ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ የአስቸኳይ ጊዜ መንግሥት እና የጦርነት ካቢኔ አቋቋሙ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ቤኒ ጋንትዝ የአስቸኳይ ጊዜ መንግሥት ለማቋቋም ተስማሙ።
ሁለቱ ፖለቲከኞች እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት ሐማስ ድንገተኛ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ እስራኤል መጠነ ሰፊ የአጸፋ እርምጃ በጋዛ ላይ እያካሄደች ባለበት አምስተኛ ቀን ላይ ነው።
ይህንን ስምምነት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ፣ ጋንትዝ እና የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ያሉበት “የጦርነት ካቢኔ” ያቋቁማሉ ተብሏል።
በስምምነቱ መሠረት ጦርነቱ በሚካሄድበት ጊዜ “የጦርነቱን ሂደት ከሚመለከቱ ጉዳዮች በስተቀር ማንኛውም አይነት ሕግም ሆነ የመንግሥት ሃሳብ ለውሳኔ አይቀርብም።”
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣንን እንዲይዙ የተሾሙ ሰዎች የኃላፊነት ጊዜ በጦርነቱ ወቅት ሁሉ የሚቀጥል ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እና የናሽናል ዩኒቲ ፓርቲ ሊቀ መንበር ጋንትዝ የአስቸኳይ ጊዜ መንግሥት ለማቋቋም የተስማሙት ላለፉት ቀናት ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው።
ከስምምነቱ በኋላ ከሁለቱም ወገን በጋራ በወጣ መግለጫ ላይ “የአስቸኳይ ጊዜ መንግሥት ለመመሥረት እና ጦርነቱን የሚመራ ካቢኔ ለማቋቋም ተስማምተዋል።
“ጦርነቱን የሚመራው ካቢኔም ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩን እና የተቃዋሚ ፓርቲውን መሪ በአባልነት ይዞ ይመሠረታል” ተብሏል።
ከሦስቱ ባለሥልጣናት በተጨማሪ የጦርነቱ መሪ ካቢኔን በታዛቢነት የሚያገለግሉ ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይካተቱበታል።