የቢቢሲ አማርኛ የሰኔ 16/2012 ዓ.ም የቀጥታ ዘገባ ገጽ
እንደምን አደራችሁ?
ዕለተ ማክሰኞ ሰኔ 16/2012 ዓ.ም።
ይህ ቢቢሲ አማርኛ በኮሮናቫይረስ ዙሪያ ከኢትዮጵያና ከቀሪው ዓለም የሚወጡ ዜናና መረጃዎችን በማሰባሰብ የሚያቀርብበት የቀጥታ ዘገባ ገጽ ነው።
ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ይህንን ገጽ በመጎብኘት በየደቂቃው የምናወጣቸውን ዘገባዎች እንድትከታተሉ በአክብሮት እንጋብዛለን።
ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት እየተስፋፋ ባለባት ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት 141 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ቁጥሩን 5175 አድርሶታል። በዛሬው ዕለት በህክምና ማዕከል የነበሩ የሶስት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ አገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥርም 81 ሆኗል። በአጠቃላይ ከበሽታውም 1ሺህ 544 ሰዎች ማገገማቸውንም የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጋራ ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል። ታሞ ለከፋ ጉዳት ከመዳረግና ከህመሙ ከማገግም ይልቅ ባለሙያዎች እንደሚመክሩት በሽታውን አስቀድሞ መከላከል ዋነኛው መፍትሄ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብና አፍና አፍንጫን መሸፈን ዋነኞቹ ናቸው።
እንደምን አደራችሁ?
ዕለተ ማክሰኞ ሰኔ 16/2012 ዓ.ም።
ይህ ቢቢሲ አማርኛ በኮሮናቫይረስ ዙሪያ ከኢትዮጵያና ከቀሪው ዓለም የሚወጡ ዜናና መረጃዎችን በማሰባሰብ የሚያቀርብበት የቀጥታ ዘገባ ገጽ ነው።
ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ይህንን ገጽ በመጎብኘት በየደቂቃው የምናወጣቸውን ዘገባዎች እንድትከታተሉ በአክብሮት እንጋብዛለን።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ወደ ጊዜያዊ ኮቪድ -19 የህክምና ማዕከል መቀየሩን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በፌስቡክ ገጻቸው አስታወቁ።
ማዕከሉ 300 ታማሚዎችን ለመቀበል ዝግጁ መደረጉንም ጨምረው አመልክተዋል።
ሚኒስትሯ እንዳሉት ማዕከሉ የሚቀበለው ቀላል ምልክት የሚያሳዩና ምንም ምልክት የሌላቸው ነገር ግን በቤታቸው ራሳቸውን ነጥለው ለመቆየት አመቺ ሁኔታ የሌላቸውን ነው።
በኢትዮጵያ እስካሁን 4 ሺህ 663 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ሲገኙ ከመካከላቸው የ75 ሰዎች ሕይወት አልፏል።
በአሜሪካ ደቡብ ካሮሊና ግዛት 'የጥቁር ሕይወት ዋጋ አለው' [ብላክ ላይቭስ ማተር] ተቃውሞዎች አስተባባሪ፤ በግዛቷ አብዛኞቹ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ከተቃውሞ ሰልፍ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የታቀዱ ሰልፎች በሙሉ መሰረዛቸውን አስታወቀ፡፡
አስተባባሪው ሎረንስና ታኔል በፌስቡክ ገጹ ባጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል በቅርቡ በትንሹ 24 የመብት ተሟጋቾች በበሽታው ተይዘዋል፡፡
"ተቃውሞዎችን ማካሄድ ከቀጠልን የምናወራው ስለ ጥቁሮች ሕይወት ዋጋ ነው፤ ኮቪድ -19 ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃ ያለው ጥቁር አሜሪካዊንን ነው፤ በመሆኑም አሁን ላይ መሰባሰብ አንችልም" ብሏል አስተባባሪው፡፡
ሎረንስ የራሱን የምርመራ ውጤትም እየተጠባበቀ እንደሆነ አክሏል፡፡
"ስለጥቁሮች ሕይወት ከተጨነቃችሁና ተቃውሞ ማካሄድ ከፈለጋችሁ፤ ቤታችሁ ቆዩ" ያለ ሲሆን ተቃዋሚዎች በአፋጣኝ ምርመራ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በደቡብ ካሮሊና ግዛት እሁድ እለት ብቻ ከ900 በላይ አዲስ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
ምንም እንኳን ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በሚኒያፖሊስ በፖሊስ በግፍ ከተገደለ በኋላ እንደታየው ሰፊ ተቃውሞ ባይሆንም 'የጥቁር ሕይወት ዋጋ አለው' በሚል የሚካሄደው ተቃውሞ በአሜሪካ እንደቀጠለ ነው፡፡
የዩናይትድ ኪንግደም ጤና ሚኒስትር ማት ሃንኮክ ስለወረርሽኙ በሚሰጡት እለታዊ መግለጫቸው ላይ እንደተናገሩት ቫይረሱ እየቀነሰ መሆኑን አመልክተዋል።
እስካሁን በመላዋ ዩናይትድ ኪንግደም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምርመራዎች መካሄዳቸው ተገልጾ በዛሬው እለት በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ብሎ ከአንድ ሺህ በታች ወርዷል።
ባለፉት 24 ሰዓታት ምርመራ ከተደረገላቸው ከ150ሺህ በላይ ናሙናዎች ውስጥ 958 አዳዲስ ህሙማን ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
በወረርሽኙ ምክንያት ታመው ሆስፒታል የገቡ ህሙማን አሃዝም እየቀነሰ አሁን ከ5 ሺህ ሰዎች በታች በህክምና ላይ እንደሚገኙ ባለስልጣኑ አመልክተዋል።
የጤና ሚኒስትሩ ማት ሃንኮክ "ምንም እንኳን መሰራት ያለባቸው ስራዎች ቢኖሩም ውጤቶች እየታዩ ነው፤ በዚህም በአገሪቱ በሽታውን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ጥረት ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እያመራ ነው።" ሲሉ ተናግረዋል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በፈረንሳይ ከሦስት ወራት በላይ ተዘግተው የቆዩ ትምህርት ቤቶች በመከፈታቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመለሱ።
አገሪቱ ለወራት ጥላው የነበረውን ገደብ ቀስ በቀስ ለማንሳት በወሰነችው መሰረት እስከ 15 ዓመት የሚሆኑ ታዳጊዎች ወደ ትምህርት ቤቶቻቸው እየተመለሱ ነው።
ፈረንሳይ የወረርሽኙን መስፋፋት ለመቆጣጠር የእንቅስቃሴ ገደብ ከመጣሏ አንድ ቀን በፊት ነው ትምህርት ቤቶችን የዘጋችው።
ኒስ በተባለችው የፈረንሳይ ከተማ ነዋሪ የሆነች እናት ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገረችው ሁለት ልጆቿ ሙሉ ለሙሉ ወደ ትምህርት ቤታቸው እንደሚመለሱ ስትነግራቸው “በደስታ እንባ እየተናነቀኝ ነበር” ብላለች።
የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ዓለም አቀፋዊ የአመራር ችግር መኖሩን አስታወቀ።
የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም፤ ዓለም ብሔራዊ አንድነትና ዓለም አቀፍ ትብብር ትፈልጋለች ያሉ ሲሆን ወረርሽኙን ፖለቲካዊ ማድረግም ችግሩን የበለጠ እንዳባባሰው ገልጸዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ አክለውም "አሁን ላይ እያጋጠመን ያለው ችግር ቫይረሱ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ትብብር አለመኖር ነው" ብለዋል።
ድርጅቱ ወረርሽኙ አሁንም እየተስፋፋ መሆኑን ጠቅሶ በምጣኔ ሃብትና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖም ለአስርተ ዓመታት ሊዘልቅ ይችላል ብሏል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እስካሁን 9 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 470 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።
በጀርመን ጎቲንገን ከተማ በሚገኙ የመኖሪያ ሕንጻዎች ላይ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ግጭት ለመቆጣጠር ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል መሰማራቱ ተገለጸ።
የመኖሪያ ህንጻዎቹ ሐሙስ ዕለት ከእንቅስቃሴ ተለይቶ እንዲቆይ የተደረገው ሁለት ነዋሪዎች በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነበር።
አርብ ዕለት ደግሞ 120 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በርካታ ሰዎችም በቫይረሱ ሳይያዙ እንደማይቀሩ ተሰግቷል።
አብዛኞቹ ነዋሪዎችም ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ በመደረጉ ቅሬታ እያሰሙ ነው።
በእዚህ ነዋሪዎቹ ከቤታቸው እንዳይወጡ በተከለከለባቸው ሕንጻዎች ውስጥ የሚኖሩት 700 ሰዎች የነበሩ ሲሆን 200 የሚሆኑት ካሉበት ለመውጣት በመሞከራቸው ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው ነበር።
ግጭቱን ተከትሎ ነዋሪዎቹ ርችት፣ ጠርሙሶች እንዲሁም ብረቶችን በመጠቀም በፖሊስች ላይ ጥቃት አድርሰዋል።
ቅዳሜ እለት በተፈጠረው በዚህ ግጭት 8 ፖሊሶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በድርጊቱ የተጠረጠሩ ሰዎች ቢያዙም ቃላቸውን ሰጥተው ተለቀዋል።
ባለሥልጣናት እንዳሉት ከሆነ ከግጭቱ ጀርባ ለነዋሪዎች ተገቢው መረጃ እንዳልተሰጠና ነዋሪዎቹ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ከተረጋገጠም በኋላ ከሕንጻው ከመውጣታቸው በፊት ሁለተኛ ዙር ምርመራ እንደሚያስፈልጋቸው አያውቁም ነበር።
ነዋሪዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋግጥ በበርሊን እንዲሁም በጎቲንገን የሚገኙ ሁሉም የመኖሪያ ህንጻዎች ነዋሪዎች በቤታቸው እንዲቆዩ ተደርጓል።
ነዋሪዎች ወደ ውጭ እንዳይወጡ ለመቆጣጠርም መኖሪያዎቹ በፖሊስ እንዲጠበቁ ተደርጓል።
የመኖሪያ ሕንጻዎቹ በርካታ ሰዎች የሚኖሩባቸው ሲሆን፤ በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥም አራት ወይም አምስት የቤተሰብ አባላት አንድ ላይ የሚኖሩበት ነውም ተብሏል።
በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ 3238 የላብራቶሪ ምርመራ 131 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴርና የሕብረሰብ ጤና ተቋም በዕለታዊ መግለጫቸው አስታወቁ።
ይህም በአጠቃላይ በቫይረሱ ተያዙ ሰዎችን ቁጥር 4663 አድርሶታል።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ግለሰቦች 94ቱ ወንዶች ሲሆኑ 37ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው። እነሱም ከ 2 ዓመት እስከ 80 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ተገልጿል።
በቫይረሱ ከተያዙት መካካልም አንድ የውጭ አገር ዜጋ ይገኝበታል።
ባለፉት 24 ሰዓታትም አንድ ግለሰብ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን እስካሁን በአጠቃላይ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 75 ደርሷል።
84 ተጨማሪ ሰዎችም ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ 1297 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
በሕንድ ሰሜናዊ ከተማ ካንፑር በመንግሥት መጠለያ ውስጥ የነበሩ 57 ሴቶች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡
በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠው አብዛኞቹ የበሽታው ምልክት ያልታየባቸው ሲሆን ሁሉም ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው ባለፈው ሳምንት ከመካከላቸው አንዷ ትኩሳት በማሳየቷ ወደ ሆስፒታል ተወስዳ በቫይረሱ መያዟ ከተረጋገጠ በኋላ በመጠለያው የሚገኙ ሌሎችም እንዲመረመሩ ተደርጓል፡፡
ከ57ቱ ሴቶች መካከልም አምስቱ ነፍሰ ጡር መሆናቸውን ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ሂንዲ ተናግረዋል፡፡
የኡታር ፕራዴሽ ግዛት የሴቶች ኮሚሽን እንዳለው በመጠለያው የሚገኙ ሴቶች አብዛኞቹ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ናቸው፡፡
በሕንድ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች በቫረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህም በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ከዓለም አገራት በ4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም ቤት የመቀመጥ ገደቡ በአዕምሮ ጤና ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የተሰራ የዳሰሳ ጥናት አመለከተ፡፡
ከብሔራዊ ስታስቲክስ ቢሮ የወጣው ይህ ጥናት ከአስር ታዳጊዎች መካከል አራቱ ኮሮናቫይረስ በጤንነታቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ እና ቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደቡም የአዕምሮ ጤናቸውን እንዳቃወሰው ተናግረዋል፡፡
ዕድሜያቸው ከ16-29 ከሆኑ ወጣቶች መካከል 42 በመቶ የሚሆኑት የአዕምሮ ጤናቸው መታወኩን ገልጸዋል፡፡
በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት የአዕምሮ ጤና ችግር አጋጥሞናል ካሉትና ዕድሜያቸው ከ30-59 ከሆኑት 25 በመቶዎች ሲሆኑ ዕድሜያቸው ከ60 በላይ ከሆኑት ደግሞ 15 በመቶዎቹ ተመሳሳይ ችግር እንዳጋጠማቸው አስረድተዋል፡፡
በዕድሜ ክልላቸው ሲነጻጸርም ወጣቶች ለከፋ የአዕምሮ ጤና መዳረጋቸውን ጥናቱ ያሳያል፡፡
የብሔራዊው የስታስቲክስ ቢሮ ጥናት የሸፈነው ከፈረንጆቹ ሚያዚያ3 እስከ ግንቦት 10 ያሉትን ቀናት ሲሆን በእንግሊዝ በተሰራ መደበኛ የዳሰሳ ጥናት ላይ የተመሰረተም ነው፡፡
በዚህ የዳሰሳ ጥናት ላይም በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ጤንነታቸው ላይ ጫና መፈጠሩን ከተናገሩትና እድሜያቸው ከ16-29 ከሆነው 51 በመቶዎቹ ብቸኝነት ተሰምቶናል ብለዋል፡፡
እድሜያቸው ከ30- 59 ከሆኑት 27 በመቶዎቹ፤ ከ60 በላይ የሆኑት ደግሞ 26 በመቶዎቹ ተመሳሳይ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ታክሲ ማኅበር ከመንግሥት የተመደበለትን የእፎይታ ገንዘብ አልቀበልም በማለት አድማ መቷል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ፊኪሌ ምባሉላ የታክሲ ማኅበሩ ከመንግሥት የተመደበለትን 1.1 ቢሊዮን የደቡብ አፍሪካ ራንድ አልቀበልም ብሏል ሲል አሳውቀዋል።
ገንዘቡ ወደ ብር ሲመታ 2.2 ቢሊዮን ገደማ ይሆናል።
መንግሥት ገንዘቡን የመደበው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳውን የታክሲ ኢንዱስትሪ እንዲያንሰራራ ለማገዝ ነው።
ማኅበሩ የተመደበው ገንዘብ አይበቃም ሲል ይሞግታል፤ መንግሥት ደግሞ ድንቡሎ አልጨምርም ብሏል።
በዚህ መሃል ሰኞ ማለዳ ከቤታቸው ወጥተው ወደየፊናቸው ሊያቀኑ የተሰለፉ የታክሲ ተጠቃሚዎች መንገላታት ደርሶባቸዋል።
ጉዋቴንግ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የንግድ ማዕከሏ ጆሃንስበርግ በታክሲ አድማ በመመታቷ በርካቶች ለእንግልት መዳረጋቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።
ደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ግዛቷ መግባቱን ተከትሎ ጠበቅ ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላ እንደነበር አይዘነጋም።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከወራት በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ቅስቀሳ ላይ ሃገራቸው ከዓለም በርካታ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ያሉባት ልትሆን የቻለችው ብዙ ምርመራ በማካሄዷ መሆኑን ተናግረዋል።
«ብዙ ምርመራ ሲካሄድ ብዙ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው የግድ ነው» ሲሉ ተስላ በተሰኘችው የኦክላሆማ ግዛት ከተማ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።
«እናም ለሰዎቼ እንዲህ አልኳቸው፡ ምርመራውን ረጋ አድርጉት።» ሲሉም አክለዋል።
ይህ ንግግራቸው ብዙዎች ሲያነጋግር፤ ሲያስገርምም ነበር።
ዋይት ኃውስ ግን ፕሬዝደንቱ ይህን ያሉ በቀልድ ቢጤ ነው ሲል አስተባብሏል።
ነገር ግን ትራምፕ ሰኞ ዕለት በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሑፍ ተመሳሳይ ሐሳብ አንፀባርቀዋል። ብዙ ከተመረመረ ብዙ መገኘቱ አይቀሬ ነው የሚል ሃሳብ ያለውን ትዊት ግን ሁሉም አልተቀበለውም።
አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ይህ የፕሬዝደንቱ ፅንሰ-ሐሳብ ትክክል አይደለም ይላሉ።
አሜሪካ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን አረጋግጣለች። 120 ሺህ ገደማ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሞተዋል።
የኬንያ መከላከያ ሠራዊት የትኛውም የወታደር ካምፕ ውስጥ እንቅስቃሴ አልተገታም ሲል አስታባበለ።
የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በርካታ የኬንያ ወታደሮች በኮቪድ-19 ምክንያት ለይቶ ማቆያ ገብተዋል ሲሉ መዘገባቸውን ተከትሎ ነው መከላከያ ሠራዊቱ ይህንን ያለው።
የኬንያ መከላከያ ሠራዊት ቃል-አቀባይ ኮሎኔል ዚፖራህ ኪዮኮ ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ መግባትና መውጣት አልተከለከለም፤ ነገር ግን ወታደሮች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተነግሯቸዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በርካታ ወታደሮች እንዲመረመሩ፣ የሰውነት ሙቀታቸው በየጊዜው እንዲለካ፣ ጭምብል እንዲያጠልቁ እንደሁም እጅ ማፅጃ ፈሳሾች [ሳኒታይዘር] በየሥፍራው እንዲቀመጥ መደረጉን ኮሊኔሉ አሳውቀዋል።
ሲቲዝን የተሰኘው ቴሌቪዥን ጣብያ ምንጮቼ ነገሩኝ ብሎ እንደዘገበው አንድ ወታደር በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወቱን ሲያጣ በርካቶች ደግሞ ለይቶ ማቆያ ገብተዋል።
ካሃዋ የተሰኘው በመዲናዋ ናይሮቢ የሚገኝ የወታደር ካምፕ እንቅስቃሴው እንዲገታ ሆኗል ሲልም ጣቢያው ዘግቧል።
ኮሎኔሉ በቫይረሱ የተያዙ ወታደሮች ካሉ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።
ኬንያ እስከ ሰኞ ማለዳ ድረስ 140 ሺህ ሰዎችን መርምራ 4738 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ይፋ አድርጋለች።
ኮሮናቫይረስን ለመከላከል በተደነገገው የአስቸኳይ አዋጅ ስር የነበሩ አንዳንድ መመሪያዎች ማሻሻያዎች እንደተደረገባቸው ተገልጿል።
ከማሻሻያዎቹ መካከል አንዱ ምንም ዓይነት ምልከት የማያሳዩ ወይንም ቀላል ምልክት ብቻ የሚታይባቸው በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን የሚመለከት ነው።
በማሻሻያው መሰረት የሚያገለግሏቸው የቤተሰብ አባላትና የራሳቸው ፍላጎት ከግምት ውስጥ ገብቶ የአኗኗር ሁኔታቸው የሚፈቅድ ከሆነ በቤታቸው ሆነው ራሳቸውን በማግለል እንዲቆዩ እንደሚደረግ ተገልጿል።
በቤታቸው ውስጥ ራሳቸውን ለይተው መቀመጥ የማይችሉ ከሆነ ከጤና ተቋማት ውጪ በተዘጋጁ ለይቶ ማቆያዎች እስኪያገግሙ ድረስ እንዲቆዩ ይደረጋል ተብሏል።
ሁለተኛው ማሻሻያ ከውጭ የሚገቡ ሰዎች ወደ ሀገር ውስጥ በገቡበት ሰዓት፣ ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ ከመጡበት ሀገር ተመርምረው ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ ካቀረቡ፣ ናሙና ተወስዶ በቤታቸው 14 ቀናት እንዲቆዩ ይደረጋል የሚል ነው።
ሶስተኛው ደግሞ ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋገጥ ማስረጃ ይዘው ለማይመጡ መንገደኞች ለሰባት ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ የሚደረግ ሲሆን ተመርምረው ነጻ ከሆኑ ቀሪውን ሰባት ቀን በቤታቸው እንዲቆዩ ይደረጋል ተብሏል።
አራተኛው ማሻሻያ በቤት ውስጥም ሆነ በጤና ተቋም ውስጥ የሚከሰት ማንኛውንም ሞት ይመለከታል።
በየትኛውም ስፍራ የሚከሰት ሞት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በቤተሰብ የቀብር ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸም ይሆናል ተብሏል።
ነገር ግን ከማንኛውም ሞት በኋላ የኮቪድ 19 ምርመራ ናሙና የሚወሰድ ሲሆን የምርመራ ውጤቱ ሳይጠበቅ አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ ቤተሰብ ባዘጋጀው ቦታ 50 ሰዎች ብቻ ተገኝተው ሥርዓቱን እንዲያካሄዱ ተብሏል።
የኮሮናቫይረስን ለመመርመር ናሙና የሚወሰደው ከአፍንጫ ውስጥ ነው። ይህ ከአፍንጫ ውስጥ ናሙና ለመውሰድ የሚኖር ሂደት የተመርማሪውን ምቾት የሚነሳ መሆኑ ይነገራል።
ወደ አፍንጫ ውስጥ ቀጠን ያለች ናሙና መሰብሰቢያ መሳርያ ስትገባ ምንም እንኳ ጉዳት የሚያስከትል ባይሆንም በርካታ ሰዎች ግን ደስተኞች አይደሉም።
በጃፓን የሚገኝ የተመራማሪዎች ቡድን በ25 ደቂቃ ውስጥ ውጤትን ማወቅ የሚያስችል እና ኮሮናን ከምራቅ ላይ መመርመር የሚያስችል ሙከራ እያደረግሁ ነኝ ብሏል።
የሕክምና ተቋሙ ሺኦኖጊ እንዳለው ከጃፓን ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን አስታውቆ ሰዎች፣ ይህ ሙከራ ከተሳካ ሰዎች በቤታቸው ምርመራ ማድረግ እንዲችሉ ያስችላል ብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደምም በተመሳሳይ ከምራቅ ላይ መመርመር የሚያስችል ሙከራ እየተካሄደ ሲሆን እስካሁን ድረስ 14 ሺህ ጤና ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል ተብሏል።