በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 5175 ሲደርስ ሟቾች 81 ሆኑ

የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት እየተስፋፋ ባለባት ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት 141 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ቁጥሩን 5175 አድርሶታል። በዛሬው ዕለት በህክምና ማዕከል የነበሩ የሶስት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ አገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥርም 81 ሆኗል። በአጠቃላይ ከበሽታውም 1ሺህ 544 ሰዎች ማገገማቸውንም የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጋራ ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል። ታሞ ለከፋ ጉዳት ከመዳረግና ከህመሙ ከማገግም ይልቅ ባለሙያዎች እንደሚመክሩት በሽታውን አስቀድሞ መከላከል ዋነኛው መፍትሄ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብና አፍና አፍንጫን መሸፈን ዋነኞቹ ናቸው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. "በኮሮናቫይረስ ላይ ኅብረተሰቡን እያሳመጽኩ ነው"፡ ትዕግስት ሲሳይ

  2. በናይጄሪያ የስራ ማቆም አድማ መትተው የነበሩ ሐኪሞች ሥራ ጀመሩ

    የናይጄሪያ ዶክተሮች ኮቪድ-19 ሕሙማንን ሲያክሙ የመከላከያ ቁሳቁስ እጥረት እንዳለባቸው ይገልጻሉ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የናይጄሪያ ዶክተሮች ኮቪድ-19 ሕሙማንን ሲያክሙ የሚገጥማቸውን የመከላከያ ቁሳቁስ እጥረት በሚመለከት ጥያቄ በማቅረብ የጠሩትን የስራ ማቆም አድማ ማብቃታቸውን አሳወቁ።

    የአገር አቀፉ የተለማማጅ ሐኪሞች ማህበር በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ዶክተሮች 40 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን ያቀረቡትን ጥያቄ መመለስ እንዲችል ለመንግሥት ጊዜ ለመስጠት በሚል የስራ ማቆም አድማቸውን ማብቃታቸውን ተናግሯል።

    ለሳምንት ያህል የዘለቀው የሀኪሞቹ ተቃውሞ ሰኞ ጠዋት ጀምሮ ማብቃቱን ማስታወቃቸውን በአገር ውስጥ መገናፃኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

    ማህበሩ የተወሰኑ ሆስፒታሎች የመከላከያ ቁሳቁስ እንደቀረበላቸው ገልጾ ለተቀሩትም ቢሆን መንግሥት ለማቅረብ ቃል ገብቷል ብሏል።

  3. የዓለም ጤና ድርጅት በ24 ሰዓታት 183 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን መዘገበ

    የዓለም ጤና ድርጅት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የዓለም ጤና ድርጅት በአንድ ቀን ከፍተኛ የሆነውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መዘገበ።

    ለዚህ ደግሞ አሜሪካ ከፍተኛውን ድርሻ እንደምትይዝ ተገልጿል።

    የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 183 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

    ከእነዚህ መካከል ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከብራዚል የተገኙ ሲሆኑ ቀረዎቹ ደግሞ ከአሜሪካና ከሕንድ ናቸው።

    በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር በከፊል የሚያሳየው በዓለም ላይ የመመርመር አቅም እያደገ መሆኑን ነው ተብሏል።

    እስካሁን ድረስ በመላው ዓለም 9 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በኮቪድ-19 ሲያዙ 467 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

  4. በብራዚል የሟቾች ቁጥር ከ50ሺህ ዘለለ

  5. እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች!

    ምርመራ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአዲስ አበባ ከተማ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 3,105 ደርሷል። በኢትዮጵያ ተሰራጭቶ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን ድረስ በዚሁ የተነሳ የ74 ሰዎችን ህይወትም አልፏል።

    ኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር እያንዳንዱ ሰው ከመንግሥትና ከባለሙያዎች የሚሰጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባ ባለሙያዎች ዘወትር ይናገራሉ።

    እናንተም የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች እነዚህን የጥንቃቄ መልዕክቶች ተግባራዊ በማድረግ የራሳችሁንም የወዳጆቻችሁንም ጤና እንደምትጠብቁ ተስፋ እናደርጋለን። ከመላው ዓለም የሚሰበሰቡ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ የቀጥታ ዘገባዎችን እዚህ መከታተል ትችላላችሁ።

    መልካም ቀን!