ስድስተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ 2013

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በትናንትናው ዕለት ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ተጀምሮ በአንዳንድ ቦታዎችም እስከ ሌሊት እንዲሁም በዛሬው ዕለትም እንዲሁ ድምፅ የሚሰጥባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በዚህ ምርጫ ለመሳተፍ ከትግራይ ክልል በስተቀር ከ37 ሚሊየን በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን የኢትጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል። 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ዕጩዎቻቸውን ለተወዳዳሪነት አቅርበዋል። በዚህ ምርጫ ዕጩዎች ለአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች ይወዳደራሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ምርጫ ቦርድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

  2. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሻሻ ውስጥ ድምጻቸውን ሰጡ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ደምጽ ሲሰጡ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጂማ ውስጥ በምትገኘው የትውልድ ስፍራቸው በሻሻ ተገኝተው ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወዳደሩበት የምርጫ ጣብያ ጎማ 2 የሚሰኝ ሲሆን ከእርሳቸው ጋር አብረው የሚፎካከሩት የኢዜማ እና እናት ፓርቲ ዕጩዎች ናቸው።

    የኢዜማ ዕጩ ተወዳዳሪው አቶ ካሊድ ጀማል የሚባሉ ሲሆን የእናት ፓርቲው ተወካይ ደግሞ ዳግም ወሪሶ ናቸው።

  3. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ በሻሻ ከመሄዳቸው በፊት አዲስ አበባ ውስጥ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአዲስ አበባ 'ዶ/ር አብይ ስፔሻል' የተሰኘ ምግብ ሲመገቡ

    የፎቶው ባለመብት, PM Abiy twitter page

    በትውልድ መንደራቸው በሻሻ ድምጽ ይሰጣሉ ተብለው የሚጠበቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በምርጫው ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

    አዲስ አበባ ውስጥ ሰሜን ማዘጋጃ በሚባለው አካባቢ በአንዲት እናት የሚዘጋጅና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስም የተሰየመና በከተማው መነጋጋሪያ የሆነውን የምግብ አይነት በሚያቀርበው ምግብ ቤት ተገኝተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚህ ጉብኝታቸው ‘እማማ ፊሽካ’ በሚል ቅጽል የሚታወቁት እናት በሚያስተዳድሩት ምግብ ቤት ተገኝተው “ዶክተር ዐቢይ ስፔሻል” የተባለውን እና አራት ሰዎች ሊመገቡት የሚችለውን 200 ብር የሚከፈልበትን ምግብ ቀርቦላቸዋል።

    ከዚህ ባሻገር ረፋድ ላይ ከከተማዋ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውን በመገንባት ላይ የሚገኘውን ከፑሽኪን አደባባይ ወደ ጎተራ ማሳላጫ የሚወስደውን የመንገድ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል።

    አስከትለውም በባለቤታቸው በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በኩል ችግረኞችን ለመደገፍ የሚገነባውን በቀን አንድ ሚሊዮን ዳቦ የማምረት አቅም አለው የተባለውን የዳቦ ፋብሪካንም ጎብኝተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ችግኝ ሲተክሉ

    የፎቶው ባለመብት, PM Abiy twitter page

  4. የአዲስ አበባ ጉዳይ፡ የ2013 ምርጫ ዋነኛ ጉዳይ

  5. ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር እየተካሄደ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ

    ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ እስከአሁን ባሰባሰበው መረጃ መራጩ ህዝብ6ኛውን አገራዊ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላማዊና በተረጋጋመንገድእያካሄደ መሆኑን ገልጿል።

    በቀጣይም ተመሳሳይ መረጃዎችን ከፌዴራልና ከክልል እንዲሁም ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እያሰባሰበ ተአማኒነት ያለው፣ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለህዝቡ ተደራሽ እንደሚያደርግ ኮሚሽኑ ጨምሮ ገልጿል፡፡

    ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

    የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Federal Police Commission

  6. ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የፖለቲካ አመራሮች ድምጻቸውን ሰጡ

    ዛሬ እየተካሄደ ባለው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተለያዩ የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚገኙ ባለሥልጣናትና የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

    አዲስ አበባ ውስጥ የዋና ከተማዋ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የኢዜማ መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ምክትላቸው አቶ አንዱዓለም አራጌ ድምጻቸውን በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ድምጽ ሰጥተዋል።

    የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ
    የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ
    የኢዜማ መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ
  7. ምርጫ 2013 እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት የተጣለባቸው አምስቱ የቦርድ አባላት

  8. ኢሰመኮ በምርጫው ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል እንደሚያደርግ ገለፀ

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

    የፎቶው ባለመብት, EHRC

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በሚደረገው ብሔራዊ ምርጫ ላይ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ለማድረግ ባለሙያዎች ማሰማራቱን አስታወቀ።

    ኮሚሽኑ ዛሬ እሁድ ሰኔ 13/2013 ዓ.ም በማኅበራዊ የትስስር ገፁ ባወጣው መግለጫ የሰብአዊ መብቶችን ሁኔታ ለመከታተል ያስችል ዘንድ የምርጫ ክትትል ቡድኖች ማቋቋሙንና ምርጫ በሚካሄድባቸው ሁሉም ክልሎች ባለሙያዎች ማሰማራቱን አመልክቷል።

    ኮሚሽኑ ለዚህም በተሻሻለው የማቋቋሚያ አዋጁ አንቀፅ 6 መሰረት በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅን ክትትል የማድረግ ስልጣን እና ኃላፊነት እንደተሰጠውም አስታውቋል።

    እነዚህ ቡድኖች በምርጫው ዕለት እና ከምርጫው በኋላ ባሉት ቀናት በተለያዩ ክልልሎች በመገኘት ምልከታ እንደሚያደርጉም በመግለጫው ሰፍሯል።

    በምርጫው ላይም መራጮችን ጨምሮ የምርጫ አስተባባሪዎች፥ የፀጥታ አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዕጩዎች፣ ታዛቢዎችንና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር መረጃዎችን እንደሚሰበስቡ ተገልጿል።

  9. “ምርጫው የሠላምና ዲሞክራሲ ሒደት አጋዥ እንጂ ሁሉንም ችግር አይፈታም”

    የአብን ምክትል ሊቀመንበርና የፓርቲው የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ የሱፍ ኢብራሒም

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበርና የፓርቲው የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የሱፍ ኢብራሂም ምርጫው የሠላምና ዲሞክራሲ ሒደት አጋዥ እንጂ ሁሉንም ችግር አይፈታም አሉ።

    ምክትል ሊቀመንበሩ ይህን ያሉት ዛሬ በደሴ ከተማ ሳላይሽ ለ1 ምርጫ ጣቢያ ድምጻቸውን ለመስጠት በተገኙበት ነው።

    አቶ የሱፍ ኢብራሂም በድምጽ አሰጣጡ ሂደት ምንም ችግር እንዳላጋጠማቸውና ሂደቱን የተከተለ እንደሆነ ተናግረዋል።

    ይሁን እንጅ “ለመምረጥ ካርድ ይዤ ስመጣ መታወቂያ አልተጠየቅኩም፤ ይህ ሊያጋጥም የሚችል ቢሆንም ያልተመዘገበ እንዲመርጥ በር ይከፍታል” ሲሉ ተችተዋል።

    በቅድመ ምርጫው ወቅት በተለያዩ ቦታዎች የምርጫ ቅስቀሳ ባነሮችና ምልክቶች እንደተቀደዱባቸውና በተለይ በአማራ ክልል ውስጥ ችግሮች እንዳጋጠሟቸው የገለጹት አቶ የሱፍ፤ ይህንንም ለምርጫ ቦርድ እንዳሳወቁ ተናግረዋል።

    አገሪቷ ውስብስብ ነገሮች ውስጥ ማለፏን ገልጸው፤ ለሠላምና ዲሞክራሲያዊ ሂደት ምርጫው አጋዥ እንጂ ሁሉንም ነገር ፈቺ አይደለም ብለዋል።

    በድህረ ምርጫው በትብብር በአገራዊ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ከመንግሥትም ከተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሃሳብ እንዳለ ጠቁመዋል።

  10. በምርጫ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች

    የምርጫ ታዛቢ

    በደሴ ከተማ ከማለዳው 12፡00 ሰዓትጀምሮ ከተቋም እስከ ፒያሳ፣ ከቧንቧ ውሃ እስከ መርሆ ግቢ፣ ከአራዳ እስከ ሳላይሽ ያሉ የምርጫ ጣቢያዎችን ቢቢሲ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

    በተመለከትናቸው የምርጫ ጣቢያዎች አብዛኞቹ መራጮች እና ምርጫ አስፈጻሚዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሲወስዱ ታይተዋል።

    አብዛኞቹ መራጮችና የምርጫ አስተናባሪዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አድርገዋል።

    አስተባባሪዎች ሳኒታይዘር [የእጅ ማጽጃ] በመያዝ መራጮች ድምፅ ለመስጠት ሲገቡ እጃቸውን አጽድተው እንዲገቡ ቆመው ያስተናብራሉ። ፈታሾችም የእጅጓንት አጥልቀው ሲፈትሹ አስተውለናል።

    ነገር ግን በአንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ ጣቢያዎች ዘግይቶ መከፈትና የመራጮች መበራከት አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ አደጋች አድርጎታል።

    አስተባባሪዎች መራጮች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ ደጋግመው ያስታውሳሉ።

  11. የኦሮሚያ ክልላዊ ፕሬዝዳንት ድምጻቸውን ሰጡ

    የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ

    የፎቶው ባለመብት, OBN

    የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በግንጪ ከተማ የምርጫ ጣቢያ 01 ተገኝተው ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

    ርዕሰ መስተዳድሩ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ "ይህ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ያገኟቸውን ድሎች ለማስቀጠል መሠረት የሚጥሉበትና የአገሪቱን ፖለቲካ ወደ ክልል ምክር ቤትና ወደ ፓርላማ ለማስገባት ትልቅ እድል ነው" ብለዋል።

    በተጨማሪም ይህ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው መሬት እንዲይዝ መሠረት የሚጥል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

  12. የአዲስ አበባው ሥራ አስኪያጅ ሐዋሳ ላይ ድምጻቸውን ሰጡ

    ጥራቱ በየነ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ

    የቀድሞ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ “የከተማው ሥራ አስኪያጅ" የሆኑት አቶ ጥራቱ በየነ፣ በሐዋሳ ከተማ ተገኝተው ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

    ከንቲባው በርካታ መራጭ ተሰልፎ ድምጹን ለመስጠት እየተጠባበቀ በነበረበት በጉዱማሌ 02 ምርጫ ጣቢያ ነው ድንገት የተገኙት።

    አቶ ጥራቱ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመግባት ነው እየተወዳደሩ የሚገኙት።

    ወረፋውን ሲጠባበቅ የነበረው ድምጽ ሰጭ ማኅበረሰብ ከተቀመጠበት አግዳሚ ወንበር ተነስቶ ለከንቲባው ቅድሚያ በመስጠት ድምጻቸው ኮሮጆ ውስጥ ከትተው እንዲሄዱ ፈቅዶላቸዋል።

    አቶ ጥራቱ ድምጽ ሰጥተው ከወጡ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ድምጽ “ውጤቱ ምንም ሆነ ምን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ“ ብለዋል።

    “ወደ ዴሞክራሲ እየሄድን እንደሆነ ማሳያው ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ መምረጡ ነው” ያሉት ምክት ከንቲባው “ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ከምርጫው በኋላም ቢሆን አብሬ እሠራለሁ” ብለዋል።

    በሌላ በኩል የሕብር ኢትዮጵያ ፓርቲ አባል የሆኑት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪው ታምራት አሰፋ ከብልጽግና ፓርቲ ተወካዩ አቶ ጥራቱ ጎን ቆመው “ምርጫው እስካሁን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ነው፤ ምንም ዓይነት ችግር አላየንም” ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

    ተቀናቃኙ አቶ ታምራት “ማንም ያሸንፍ ማን በፀጋ እንቀበለዋለን፤ ምክንያቱም ሥልጣን ሰጪው ሕዝብ ነው” ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም ተናግረዋል።

  13. በአዳማ እና በሻሻ በርካታ መራጮች ድምጻቸውን ለመስጠት ወጥተው ታይተዋል

    ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የተለያዩ ከተሞች በርካታ መራጮች ድምጻቸውን ለመስጠት በነቂስ ወጥተው ታይተዋል። በአዳማ

    በስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ በብዛት መራጮች ከታዩባቸው አካባቢዎች በሻሻ አንዱ ነው
    የምስሉ መግለጫ, በስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ በብዛት መራጮች ከታዩባቸው አካባቢዎች መካከል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የትውልድ ስፍራ የሆነው በሻሻ አንዱ ነው
    በአዳማ በርካታ መራጮች ድምጻቸውን ለመስጠት እየተጠባበቁ ይታያሉ
    በአዳማ በርካታ መራጮች ድምጻቸውን ለመስጠት እየተጠባበቁ
    የምስሉ መግለጫ, በአዳማ በርካታ መራጮች ድምጻቸውን ለመስጠት እየተጠባበቁ ይታያሉ
  14. "የምንታገለው ከሥልጣን ግብግብ ይልቅ ሕዝብ የሚያሸንፍበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመጣ ነው" ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ (አብን)

    ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ
    የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ

    በአማራ ክልል ሰፊ ድጋፍ አለኝ የሚለው አብን ለተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት በድምሩ 513 ዕጩዎችን በአገር ደረጃ አቅርቧል።

    ከነዚሀች ዕጩዎች መሀል 419 የሚሆኑት በአማራ ክልል የሚወዳደሩ ናቸው። ከጥቂት ሰዓት በፊት የአብን የቀድሞ ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለተወካዮች ምክር ቤት በሚወዳደሩበት የባሕር ዳር ምርጫ ጣቢያ (ጣና ክፍለ ከተማ 2ሀ) ድምጽ ሰጥተዋል።

    ዶ/ር ደሳለኝ በርካታ ጋዜጠኞች በተገኙበት የተሰለፈውን ሕዝቡን አስፈቅደው ቀድመው ድምጽ ለመስጠት ወደ አዳራሹ ገብተው ድምጽ ሰጥተው ወጥተዋል።

    ከአዳራሹ ደጅ አጭር ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጥተዋል። "ይመራኛል የምለውን ፓርቲ ድምጽ ሰጥቻለሁ። እኔ በመረጥኩበት ጣቢያ ምርጫው በጣም ሰላማዊና የተረጋጋ ነው። ምርጫው ሒደቱን ጠብቆ እየተካሄደ መሆኑን መረዳት ችያለሁ" ብለዋል።

    ስለ ምርጫው ፍትሐዊነትና የተጠየቁት ዶ/ር ደሳለኝ "ስለ ምርጫው ነጻነት አጠቃላይ ድርጅታችን ዝርዝር ግምገማ ካካሄደ በኋላ ነው መናገር የምንችለው። አሁን ባለበት ሁኔታ ላይ ሆኜ ስለ ምርጫው ፍትሀዊነትና ነጻነት መናገር ያስቸግረኛል" ብለዋል።

    ብትሸነፉ ውጤቱን በጸጋ ትቀበላላችሁ ወይ ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ደሳለኝ ይህን ብለዋል። "በኛ በኩል ስንታገልለት የነበረውም ከጥሬ የሥልጣን ግብግብ ይልቅ ሕዝብ የሚያሸንፍበት ዲሞክራሲያው ሥርዓት እንዲመሠረት ነው። የሕዝባችንን ድምጽ እናከብራለን። ነገር ግን በሂደቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን፣ ቅድመ ምርጫን ጨምሮ ያጋጠሙ አንዳንድ ችግሮች አሉ። አሁንም አንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ እየደረሱን ያሉ ሪፖርቶች አሉ። አንዳንዶቹ ላይ ቀለል ያሉ ጥሰቶች ተፈጽመዋል። ዙሮ ዙሮ እነዚህ አጠቃላይ ሁኔታዎች በምርጫው ውጤት ላይ ምን ተጽእኖ አላቸው የሚለውን ከገመገምን በኋላ በዝርዝር ለሕዝባችን እናሳውቃለን። በመርህ ደረጃ ግን ሕዝባችን የሚሰጠውን ማንኛውንም ድምጽ በጸጋ እንቀበላለን" ብለዋል።

  15. አንድ ሳጥን የሕዝብ ተወካዮች የድምፅ መስጫ ወረቀት የሌላ ወረዳ ሆኖ ተገኘ

    በደሴ ከተማ ወ/ሮ ሲህን ምርጫ ጣቢያ ለ14፣ አንድ ሳጥን የሕዝብ ተወካዮች የድምፅ መስጫ ወረቀት ታዛቢዎች በተገኙበት ሲከፈት የወረኢሉ ወረዳ ሆኖ መገኘቱን የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ገለጸ።

    የምርጫ ጣቢያው ከማለዳው 12፡00 አልተከፈተም ነበር። መራጮችም ተሰልፈው በመጉላላታቸው ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ነበር።

    የምርጫው ጣቢያ ኃላፊ ኤርሚያስ አበበ የምርጫ ጣቢያው ዘግይቶ የተከፈተው የድምጽ መስጫ ወረቀት ከሌላ ወረዳ [ወረኢሉ ወረዳ] ጋር በመቀያየሩ እርሱ እስከሚስተካከል እንደሆነ ተናግሯል።

    “ምርጫ ጣቢያው ማለዳ 12፡00 ቢከፈትም የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ታዛቢዎች በተገኙበት ሲከፈት አንዱ ሳጥን የሌላ ወረዳ ሆኖ ተገኝቷል” ብሏል።

    ኃላፊው እንደገለፀልን የድምፅ መስጫ ወረቀቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድምፅ መስጫ ወረቀት ነው።

    ያጋጠመውን ችግር ለደሴ ምርጫ ክልል ሪፖርት ተደርጎ ሌላ መጠባበቂያ የድምጽ መስጫ ወረቀት መለወጡና የተሳሳተውን በላስቲክ እንደታሸገ ተቆጥሮ መመለሱን የምርጫው ጣቢያ ኃላፊ ገልጿል።

    በደሴ መራጮች ተሰልፈው
  16. ዛሬ ምርጫ የማይካሄድባቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?

    በአጋሮ ድምጻቸውን የሚሰጡ መራጭ

    ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ዛሬ በመላ አገሪቱ እየተካሄደ ይገኛል። ዛሬ ምርጫ ማካሄድ ባልተቻለባቸው አካባቢዎች ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

    በሶማሌ እና ሐረሪ ክልል ምርጫ የሚካሄደው ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም እንዲሆን መወሰኑን ቦርዱ አስታውቋል።

    በተጨማሪም ስድስተናው አገራዊ ምርጫ በዛሬው ዕለት በትግራይ ክልል አይካሄድም።

    ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተጨማሪ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ከምርጫው ጋር ሰኔ 14 በአንድ ቀን እንዲካሄድ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኗል።

    በጸጥታ ችግር ምክንያት ጳጉሜ 1 ምርጫ ከሚደረግባቸው ስፍራዎች መካከል በቤንሻንል ጉሙዝ ክልል (መተከል ሺናሻ ልዩ፣ ካማሺ እና ዳለቲ)፣ በኦሮሚያ ክልል (ቤጊ፣ ሰኞ ገበያ፣ አያና፣ ገሊላ፣ አሊቦ፣ ጊዳሚ፣ ኮምቦልቻ) ይገኙበታል።

    በተጨማሪም በአማራ ክልል (ማጀቴ፣ ማኮይ፣ አርጎባ ልዩ፣ ሸዋሮቢት፣ ኤፌሶን፣ ጭልጋ 1፣ ጭልጋ 2፣ ላይ አርማጭ፣ አንኮበር፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል (ሱርማ ልዩ ፣ ዲዚ ልዩ፣ ቀይ አፈር መደበኛ፣ ማጀቴ መደበኛ፣ ሸኮ ልዩ፣ ቴፒ) እና በሐረሪ ክልል (ጀጎል ልዩ ፣ ጀጎል መደበኛ ) ጳጉሜ 1 ምርጫ ከሚደረግባቸው ስፍራዎች መካከል ተካትተዋል።

    በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአምስት የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀት የያዙ ሳጥኖች ተከፍተው በመገኘታቸው የድምጽ አሰጣጥ እንደማይኖር ያስታወቀባቸው ቦታዎች አሉ።

    የድምጽ አሰጣጥ የማይካሄድባቸው የምርጫ ክልሎች ግንደበረት ምርጫ ክልል (ምዕራብ ሸዋ ኦሮሚያ)፣ ተሁለደሬ ምርጫ ክልል 1 እና 2 (ደቡብ ወሎ አማራ)፣ ነገሌ ጉጂ (ኦሮሚያ) እና ደንቢያ ምርጫ ክልል (አማራ) ናቸው።

  17. የኢትዮጵያን ምርጫ የሚመሩት የቀድሞዋ የፖለቲካ እስረኛ ማን ናቸው?

    ብርቱካን ሚደቅሳ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ብርቱካን ሚደቅሳ

    በርካታ ኢትዮጵያዊያን ብርቱካን ሚደቅሳ ከሚለው ስም ጋር የተዋወቁት በ1993 ዓ.ም ለቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር እና በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባላንጣ ለነበሩት ስዬ አብረሃ የዋስትና መብት የፈቀዱ ዕለት ነው። አቶ ስዬ በወቅቱ ከስድስት የቤተሰባቸው አባላት ጋር የሙስና ክሶች ቀርቦባቸው ነበር።

    ብርቱካን በዚያች ታሪካዊ ዕለት በአቶ ስዬ ችሎት ላይ የተሰየሙት መዝገቡን ይመለከቱ የነበሩት የመሃል ዳኛ በህመም ፈቃድ ላይ በመሆናቸው ነበር።

    ብርቱካን እና ጓደኞቻቸው በወቅቱ በቀጥታ ከሕግ ትምህርት ቤት ወደ ረዳት ዳኝነት የመጡ የመጀመሪያዎቹ ቅጥሮች ነበሩ። እናም እነዚህ ወጣት ዳኞች በጊዜ ቀጠሮ ምክንያት ያለ አግባብ ተይዘው የሚቆዩ ሰዎችን በመልቀቅ ለፖሊስ ራስ ምታት በመሆናቸው ከምክር እስከ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸውም ነበር።

    ብርቱካን ዳኛ ከሆኑ በኋላ የተመደቡበት የወንጀል ችሎት ትልልቅ መዝገቦች ይታዩባበት ስለበር በአስፈጻሚው አይን ውስጥ መግባታቸው አልቀረም። በአንድ ወቅት ፍሪደም ኮሌክሽን ለተባለ ተቋም በሰጡት ቃለ ምልልስልም የዲሲፕሊን ክስ ቀርቦባቸው እንደነበረ ብርቱካን ተናግረዋል።

    "የስዬ ጉዳይ ጎልቶ የሚታይ ስለሆነ እንጂ በበርካታ መዝገቦች ሥርዓቱን የሚፈትኑ ውሳኔዎችን ሰጥታለች" ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በወቅቱ የብርቱካን የቅርብ ጓደኛ አቶ ቢኒያም* [ስማቸው የተቀየረ] ይናገራሉ።

    የብርቱካን የፖለቲካ ህይወት ከ1997 ምርጫ በኋላ ከፍተኛ እውቅና ላይ ደርሶ ነበር። ነገር ግን በወቅቱ በምርጫው አልተወዳደሩም። ከፍርድ ቤት ለቀው በጥብቅና ሙያ ላይ የነበሩት ብርቱካን በተለይም ፓርቲዎቹን በማማከር ነበር ተሳትፏቸው።

    ነገር ግን ቀደም ባለው የ1992ቱ ምርጫ በግላቸው ተወዳድረው ነበር። በዚህም በገዢው ፓርቲ ተሸንፈዋል። በወቅቱ ታዋቂ የምክር ቤት አባል የነበሩትን ሻለቃ አድማሴን ማለፋቸውን ተከትሎ እሳቸውን ለመተካት የተወዳደሩት ብርቱካን ዋና አጀንዳቸው ሙስናን ማጥፋት እንደነበረም የቅርብ ወዳጃቸው ይናገራሉ። ሙሉውን ታሪክ ከዚህ ያንብቡ https://bbc.com.im/amharic/news-57534536

  18. ምርጫ 2013

    ዛሬ በሚካሄደው ምርጫ በተለያዩ አካባቢዎች የተመዘገቡ መራጮች ድምጻቸውን እየሰጡ ይገኛሉ። ቢቢሲ አማርኛ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የምርጫ ሂደቱን የተመለከተ ዘገባ በቀጥታ ያቀርባል።

    ምርጫ 2013
  19. በአዲስ አበባ ረዥም ሰልፍ የታየበት የምርጫ ጣብያ

    በአዲስ አበባ በምርጫ ክልል 17 ወረዳ 6 ምርጫ ጣቢያ 17 በርካታ ድምፅ ሰጪዎች ድምፃቸውን ለመስጠት እስከ 200 ሜትር የሚረዝም ሰልፍ ይዘው ይታያሉ።

    ተራ እስኪደርሳቸው ዱካ መቀመጫ ይዘው እስከመምጣት የደረሱ ድምፅ ሰጪዎችም አሉ።

    መራጮች ድምፃቸውን ለመስጠት ከተሰለፉ 1 ሰዓት ቢያልፍቸውም አሁን ከእነርሱ በፊት በርካታ ድምፅ ሰጪዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

    የጣቢያው ምርጫ አስፍጻሚ አቶ ጎሳዬ ተሾመ በምርጫ ጣቢያው መራጮች ድምፅ መስጠት የጀመሩት ከንጋት 12 ጀምሮ ቢሆንም ሰዎች በሚስጥር ድምፃቸውን የሚስጡባቸው ሳጥኖች በቁጥር ሦስት ብቻ መሆናቸው ለረዥም ስልፉ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

    በአዲስ አበባ በምርጫ ክልል 17 ወረዳ 6 ምርጫ ጣቢያ 17በርካታ ድምፅ ሰጪዎች ድምፃቸውን ለመስጠት ወረፋ ይዘው ይታያሉ
    የምስሉ መግለጫ, በአዲስ አበባ በምርጫ ክልል 17 ወረዳ 6 ምርጫ ጣቢያ 17በርካታ ድምፅ ሰጪዎች ድምፃቸውን ለመስጠት ወረፋ ይዘው ይታያሉ
  20. ዛሬ ለ445 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ድምጽ ይሰጣል

    • ዛሬ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በሚካሄደው ምርጫ ለ445 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ድምጽ የሚሰጥ ሲሆን ለ64ቱ ወንበሮች ደግሞ ጳግሜ 1/2013 ዓ.ም ድምጽ ይሰጣል።

    • በሶማሌና በሐረሪ ክልሎች ሙሉ በሙሉ እና በሌሎች ክልሎች የወሰኑ የምርጫ ክልሎች ዛሬ ሰኔ 14 ምርጫ አይካሄድባቸውም።

    ድምጽ የሚሰጡ መራጭ
    የምስሉ መግለጫ, ድምጽ የሚሰጡ መራጭ