የድምጽ መስጠት ሂደት በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች
ዛሬ ማለዳ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ድምጽ መስጠት ተጀምሯል። የቢቢሲ ዘጋቢዎች ከሚገኙባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች የድምጽ መስጠት ሂደቱን በሚመለከት ተከታዮቹን ፎቶዎች አጋርተውናል።






ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በትናንትናው ዕለት ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ተጀምሮ በአንዳንድ ቦታዎችም እስከ ሌሊት እንዲሁም በዛሬው ዕለትም እንዲሁ ድምፅ የሚሰጥባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በዚህ ምርጫ ለመሳተፍ ከትግራይ ክልል በስተቀር ከ37 ሚሊየን በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን የኢትጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል። 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ዕጩዎቻቸውን ለተወዳዳሪነት አቅርበዋል። በዚህ ምርጫ ዕጩዎች ለአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች ይወዳደራሉ።
ዛሬ ማለዳ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ድምጽ መስጠት ተጀምሯል። የቢቢሲ ዘጋቢዎች ከሚገኙባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች የድምጽ መስጠት ሂደቱን በሚመለከት ተከታዮቹን ፎቶዎች አጋርተውናል።







ብልጽግናን ወክለው ለአማራ ክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ ድምጻቸውን ለመስጠት በማለዳ ተሰልፈው ይታያሉ።
በዚህ የምርጫ ጣቢያ ድምጽ መስጠት መጀመር ከነበረበት ሰዓት 45 ደቂቃ ዘግይቶ ነው የተጀመረው። ቢዘገይም ዶ/ር ድረስ ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

ባሕር ዳር ጣና ክፍለ ከተማ ምርጫ ጣቢያ 2ለ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዕጩ በመሆን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ድምጽ የሚሰጡት በዚህ ምርጫ ጣቢያ ነው።

ዶክተር ደሳለኝ የቀድሞ የአብን ሊቀመንበር በጣና ክፍለ ከተማ 2ሀ ለመምረጥ ተሰልፈው ይታያሉ።

ሃዋሳ ፀጥ ረጭ ብላለች። በአስፋልት መንገድ የተሞላችው የሃይቅ ዳር ከተማ ለወትሮው የነበራት በባለሶስት እግር ተሽከርካሪ የታጀበ ግርግር ተለይቷታል። ብዙዎች እግራቸው ዛሬ ወደ ተለመደ የሕይወት ሳንካቸው ሳይሆን ወደምርጫ ጣብያ መርቷቸዋል።
የድምፅ መስጫ ጣብያዎች በንጋቱ ድምፃቸውን ለመስጠት በመጡ ሰዎች ተሞልተዋል። አብዛኛዎቹ ቢቢሲ የጎበኛቸው ጣብያዎች ድምፅ አሰጣጥ የጀመሩት 12፡30 ገደማ ነው። ሰልፉም እየረዘመ የመጣው ፀሐይ ብቅ ማለት ስትጀምር ነው። የምርጫ አስተባባሪዎች ወደ ውስጥ የሚገባውን ሰው መታወቂያ ካርድ እየተመለከቱ ‘ሳኒታይዘር’ ያድላሉ።
መራጮች ወደ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ገለፃ ሲደርግላቸው ተመልክተናል። ውስጥ ገብተው ስማቸውን አጣርተው ወደ ሚስጢራዊው ቦታ የሚሰዷቸው አስተባባሪዎችም ገለፃ ያደርጉላቸዋል። የምርጫ ታዛቢዎች ቦታ ቦታቸውን ይዘው የሚሆነው ይቃኛሉ።
ሃዋሳ ከሰሞኑ ዝናብ ሲያርሳት ስለነበር አየሯቀዝቀዝ ብሏል። እናቶች ጋቢያቸውን ጣል አድርገው፤ አባቶች ደግሞ ካቦርታቸውን ደርበው ለመምረጥ ተሰልፈዋል። አስተባባሪዎቹ እባካችሁ ርቀታችሁን ጠብቁ እያሉ ቢመክሩም መራጮች ጠቅጠቅ ብለው ተሰድረዋል። ቢቢሲ ተዘዋውሮ ያያቸው በሃዋሳ ከተማ ያሉ የምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ የፀጥታ ሰዎች አሉ።
አብዛኛዎቹ የምርጫ ጣብያዎች ውስጥ የሚገኙ ሚስጢራዊ ምረጫዎች መብራት እንዲኖራቸው ቢደረግም በአንድ ድምፅ መስጫ ግን በፀሐይ የሚሠራ መብራት ለአባቶች እና እናቶች በቂ ሆኖ አልተገኘም። በዚህ ድምፅ መስጫ ጣብያ አንድ አባት “ምንም ሊታየኝ አልቻለም” ሲሉ ለአስተባባሪዎች ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ነበር።

በሐዋሳ ከተማ መራጮች ድምጻቸውን መስጠት የጀመሩት ከማለዳው 12 ሰዓት ነው።



በደሴ ከተማ አገር ግዛት መርሆ ግቢ ምርጫ ጣቢያው ቢቢሲ የደረሰው ከማለዳው 12፡00 ላይ ነበር።
ሰሞኑን ጸሐያማ ሆኖ የሰነበተው የደሴ የአየር ሁኔታ ትናንት በምርጫው ዋዜማ በስሱ ዝናብ ጎብኝቶት ነበር።
አየሩ ትንሽ ቀዝቀዝ ይላል። ቢሆንም ግን መራጮች ተሰልፈው ለመምረጥ እየተጠባበቁ ነው።
በጣቢያው እያንዳንዱ ፓርቲ የወከላቸው እንዲሁም ሌሎች የምርጫ ታዛቢዎች፣ ምርጫ አስፈፃሚ የጸጥታ አካላትና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል መመሪያ አስከባሪዎች ይገኛሉ።
ያነጋገርናቸው መራጮች “ስለ ምርጫና አመራረጡ በቂ ግንዛቤ አለን፤ ድምጻችን ለውጥ ያመጣል ብለን እናስባለን” ብለዋል።
ረቢዓ አራጋው ለመምረጥ የ3 ወር ልጇን ይዛ ነው ወደ ምርጫ ጣቢያው ያቀናችው። ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ድምጿን የምትሰጠው።
ከዚህ በፊት በተካሄዱት ምርጫዎች አልመረጠችም። "አሁን በመምረጤ ደስተኛ ነኝ" ብላለች። “ካልተመረጠ አገር ሠላም አትሆንም” የምትለው ረቢዓ የምትመርጠው ፓርቲ ይህንን ለውጥ ያመጣልኛል ብላ ተስፋ አድርጋለች።
ዐይነኩሉ ገ/ጻድቅ ይባላሉ። የ77 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ናቸው። ከልጅ ልጃቸው ጋር ነው ለመምረጥ ወደ ምርጫ ጣቢያው በማለዳ ያመሩት። ከዚህ በፊት ያሉትን አምስቱን ምርጫዎች መርጠዋል። “የዘንድሮው ምርጫ በጸጥታውና በሥነ ሥርዓቱ ለየት ብሎብኛል፤ ምርጫው በሰላም ይጠናቀቃል ብዬ እጠብቃለሁ” ብለዋል።
ከምርጫው በኋላ በአገሪቷ ያጋጠሙ ችግሮች እንደሚፈቱ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ይህ አዲስ አበባ 22 እካባቢ የሚገኘው የቀጠና 6 ምርጫጣቢያ 10 ሲሆን ወደ ጣቢያው ዘግይቶ የደረሱ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እየተራገፈ ነው።
በዚህ አካባቢ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚንስትሩ ስለሺበቀለ (ዶ/ር፣ኢንጂነር) የብልጽግና ፓርቲን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።
እንዲሁም የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አቶ በቃሉ አጥናፉን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ አድርጎ አቅርቧል።


• በስድስተኛው ምርጫ ላይ ድምጽ ለመስጠት 37 ሚሊዮን 408 ሺህ 600ዜጎች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ መካከልም 20 ሚሊዮን 317 ሺህ 472 ወንዶች እንዲሁም 17 ሚሊዮን 91 ሺህ 128 ሴቶች ናቸው።
• በምርጫው 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 8,209 ዕጩዎችንያረቡ ሲሆን በግል ደግሞ 125 ዕጩዎች ለፌደራልና ለክልል ምክር ቤቶች ተወዳዳሪሆነው ቀርበዋል።
• ገዢው ብልጽግናፓርቲ 2,432 ተወዳዳሪዎችን በማቅረብ በዕጩዎች ብዛት ቀዳሚ ሲሆን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 1,385 ዕጩዎችን እንዲሁም እናት ፓርቲ ደግሞ 573 ዕጩዎችን በማቅረብ ዋነኞቹ ናቸው።
·ዛሬ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በሚካሄደው ምርጫ ለ445 የፓርላማ መቀመጫዎች ድምጽ የሚሰጥ ሲሆን ለ64ቱ ወንበሮች ደግሞ ጳግሜ 1/2013 ዓ.ምድምጽ ይሰጣል።
