በኢትዮጵያ በ704 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቶ ከፍተኛው የህሙማን ቁጥር ተመዘገበ

የኮሮናቫይረስ የማኅበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለባት ኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 10 ሺህ 207 ደርሷል። ከእነዚህም ውስጥ 5 ሺህ 237 አገግመዋል። አገሪቱ እስካሁን 170 ዜጎቿን በኮሮናቫይረስ አጥታለች። በኢትዯጵያ እስካሁን ድረስ 331 ሺህ 266 ምርመራዎች መከናወናቸውን ከጤና ሚኒስቴርና ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጫ የተገኘው መረጃ ያሳያል። በሕብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት እየተስተዋለ በመሆኑ ሕዝቡ በሽታውን የመከላከያ መንገዶች ተግባራዊ በማድረግ እራሱንና ሌሎችን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ባለሙያዎች እየመከሩ ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኮሎምቢያዊያን በቤታቸው ደጅ ለምን ቀይ ጨርቅ ይሰቅላሉ?

    በደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ኮሎምቢያ እስካሁን ከ165 ሺህ ሰዎች በላይ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ 5 ሺህ 800 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

    በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ በመሆኑ የተጣሉ ገደቦች ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታት እንዲራዘሙ ተደርጓል።

    ይህ ደግሞ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ለሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ያለ ምንም ገቢ የሚቆዩበት ተጨማሪ ጊዜ ሆኗል።

    ታዲያ እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሚኖሩባቸው መንደሮች ሰዎች ቀይ ጨርቅ በእንጨት አስረው ደጃቸው ላይ ይሰቅላሉ።

    ይህን ማድረጋቸው መንግሥት እርዳታ እንዲያደርግላቸው ለመጠየቅ ነው።

    የኮሎምቢያ ዋና መዲና ቦጎታ ጎረቤት በሆነችው ላ ፔርሰቨራንሲያ የምትኖረው ክላውዲያ፤ ቆሻሻዎችን በመሰብሰብና እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል ሥራ ነው የምትተዳደረው።

    "ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ማናችንም ሥራ አንሰራም ነበር። ማንም ዞር ብሎ ያየንም አልነበረም" በማለት እርዳታ ለመጠየቅም ቀይ ጨርቅ በደጃቸው ማንጠልጠላቸውን ለቢቢሲ ተናግራለች።

    አሁንም ግን ከመንግሥት የተደረገላቸው እርዳታ እንደሌለ ገልፃለች።

    ሌላኛዋ በሶአቻ የምትኖረው የአምስት ልጆች እናትም ከመንግሥት ያገኘችው ድጋፍ እንደሌለ ትናገራለች።

    "ለቁርስ የምንመገበው ብናገኝ፤ ምሳ አናገኝም፤ ልጆቹም እየከሱ ነው" ስትል ችግር ውስጥ መሆናቸውን አስረድታለች።

  2. የሩሲያ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች የኮቪድ-19 ክትባት ምርምርን ኢላማ ማድረጋቸው ተነገረ

  3. 328 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ሲገኝ 250ው ከአዲስ አበባ ከተማ ናቸው

    የጤና ሚኒስቴር የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዛሬ ሐሙስ ባወጡት ዕለታዊ ሪፖርት በኢትዮጵያ 6 ሺህ 911 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ 328 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱን አስታወቀ።

    ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች አብዛኞቹ ማለትም 250ዎቹ አዲስ አበባ ውስጥ የተገኙ ሲሆን 27 ከጋምቤላ፣ 15 ከኦሮሚያ፣ 13 ከትግራይ፣ 8 ከአፋር፣ 5 ከድሬዳዋ፣ 5 ከሶማሌ፣ 3 ከሲዳማ፣ 1 ከቤኒሻንጉልና 1 ከአማራ ክልል ናቸው።

    እስከ ዛሬ በአገሪቱ በ309 ሺህ 639 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ቫይረሱ በ8 ሺህ 803 ሰዎች ላይ መገኘቱ ተረጋግጧል።

    ከዚህ ባሻገር ቀደም ሲል ወረርሽኙ ተገኝቶባቸው በህክምና ማዕከላት ውስጥ ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩ ህሙማን መካከል 46ቱ ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ 4 ሺህ 814 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በአስከሬን ላይ በተደረገ ምርመራ ቫይረሱ በ2 ሰዎች ላይ የተገኘ ሲሆን እስካሁን ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው አልፏል ተብሎ የሚታመኑ ሰዎች ብዛት 150 ደርሷል።

  4. የኮሮናቫይረስ ክትባት የሚሞከርባቸው ፈቃደኞች እየተፈለጉ ነው

  5. የሕንድ በርካታ ግዛቶች በድጋሚ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣሉ

    በሕንድ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ በአገሪቷ የሚገኙ በርካታ ግዛቶች ባለሥልጣናት አንስተውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ምንም ያህል ሳይቆዩ መልሰው ጥለዋል።

    ግዛቶቹ የእንቅስቃሴ ገደቡን የጣሉት በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ900 ሺህ ማለፉን ተከትሎ ሲሆን፤ ረቡዕ ዕለት ብቻ 30 ሺህ የሚሆኑ አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ከግዛቶቹ አንዷ የሆነችው ቢሃር ሐሙስ ዕለት የእንቅስቃሴ ገደብ በድጋሜ ጥላለች። በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘውና ከኔፓል ጋር የምትዋሰነው ግዛቷ፤ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ከ600 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሞተዋል። በግዛቷ 100 ሚሊየን ሰዎች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።

    በዚህም የእንቅስቃሴ ገደቡ ለ15 ቀናት ይዘልቃል የተባለ ሲሆን ሁሉም ትምህርት ቤቶች፣ ቤተ መቅደሶች እና ወሳኝ ያልሆኑ የንግድ ተቋማት እንዲዘጉ ተወስኗል።

    የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት የተቋረጠ ቢሆንም ሰዎች ግን አሁንም እንቅስቃሴው እንደወትሮው መሆኑን ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

  6. አዕምሯችን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን እንዴት እያስተናገደው ነው?

  7. በዩናይትድ ኪንግደም የሥነ ልቦና ድጋፍ የሚፈልጉ ታዳጊዎች ቁጥር ጨምሯል ተባለ

    በዩናይትድ ኪንግደም በእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ የምክክር አገልግሎት የሚፈልጉ እድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ቁጥር በአንድ ሦስተኛ መጨመሩን አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት አመለከተ።

    በሕፃናት ጥበቃ ላይ የሚሰራው 'ኤንኤስፒሲሲ' የተባለው ይህ ድርጅት በኦንላይንና በስልክ ለህጻናት ባዘጋጀው የምክክር አገልግሎት ባለፉት አራት ወራት ውስጥ 21 ሺህ 827 የአዕምሮ ጤና የምክክር አገልግሎቶችን መሰጠቱን ጠቅሷል።

    ከእነዚህ መካከል 2 ሺህ የሚሆኑት አስራ አንድ ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑ ታዳጊዎች መሆናቸውን አስታውቋል።

    ይህም በሳምንት ከሚደረጉ አማካይ የምክክር አገልግሎቶች ጋር ሲነፃፀር በ37 በመቶ መጨመሩን ያሳያል ብሏል። ድርጅቱ እንዳለው የእንቅስቃሴ ገደቡ ከመጣሉ በፊት 97 የምክክር አገልግሎቶች ይሰጡ የነበረ ሲሆን የእንቅስቃሴ ገደቡ ከተጣለ በኋላ ግን ቁጥሩ ወደ 133 አሻቅቧል።

    አንዲት የ8 ዓመት ታዳጊ “የምኖረው ከእናቴ ጋር በአንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ ነው፤ አባቴን ብዙም አላየውም፤ አንዳንዴ አንዳችን በአንዳችን ላይ እንቆጣለን፤ ይህም በመደባደብ ይጠናቀቃል፤ ከተደባደብን በኋላ ጥሩ ሰው እንዳልሆንኩ ስለሚሰማኝ መልሼ ራሴን እጎዳለሁ” ስትል ተናግራለች።

    የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ኃላፊ ፒተር ዋንለስም “የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአገሪቱ ባሉ በርካታ ህፃናትና ታዳጊዎች ላይ ቀጥተኛ የሆነ የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳስከተለ ምንም ጥርጥር የለውም። " ብለዋል።

    ኃላፊው አክለውም የምክክር ድጋፍ ፈልገው ወደ እነርሱ የሚደውሉ ከ11 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ቁጥር መጨመሩን በመግለፅ፤ የወረርሽኙ ተፅእኖ በህፃናትም ላይ ጠባሳ መጣሉን አፅንኦኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

  8. ስፔን በኮሮናቫይረስ ያጣቻቸውን ዜጎቿን አሰበች

    ስፔን በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎቿ የመታሰቢያ ሥርዓት አካሄደች።

    የመታሰቢያ ፕሮግራሙ የ28 ሺህ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ወረርሽኙ በአገሪቷ ላይ ያደረሰው ጉዳት ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ የሚያስታውስ ነው ተብሏል።

    በተለይ በመጋቢትና ሚያዚያ ወራት ላይ ወረርሽኙ የአገሪቱን የጤና ሥርዓት በእጅጉ ተፈታትኖት ነበር።

    በዚህ የመታሰቢያ ፕሮግራም ላይ አንድ ወንድሙን በቫይረሱ ያጣ ግለሰብ፤ በእንደዚህ ዓይነት ቀውስ ወቅት ርህራሄና ፍቅር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ገልጿል።

    ከካታሎኒያ የመጣች የጤና ባለሙያም የወረርሽኙ ደረጃ ከፍተኛ በነበረበት ጊዜ እርሷ እና የሥራ ባልደረቦቿ የተጋፈጧቸውን ተግዳሮቶች አስረድታለች።

    ምንም እንኳን ይህ የመታሰቢያ ፕሮግራም የተካሄደው አገሪቱ ጥላው የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ካነሳች ከሳምንታት በኋላ ቢሆንም፤ አሁንም ግን ቫይረሱ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

    ከዚህ ቀደም ከነበረው ያነሰ ይሁን እንጂ አሁንም በርካታ አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ ነው።

    በተለይ በሰሜን ምሥራቅ ካታሎኒያ ግዛት በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች የእንቅስቃሴና ሌሎች ገደቦች በድጋሚ ተጥለዋል። የጤና ተቋማትም በተመሳሳይ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች እየተጨናነቁ ነው ተብሏል።

  9. ሩዋንዳ ለቤተ እምነቶች በጥሬ ገንዘብ መባ መስጠትን ከለከለች

    ሩዋንዳ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችሉ ጥብቅ መመሪያዎችን በማስተላለፍ ቤተ እምነቶች እንዲከፈቱ ፈቀደች።

    ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ወደ ቤተ እምነቶች የሚሄዱ ምዕመናን መግቢያ በር ላይ እንዲመዘገቡ ይደረጋል።

    ሁሉም ምእመናን 1.5 ሜትር ርቀት መጠበቅና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

    ለቤተ እምነቱ የሚሰጥ መባ በጥሬ ገንዘብ መስጠት አይፈቀድም ተብሏል።

    እድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትም ወደ ቤተ እምነት እንዲገቡ አልተፈቀደም።

    ሩዋንዳ ትምህርት ቤቶችንና ቤተ እምነቶችን የዘጋችው የመጀመሪያውን በቫይረሱ የተያዘ ሰው እንዳገኘች በመጋቢት ወር ላይ ነበር።

    ሩዋንዳውያን ይህንን የመንግሥታቸውን ውሳኔ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ ያደነቁ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የተዘጉ መጠጥ ቤቶችም መከፈት አለባቸው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።

    ትምህርት ቤት እስከ መስከረም ድረስ ዝግ ሆኖ ይቆያል።

    ሩዋንዳ እስካሁን ድረስ 1435 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን ስታረጋግጥ ከእነዚህ መካከል አራት ሰዎች ሞተዋል።

  10. ቺሊ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን የሚለዩ አነፍናፊ ውሻዎችን እያሰለጠነች ነው

    በቺሊ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን መለየት የሚችሉ አነፍናፊ ውሻዎችን ፖሊሶች እያሰለጠኑ መሆናቸው ተገልጿል።

    አነፍናፊ ውሻዎች በአብዛኛውን ጊዜ አደንዛዥ ዕፆችን፣ ተቀጣጣይ ፈንጅዎችን ወይም የተቀበሩ ቦምቦችን ለማውጣት እንዲሁም የጠፉ ሰዎችን በመፈለግ ላይ ይሰማራሉ።

    ምንም እንኳን ቫይረሱ የተለየ ጠረን ባይኖረውም በህመሙ የተያዙ ሰዎች በላብ ስለሚጠመቁ የተለየ ሸታ አላቸው በማለት የእንስሳት ጥናት ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ፈርናንዶ ማርዶኔዝ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    ውሾቹ እስከ ነሐሴ ድረስ ስልጠናቸውን የሚጨርሱ ሲሆን በባቡር ጣቢያዎችና በአየር ማረፊያዎች ይሰማራሉ ተብሏል።

    በእንግሊዝ ተቀማጭነቱን ያደረገ አንድ የእርዳታ ድርጅትም እንዲሁ ውሾችን በህክምና ዘርፉ ላይ ተሰማርተው ማነፍነፍ እንዲችሉ ስልጠና እንደጀመረም እንዲሁ ተዘግቧል።

  11. የቻይና ሲኒማ ቤቶች ከስድስት ወራት በኋላ ሊከፈቱ ነው

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተዘግተው የነበሩ ሲኒማ ቤቶች ከስድስት ወራት በኋላ ሊከፈቱ መሆኑ ተገልጿል።

    የአገሪቱ የመንግሥት ሚዲያዎች እንደዘገቡት ሲኒማ ቤቶቹ ከቀናት በኋላ ይከፈታሉ ተብሏል።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መነሻ በሆነባት ቻይና ከጥር ወር ጀምሮ ተዘግተዋል።

    በባለፉት ስድስት ወራት ውስጥም የሲኒማ ቤቶቹ መዘጋት ከፍተኛ ቀውስ በኢንዱስትሪው አስከትሏል፤ ሺዎችንም ስራ አልባ አድርጓል።

    በአሁኑ ወቅት ግን ሁሉም ሲኒማ ቤቶች ሳይሆን የሚከፈቱት ለስጋት ባልተጋለጡ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው ተብሏል።

  12. የማንዴላ ልጅ በኮቪድ-19 ተይዘው እንደነበር ተነገረ

    የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ልጅ፣ ዚንዲዚ ማንዴላ በሞቱበት እለት በተደረገላቸው ምርመራ በኮቪድ-19 መያዛቸው መታወቁ ተገለፀ።

    ዚንዲዚ በጆሃንስበርግ ሆስፒታል ውስጥ በ59 ዓመታቸው ሰኞ እለት ነው ህይወታቸው ያለፈው።

    ልጃቸው ዞንድዋ ለኤስኤቢሲ እንደገለፀው የሞታቸው መንስዔ ግልጽ እንዳልሆነና ቤተሰቡ የአስከሬን ምርመራ ውጤቱን እየተጠባበቀ መሆኑ ተገልጿል።

    አክሎም ቫይረሱ እንደተገኘባቸው አስታውቆ የቀብር ስነስርዓታቸውም ቢሆን በተቀመጠው መመሪያ መሰረት እንደሚከናወን ተናግሯል።

    እናቱ አርብ እለት እንደሚቀበሩ ጨምሮ መናገሩ ተዘግቧል።

    ዚንዲዚ ማንዴላ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስም በዴንማርክ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።

    ዚንዲዚ በዴንማርክ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ከአምስት ዓመታት በፊት ሲሆን በላይቤሪያ ሞንሮቪያ ደግሞ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።

  13. የማላዊ ፕሬዝዳንት ህዝባቸውን ስለኮቪድ-19 ጾምና ፀሎት እንዲያደርግ ጠየቁ

    የማላዊ ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻክዌራ ህዝባቸውን በአገራቸው የኮቪድ-19 መስፋፋትን ለመግታት በሚያደርጉት ፀሎትና ጾም አብሯቸው እንዲሆን ጥሪ አቀረቡ።

    ፕሬዝዳንቱ "ሁሉም ሃይማኖተኛ የማላዊ ዜጎች" ከዛሬ ጀምሮ ለሶሰት ቀናት ጾም ፀሎት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

    አክለውም እሁድን ብሔራዊ የምስጋና ቀን በማለት አውጀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ጾም ፀሎት እንዲደረግ የጠየቁት በኮቪድ-19 ታምመው አልጋ ላይ ላሉና ለተጎዱ፣ የኮሮና መከላከል ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች፣ በቫይረሱ ላልተያዙ እንዲሁም ፕሬዝዳንቱ ላቋቋሙት የኮሮና መከላከል ግብረኃይል መሆኑን የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር ጎስፔል ካሳኮ ገልፀዋል።

    የማላዊ ፕሬዝዳንት ቀድሞ አሴምብል ኦፍ ጋድ በተሰኘ ቤተ እምነት ውስጥ ለ24 ዓመት ያህል ፓስተር በመሆን አገልግለዋል።

    የፕሬዝዳንቱ ጾምና ፀሎት ጥሪ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ የተደበላለቀ ስሜት ፈጥሯል።

  14. የሆስፒታል ባለቤቱ ሀሰተኛ የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤቶች በመስጠት በቁጥጥር ስር ዋለ

    በባንግላዴሽ አንድ የሆስፒታል ባለቤት በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ከኮሮና ነፃ መሆናቸውን የሚገልጽ የሕክምና ማስረጃ በመስጠት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ዋለ።

    ሞሀመድ ሻሂድ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን ለሚገልጹ ደንበኞቹ ምንም ዓይነት ምርመራ ሳያካሂድ የህክምና ማስረጃ መስጠቱን የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ሪፖርት ያሳያል።

    ፖሊስ የ42 ዓመቱን ግለሰብ ለዘጠኝ ቀናት ሲፈልግ የቆየ ሲሆን ግለሰቡ ቡርቃ ለብሶ ወደ ሕንድ ሊያመልጥ ሲል ተይዟል።

    " ሆስፒታሉ 10 ሺህ,500 የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች ያደረገ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 4 ሺህ 200 በትክክሉ የተመረመሩ ቢሆንም 6 ሺህ 300 ግን ምርመራ ሳያደረጉ ነጻ መሆናቸውን የሚገልጽ ማስረጃ የተሰጣቸው መሆኑ ታውቋል" ሲሉ ኮሎኔል አሺቅ ቢላህ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    ሻሂድ በባንግላዲሽ ዋና ከተማ ዳካ በሚገኘው ሆስፒታሉ በነጻ አገልግሎቱን ለመስጠት ቢስማማም ክፍያ ተቀብሏል በሚልም ተወንጅሏል።

  15. በአንድ ወር ሁለት ጊዜ ለማግባት የተገደደችው የ12 ዓመት ታዳጊ ነጻ ወጣች

  16. በኮሮናቫይረስ ሰበብ ትኩረት የተነፈጉት የዓለማችን ገዳይ ችግሮች

  17. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች

    በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 4768 ሰዎች ከኮቪድ-19 ሲያገግሙ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 148 ደርሷል።

    በመላው ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከ300 ሺህ በላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች የተደረጉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 8 ሺህ 475 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ታውቋል።

    አሁንም የቫይረሱ ከፍተኛ ስርጭት ያለው በአዲስ አበባ ቢሆንም ሌሎች ክልሎች ላይም ቁጥሩ ከፍ እያለ በአንዳንድ ክልሎችም በማህበረሰቡ መካከል ስርጭቱ እየታየ ነው።

    አሁንም ቢሆን የኮቪድ-19 መከላከያ ተብሎ በዋናነት የሚጠቀሰው እጅን በሳሙናና በውሃ በተደጋጋሚ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም አፍና አፍንጫን መሸፈን በመሆኑ እነዚህን መከላከያዎች ቸል ሳይሉ ይተግብሯቸው።

    የቢቢሲ አማርኛን ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ የቀጥታ ዘገባዎች በድረገጻችን እንዲሁም በፌስቡክ ገፃችን ይከታተሉ።

    ሰናይ ውሎ!

  18. ኢራን 140 ጤና ባለሙያዎችን በኮቪድ-19 ምክንያት አጣች

    ኢራን 140 የጤና ባለሙያዎችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በቫይረሱ ምከንያት በሞት መነጠቋን አስታወቀች።

    የኢራን ጤና ሚኒስቴር ባለስልጣን ሲማሳዳት ላሪ፣ የሕክምና ባለሙያዎቹ የዜጎችን ህይወት ለማዳን ሕይወታቸውን መክፈላቸውናና ክብር እንደሚገባቸው ጠቅሰው “. . . ሁላችንም የተደነገጉ የጤና መመሪያዎችን መከተል አለብን” ብለዋል።

    አገሪቷ ጥላው የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ከሚያዚያ ወር አጋማሽ ጀምሮ ካላላች በኋላ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየተስፋፋ መጥቷል።

    እስካሁን ድረስ በኢራን 264 ሺህ 561 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ 13 ሺህ 410 ደግሞ መሞታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ያሳያል።

    የጤና ባለስልጣናት አሁን በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙት በቫይረሱ የተያዙ አዳዲስ ሰዎችን አገሪቷ የመመርመር አቅም በማደጉ የተገኘ ሊሆን እንደሚችል ገልፀው፣ ዜጎች የአካላዊ ርቀት መጠበቅ ላይ ቸልተኝነት ማሳየታቸውን ገልፀዋል።

    ረቡዕ እለት የኢራን ፕሬዝዳንት ሃሰን ሮሃኒ፣ ዜጎች የጤና መመሪያዎችን እንዲያከብሩ በይበልጥ ደግሞ አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

    “ ሰዎች ምንም አይነት መሰባሰብን ማስወገድ እና ከወቅታዊ ሁናቴ ጋር አኗኗራቸውን እንዲያስተካክሉ እንጠይቃለን” ብለዋል በሚኒስትሮች ካቢኔ ስብሰባ ወቅት።

  19. በርካታ ሕጻናት ወሳኝ የሆኑ ክትባቶችን አለመውሰዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ገለፀ

    ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም 14 ሚሊዮን ሕፃናት በቀላሉ መከላከል ከሚቻሉ ሕመሞች ለመጠበቅ የሚያስችለውን ክትባት አለመከተባቸውን የዓለም ጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታወቁ።

    በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጣው ሪፖርት ጨምሮ እንዳስታወቀው በዚህ ዓመትም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ክትባቶች በመቋረጣቸው ይህ ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል።

    ድርጅቶቹ አክለው እንደገለፁት ከ30 ዓመታት ወዲህ በኮሮናቫይረስ ምከንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕጻናት ህይወት አድን የሆኑ ክትባቶች አለመከተባቸውን በመጥቀስ አስጠነቅቀዋል።

    ከእነዚህ ሕጻናት መካከል ግማሽ ያህሉ የሚገኙት ግጭት በሚያጠቃቸው የአፍሪካ አገራት መሆኑን ተገልጿል።

    የተባበሩት መንግሥታት በጎርጊሳውያኑ በ2020 የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ብቻ የፖሊዮ፣ ኩፍኝ፣ ማጅራት ገትር፣ ቴታነስ እና የማያቋርጥ ሳል መከላከያ ክትባቶችን የወሰዱ ሕጻናት በከፍተኛ መጠን ቁጥራቸው መቀነሱን ገልጿል።

    ድርጅቶቹ አክለውም የኩፍኝ ክትባት ያልተከተቡ ሕጻናት ጤንነት ይበልጥ እንደሚያሳስብ ተናግረዋል።

    በእነዚህ በሽታዎች ተይዘው የሚሞቱ ሕጻናት በኮቪድ-19 ተይዘው ከሚሞቱት እንደሚልቅ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል።

    እርሳቸው እንዳሉት እነዚህ ክትባቶች በህብረተሰብ ጤና ታሪክ በጣም ውጤታማ ክትባቶች ናቸው።

    ከመሃል ከተማ ርቀው የሚገኙ እና በከተማ በድህነት በሚታወቁ መንደሮች የሚኖሩ ሕጻናት ይበልጥ ለእነዚህ በሽታዎች ተጋላጭ መሆናቸውም ተገልጿል።

    ናይጄሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና ደቡብ ሱዳን በከፍተኛ ቁጥር ሕጻናት ካልተከተቡባቸው አገራት መካከል ናቸው።

    በመጋቢት ወር የዓለም ጤና ድርጅት አገራትን ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችል ውጤታማ መንገድ እስኪዘረጋ ድረስ በዘመቻ የሚደረጉ ክትባቶችን እንዲያቋርጡ መክሮ ነበር።

    እስከ አሁን አንጎላ፣ ኢትዮጵያ እና ቡርኪናፋሶ የዘመቻ ክትባቶችን ከጥብቅ መመሪያዎች ጋር ማካሄድ ጀምረዋል።

  20. "ወረርሽኙ ሴቶች ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ ቸል ማለት ዓለምን 5 ትሪሊየን ዶላር ያከስራታል"

    ኮሮናቫይረስ ሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ፍትሃዊ ያልሆነ ተጽእኖ አለመመልከት ዓለምን በጎርጎሳውያኑ በ2030፣ 5 ትሪሊየን ዶላር ያሳጣታል ሲሉ የቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ኃላፊ ሚሊንዳ ጌትስ አስጠነቀቁ።

    ወረርሽኙ በሚያስከትለው የኢኮኖሚ ድቀት የተነሳ ሴቶች የተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ከወንዶች 1.8 በመቶ በላቀ መልኩ ይጎዳል ሲሉ ጽፈዋል።

    በተመሳሳይ ሁኔታ ልጆችን መንከባከብ፣ ቤተሰብንና አባላቶቹን መርዳት በብዛት የሴቶች ትከሻ ላይ መውደቁን ጠቅሰው በመላው ዓለም ትምህርት ቤቶች መዘጋታት ሴቶች ወደ ስራ እንዳይሄዱ አደጋ ጥሎባቸዋል ብለዋል።

    ሚሊንዳ ጌትስ አክለውም መንግሥታት ኮሮናቫይረስ ካስከተለው ቀውስ ለመውጣት መንግሥታት ፖሊሲዎቻቸውን ሲቀርፁ በስርዓተ ጾታ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲያጤኗቸው መክረዋል።