጥ አምስት ሺህ ያህሉን እንደምታስወጣ ዝተዋል።

    የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የትራምፕ ፖሊሲዎች ከዚህ ቀደም በአሜሪካ እና ጀርመን መካከል የነበረውን ጥብቅ ግንኙነት መቀየሩን ሲጠቁሙ ቆይተዋል።

    ባለፈው የካቲት ላይ “በአውሮፓ እና አሜሪካ መካከል ጥልቅ ክፍተት ተፈጥሯል” በማለት መናገራቸው አንዱ ማሳያ ነው። ይሁን እንጂ የጀርመኑ መሪ በአሜሪካ እና አውሮፓ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማለሳለስ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለቴ ወደ ዋይት ሃውስ ተጉዘዋል።

    እንደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ሁሉ ጀርመንም አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት ወር ኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተችታለች። ጦርነቱ የዓለም ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ትልቅ እንደሚሆን ተፈርቷል።

    የጀርመን ጥምር መንግሥት በከፍተኛ የኤነርጂ ዋጋ እና በኤክስፖርት ፍላጎት መቀነስ ምክንያት ለዓመታት ባለበት ቆሞ ያለውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እየጣረ ነው።

    ባለፈው ወር መራሔ መንግሥቱ መርዝ ለተማሪዎች ባደረጉት ንግግር፤ “አሜሪካውያኑ ምንም ስትራቴጂ እንደሌላቸው ግልጽ” መሆኑን እንዲሁም ሊመርጡ የሚችሉት “ስትራቴጂያዊ መውጫ” እንደማይታያቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

  3. ቴህራን የአሜሪካ ጦር መርከብን ዒላማ ስታደርግ ዋሽንግተን በኢራን ከተሞች ጥቃት ፈጸመች

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ እና ኢራን ሐሙስ ምሽት አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ተኩስ አቁም አሁንም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናገሩ። በትናንቱ የተኩስ ልውውጥ ማን ቀድሞ ጥቃት እንደፈጸመ ግልጽ አይደለም።

    የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ አሜሪካ ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ እየተጠጉ የነበሩ የኢራን ነዳጅ ጫኝ እና ሌላ መርከብን ዒላማ እንዳደረገች እንዲሁም፤ በተለያዩ የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተናግረዋል።

    አሜሪካ በበኩሏ ወሽመጡ ላይ በሰፈረው ሚሳዔል ተሸካሚ አውዳሚ መርከቧ ላይ ለፈጸመችባት ጥቃት “የራስን መከላከል ጥቃቶችን” በማድረስ ምላሽ መስጠቷን አስታውቃለች።

    ሁለቱ አገራት ወታደራዊ እርምጃ መውሰዳቸው የተሰማው የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ ያቀረበችው የድርድር ዕቅድ እየተገመገመ መሆኑን በተናገሩ ማግሥት ነው።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን በቅድሚያ ባወጣው ዘገባ በሆርሙዝ ወሽመጥ “ፍንዳታ” መሰማቱን አስታውቆ ነበር። ሁኔታውንም “ከጠላት” ጋር የተደረገ “የተኩስ ልውውጥ” ሲል ገልጾታል። ሌላ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ቴህራን ውስጥ ፍንዳታ መሰማቱን ዘግቧል።

    ከቆይታ በኋላ መግለጫ ያወጡት የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ በበኩላቸው አሜሪካ በፈጸመቻቸው “የአየር ጥቃቶች” ባንዳር ኻሚር፣ ሲሪክ እና ቃሽም ደሴት መመታታቸውን አስታውቀዋል።

    ኢራን ወዲያውኑ የአሜሪካ የጦር መርከብን በመምታት ምላሽ እንደሰጠች እና በዚህም “ከፍተኛ ጉዳት” ማድረሷን ገልጸዋል። አሜሪካ “የተኩስ አቁም ጥሰት” ፈጽማለች ሲሉም ከስሰዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) የኢራንን ጥቃቶች “ትንኮሳ ሳይኖር” የተፈጸሙ በማለት ገልጿቸዋል። የኢራን ኃይሎች በወሽመጡ እያለፈ በነበረው የአሜሪካ አውዳሚ የጦር መርከብ ላይ “በርካታ ሚሳዔሎች፣ ድሮኖች እና አነስተኛ ጀልባዎችን” ማሰማራታቸውን አስታውቋል።

    “የተቃጡ ስጋቶችን ማስወገዱን” የገለጸው ማዕከላዊ ዕዙ፤ “አሜሪካ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂ የሆኑ እንደ የሚሳኤል እና የድሮን ማስወንጨፊያ ቦታዎችን፣ የዕዝ እና የቁጥጥር ማዕከላትን፣ እንዲሁም የመረጃ፣ የክትትል እና የስለላ ይዞታዎች ያሉ የኢራን ወታደራዊ ተቋማትን መምታቱን” ገልጿል።

    "ማዕከላዊ ዕዙ ውጥረቱ እንዲባባስ አይፈልግም፤ ነገር ግን የአሜሪካ ኃይሎችን ለመጠበቅ በተጠንቀቅ እና በዝግጁነት ላይ ይገኛል" ሲል በመግለጫው ጠቅሷል።

    ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ የጻፉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ በርካታ የኢራን አነስተኛ ጀልባዎችን ማውደሟን ገልጸዋል።

    “ቢራቢሮ ወደ መቃብሯ እንደምትወርድ ሁሉ፤ በጣም በሚያምር ሁኔታ ወደ ውቅያኖሱ ሰምጠዋል" ብለዋል። “በኢራን አጥቂዎች ላይ ትልቅ ጉዳት እንደደረሰም” ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በጽሑፋቸው የሰላም ስምምነቱን በተመለከተ በድጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። “ዛሬ በድጋሚ እንደዘረርናቸው ሁሉ፤ ስምምነታቸውን በፍጥነት ካልፈረሙ ወደፊት በበለጠ ጥንካሬ እና ከፍ ባለ ኃይል እንዘርራቸዋለን” ብለዋል።

    በትናንቱ ጥቃት ላይ “የእስራኤል ተሳትፎ እንዳልነበረ” አንድ የእስራኤል ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

  4. የኢራኑ ፕሬዝዳንት በሕዝብ ታይተው ከማያውቁት ጠቅላይ መሪ ጋር መወያየታቸውን ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን እና ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ

    የፎቶው ባለመብት, IRNA

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን እና ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን የኢራን ጠቅላይ መሪ ከሆኑ በኋላ የጽሁፍ መልዕክት ከማስተላለፍ ውጪ አስካሁን በይፋ ያልታዩትን ሞጅታባ ኻሜኒን አግኝተው መወያየታቸውን ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ መሪውን ሞጅታባ ኻሜኒን “ለሁለት ሰዓት ተኩል” ያህል አግኝተው መወያየታቸውን ከመግለጽ ውጪ ጊዜውን እና ቦታውን ከማሳወቅ ተቆጥበዋል።

    ፔዜሽኪያን ከሞጅታባ ኻሜኒ ጋር በነበራቸው ውይይት “እርጋታ እና ብልህነትን” በኢራን አስላማዊ አብዮታዊ ጠቅላይ መሪ ላይ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

    እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት በከፈቱበት ዕለት የተገደሉትን አባታቸውን በመተካት ከሳምንት በኋላ መንበሩን የተረከቡት ሞጅታባ ኻሜኒ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ከተመሠረተች በኋላ ሦስተኛው ጠቅላይ መሪ ናቸው።

    በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት አባታቸው እና ሌሎችም የቤተሰቦቻቸው አባላት የተገደሉባቸው አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በጥቃቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

    አስካሁን ድረስም ጠቅላይ መሪው በይፋ ወጥተው ወይንም በቴሌቪዥን ቀርበው ለሕዝብ ያልታዩ ከመሆኑ በተጨማሪ ድምቸጻውም ተሰምቶ አያውቅም። በተለያዩ ጊዜያት የኢራን መገናኛ ብዙኃን የጠቅላይ መሪው ናቸው የተባሉ መልዕክቶችን በንባብ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን ከጠቅላይ መሪው ጋር ለሰዓታት የዘለቀ ውይይት ማድረጋቸውን ዛሬ ሲያስታውቁ ሞጅታባ ኻሜኒ የእስላማዊው ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪነትን ከተረከቡ በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ግንኙነት ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።

  5. ሳዑዲ አረቢያ የትራምፕ ሆርሙዝን የማስከፈት ዘመቻ እንዲቋረጥ ማድረጓን ኤንቢሲ ዘገበ

    የሳዑዲው ልዑል እና ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ መንቀሳቀስ ያልቻሉ መርከቦችን አጅቦ ለማስወጣት የነበራቸውን ዕቅድ ያቋረጡት በሳዑዲ አረቢያ ምክንያት መሆኑን ኤንቢሲ ዘገበ።

    ኤንቢሲ ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ሳዑዲ አረቢያ እሁድ ዕለት ትራምፕ ዕቅዳቸውን ይፋ ሲያደርጉ መደነቃቸውን ተናግረዋል።

    የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖችም ሆኑ የጦር ጄቶች ከሳዑዲ የልዑል ሱልጣን የአየር ኃይል መነሳት ወይም በሆርሙዝ ወሽመጥ መውጫ ያጡትን መርከቦች ለማጀብ በሚደረገው ዘመቻ የሳዑዲ አየር ክልል መጠቀም አንደማይችሉ መናገራቸውን ምንጮቹ ለኤንቢኤስ ተናግረዋል።

    ትራምፕ በጉዳዮ ላይ ከሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ቢነጋገሩም ሊያሳምኗቸው እንዳልቻሉ ጨምረው ተናግረዋል።

    ከዚህ በኋላ ትራምፕ ወሳኝ የሆነውን የአየር ክልል ‘ፕሮጀክት ፍሪደም’ ሲሉ ለሰየሙት ወታደራዊ ዘመቻ መጠቀም ስለሚያስፈልግ ዕቅዳቸውን ለጊዜው ለማዘግየት ወስነዋል ሲሉ ምንጮቹ ለኤንቢኤስ ተናግረዋል።

    አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በመሆን በኢራን ላይ ጦርነት በከፈተችበት ወቅት ሳዑዲ አረቢያ የጦር ሠፈሯን እና የኤር ክልሏን የዩናይትድ ስቴትስ ጦር እንዲጠቀምበት ፈቅዳ ነበር።

    አንድ የአሜሪካ ባለሥጣን ለኤንቢሲ አንደተናገሩት የሳዑደ አረቢያ ትብብር በቀጠናው ለሚደረግ ማንኛውም ዘመቻ ወሳኝ ነው።

    ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ይዘውት በነበረው ዕቅድ የጦር አውሮፕላኖች የመከላከያ ሽፋን ለመስጠት ወሳኝ በመሆኑ በቀጣናው የሚገኝ የአየር ክልልን መጠቀም አስፈላጊ አድርጎታል።

    ማክሰኞ ምሽት አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ቆመው የሚገኙትን መርከቦች እያጀበች ለማስወጣት ይዛ የነበረውን ዕቅድ "ለአጭር ጊዜ" እንደምታቆም ፕሬዚዳንት ትራምፕ አስታውቀዋል።

    ሰኞ ዕለት የተጀመረው "ፕሮጀክት ፍሪደም" እንዲቆም የተደረገው ከኢራን ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት "ትልቅ መሻሻል" እያሳየ በመምጣቱ ምክንያት "በጋራ ስምምነት" ከውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

  6. አሜሪካ እና አጋሮቿ ሆርሙዝ ካልተከፈተ ኢራን ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የውሳኔ ሃሳብ ለተመድ አቀረቡ

    የተባበሩት መንግሥታት ጸጥታው ምክር ቤት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ እና የባሕረ ሰላጤው አጋሮቿ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ካላቆመች ማዕቀብ እንዲጣልባት ወይም ሌላ እርምጃ እንዲወሰድባት የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ለተባበሩት መንግሥታት ማቅረባቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ የዜና ወኪል (ኤፒ) ዘገበ።

    ለፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ “ሕገ ወጥ ክፍያዎችን” መጣሏን እንድታቆም እንዲሁም ፈንጂ የተጠመደባቸውን ቦታዎች በሙሉ በማሳወቅ የጉዞ ነጻነትን እንድትፈቅድ ይጠይቃል።

    የተባበሩት መንግሥታት ወሳኝ እርዳታ፣ ማዳበሪያ እና ሌሎች ምርቶችን በወሸመጡ የሚያልፍበት የሰብዓዊ ኮሪደር ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ኢራን “በአስቸኳይ እንድትሳተፍ እና እንድታመቻች” የሚል ጥያቄም መካተቱን ከውሳኔ ሃሳቡ እንደተመለከተ ኤፒ ዘግቧል።

    አሜሪካ እና የባሕረ ሰላጤው አጋሮቿ ይህን ዓይነቱን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሲያደርጉ የመጀመሪያው አይደለም። መጋቢት መጨረሻ ላይ በተካሄደው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት ለማድረግ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በቻይና እና በሩሲያ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ውድቅ ተደርጓል።

    አሜሪካ እና ኢራን ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸው የተገለጸው ከዚህ ስብሰባ ከሰዓታት በኋላ ነበር።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማርኮ ሩቢዮ ማክሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ፤ ኢራን ወሽመጡን ለመዝጋት በመሞከር፣ መርከቦችን እንደምታጠቃ በመዛት፣ የባሕር ፈንጂዎችን በማጥመድ እና ክፍያ ለመሰብሰብ በመሞከር “የዓለምን ኢኮኖሚ አግታ” መያዝ ቀጥላለች የሚል ክስ አቅርበዋል።

    ለፀጥታ ምክር ቤት የቀረበው ውሳኔ ሃሳብ በመጪዎቹ ቀናት ድምጽ ይሰጥበታል ብለው እንደሚጠብቁ ሩቢዮ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። አሜሪካ በሰነዱ ላይ ያደረገችው “አነስተኛ ማስተካከያ” በምክር ቤቱ የሚገኙ የቴህራን አጋሮች ውድቅ እንዳያደርጉት የታለመ እንደሆነ ግን እርግጠኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

    እንደ ኤፒ ዘገባ፤ በውሳኑ ሃሳቡ ላይ ኃይል መጠቀምን የሚፈቅድ አገላለጽን በማስወጣት ማስተካከያ የተደረገ ሲሆን ይህም በማዕቀብ እንዲተካ ተደርጓል።

  7. ሼል የዓለም የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ ውስጥ በገባበት በዚህ ጊዜ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

    የሼል ነዳጅ ጫኝ መኪና

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ዓለም የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ በገጠማት ጊዜ ሼል ከፍተኛ ትርፍ አገኘ

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት ከጀመረ በኋላ ባሉት ወራት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ የነዳጅ ምርት አቅራቢ ኩባንያው ሼል ከፍተኛ ማግኘቱ ተዘገበ።

    ሼል እንዳስታወቀው ባለፉት ሦስት ወራት ያገኘው ትርፍ ወደ 92.6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ይህ የገንዘብ መጠን ከተጠበቀው በላይ እና ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ካገኘው የበለጠ መሆኑን ገልጿል።

    ባለፈው ሳምንት የሼል ተፎካካሪ የሆነው የብሪታኒያው የነዳጅ ድርጅት ቢፒ በተመሳሳይ ወቅት ከእጥፍ በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቆ ነበር።

    እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ከዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና ጋዝ የሚተላለፍበት ሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቷል። ይህ እርምጃ የነዳጅ ዋጋ በአራት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የተባለ ጭማሪ እንዲታይበት ምክንያት ሆኗል።

    በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚካሄደው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የዓለም የነዳጅ ዋጋ መነሻ የሆነው የብሬንት ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 73 ዶላር ገደማ ነበረ።

    ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ከፍ እና ዝቅ ሲል ቆይቷል። የሆርሙዝ መከፈት እና መዘጋት እንዲሁም የጦርነቱ ማቆም እና መልሶ ማገርሸት በታየበት በዚህ ወቅት የተመዘገበው ከፍተኛ ዋጋ 120 ዶላር ነበር።

    በሁለት ወር ውስጥ የተመዘገበው ዝቅተኛ ዋጋ ከ100 ዶላር በታች ነው። አሁን የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 101 ዶላር ገደማ ደርሷል።

  8. የኢራኑ ሚኒስትር ኢንተርኔት ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ መፈቀዱን ተቹ

    የኢራን ወታደር

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images

    የኢራን የሳይንስ፣ ምርምር እና ቴክሎኖጂ ሚኒስትር ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የተወሰደው ኢንተርኔት የመዝጋት እርምጃ እና አገልግሎቱ ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ መፈቀዱን “ከብሔራዊ ደኅንነት የተቃረነ ተግባር ነው” ሲሉ ተቹ።

    ሚኒስትሩ ሆስኒ ሲማይ፤ "የኢንተርኔት አገልግሎት መገደቡ የአገሪቱን የሳይንሳ እና የምርምር ግንኙነቶች እያደናቀፈ ነው፤ ለጠቅላላው ሕዝብ የኢንተርኔት መቆራረጥ መቀጠሉም የብሔራዊ ደኅንነትን የሚቃረን ተግባር ነው" ብለዋል።

    የአገሪቱ መንግሥትም ቢሆን በኢንተርኔት በመዘጋቱ እንደማይስማማ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ “ይህ ሁኔታ የሚቀጥልበት ምክንያት ፕሬዝዳንቱን ራሱ አላሳመነም” ሲሉ ተናግረዋል።

    እንደ ሚኒስትሩ ሆስኒ ሲማይ፤ የኢንተርኔት አቅርቦት ለተወሰኑ ሰዎች ተፈቅዶ ሌሎችን “ማግለሉ፤ ከኢንተርኔት መቋረጥ የበለጠ አደገኛ ድርጊት ነው” የሚል አቋማቸውን ገልጸዋል።

    “የተለያዩ ደረጃዎችን መሠረት ያደረገ እና የተገደበ ኢንተርኔት መፈጠር የእኩልነት አለመኖር እና የማኅበራዊ ቅሬታ ስሜቶችን ያባብሳል” ብለዋል።

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረበት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. አንስቶ ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ የዓለም አቀፍ ኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል።

    የኢራን ባለሥልጣናት እና ተቋማት በቅርቡ ‘ኢንተርኔት ፕሮ’ የተሰኘ አዲስ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል። ይህ የአገልግሎት ነጋዴዎች ወይም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተጨማሪ ክፍያ በመክፈል በተገደበ ደረጃ ዓለም አቀፍ ኢንተርኔትን እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

    ይህ አሠራር ከማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶበታል። ‘ነጭ ሲም ካርድ’ ተብሎ የሚጠራውን ይህንን አገልግሎት ለተወሰኑ ቡድኖች መፈቀዱ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት በመደብ የተከፋፈለ እንዲሆን ያደርጋል እንዲሁም በተለያዩ የሕብረሰተሰብ ክፍሎች መካከል ልዩነት ይፈጥራል የሚል ትችት አቅርበዋል።

    ‘ነጭ ሲም ካርድ’ ተብሎ የሚጠራው አገልግሎት ከፍተኛ ፍጥነት ያለው እና ምንም ዓይነት የድረ ገጽ ዕገዳ የማይደረግበት የሞባይል ስልክ መስመር ነው። ይህ ሲም ካርድ ያላቸው ሰዎች ያለ ምንም ገደብ ኢንተርኔት መጠቀም እና ለጠቅላላው የኢራን ሕዝብ የታገዱ ድረ ገጾችን መጎብኘት ይችላሉ።

    ኢንተርኔት የተዘጋባቸው ኢራናውያን ስለሚከተሉት አማራጭ መንገድ ተጨማሪ ያንብቡ፦ የኢራን መንግሥትን የኢንተርኔት እገዳ ለማለፍ የስታርሊንክ ቴክኖሎጂን ወደ አገሪቱ የሚያስገባው ድብቅ መረብ

  9. ፈረንሳይ ሆርሙዝ ለሚካሄድ ተልዕኮ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧን ማንቀሳቀስ ጀመረች

    ቻርለስ ደ ጎል የተሰኘው እና በጣልያን እና ጀርመን ጦር መርከቦች የሚታጀበው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, ቻርለስ ደ ጎል የተሰኘው እና በጣልያን እና ጀርመን ጦር መርከቦች የሚታጀበው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ

    አሜሪካ እና ኢራን የጣሏቸው እገዳዎች በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ባመጡት ጫና ምክንያት የቀረበውን የሰላም ዕቅድ እንዲስማሙበት እየጠየቀች ያለችው ፈረንሳይ፤ የሆርሙዝ ወሽመጥን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሊካሄድ ለሚችል ተልዕኮ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧን በቀይ ባሕር ማንቀሳቀሷ ተዘገበ።

    ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም በኢራን ጦርነት የተፈጠረው ሁኔታ በሚረጋጋበት ወቅት ወይም ጦርነቱ ሲቋጭ በወሽመጡ የሚደረግ ጉዞ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚያደርግ ዕቅድ ላይ ለበርካታ ሳምንታት ሲሠሩ መቆየታቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

    ይህንን ዕቅድ ለመተግባር ከኢራን ጋር መቀናጀት ይጠይቃል። ሁለቱ አገራት ባዘጋጇቸው ስብሰባዎች ላይ የተገኙ በርካታ አገራት በተልዕኮው ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

    የፈረንሳይ ጦር ባወጣው መግለጫ፤ ቻርለስ ደ ጎል የተሰኘው እና በጣልያን እና በጀርመን ጦር መርከቦች የሚታጀበው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ በደቡባዊ ቀይ ባሕር በኩል ጉዞ እንደጀመረ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።

    የጦር መርከቡ ስምሪት ቀጣናው የኦፕሬሽን ሁኔታውን የመገምገም እና ደኅንነትን ለማጠናከር የሚረዱ የቀውስ አስተደዳር አማራጮችን የማስፋት ዓላማ እንዳለው ጦሩ አስታውቋል።

    የአጋር አገራት ኃይሎች ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር በሚጣጣም የመከላከያ ማዕቀፍ ስር እንዲቀናጁ የማስቻል ዓላማ እንዳለውም ተገልጿል።

    ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡ አንድ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ባለሥልጣን፤ “እያቀረብን ያለነው ዕቅድ ኢራን መርከቦቿን በወሽመጡ ማሳለፍ እንድትችል፤ በምላሹም የኒውክሌር ቁሶችን፣ ሚሳዔሎችን እና ቀጣናውን በተመለከተ ከአሜሪካውያን ጋር እንድትደራደር ነው” ብለዋል።

    “አሜሪካም በበኩሏ በሆርሙዝ ወሽመጥ የጣለችውን ዕገዳ በማንሳት፤ በምላሹ የኢራንን የድርድር ቁርጠኝነት ታገኛለች” ሲሉ የፈረንሳይን አቋም ገልጸዋል።

  10. እስራኤል ቤይሩት ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት የሄዝቦላህ ጦር ከፍተኛ አዛዥ መገደሉ ተዘገበ

    ሊባኖስ ውስጥ ጥቃት የተፈጸመበት ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት አንድ የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥ በዋና ከተማዋ ቤይሩት ደቡባዊ ክፍል ውስጥ መገደሉን ከቡድኑ ጋር ቅርበት ያለው ምንጭ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ተናገረ።

    ይህ ጥቃት እስራኤል በሊባኖስ ላይ ስታካሂድ የቆየውን ወታደራዊ ዘመቻ ያስቆመው የተኩስ አቁም ከተደረሰ ከሁለት ሳምንት በኋላ ዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ የተፈጸመ የመጀመሪያው ጥቃት ነው።

    የሄዝቦላህ ምንጩ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንዳስታወቀው በእስራኤል ጥቃት የተገደለው የቡድኑ ከፍተኛ አዛዥ ማሊክ ባሉት እንደሚባል እና የሄዝቦላህ ራድዋን ጦር የዘመቻ አዛዥ መሆኑን ገልጿል።

    ያልተረጋገጡ ዘገባዎች እንዳሉት የሄዝቦላህ አዛዡ የተገደለው እስራኤል ዒላማ ባደረገችው ሕንጻ ውስጥ ከቡድኑ መሪዎች ጋር ስብሰባ እያደረገ ሳለ ነው።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በበኩላቸው የጦራቸው ጥቃት ዒላማ የሄዝቦላህ ራድዋን ጦር አዛዥ መሆኑን ገልጸዋል።

    ሊባኖስ ውስጥ ጥቃት የተፈጸመበት ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ሊባኖስ ውስጥ ጥቃት የተፈጸመበት ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሊባኖስ ውስጥ ጥቃት የተፈጸመበት ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

  11. እስራኤል የሊባኖስ ተኩስ አቁም ከተፈረመ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤይሩት ውስጥ ጥቃት ፈጸመች

    ቤይሩት ውስጥ ጥቃት የተፈጸመበት ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል ከሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር የምታደርገውን ጦርነት ለመግታት የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈጸመች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ ጥቃት ፈጸመች። ይህ የእስራኤል ጥቃት ግጭቱን ማስቆም ባልቻለው ስምምነት ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል።

    የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው ሄዝቦላህ በሚገኝበት ዳሂዬህ በተሰኘው የከተማዋ ደቡባዊ ክፍል ውስጥ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ምሥሎች ከፍተኛ እሳት መከሰቱን እና ቢያንስ አንድ ሕንጻ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ያሳያሉ።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባወጡት መግለጫ፤ የሄዝቦላህ ራድዋን ኃይል አዛዥን ዒላማ ያደረገው ጥቃት እንዲፈጸም ውሳኔ ያስተላለፉት ራሳቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰዓት የታጣቁ ቡድኑ አባላት ስብሰባ ላይ ነበሩ። ሄዝቦላህ እስካሁን ስለ ጥቃቱ አስተያየት አልሰጠም።

    ከሦስት ሳምንት በፊት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት መፈጸሙን ካስታወቁ ወዲህ ዳሂዬህ ውስጥ ጥቃት ሲደርስ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    የተኩስ አቁሙ ቢፈረምም እስራኤል እና ሄዝቦላህ ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል፤ አንዳቸው ሌላኛቸውንም ጥሰት በመፈጸም ይከስሳሉ።

    አብዛኛው የእስራኤል የአየር ጥቃት የመታው ደቡባዊ ሊባኖስን ነው። የእስራኤል ጦር በዚህ የአገሪቱ ክፍል የሄዝቦላህ የጥቃት መሠረተ ልማት እና ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ይናገራል።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው አንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ከ120 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። የሚኒስቴሩ ቁጥር የተዋጊዎች እና ንጹኃንን ቁጥር ለይቶ አላስቀመጠም።

    የእስራኤል ጦር በድንበር በኩል ያለውን የሊባኖስ መሬት ወርሮ ይዟል። ዓላማውም የሰሜናዊ እስራኤል ማኅበረሰቦችን ደኅንነት የሚያስጠብቅ ከሄዝቦላህ ነጻ የደኅንነት ቀጣና ማቋቋም እንደሆነ ባለሥልጣናቱ ይናገራሉ።

    እስራኤል በተቆጣጠረችው የሊባኖስ ግዛት ውስጥ የሚገኙ መንደሮችን ሙሉ በሙሉ በማውደም ጦሯ ጋዛ ውስጥ ካደረገው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ድርጊት ፈጽማለች።

  12. ኢራን ጦርነቱን ለመቋጨት በአሜሪካ የቀረበውን ዕቅድ እየገመገመች መሆኑን አስታወቀች

    የኢራን ባንዲራ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዋሽንግተን እና ቴህራን ስምምነት ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ፤ ኢራን በአሜሪካ የቀረበው የድርድር ዕቅድ “አሁንም እየታሰበበት” መሆኑን ገለጸች።

    የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ረቡዕ ዕለት ባወጣው ዘገባ፤ ዋይት ሀውስ 14 ነጥቦችን የያዘ የመግባቢያ ስምምነት ከኢራን ጋር ሊፈረም ይችላል የሚል እምነት እንዳለው አስነብቦ ነበር።

    አንድ ከፍተኛ የኢራን ፓርላማ አባል ጉዳዩን “ምኞት” ሲሉ አጣጥለውት የነበረ ቢሆንም፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግን ቴህራን በአሜሪካ የስምምነት እቅድ ላይ ያላትን አቋም ለፓኪስታን አደራዳሪዎች እንደምታሳውቅ ተናግረዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኢል ባጋኢ፤ "የአሜሪካ የውሳኔ ሐሳብ አሁንም በኢራን እየተገመገመ ነው፤ እንደተጠናቀቀ አስተያየቷን ለፓኪስታን ወገን ታሳውቃለች" ሲሉ ‘ኢስና’ ለተሰኘው ለኢራን ተማሪዎች የዜና ወኪል አስረድተዋል።

    የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው አገራቸው "ይህንን የተኩስ አቁም ወደ ዘላቂ የጦርነት ማቆሚያ ለመቀየር እየጣረች” መሆኑን ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ አሜሪካ "ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከኢራን ጋር እጅግ ጥሩ ንግግር አድርጋለች" ሲሉ ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ጠቁመዋል።

    የአክሲዮስ ዘገባ እንደሚያመለክተው ባለ አንድ ገጹ የመግባቢያ ስምምነት፤ በዝርዝር ለሚካሄድ የኒውክሌር ድርድር በማዕቀፍነት የሚያገለግሉ 14 ነጥቦችን ይዟል።

    ከስምምነት ነጥቦቹ መካከል ኢራን ኒውክሌር የማበልጸግ ተግባሯን እንድታቆም ስለማድረግ፣ ማዕቀቦችን ስለማንሳት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ነጻ ጉዞን መመለስ የሚሉት ይገኙበታል።

    በዘገባው የተጠቀሱ ሁለት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች እንደተናገሩት፤ ኋላ የሚደረሰው የመጨረሻ ስምምነት የሚመሠረተው በዚህ ዕቅድ ውስጥ በተካተቱት ነጥቦች ላይ ነው።

    ሮይተርስ የዜና ወኪልም ባወጣው ዘገባ ይህንኑ ቢያረጋግጥም፤ እስካሁን ድረስ የስምምነቱ ነጥቦች ለሕዝብ ይፋ አልሆኑም።

    በኤክስ ገጻቸው አክሲዮስ ላወጣው ዘገባ ምላሽ የሰጡት የኢራን ፓርላማ የብሔራዊ ደኅነንት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ኢብራሂም ረዛኢ፤ “አሜሪካውያን ፊት ለፊት በሚደረግ ድርድር ያላገኙትን ነገር እየተሸነፉ ባሉበት ጦርነት አያገኙትም" ብለዋል።

    ኢራን "ጣቷ ቃታው ላይ እንደሆነ እና ዝግጁ መሆኗን" የገለጹት ረዛኢ፤ አሜሪካ “እጅ ሰጥታ” ከአቋሟ ፈቀቅ የማትል ከሆነ ቴህራን “ከባድ እና ጸጸት የሚያመጣ ምላሽ” እንደምትሰጥ አስጠንቅቀዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም አሜሪካ እርምጃ መውሰድ እንደምትጀምር ዝተዋል። ትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ኢራን ስምምነት ላይ ካልደረሰች “ድብደባው ይጀምራል፤ በሚያሳዝን ሁኔታም ከበፊቱ የበለጠ ከፍተኛ ደረጃ እና ክብደት ይኖረዋል" ብለዋል።

  13. ከአሜሪካ ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር ወደ ስምምነት አለመድረሱን የኢራን ባለሥልጣናት ተናገሩ

    ኢብራሂም ባጊይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢብራሂም ባጊይ

    አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ከአሜሪካ ጋር ከስምምነት ለመድረስ መቃረቡን በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎች ከእውነታነት ይልቅ የአሜሪካ “ምኞት ናቸው” በማለት ውድቅ አደረጉ።

    የአሜሪካው የዜና ድረ ገጽ አክሲዮስ ከሰዓታት በፊት አሜሪካ ከኢራን ጋር በባለ 14 ነጥብ የሰላም መግባቢያ ሰነድ ላይ ከስምምነት መቃረቧን እንደምታምን ዘግቧል።

    በዚህ ዘገባ ላይ ምላሽ የሰጡት የኢራን ፓርላማ ከፍተኛ ባለሥልጣን ኢብራሂም ራዛኢ “አሜሪካ በፊት ለፊት ድርድር ያላገኘችውን ባልተሳካ ጦርነት አታገኘውም” ሲሉ ከስምምነት የመድረሱ ጉዳይ ገና መሆኑን አመልክተዋል።

    ባለሥልጣኑ በፋርስ ቋንቋ በኤክስ ገጽ ላይ ባወጡት መግለጫ ኢራን ለሚመጣው ጦርነት ዝግጁ መሆኗን በመግለጽ አሜሪካ የቀረበላትን ሃሳብ ተቀብላ ካልተስማማች ኢራን “ጸጸትን የሚያስከትል” እርምጃን ትወስዳለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    በተጨማሪም ከኢራን ጋር የሚካሄደውን ጦርነት ለማብቃት በአሜሪካ የቀረበው ሃሳብ አሁንም ገና ውሳኔ ያልተሰጠው መሆኑን የኢራን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ለአገራቸው ዜና ወኪል ገልጸዋል።

    ኢስማኤል ባጊይ እንደተናገሩት ኢራን በቀረበው የሰላም ስምምነት ሃሳብ ላይ ያላትን አመለካከት በፓኪስታን አደራዳሪዎች በኩል ለአሜሪካ እያሳወቀች እንደሆነም አመለክተዋል።

    ቃል አቀባዩ ጨምረውም የሚደረገው ድርድር ከመጥፎ እሳቤ ውጪ ‘በቅን ልቦና’ ሊሆን እንደሚገባው አገራቸው እንደምታምን በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

  14. የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሆርሙዝ እንደሚከፈት ፍንጭ ሲሰጥ፣ ትራምፕ ማስጠንቀቂያ ሰጡ

    መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ እና ኢራን ወደ ስምምነት እየተቃረቡ መሆናቸው እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሆርሙዝ ወሽመጥ ሊከፈት የሚችልበት ዕድል እንዳለ ፍንጭ ሰጠ።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን የቀረበውን ስምምነት ካልተቀበለች ከፍተኛ ጥቃት እንደሚጠብቃት አስጠንቅቀዋል።

    አብዮታዊ ዘቡ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው “የወራሪዎች ስጋት የሚያበቃ ከሆነ” ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ መስመር መልሶ የሚከፈትበት ሁኔታ መቃረቡን አመለክቷል።

    መግለጫው ጨምሮም “የወራሪዎች ስጋት ሲያበቃ በአዲሱ አሠራር አሠራር መሠረት በወሽመጡ በኩል የሚደረጉ ጉዞዎች ዘላቂ እና አስተማማኝ ይሆናል” በማለት ኢራን ያወጣችው ወሽመጡን የማስተዳደር ደንብ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጿል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጦርነቱ እና የሆርሙዝ መዘጋት ከኢራን ጋር በሚደረስ ስምምነት እንደሚያበቃ፤ ነገር ግን ኢራን ከስምምነት የማትደርስ ከሆነ የቦምብ ድብደባው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ኢራን “የተስማማንበትን የምትፈጽም ከሆነ” የተከፈተባት ጦርነት እንደሚያበቃ እና የሆርሙዝ ወሽመጥ “ኢራንን ጨምሮ ለሁሉም ክፍት ይሆናል” ብለዋል።

    በተጨማሪም ትራምፕ ኢራን ከስምምነት የማትደርስ ከሆነ “የቦምብ ድብደባው ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን መካሄድ ይጀምራል” በማለት ማስጠንቅቀዋል።

    በፓኪስታን አማካኝነት እየተካሄደ ያለው የሁለቱ አገራት ድርድር ከስምምነት ወደ ሚደረስበት ደረጃ እየተቃረበ መሆኑን የተለያዩ ምንጮች እየጠቆሙ ነው።

  15. ቻይና በተቻለ ፍጥነት የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም እንዲከፈት ጠየቀች

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እና የኢራኑ አባስ አራጋቺ

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ከኢራኑ አቻቸው ጋር በተወያዩበት ወቅት የሆርሙዝ ወሽመጥ “በተቻለ ፍጥነት” ዳግም እንዲከፈት ጠየቁ።

    ረቡዕ ዕለት በቤይጂንግ የተገናኙት ባለሥልጣኖቹ በሁለትዮች ጉዳዮች በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተዘግቧል።

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ቤይጂንግ የሄዱት ከዶናልድ ትራምፐ ይፋዊ ጉብኝት አንድ ሳምንት ቀድመው ነው።

    ዋንግ ዪ "ቻይና ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ አስቸኳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ታምናለች፣ ግጭት ዳግም መቀስቀስ አስፈላጊ አይደለም" ማለታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    “የባህር ወሽመጡን በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መደበኛ እና ደህንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ ረገድ የጋራ ስጋት አለው፤ ቻይናም የሚመለከታቸው አካላት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሚመጣው ጠንካራ ጥሪ በተቻለ ፍጥነት ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ ታደርጋለች።

    ቤይጂንግ በተደጋጋሚ አሜሪካ እና ኢራን እንዲደራደሩ ጥሪ የምታቀርብ ሲሆን ረቡዕ ዕለትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንኑ ደግመዋል።

    ዋንግ አክለውም ቤይጂንግ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ላለማምረት ያላትን ቁርጠኝነት ማድነቃቸውን የቻይና የመንግሥት ሚዲያ ዘግበዋል።

  16. አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ያስቆማል የተባለ የመግባቢያ ሰነድ ሊፈራረሙ ነው- ሮይተርስ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የፓኪስታን ምንጮችን ጠቅሶ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል አንድ ገጽ የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም መቃረባቸውን ዘገበ።

    በስም ያልተጠቀሱት ምንጮቹ ለሮይተርስ “በቅርቡ እናፈራርማለን፤ በጣመ ተቃርበናል” ሲሉ ተናግረዋል።

    አክሲዮስ በበኩሉ ዋይት ሐውስ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስቸል ሰነድ ላይ ለመፈራረም መቃረቡን እንደሚያምን ዘግቧል።

    ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ማናገሩን እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የተሰጣቸው ሁለት ሌሎች ምንጮችን የጠቀስው መገናኛ ብዙኃኑ የመግባቢያ ሰነዱን ሊፈረም መሆን አረጋግጠዋል።

    ባለ አንድ ገጽ ነው የተባለው የመግባቢያ ሰነድ ስለ ኒውክሌር ድርድር ማዕቀፍን እንደሚያስቀምጥ ተጠቅሷል።

    ከእነዚህም መካከል የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም መቋረጥ፣ የማዕቀብ መነሳት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለ ምንም እክል መርከቦች እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ በሰነዱ ላይ መካተታቸው ተዘግቧል።

    በሁለቱ አገራት ንግግር ውስጥ የኒውክሌር ፕሮግራም መቋረጥ እና የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም መከፈት ሳያግባቧቸው የቆዩ ጉዳዮች ናቸው።

    አክሲዮስ ምንጮችን ጠቅሶ በርካቶቹ በሰነዱ ላይ የተጠቀሱት ነጥቦች የመጨረሻ ስምምነት እንዳልተደረሰባቸው ዘግቧል።

    ዩናይትድ ስቴትስ በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውሰጥ ከቴህራን ምላሽ ለማግኘት እየጠበቀች ሲሆን እስካሁን ምንም ዓይነት ስምምነት የተደረሰበት ነገር አለመኖሩን ምንጮችን ጠቅሶ አክሲዮስ ዘግቧል።

    ቢቢሲ ከዋይት ሐውስን እንዲሁም ከኢራን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

  17. የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በ26 መርከቦች ላይ ጥቃቶች ተፈጽመዋል

    የታይላንድን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልብ ጥቃት ከደረሰባቸው መከካል አንደኛው ነው

    የፎቶው ባለመብት, Royal Thai Navy

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በመካከለኛው ምሥራቅ 26 መርከቦች ላይ ጥቃቶች ደርሰዋል ሲል የዩኬ የባህር ትራንስፖርት ንግድ ተቋም (ዩኬኤምቲኦ) ገለጸ።

    ከየካቲት 21 ጀምሮ በባህረ ሰላጤው፣ በኦማን ባሕረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ እና አካባቢው 46 ክስተቶች እንደደረሱት አሳውቋል።

    ከእነዚህ ውስጥ 26ቱ ጥቃቶች ሲሆኑ 18ቱ ደግሞ "አጠራጣሪ እንቅስቃሴ" እንደነበሩ እና ሁለት የጠለፋ ጥቃቶች እንደተፈጸሙ ሪፖርት ተደርጓል።

    በሌላ በኩል የፈረንሳይ የመርከብ ተቋም የሆነው ሲኤምኤ ሲጂኤም ዛሬ ጠዋት እንደገለጸው ሳን አንቶኒዮ የተባለው መርከብ ማክሰኞ ዕለት የሆርሙዝ ወሽመጥን ሲያቋርጥ የጥቃት ዒላማ ሆኖ በመርከቡ ሠራተኞች ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    በጥቃቱ የተጎዱት የመርከቡ ሠራተኞች ከአካባቢው መውጣታቸውን እና የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል ተብሏል።

    ተቋሙ አክሎም "ሲኤምኤ ሲጂኤም ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ከመርከበኞቹ ጎን ይቆማል” ብሏል።

  18. ኢራን ከአሜሪካ ጋር “ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ስምምነት” ማድረግ እንደምትፈልግ ገለጸች

    ኮንቴህነር የጫነች መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት ድርድር “ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ስምምነት” ካልሆነ በስተቀር እንደማትቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታወቁ።

    ማክሰኞ ዕለት ዶናልድ ትራምፕ ከቴህራን ጋር የሚደረገው ንግግር “ትልቅ መሻሻል” እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

    ቤጂንግ የሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ “በድርድሩ ሕጋዊ መብቶቻችን እና ጥቅሞቻችንን ለመከላከል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ሲሉ መናገራቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    አባስ አራግቺ ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር ከተገናኙ በኋላ “ፍትሃዊ እና የተሟላ ስምምነትን ብቻ” እንቀበላለን ማለታቸውን መገናኛ ብዙኃኑ ዘግበዋል።

    አራግቺ ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገውን ንግግር ለመደገፍ በሚል በሆርሙዝ ወሽመጥ የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለማጀብ ጀምረውት የነበረውን ዘመቻ ስለማቆማቸው ያሉት ነገር የለም።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በሁለቱ አገራት መካከል ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ለመርከቦች እንቅስቀቃሴ ዝግ ሆኗል።

    በዚህም የተነሳ የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና ጋዝ አቅርቦት በመስተጓጎሉ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል።

    ትራምፕ በትናንትናው ዕለት “በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው እገዳ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኖ እየቀጠለ ሳለ ፕሮጀክት ፍሪደም. . . ስምምነቱ ይጠናቀቅ እና ይፈረም እንደሆነ ለማየት ለአጭር ጊዜ እንዲቆም በጋራ ተስማምተናል” ብለዋል።

    የትራምፕን የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፍ ተከትሎ ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በ1.2 በመቶ ቅናሽ በማሳየት በበርሜል 108.6 ዶላር መሸጥ ጀምሯል።

    ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኢራን በሆርሙዝ ላይ የሚደረግን እንቅስቃሴ ልትቆጣጠር አይፈቀድላትም ሲሉ ተናግረዋል።

  19. የቻይና እና የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቤይጂንግ ተገናኝተው ተወያዩ

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢራኑ አቻቸው ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Tasnim

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረቡዕ ዕለት የኢራኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺን ተቀብለው ማነጋገራቸው ዢንዋ ዘገበ።

    አራግቺ አገራቸው ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ወዲህ ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ሲገናኙ ይህ የመጀመርያቸው ነው።

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቤይጂንግ የተገኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከመምጣታቸው ጥቂት ቀን ቀደም ብሎ ነው።

    የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዢንዋ አራግቺ በቤዢንግ የተገኙት በቻይና መንግሥት ግብዣ መሆኑን ተናግረዋል።

    አራጋቺ ቻይና ከገቡ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጀመሩትን ዘመቻ ለጊዜው መቆሙን ሲያስታውቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው አሜሪካ ዓላማዎቿን በማሳካቷ ኢራን ላይ የከፈተችው የማጥቃት ዘመቻ “አብቅቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት በሁለትዮሽ ጉዳዮች በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንደሚወያዩ ተናግረዋል።

    ሁለቱ ሚኒስቴሮች የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሦስት ጊዜ በስልክ የተወያዩ ሲሆን ቤጂንግ በተደጋጋሚ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ እና የሆርሙዝ ወሽመጥ ለንግድ መርከቦች ክፍት እንዲሆን ሲጠይቁ ቆይተዋል።

    ከጦርነቱ በፊት 20 በመቶ የዓለም ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚያልፈው በወሽመጡ በኩል ነበር።

    ነገር ግን ከጦርነቱ በኋላ የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ በእጅጉ ተስተጓጉሏል።

    ቻይና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ነዳጅ እና ጋዝ ከሚገዙ አገራት ግንባር ቀደሟ ናት።

  20. ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ስላካሄዱት ‘ፕሮጀክት ፍሪደም” ምን እናውቃለን?

    በወሽመጡ ላይ የቆሙ ጀልባዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ መንቀሳቀሻ አጥተው የቆሙትን መርከቦች አጅበው ለማስወጣት ይዘውት የነበረውን ዕቅድ ለጊዜው ማቆማቸውን ተናግረዋል።

    ትራምፕ ዘመቻው ሰብዓዊ አላማ እንዳለው “ሰዎችን ነጻ ማውጣት፣ ኩባንያዎችን እና ምንም ጥፋት የሌለባቸውን አገራት ነጻ ማውጣት ማለት ው” ሲሉ ተናግረው ነበር።

    ኢራን መርከቦች በወሽመጡ በኩል ማለፍ የሚችሉት በእርሷ ፈቃድ ብቻ መሆኑን ተናግራለች።

    ትራምፕ ይህንን ዘመቻ ይፋ አድርገው የነበረው እሁድ ዕለት ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የኢራን ጦር ወደ ወሽመጡ ለመግባት የሞከረ የአሜሪካ ጦር መርከብ ላይ መተኮሱን ሲናገር አሜሪካ በበኩሏ አነስተኛ ጀልባዎችን መትታ ማስመጧን ተናግራለች።

    አሜሪካ ይህንን ዘመቻ ይፋ ካደረገች ከሁለት ቀናት በኋላ፣ ማክሰኞ ዕለት ትራምፕ ከኢራን ጋር ከስምምነት ላይ መድረስ ይቻል እንደሆነ ለማየት በሚል ዘመቻው ለአጭር ጊዜ እንደሚቆም ተናግረዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ የተዘጋው እስራኤል እና አሜሪካ ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ቴህራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ኢራን በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ነው።

    ቴህራን የዓለም 20 በመቶ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ ዘግታለች።

    አሜሪካ 22,500 ባህረተኞች እና 1,550 የንግድ መርከቦች መንቀሳቀሻ አጥተው መቆማቸውን ትናገራለች።

    እነዚህ ባህረተኞች የ87 አገራት ዜጎች መሆናቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) አዛዥ አድሚራል ብራድ ኩፐር ተናግረዋል።

    ሰኞ ዕለት ሴንትኮም የአሜሪካ ባሕር ኃይል በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መሰማራቱን ገልጾ ነበር።

    ኢራን የአሜሪካ ዘመቻ ከመጀመሩ ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብላ ማስጠንቀቂያ በማውጣት ወደ ወሽመጡ ለመግባት የሞከሩ የአሜሪካ መርከቦች ላይ ሁለት ሚሳዔሎችን መተኮሷን ተናግራለች።

    ሴንትኮም የኢራንን መግለጫ ወዲያውኑ ውድቅ አድርጓል። አክሎም ኢራን ወደ ጦር መርከብ እና የአሜሪካ ባንዲራ ወደምታውለበልብ የንግድ መርከብ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን መተኮሷን እንዲሁም አነስተኛ ጀልባዎች በመጠቀም ጥቃት ለመፈጸም መሞከሯን ተናግሯል።

    ዩኤኢ ከኢራን በተተኮሱ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ጥቃት እንደደረሰባት አስታውቃለች።

    በጥቃቱም የነዳጅ ማከማቻ ስፍራ መመታቱን ነገር ግን በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አስታውቃች።

    በወሽመጡ በዩኤኢ አቅራቢያ የቆመ የደቡብ ኮሪያ የጭነት መርከብም ጥቃት እንደደረሰበት ተገልጿል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ሴንቲኮም አሜሪካ ሂሊኮፕተሮችን ስድስት አነስተኛ ኢራን ጀልባዎች መትተው ማስመጣቸውን አሰታውቋል። ኢራን ግን እህንን አስተባብላለች።

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ለማለፍ አገዛዙን ፈቃድ በማይጠየቁ ላይ “ወሳኝ እርምጃ እወሰዳለሁ” ስትል አስጠንቅቃለች።

    ይህ በእንዲህ አንዳለ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በሰጡት መግለጫ ላይ የተኩስ አቁሙ አለመክሸፉን ተናግረዋል።