ማክሮን እስራኤል ሕጻናት እና ሴቶችን በቦምብ ከመደብደብ ትቆጠብ አሉ

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እስራኤል በጋዛ ያሉ ሕጻናት እና ሴቶችን በቦምብ ከመደብደብ መቆጠብ አለባት አሉ። ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር በጦርነቱ አስካሁን የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 11,078 ከፍ ማለቱን ይፋ ካደረገ በኋላ ነው። በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉት ፍልስጤማውያን መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ሕጻናት እና ሴቶች ናቸው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. እስራኤል እና ሐማስ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን እየገለጹ ነው

    የእስራኤል ታንኮች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዛሬ ጠዋት እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ከ10 ሰዓታት ከባድ ውጊያ በኋላ “የሐማስ ጠንካራ ይዞታ ነው” የተባለ ስፍራን ሠራዊቷ መቆጣጠሩን አስታውቃለች።

    በተመሳሳይ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው አል-ቃሳም ብርጌድ ውጊያውን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ በእስራኤል ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ጉዳት ዘርዝሯል።

    በዚህም አል-ሻቲ ከተባለው ካምፕ አቅራቢያ ሦስት የእስራኤል ተሽክርካሪዎች እና አንድ ቡልዶዘር፣ ጋዛ ከተማ ውስጥ ሼክ ራድዋን ከተባለው ስፍራ በስተሰሜን አንድ ታንክ፣ ጋዛ ከተማ አል-ታዋም ውስጥ አንድ ታንክ ተዋጊዎቹ ማውደማቸውን አሳውቋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ቡድን አካል የሆነው አል-ቁዱስ ብርጌድ በጋዛ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንሳር በሚባል ስፍራ የእስራኤል ወታደራዊ ተሽክርካሪዎችን በቦምብ ማጥቃቱን ገልጿል።

    ቡድኑ በተጨማሪም የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወል በተሰማባት የእስራኤሏ አሽዶድ ከተማ ላይ ሮኬቶችን መተኮሱን አሳውቋል።

    ቢቢሲ በጦርነቱ ውስጥ ስለተፈጸሙት ጥቃቶች ወዲያውኑ ለማረጋገጥ አልቻለም።

  2. እስራኤል ከ10 ሰዓታት ውጊያ በኋላ የሐማስን 'ጠንካራ ይዞታ' ተቆጣጠርኩ አለች

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሰሜናዊ ጋዛ ጃባሊያ የሚገኘውን የሐማስን ጠንካራ ይዞታ መቆጣጠሩን አስታወቀ።

    ጦሩ በኤክስ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው "10 ሰዓታት ከፈጀ ውጊያ በኋላ አሸባሪዎችን ደምስሰናል፤ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን ማርከናል። የአሸባሪዎች መመላለሻ ዋሻዎችን አግኝተናል።

    አንደኛው ዋሻ በመዋዕለ ህጻናት አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን በመሬት ውስጥ ሰፊ ስፍራን የሚሸፍን ነው ነው" ብሏል።

    የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ የሚገኝ መኖሪያ ቤትን እንደበደቡ የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ ዘግቧል።

    ነዋሪዎች በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው ይገኛሉ ብሏል። እስራኤል በጋዛ ከተማ በፈጸመችው ጥቃትም በርካቶች መቁሰላቸውን አክሎ ዘግቧል። ቢቢሲ ሪፖርቶቹን ማረጋገጥ አልቻለም።

  3. በጋዛ የቀጠለው ጥቃት

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በጋዛ ሰርጥ የአየር እና የመሬት ጥቃት እንዲሁም ከባህር በሚወነጨፉ ሚሳኤሎች የተቀናጁ ጥቃቶች መቀጠላቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።

    በጋዛ የማያባራው የአየር ጥቃት በትናትናው ምሽትም ቀጥሏል። የእስራኤል ጦር የሐማስ ወታደራዊ እዝን መትቻለሁ ብሏል።

    እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ኻን ዩኒስ በአንድ መኖሪያ ቤት ሌሊቱን በፈጸመችው ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ከዚህም በተጨማሪ በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኘው የጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ እንዲሁም በጋዛ ከተማ በፈጸመችው ጥቃት ጉዳት መድረሱንም በሐማስ ከሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

    በርካቶችም ቤተሰቦቻቸውን ከፍርስራሾች ለማውጣት ሲታገሉ የሚያሳዩ ምስሎችን ቢቢሲ አግኝቷል።

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  4. ቀይ መስቀል የእርዳታ መኪናው በጋዛ እንደተመታ አስታወቀ

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አለም አቀፉ ቀይ መስቀል በደቡባዊ ጋዛ ወደሚገኘው አልቁድስ ሆስፒታል ህይወት አድን መድኃኒቶች ጭነው ሲጓዙ ከነበሩት ውስጥ አንዱ መኪናው እንደተመታ እና አሸከርካሪውም እንደተጎዳ አስታወቀ።

    አሽከርካሪው ከሞት "በሳንቲሜትሮች" ርቀት ውስጥ ነበር ብሏል። "እውነት ለመናገር ለሰብዓዊ ረድዔት ተቋማት እርዳታ ለማድረስ ምቹ አይደለም መኖር ይቅርና" ሲሉም ከእርዳታ ጭነቱ ጋር አብረው ሲጓዙ የነበሩት የተቋሙ የጋዛ ቢሮ ኃላፊ ዊልያም ሾምቡርግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    "መሰረታዊ የደህንነት ከለላ እና አቅርቦቶች እንፈልጋለን። ሰራተኞቻችን የምናፈራርቅበት ሁኔታም መረጋገጥ አለበት" በማለት የተናገሩት ኃላፊ ሆስፒታሎች ያላቸው ነዳጅ እንደተመናመነ እንዲሁም የሚጠጣ ውሃ ማግኘትም የእለት ተዕለት መሆኑንም ገልጸዋል።

    "በጋዛ ውስጥ የትኛውም ቦታ ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም" ብለዋል። ኃላፊው በደቡባዊ ጋዛ ያለውን ሁኔታ "ሰብዓዊ ጥፋት" ሲሉ ገልጸውታል።

    በፍርሓት የተዋጡ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶች ህይወታቸውን ለማትረፍ በባዶ እግራቸው አይተናል። በርካቶችም ምግብ እና የሚጠጣ ውሃ ፍለጋ እየተንከራተቱ ነው ብለዋል።

  5. በጋዛ የቦምብ ጥቃት ከቀጠለ ቀጠናዊ ጦርነት እንደሚቀሰቀስ ሄዝቦላህ አስጠነቀቀ

  6. የእስራኤል ጦር በጋዛ 130 የሐማስ ዋሻዎችን ማውደሙን አስታወቀ

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል

    የፎቶው ባለመብት, IDF

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል በጋዛ ሰርጥ ጦሩን ካስገባ በኋላ 130 የሐማስ ዋሻዎችን ማውደሙን አስታወቀ።

    "የእስራኤል መከላከያ ተዋጊ መሐንዲሶች በአሁኑ ወቅት በጋዛ ውስጥ የሚገኙ ዋሻዎችን ጨምሮ የሐማስ የሽብር መሰረተ ልማቶችን ለማጋለጥ እና ለማውደም እየሰሩ ነው። በዋሻዎቹ ውስጥ የተገኙት የውሃ እና የኦክስጂን ክምችት ሐማስ ከመሬት በታች ለረጅም ጊዜ ለመቆየት ያለውንም ዝግጅት የሚያሳይ ነው" ሲል የመከላከያው መግለጫ አትቷል።

    ረቡዕ ዕለት በሰሜን ጋዛ ቤይት ሐኖን አካባቢ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ድጋፍ በሚያደርግበት ትምህርት ቤት አቅራቢያ የሚገኘውን የሐማስ ዋሻ ማውደሙን አስታውቋል።

    መከላከያ በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ የሚገኘውን እና የሐማስ ዋሻ ነው በሚል አውድሜያለሁ ያለውንም በድሮን የተቀረጸ ቪዲዮ አጋርቷል።

    እስራኤል ሐማስ መስከረም 26 ላደረሰው ጥቃት ምላሽ ነው በሚል የጋዛ ሰርጥን በማያባራ የአየር ጥቃት እየመታች ትገኛለች።

    በሙሉ ከበባ ውስጥ በማስገባት መብራት፣ ውሃ እና ነዳጅ የቆረጠች ሲሆን እግረኛ ጦሯም ገብቶ የተቀናጀ ጥቃት እየፈጸመ እንደሚገኝ አስታውቋል።

    ሐማስ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 400 ሰዎች ሲገደሉ ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ታግተዋል። እስራኤል እየፈጸመች ባለችው የተቀናጀ ጥቃት ከ10 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በርካቶቹም ህጻናት መሆናቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    የተባበሩት መንግሥታት ጋዛ ወደ ህጻናት ስፍራ መቀበሪያነት እየተቀየረች ነው ሲል አስከፊነቱን ጠቅሶ የተኩስ አቁም በአፋጣኝ መደረግ አለበት ብሏል።

  7. ተመድ እስራኤል እና ሐማስን የጦር ወንጀሎች በመፈጸም ከሰሰ

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኃላፊ እስራኤል እና ሐማስ የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል ሲሉ ከሰሱ።

    ቮልከር ተርክ ሐማስ ታጋቾቹን አለመልቀቁ እንዲሁም እስራኤል በፍልስጤም ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየፈጸመች ያለውን ህዝብን በጋራ የመቅጣት እና ነዋሪዎች በህገወጥ መንገድ በአስገዳጅ ሁኔታ ማፈናቀሏን ጠቅሰዋል።

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው በጋዛ የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች አኃዝ የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ “በግልጽ ስህተት እየተፈጸመ እንደሆነ ማሳያ ነው” ብለዋል። ሐማስንም ሰላማዊ ሰዎችን እንደ ሽፋን በመጠቀሙ ወቅሰውታል።

    • የእስራኤል ጦር 50 ሺህ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ከሰሜን ጋዛ ወደ ደቡብ መሸሻቸውን አስታውቋል። እስራኤል በሰሜን ጋዛ ነዋሪ የሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንዲሸሹ ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
    • የዓለም አቀፉ ቀይ ጨረቃ የጋዛ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በደቡባዊ ጋዛ ያለውን ሁኔታ “ሰብዓዊ ጥፋት” ሲሉ ገልጸውታል። በፍርሓት የተዋጡ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶች ህይወታቸውን ለማትረፍ በባዶ እግራቸው አይተናል። በርካቶችም ምግብ እና የሚጠጣ ውሃ ፍለጋ እየተንከራቱ ነው ብለዋል። የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እየፈጸመችው ባለው የማያባራ የአየር ጥቃት ንጹህ ውሃ ማግኘት ተስተጓጉሏል ብሏል። እንዲሁም መጠለያዎች በተፈናቃዮች ስለተጨናነቁ በጋዛ ሰርጥ በሽታዎች ሊዛመቱ እንደሚችሉም አስጠንቅቋል።
    • የህክምና ቁሳቁሶችን የጫነ እርዳታ በጋዛ ከተማ ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ ደርሷል። እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ በአንድ ወር ውስጥ መድኃኒት ሲደርስ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
    • የአሜሪካ ሪፐብሊካን እጩዎች እስራኤል ከሐማስ ጋር እያደረገችው ላለው ጦርነት ድጋፋቸውን ገልጸው የተኩስ አቁም ጥሪን ውድቅ አድርገዋል።
    • አስራ ሁለት የሚሆኑ ታጋቾችን ለማስለቀቅ እና በምላሹም ለሶስት ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግም ውይይቶች መጀመራቸውን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከነዚህም መካከል ግማሾቹ አሜሪካውያን መሆናቸውን ቢቢሲ ሰምቷል።
    • የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እየተደረጉ ነው የተባሉ ውይይቶችን “ሐሰተኛ ወሬዎች” ናቸው ሲሉ አጣጥለዋል። “ታጋቾች እስካልተለቀቁ ድረስ” የተኩስ አቁም አይኖርም ብለዋል።
    • የቢቢሲ አለም አቀፍ ጉዳዮች አዘጋጅ ጄረሚ ባውን ከእስራኤል ጦር ጋር ወደ ጋዛ ተጉዟል። በጋዛ ቆይታውም ጉዳት ያልደረሰበት ህንጻ እንደሌለ ተመልክቷል። የእስራኤል ጦር አንድ የቤተሰብ መኖሪያ ያለበትን እና የጦር መሳሪያዎች ይመረቱበታል የተባለውን ህንጻም ለጋዜጠኛው አሳይቶታል።
  8. ከጦርነቱ በኋላ እስራኤል ጋዛን ይዛ መቆየት እንደሌለባት አሜሪካ አስጠነቀቀች

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, ISRAEL DEFENSE FORCES

    ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ እስራኤል ጋዛን ተቆጣጥራ መቆየት እንደሌለባት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን አስጠነቀቁ።

    ሐማስ ከወር በፊት ያደረሰውን ጥቃት ሊደግም እንደሚችል ስጋት በመደቀኑ ጋዛን በመምራት መቀጠል እንደሌለበትም አጽንኦት ኃላፊው ሰጥተዋል።

    ነገር ግን እስራኤል ሳትሆን በዌስት ባንክ ተቀማጭነቱን ያደረገው የፍልስጤም አስተዳደር ጋዛን ሊመራ ይገባል ብለዋል።

    እስራኤል በጋዛ ነዋሪዎች ላይ አስገዳጅ ማፈናቀል፣ ከበባም ሆነ ክልከላ እንዲሁም የጋዛ ግዛትንም መቁረስ የለባትም ሲሉ ተናግረዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል ላልተወሰነ ጊዜ በጋዛ ላይ አጠቃላይ የጸጥታ ኃላፊነት እንደሚኖራት ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠቃላይ የጸጥታ ኃላፊነት የእስራኤል ነው ለሚለው ንግግራቸው ማብራሪያ ባይሰጡም አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ባለስልጣን እስራኤል ጋዛን እንደገና ይዛ የመቆየት ወይም "ለረዥም ጊዜ ተቆጣጥራ የመቆየት ፍላጎት የላትም" ብለዋል።

    እስራኤል ሐማስን አጠፋለሁ በሚል በጋዛ ላይ የማያባራ የአየር ጥቃቶችን ከጀመረች አንድ ወር አልፎታል።በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ኤሌክትሪክ፣ ውሃና ነዳጅ ቆርጣለች እንዲሁም እግረኛ ጦሯን አስገብታ የተቀናጀ ጥቃት መክፈቷን አስታውቃለች።

    በነዚህ ጥቃቶች ከ10 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በርካቶቹም ህጻናት መሆናቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    የተባበሩት መንግሥታት ጋዛ ወደ ህጻናት ስፍራ መቀበሪያነት እየተቀየረች ነው ሲል አስከፊነቱን ጠቅሶ የተኩስ አቁም በአፋጣኝ መደረግ አለበት ብሏል። ሐማስ ባደረሰው ጥቃት ከ1400 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ 240 ሰዎችም በታጋችነት ተወስደዋል።

  9. በኢራን የሚደገፈው አማፂ ቡድን የአሜሪካን ወታደራዊ ድሮን መትቶ ጣለ

  10. “ሐሎ! ከእስራኤል ደኅንነት ቢሮ ነበር የምደውለው። ቤትህን ልናጋየው ትዕዛዝ ተሰጥቶናል”

  11. እርዳታ እንዲቀርብ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ እስራኤል ጥቃቷን ጋብ ማድረጓ ተነገረ

    እርዳታ እንዲቀርብ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ እስራኤል ጥቃቷን ጋብ ማድረጓ ተነገረ

    የፎቶው ባለመብት, AP

    እስራኤል በጋዛ ላይ ጥቃት መፈጸም ከጀመረችበት ከአንድ ወር በኋላ ሠራዊቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአራት ሰዓታት የሚቆይ ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ጥቃቱን ጋብ ማድረጉን አስታውቋል።

    በዚህ ለጥቂት ሰዓታት በሚቆየው ከጥቃት ፋታ የሚገኝበት ጊዜ በጋዛ ከተማ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ በሚገኙ ትላልቅ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ውሃ እና ምግብ እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።

    ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ ከነበረው የአየር ጥቃት አንጻር ዛሬ ረቡዕ በጋዛ ሰርጥ እና በደቡባዊው ክፍል ውስጥ የተፈጸመው የአየር ጥቃት መጠን ዝቅ ያለ መሆኑ ተዘግቧል።

    ነገር ግን ረቡዕ ማለዳ ላይ በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ ዴር አል-ባላህ እና በሌሎች ከተሞች ላይ ያነጣጠሩ የአየር ጥቃቶች ተፈጽመው 40 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸው ተነግሯል።

    በሰሜን ጋዛ ውስጥ ውጊያ እየተካሄደ በመሆኑ የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው በእግራቸው እየወጡ ናቸው።

    በስምንት ግንባሮች እየተካሄደ ያለው ውጊያ አዝጋሚ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ የእስራኤል እግረኛ ወታደሮች በጋዛ ከተማ ላይ ከበባቸውን ለማጥበቅ ከከተማዋ በስተምዕራብ ወደሚገኘው ቁልፍ የባሕር ዳርቻ መንገድ እየገፉ ናቸው።

  12. የቡድን 7 አገራት ለጋዛ እርዳታ እንዲቀርብ ግጭት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ

    የጂ7 የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ጃፓን ላይ የተሰባሰቡት የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባወጡት መግለጫ በጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ ከጦርነቱ ፋታ እንዲገኝ እና መተላለፊያ እንዲዘጋጅ ጠየቁ።

    ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ የሚገኙበት ቡድን ሰባት አባላት “ጋዛ ውስጥ እየተባባሰ ያለው ሰብአዊ ቀውስን ለማስቆም አስቸኳይ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት” በመግለጫቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

    “በጋዛ ጦርነቱ ጋብ ብሎ ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ የሚያስችል መተላለፊያ እንዲመቻች በማድረግ ሲቪሎች እንዲንቀሳቀሱ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ” ጠይቋል።

    ቢሆንም ግን መግለጫው በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ አልጠየቀም። ለሰብአዊ እርዳታ ሲባል የሚደረግ ግጭት የማቆም ፋታ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ ነው። ተኩስ አቁም የረጅም ጊዜ እና የፖለቲካዊ ሂደት አካል ነው።

    ጃፓን ቶኪዮ ውስጥ የተሰበሰቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ መግለጫ፣ “በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት” እስራኤል እራሷን የመከላከል መብት አላት ብሏል።

  13. ማኅበራዊ ሚድያ እና የጋዛ ግጭት፡ ሞሐመድ ሳላህ ለስፖርቱ ዓለም “አርአያ” ነው

  14. የአሜሪካ ፖለቲከኞች እስራኤላውያንን ሻማ በማብራት አሰቡ

    የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እስራኤላውያንን ሻማ በማብራት አሰቡ

    የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እስራኤላውያንን ሻማ በማብራት አሰቡ

    አሜሪካውያን ፖለቲከኞች ሐማስ የፈጸመበትን ድንገተኛ ጥቃት አንድ ወር በማስመልከት ሻማ በማብራት እስራኤላውያንን አስበው ዋሉ።

    የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዋሽንግተን ዲሲ ባደረጉት የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት በሐማስ ጥቃት የተገደሉትን እና ታግተው የተወሰዱትን ሰዎች አስበዋል።

    ሐማስ ከአንድ ወር በፊት በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ ከ1ሺህ 400 ያላሱ ሰዎችን ገድሎ 240 ሰዎች ማገቱ ይታወሳል።

    በተቃራኒው የእስራኤል ጦር በወሰደው የአጸፋ እርምጃ በሐማስ የሚተዳደረው ጤና ሚንስቴር ከ10ሺህ 300 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

  15. ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ያሉ ዳቦ ቤቶች ተዘጉ

    በጋዛ ያሉ ሁሉም ሊባሉ የሚችሉ ዳቦ ቤቶች በግብዓት እጥረት ምክንያት ተዘጉ።

    ዳቦ ቤቶቹ በነዳጅ፣ በውሃ እና በስንዴ ዱቄት እጥረት እንዲሁም በአየር ድብደባ ምክንያት ሥራቸውን ማከናወን ባለመቻላቸው ስለመዘጋታቸው ተዘግቧል።

    በጋዛ በተፈጠረው የምግብ እጥረት ምክንያት አንድ ሰው በአማካይ እየኖረ ያለው በቀን በሚያገኘው ሁለት ዳቦ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከጥቂት ቀናት በፊት አስታውቆ ነበር።

  16. ካናዳዊው “እየተሰቃዩ ያሉትን 2.3 ሚሊዮን ሰዎች ታሪክ መናገር ግዴታዬ ነው” ብሎ ከጋዛ አልወጣም አለ

  17. እስራኤል የሐማስ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ኃላፊን ገደልኩ አለች

    ሞሃሰን አቡ ዚና

    የፎቶው ባለመብት, IDF

    የምስሉ መግለጫ, ሞሃሰን አቡ ዚና

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል የሐማስ ከፍተኛ አመራር የነበረውን ሞሃሰን አቡ ዚናን ገደልኩ አለ።

    እንደ የእስራኤል ጦር ከሆነ ሞሃሰን አቡ ዚና የሐማስ የደኅንነት እና የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ኃላፊ ነበር።

    ጦሩ እንዳለው ግለሰቡ የተተኳሽ እና የሮኬቶች ምርት ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው መሪ ነበር።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ ሠራዊቱ በጋዛ ሰርጥ ገብቶ “አሸባሪዎችን እየገደለ እና ለጦር አውሮፕላኖች አቅጣጫ እየሰጠ” ዘመቻዎችን እያካሄደ እንደሆነ ጨምሮ አስታውቋል።

    በዛሬው የእስራኤል የአየር ጥቃት በጋዛ ያሉ መኖሪያ ቤቶችን አውድሞ ሰላማዊ ሰዎች ስለመገደላቸው ሪፖርቶች እየወጡ ነው።

  18. የጋዛው ነዋሪ ከእስራኤል ደኅንነት የደረሰው የሕይወትህን አድን የስልክ ጥሪ

    ማህሙድ ሻሂን
    የምስሉ መግለጫ, ማህሙድ ሻሂን

    እስራኤል ለ12 ቀናት ያህል ጋዛን በቦምብ ስትደበድብ ነበር ማህሙድ ሻሂን የስልክ ጥሪ የደርሰው።

    በጋዛ ሰርጥ በስተሰሜን ባለ ሦስት መኝታ አፓርታማው ሦስተኛ ወለል ላይ ይገኛል። አካባቢው እስካሁን ድረስ በአየር ድብደባ ብዙም ያልተነካ ነበር።

    ማህሙድ ከውጪ ከፍተኛ ጩኸት መስማት ጀመረ። "አሁኑኑ ማምለጥ አለብህ። ህንጻዎቹን ሊመቱ ነው" ብሎ መንገድ ላይ ያለ አንድ ሰው ጮክ ብሎ ተናገረ።

    ከህንጻው ወጥቶ መንገዱን በማቋረጥ መሸሸጊያ ሲፈልግ ስልኩ ጠራ።

    ማህሙድ እንዳለው አንድ ሰው "የምደውልልህ ከእስራኤል የስለላ ድርጅት ነው" አለው። ማህሙድን በሙሉ ስሙ ከመጥራት ባለፈ ጥረት ያለ አረብኛ ይናገራል።

    "ሦስት ህንጻዎችን ማጥቃት እንደሚፈልግ ነገረኝ… እናም አካባቢውን እንድለቅ አዘዘኝ።"

    በዚህ ግጭት ወቅት ጋዛውያንን ከአየር ድብደባ በፊት ለማስጠንቀቅ የእስራኤል ጦር አንዳንድ ጊዜ ስልክ ይደውላል። ይህ የማህሙድ ታሪክም ስለሚደረገው የስልክ ጥሪ ግንዛቤ ይሰጣል።

  19. ሳዑዲ አረቢያ በጋዛ ግጭት ዙሪያ ጉባኤዎችን እንደምታዘጋጅ አስታወቀች

    ሳዑዲ አረቢያ በእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት ላይ ለመወያየት በሚቀጥሉት ቀናት የአረብ እና የሙስሊም አገራት መሪዎችን እንደሚሰባሰቡ ተገለጸ።

    የሳዑዲ የኢንቨስትመንት ሚኒስትር “በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ሳዑዲ አረቢያ አስቸኳይ የአረብ ስብሰባ በሪያድ ታዘጋጃለች” ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    "ከቀናት በኋላ ሳዑዲ አረቢያ እስላማዊ ጉባኤ ታዘጋጃለች" ብለዋል።

    "በአጭር ጊዜ ውስጥ ሦስት ስብሰባዎችን በሳዑዲ አረቢያ መሪነት የማዘጋቱ ዓላማ ግጭቱን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ለእስላማዊ ትብብር ድርጅት ጉባኤ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደሚጓዙ ተዘግቧል።

    በቻይና አደራዳሪነት ቴህራን እና ሪያድ ለዓመታት የዘለቀ ቁርሿቸውን ካስወገዱ በኋላ ይህ የኢራን መሪ የሚያደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝት ይሆናል።

    ፋሊህ ቀን ሳይጠቅሱ ሳዑዲ አረቢያ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን ጉባኤ ትጠራለች ብለዋል። ማክሰኞ አመሻሽ የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በሳምንቱ መጨረሻ የተቀጠረው ስብሰባ በሁለቱ የመሪዎች ጉባኤዎች ላይ ለማተኮር ሲባል ዘግይቷል ብሏል።

  20. ግብፅ ከጋዛ ወደ ግዛቷ በሚያሻግረው የራፋህ በር ላይ ቁጥጥሯን ያጠነከረችባቸው ምክንያቶች