ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሐማስ ጥቃት ፈጽሞ እስራኤል ጋዛ ላይ የአየር ድብደባ ከጀመረች አንድ ሳምንት ሆነ
ልክ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ማለዳ ሐማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው የተቀናጀ ጥቃት የተጀመረው ግጭት ተባብሶ ቀጥሏል። ባለፉት ሰባት ቀናት እስራኤል በጋዛ ላይ ቀን አና ሌሊት ያለተቋረጠ የአየር ድብደባ አየፈጸመቸ ሲሆን፣ ሐማስም ወደ እስራኤል ሮኬቶቸን ሲተኩሰ ቆይቷል።
የቀጥታ ሽፋን
በእስራኤል- ሐማስ ግጭት የተከሰቱ ዋና ዋና ጉዳዮች
እስራኤል ሐማስ ላደረሰው ጥቃት ምላሽ ነው በሚል በጋዛ ሰርጥ የምታደርጋቸው ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች ቀጥለዋል።
- 1.1 ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሉባት የሰሜን ዋዲ ጋዛ ነዋሪዎች ወደ ደቡብ እንዲሸሹ የእስራኤል ጦር የ24 ሰዓታት ትዕዛዝ መስጠቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
- የእስራኤል ጦር የጋዛን ህዝብ "ለደህንነታቸው" ሲሉ አካካቢውን ለቀው እንዲወጡም መልዕክቱን አስተላልፏል።
- እስራኤል ሃማስን ለማጥፋት የምድር ላይ ዘመቻ ለማካሄድ እየተጠበቀችበት ባለበት ወቅት ነው ይህን ማስጠንቀቂያ የተሰማው
- የተባበሩት መንግሥታት ይህንን ያህል ህዝብ ማስወጣት የማይቻል ነው በሚል "አሰቃቂ ሰብዓዊ መዘዝ እንደሚያስከትል" በማስጠንቀቅ እስራኤል ውሳኔዋን እንድትቀለብስ ጠይቋል።
- እስራኤል በበኩሏ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየሞከረች መሆኗን ጠቅሳ የተመድን ምላሽ "አሳፋሪ ነው" ስትል ተችታለች።
- የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከፍልስጥኤም ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ጋር ዛሬ ይገናኛሉ ተብሏል።
- የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲንም እስራኤል ገብተዋል ተብሏል።
- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በእስራኤል እና በሐማስ ግጭት ላይ ለመምከር ዛሬ የዝግ ስብሰባ ያደርጋል ተብሏል።
ሐማስ የእስራኤልን ከሰሜን ጋዛ ለቃችሁ ውጡ ማስጠንቀቂያ ህዝቡ እንዳይሰማ ተናገረ
እስራኤል 1.1 ሚሊዮን ፍልስጥኤማውያን ከሰሜን ጋዛ ለቀው ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንዲሸሹ ማስጠንቀቂያ መስጠቷን ተክትሎ ሐማስ ህዝቡ እንዳይሰማ ተናገረ።
ሐማስ ማስጠንቀቂያውን "ሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳ" እንደሆነ ገልጾ ዜጎች ችላ እንዲሉትም አሳስቧል። የተባበሩት መንግሥታት የጋዛን ህዝብ የማስወጣት እቅድ በመቃወም ሁኔታውን የከፋ ያደርገዋል ሲልም እስራኤል ውሳኔዋን እንድትቀለብስ አጥብቆ ተማጽኗል።
"እንዲህ ያለ የህዝብ እንቅስቃሴ አስከፊ ሰብዓዊ መዘዞች ሳያስከትል መተግበር አይቻልም" ሲልም የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል።
ሐማስ ታጣቂዎቹን ለመጠበቅ ሲል ንጹሃን ዜጎችን አደጋ ውስጥ በመክተት እንደ ሽፋን ይጠቀምባቸዋል የሚሉ ትችቶች ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ይቀርብበታል።
ሐማስ በጋዛ ሰርጥ በአውሮፓውያኑ 2006 የተካሄደውን የህግ አውጭ ምርጫ ካሸነፈ በኋላ አካባቢውን ማስተዳደር ጀምሯል። በቀጣዩ ዓመትም ተቀናቃኙን ፋታህን በማስወገድ በጋዛ ሰርጥ ስልጣኑን አጠናክሯል።
ፈረንሳይ የፍልስጥኤም የድጋፍ ሰልፎችን ከለከለች
ሰበር, እስራኤል 1.1 ሚሊዮን ፍልስጥኤማውያን ከጋዛ በ24 ሰዓታት ይውጡ አለች- ተመድ
የእስራኤል ጦር 1.1 ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎች በ24 ሰዓታት ውስጥ እንዲወጡ መጠየቋን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።
ጦሩ በሰሜን ዋዲ ጋዛ የሚኖሩ ነዋሪዎች ወደ ደቡባዊ ጋዛ በ24 ሰዓታት ውስጥ መዛወር እንዳለባቸው ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መናገሩን የተመድ ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።
በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ፍልስጥኤማውያን 1.1 ሚሊዮን አካባቢ ሲሆኑ ይህም ከጠቅላላው የጋዛ ሰርጥ ህዝብ ግማሽ ያህሉ እንደሆነም ነው ተመድ ያስታወቀው።
ነዋሪዎች እንዲወጡ ከተጠየቁበትም ውስጥ በርካታ ህዝብ በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖርባት የጋዛ ከተማን ያጠቃልላል።
ትዕዛዙ የተላለፈው በጋዛ እና እየሩሳሌም ሰዓት አቆጣጠር ትናንት ዕኩለ ሌሊት አካባቢም መሆኑ ተገልጿል። የእስራኤል ጦር መኮንኖች በጋዛ ተቀማጭነታቸውን ላደረጉ የተባበሩት መንግሥታት የቡድን አመራሮች ስለተላለፈው ትዕዛዘዝም ነግረዋቸዋል።
ትዕዛዙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞችን ጨምሮ በተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ትምህርት ቤቶች ፣ የጤና ማዕከላት እና ክሊኒኮች የተጠለሉ ፍልስጥኤማውያንንም ያጠቃልላል ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት የጋዛን ህዝብ የማስወጣት እቅድ በመቃወም ሁኔታውን የከፋ ያደርገዋል ሲልም እስራኤል ውሳኔዋን እንድትቀለብስ አጥብቆ ተማጽኗል።
"እንዲህ ያለ የህዝብ እንቅስቃሴ አስከፊ ሰብዓዊ መዘዞች ሳያስከትል መተግበር አይቻልም" ሲልም የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል።
እስራኤል ምድር ላይ ልታደርገው ላቀደችው ወታደራዊ ዘመቻ በጋዛ ሰርጥ ድንበር በርካታ ወታደሮችን፣ ከባድ መሳሪያዎችን እያሰማራች ትገኛለች።
ሐማስ ላደረገው ጥቃት ምላሽ ነው በሚል እስራኤል እረፍት የሌለው የአየር ጥቃት እየፈጸመች ትገኛለች።
ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮም የእስራኤል አየር ኃይል በጋዛ ላይ እየፈጸመ ባለው የአየር ድብደባ ስድስት ሺህ የሚደርሱ ቦምቦችን በከተማዋ ላይ መጣሉም ተገልጿል።
ከቅዳሜ ጀምሮ ጋዛ በስድስት ሺህ ቦምቦች ድብደባ ተፈጽሞባታል፡ የእስራኤል ጦር
ባለፈው ቅዳሜ ግጭቱ ከጀመረ አንስቶ የእስራኤል አየር ኃይል በጋዛ ላይ እየፈጸመ ባለው የአየር ድብደባ ስድስት ሺህ የሚደርሱ ቦምቦችን በከተማዋ ላይ መታሉ ተገለጸ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች ቃል አቀባይ እንዳሉት ውጊያው ከተጀመረ በኋላ አስከ ሐሙስ ድረስ ቀን ከሌት በጋዛ ላይ በተፈጸመው የአየር ድብደባ ነው አየር ኃይሉ ጥቃቱን የፈጸመው።
ቃል አቀባዩ ዳንኤል ሃጋሪ በጋዛ ላይ የተፈጸመው የቦንብ ውጅብኝ ስድስት ሺህ መሆኑን ያሳወቁት፣ አሁን ኤክስ በሚባለው የቀድሞው ትዊተር የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ በጭስ ተሸፍኖ በፍንዳታ የሚናወጥ አንድ ሕንጻን የሚያሳይ ቪዲዮን በማያያዝ ነው።
በእስራኤል ጥቃት ጋዛ ውስጥ ከተገደሉ 450 የሚደርሱ ሕጻናት ናቸው
የሐማስ ጥቃትን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ባለው የአየር ድብደባ ከተገደሉት መካከል 447ቱ ሕጻነት፣ 248 ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የእስራኤል የአየር ድብደባ በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፣ ከቅዳሜ ጀምሮ አስከ ዛሬ ሐመስ አመሻሽ ድረስ በአጠቃላይ 1,417 ሰዎች ጋዛ ውስጥ መገደላቸው ተገልጿል።
የሐማስ ታጣቂዎች ወደ እስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን በመተኮስ እና ወደ እስራኤል ሰርጎ በመግባት ቅዳሜ ዕለት በፈጸሙት ጥቃት ከ1300 በላይ እስራኤላውያን መገደላቸውም ተነግሯል።
አሜሪካ በየትኛውም ጊዜ ከእስራኤል ጎን ትቆማለች፡ አንቶኒ ብሊንከን
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እስራኤል በሐማስ ለተፈጸመባት ጥቃት በጋዛ ላይ የአጸፋ እርምጃ እየወሰደች ባለበት ጊዜ አሜሪካ ለአስራኤል ያላትን አጋርነት ለመግለጽ በእስራኤል ጉብኝት እያደረጉ ነው።
ብሊንከን ከእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል።
ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፣ አሜሪካ በየትኛው ጊዜ ከአስራኤል ጎን እንደምትቆምና ድጋፏን እንደምትሰጥ ገልጸዋል።
- ለጉብኝት እስራኤል የገቡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን አገራቸው “በየትኛው ጊዜ እስራኤልን ለመርዳት” ከጎኗ እንደምትቆም በመግለጽ፣ ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ ነው አሉ።
- የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ሐማስ “አይሲስ ለአይሲስ በተስተናገደበት መንገድ ምላሽ ያገኛል” ብለዋል።
- የእስራኤል ሠራዊት ጋዛ ሰርጥ ውስጥ የማስጠንቀቂያ ወረቀቶችን በመበተን ነዋሪዎች ሐማስ የሚጠቀምባቸው ሕንጻዎችን ስለሚያጠቃ ነዋሪዎች ወደ መጠለያ እንዲሄዱ አሳስቧል።
- ስድስተኛ ቀኑን በያዘው እስራኤል በጋዛ ላይ በምትፈጽመው የአየር ጥቃት ቢያንስ 1,417 ሰዎች ሲገደሉ፣ 6,268 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን የጋዛ የጤና ባለሥልጣንት ገለጹ።
- በሌላ በኩል የሐማስ ታጣቂዎች የገደሏቸው እስራኤላውያን ቁጥርም 1,300 ደርሷል። ሌሎች በርካቶች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው የእስራኤል ባለሥልጣንት አስታውቀዋል።
- ብሪቲሽ ኤርዌይስ በእስራኤል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ወደዚያው የሚያደርጋቸውን በራረቀዎች ለሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት እንዲቋረጡ ወሰነ።
- የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከእስራኤል ለቀው ለመውጣት ለሚፈልጉ ዜጎቹ የአየር ጉዞዎችን ማመቻቸቱን አስታወቀ።
እስራኤል በሶሪያ አየር ማረፊያዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟ ተዘገበ
እስራኤል በዋና ከተማዋ ደማስቆ እና በሌላኛዋ ከተማ አሌፖ ውስጥ በሚገኙ አየር ማረፊያዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን የሶሪያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
የሶሪያ ዜና አገልግሎት ሳና “የሚሳኤል ፍንዳታዎች” በአየር ማረፊያው የመንደርደሪያ ሜዳ ላይ ጉዳት በማድረስ ከአግልግሎት ውጪ አድርጓቸዋል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ የሶሪያ የአየር መከላከያ መሳሪያዎች ምላሽ ለመስጠት መተኮሳቸውን የሶሪያ መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።
የሶሪያ ሰብአዊ መብቶች ክትትል የተባለው መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የግጭት ተከታታይ ቡድንም በርካታ ፍንዳታዎች አሌፖ ውስጥ መከሰታቸውን አረጋግጧል።
ይህ የአየር ጥቃት መፈጸሙን የሚያመለክተው ዘገባ የወጣው የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሶሪያን ይጎበኛሉ ከተባለበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።
ሶሪያ እና ኢራን ከእስራኤል ጋር በጠላትንት የሚፈላለጉ አገራት ሲሆኑ፣ ኢራን አሁን እስራኤል እያደነችው ያለው ሐማስ ቡድንን እንደምትደግፍ ይነገራል።
እስራኤል ከዚህ በፊትም ሶሪያ ውስጥ ያሉ የኢራን ናቸው የተባሉ እና የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን የሆነውን ሄዝቦላህን ኢላማዎች በተደጋጋሚ ብትደበድብም በይፋ አረጋግጣ አታውቅም።
የኢራን ፕሬዚደንት እስራኤልን ‘በዘር ማጥፋት’ ከሰሱ
የኢራን ፕሬዚደንት እስራኤልን በዘር ማጥፋት ከሰሱ።
ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት ነው።
ፕሬዚደንት ኢብራሒም ሬይሲ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃ እና የነዳጅ አቅርቦት እንዲቋረጥ ተደርጎ በጋዛ ላይ የተደረገው ከበባ ሁሉንም ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የጣሰ ነው ሲሉ ኮንነውታል።
ኢራን በጋዛ ያለውን ታጣቂ ቡድን ሐማስን በመደገፍና በማስታጠቅ ትታወቃለች።
ሆኖም ማክሰኞ ዕለት የኢራን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ አገራቸው ቅዳሜ ዕለት በእስራኤል ላይ ከተፈተው ጥቃት ጀርባ እንደሌለችበት ተናግረዋል።
መሪው ይህን ይበሉ እንጂ ከጥቃቱ በኋላ በቴሌቪዥን በሰጡት በዚህ የመጀመሪያ መግለጫቸው፣በአይሁድ መንግሥት ላይ ጥቃቱን ለመፈፀም ያቀዱትን አድንቀናል ብለዋል።
ሰበር, ታጋቾች እስኪለቀቁ ጋዛ መብራት፣ ውሃ እና ነዳጅ አታገኝም- እስራኤል
ታጋቾች እስኪለቀቁ ድረስ የጋዛ ሙሉ ከበባ እንደሚቀጥል የእስራኤል ኢነርጂ ሚንስትር እስራኤል ካትዝ ገለጹ።
"ታጋቾች" እስኪፈቱ ድረስ "መብራት አይኖርም፣ ውሃ አይለቀቀም እንዲሁም ምንም ዓይነት የነዳጅ መኪና አይገባም" ሲሉ እስራኤል ካትዝ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል።
የቅዳሜውን የሐማስን ጥቃት ተከትሎ ነው እስራኤል ወደ ጋዛ ሰርጥ የሚገቡ ምርቶችን ያገደችው። እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ኤሌክትሪክ እና ውሃን ጨምሮ መሰረተ ልማቶች ተቋርጠዋል።
መውጫ መግቢያ በታጣባት ጋዛ የተወሰነ እርዳታ እንዲገባ እና ነዋሪዎች እንዲወጡ ለማድረግ አሜሪካ ከእስራኤል፣ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከግብጽ ጋር እየተነጋገረች መሆኗን ዋይት ሃውስ አስታውቋል።
ከጋዛ የተገኙ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ በምታደርገው የአየር ጥቃት የሞቱ ፍልስጥኤማውያን ቁጥር ከ1 ሺህ 200 ሰዎች በላይ መድረሱን የጤና ሚኒስቴሯ አስታውቋል።
በተጨማሪም 5 ሺህ 339 ፍልስጥኤማውያን ቆስለዋል።
እስራኤል ሃማስ ለሰነዘረብኝ ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ ነው በሚልም ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች በጋዛ ሰርጥ ላይ እየፈጸመች ትገኛለች።
ሃማስ ባደረገው የተቀናጀ ጥቃት እና እስራኤል እየፈጸመችው ባሉ የአየር ጥቃቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር 2 ሺህ 500 ደርሷል።
ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶቹንም ተከትሎ ከ338 ሺህ በላይ ፍልስጥኤማውያን መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጥኤም ስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል።
አብዛኛዎቹም በሆስፒታሎች እና በተባበሩት መንግሥታት ትምህርት ቤቶች ተጠልለው ይገኛሉ።
እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ኤሌክትሪክ እና ውሃን ጨምሮ መሰረተ ልማቶች ተቋርጠዋል።
መውጫ መግቢያ በታጣባት ጋዛ የተወሰነ እርዳታ እንዲገባ እና ነዋሪዎች እንዲወጡ ለማድረግ አሜሪካ ከእስራኤል፣ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከግብጽ ጋር እየተነጋገረች መሆኗን ዋይት ሃውስ አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት በእስራኤል እና በጋዛ ጉዳይ ነገ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በእስራኤል እና ጋዛ መካከል ያለው ግጭት ላይ ለመወያየት ነገ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው።
በጋዛ ሰርጥ ስላለው ሁኔታ ለመነጋገር ስብሰባውን የጠራችው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታውን ምክር ቤት በሊቀመንበርነት የተረከበችው ብራዚል መሆኗን የአገሪቷ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቬራ በኒውዮርክ በሚካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ እስያ የሚያደርጉትን ጉዞ አቋርጠዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት አባላት እሑድ ዕለት ባካሄዱት ስብሰባ እስራኤል እና ፍልስጥኤምን በሚመለከተው ፖሊሲ ላይ ወደ አንድ ሃሳብ መምጣት አልቻሉም ነበር።
የብራዚል ፕሬዚደንት ሊዩዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ረቡዕ ዕለት “በየትኛውም ዓለም ሕጻናት በፍጹም መታገት የለባቸውም” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ፕሬዚደንቱ ጨምረውም ሐማስ ከቤተሰቦቻቸው ነጥቆ ያገታቸውን ሕጻናት መልቀቅ አለበት ብለዋል።
ፕሬዚደንቱ እስራኤል በፍልስጥኤማዊ ሕጻናት እና እናቶቻቸው ላይ የምታዘንበውን ቦምብ እንድታቆም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህም በግብጽ በኩል ከጋዛ እንዲወጡ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
“በጦርነት እብደት ውስጥም ቢሆን ትንሽ ሰብዓዊነት ሊኖር ይገባል” ሲሉም አክለዋል።
ብሊንከን እና የፍልስጥኤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ሊወያዩ ነው
የፍልስጥኤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በመጪው አርብ ተገናኝተው ሊነጋገሩ መሆኑን የፍልስጥኤም ነጻነት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሁሴን አል-ሼክ ገለጹ።
የፍልስጥኤም የፖለቲካ መሪዎች ዌስት ባንክን በሚመራው በማህሙድ አባሱ ፋታህ ፓርቲ እና ጋዛ ሰርጥን በሚቆጣጠረው ታጣቂ ቡድን ሐማስ ተከፋፍለዋል።
ብሊንከን ከሰዓታት በኋላ እስራኤል እንደሚገቡ ይጠበቃል።
በቆይታቸውም የሐማሳን ጥቃት ተከትሎ ለእስራኤል እና ለህዝቦቿ ያላቸውን ድጋፍ ያሳያሉ ተብሏል።
የፍልስጥኤም ባለስልጣናት በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ፕሬዝዳንት አባስ ከዮርዳኖሱ ንጉስ አበዱላህ ጋር ዛሬ አማን ውስጥ ይገኛሉ።
እያንዳንዱ የሐማስ አባል በሞት ጥላ ሥር መሆኑን ኔታንያሁ ተናገሩ
በእስራኤል-ሐማስ ዙሪያ ሐሰተኛ መረጃዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ የአውሮፓ ህብረት ሜታን ጠየቀ
ሐማስ ጥቃት ከመፈጸሙ ከቀናት በፊት ግብፅ እስራኤልን አስጠንቅቃ ነበር - አሜሪካ
ሐማስ የእስራኤልን መከላከያ ለማለፍ የተጠቀመው የ2ኛው የዓለም ጦርነት መሣሪያ
የሐማስ ጥቃት እና በሕዝቡ ዘንድ የፈጠረው ድንጋጤ በቤተ እስራኤላዊው ዐይን
‘የት እንሂድ?’ የጋዛ ነዋሪዎችን መሸሸጊያ አልባ ያደረገው የተጠናከረው የእስራኤል ጥቃት