ሂዩማን ራይትስ ዎች በአምቡላንስ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ እንደ ጦር ወንጀል ሊመረመር ይገባል አለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች እስራኤል በጋዛ በአምቡላንስ ላይ ጥቃት መሰንዘሯ እንደ ጦር ወንጀል መመርመር አለበት አለ።
ከጥቂት ቀናት በፊት የእስራኤል ጦር በጋዛ አል-ሺፋ ሆስፒታል አቅራቢያ አምቡላንስ መምታቱ ይታወሳል።
እስራኤል በአምቡላንሱ ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ያመነች ሲሆን ተሸከርካሪውን ዒላማ ያደረገችው የሐማስ አባላት እየተጠቀሙበት እንደነበረ መረጃው ስለነበረኝ ነው ብላለች።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ግን ከጥቃቱ በኋላ የተነሱ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን መመልከቱን እንዲሁም የዓይን እማኞችን ማነጋገሩን ጠቅሶ በጥቃቱ 5 ሕጻናትን ጨምሮ 21 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ጨምሮም አምቡላንሱ ወታደራዊ ዓላማን ለማስፈጸም ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ምንም አይነት ማስረጃ አላገኘሁም ብሏል።


















