በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 5175 ሲደርስ ሟቾች 81 ሆኑ

የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት እየተስፋፋ ባለባት ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት 141 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ቁጥሩን 5175 አድርሶታል። በዛሬው ዕለት በህክምና ማዕከል የነበሩ የሶስት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ አገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥርም 81 ሆኗል። በአጠቃላይ ከበሽታውም 1ሺህ 544 ሰዎች ማገገማቸውንም የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጋራ ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል። ታሞ ለከፋ ጉዳት ከመዳረግና ከህመሙ ከማገግም ይልቅ ባለሙያዎች እንደሚመክሩት በሽታውን አስቀድሞ መከላከል ዋነኛው መፍትሄ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብና አፍና አፍንጫን መሸፈን ዋነኞቹ ናቸው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የናይጄሪያ ፖሊስ በሩዝ ፋብሪካ ተቆልፎባቸው እንዲሰሩ የተገደዱ 300 ሰራተኞችን ነፃ ማውጣቱን ገለፀ

  2. ኢትዮጵያ በቀን 8 ሺህ ናሙና የመመርመር አቅም ማዳበሯን አስታወቀች

    ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በአገር አቀፍ ደረጃ 32 የምርመራ ማዕከላት እንዳሏት የገለፀው ዛሬ ማምሻውን የወጣው የጤና ሚኒስቴር መግለጫ ይህም በቀን 8ሺህ ናሙናዎችን መመርመር እንደሚያስችላት ገለፀ።

    መግለጫው በተጨማሪም በቅርቡ 19 ላብራቶሪዎች ወደ ሥራ ለማስገባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ጠቅሶ ይህም በቀን የመመርመር አቅምን ወደ 15 ሺህ ከፍ እንደሚያደርገው ተግልጿል።

    እስከ ዛሬው እለት (ሰኔ 16 2012) ድረስ ብቻ 219 ሺህ 566 ናሙናዎች ላይ ምርመራ መካሄዱን መግለጫው ጠቅሷል።

    መግለጫው አክሎም በአሁኑ ሰዓት በአገር አቀፍ ደረጃ ለኮቪድ19 ብቻ 273 መካኒካል ቬንትሌተሮች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ተጨማሪ 100 በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በኩል ለህክምና ተቋማት ይሰራጫሉ ተብሏል።

    እንዲሁም 300 ያክል በግዢ ሂደት ላይ መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

  3. ታይላንድ ዝንጆሮዎቿን አኮላሸች

    በታይላንድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዝንጀሮዎች መኮላሸታቸው ተገለፀ።

    ዝንጀሮዎቹ የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ቱሪስቶች በመጥፋታቸው የተነሳ በመራባቸውና ቁጡ በመሆናቸው ነው እንዲኮላሹ የተደረገው።

    በታይላንድ ማእከላዊ ሎፑቡሪ ግዛት፣ ዝንጀሮዎቹ በአገር ጎብኚዎች ዘንድ በጣም ዝነኛና ተወዳጅ የነበሩ ሲሆን ቱሪስቶቹ ይመግቧቸው አብረዋቸው ፎቶም ይነሱ ነበር።

    ነገር ግን ታይላንድ ድንበሮቿን ከዘጋች ወዲህ ዝንጆሮዎቹ ከሁኔታው ጋር ራሳቸውን ማላመድ መቸገራቸውን የሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ለታይላንድ መንግሥት የሚሰሩት የእንስሳት ህክምና ባለሙያ የሆኑት ሱፓካርን ካኤውቾት እንዳሉት "የአገር ጎብኚዎቹ መኖርን በጣም ለምደውት ነበር፤ ይመግቧቸው ነበር። የከተማው አስተዳደር የሚቀመጡበት ስፍራ አላዘጋጀላቸውም"

    አክለውም "የአገር ጎብኚዎቹ ሲቀሩ፣ በጣም ቁጡ ሆኑ፣ ከሰዎች ጋር ምግብ ለማግኘት ሲሉ ይጋጩ ጀመር" ካሉ በኋላ "የመኖሪያ ስፍራዎችን ይወራሉ፤ ነዋሪዎች ቤታቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ ያደርጋሉ" ብለዋል።

  4. ፕሬዝዳንቱ በፍርድ ቤት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ ታዘዙ

    የብራዚል ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጃዬር ቦልሶናሮ በዋና ከተማዋ ብራሲሊያምም ሆነ በዙሪያዋ በሚገኙ የፌደራል አውራጃዎች ሕዝብ በሚንቀሳቀስባቸው ስፍራዎች ሲዘዋወሩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ አዘዘ።

    የብራዚል ፕሬዝዳንት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚደርሰውን ሞትና ሕመም አናንቀው ሲናገሩ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።

    ወረርሽኙ በጀመረበት ወቅት ኮሮናቫይረስን " ቀላል ጉንፋን" በማለት ገልፀውት ነበር።

    እንዲሁም በተደጋጋሚ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ስፍራዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ እንዲሁም ደጋፊዎቻቸውን አካላዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ሲጨብጡ ታይተዋል።

    በአንድ ለእርሳቸው ድጋፍ በተዘጋጀ ሰልፍ ላይም አፋቸውንና አፍንጫቸውን ሳይሸፍኑ ሲያስሉ የታዩ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ እጃቸውን ሸፍነው አስነጥሰው ወዲያውኑ በእድሜ የገፉ ሴትን ሲጨብጡ ታይተዋል።

    የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ሬናቶ በሬሊ እንዳሉት፣ ፕሬዝዳንቱም ሆኑ ሌሎች የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህንን ባያደርጉ ግን 387 ዶላር በቀን እንደሚቀጡ አስታውቀዋል።

    ብራዚል በወረርሽኙ ክፉኛ ከተጠቁ የዓለም አገራት መካከል ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛዋ ስትሆን 1.1 ሚሊየን ሰዎች ቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ሲረጋገጥ ከእነዚህም መካከል 51,000 ያህሉ ሞተዋል።

  5. ለሥራ ቢሮ መሄድ ብሎ ነገር ከናካቴው ሊቀር ይሆን?

  6. ባለፉት 24 ሰዓታት 185 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

    የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ በጋራ ባወጡት እለታዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገው 3775 ምርመራ185 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው ተገለፀ።

    ይህም በአጠቃላይ በአገሪቱ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 4848 አድርሶታል።

    በተያያዘ ዜና በትላንትናው ዕለት 115 ሰዎች ማገገማቸው ተገልጿል።

    እነዚህ ሰዎች 81 ከአዲስአበባ፣ 23 ከአማራ ክልል፣ ስድስት ከኦሮሚያ ክልል፣ ሁለት ከሐረሪ ክልል፣ ሁለት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አንድ ትግራይ ክልል ናቸው።

    ይህም በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርን 1412 አድርሶታል።

  7. ታዳጊውን በመግደል የተጠረጠረው ኬንያዊ ፖሊስ ነፍስ በማጥፋት ወንጀል ተከሰሰ

    የ13 ዓመቱን ያሲን ሞዮ በመግደል የተጠረጠረው ፖሊስ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሰሰ።

    ኬንያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በሚል የሰዓት እላፊ ካወጀች በኋላ ያሲን ሞዮ፣ ፖሊስ መንገደኞችን ከጎዳናው ላይ ገለል እንዲሉ ሲያደርግ በረንዳው ላይ ቆሞ እየተመለከተ ነበር በተተኮሰበት ጥይት የተመታው።

    ደንከን ኒዴማ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ አለመሆኑ ገልጿል።

    ጠበቃው፣ አቃቤ ሕግ ታዳጊውን የገደለው ከደንበኛዬ ጠብመንጃ የወጣ ጥይት መሆኑን ማረጋገጥ አለበት ሲሉ ተሰምተዋል።

    ኬንያ ኮሮናቫይረስ ከተከሰተ በኋላ ፖሊስ በሚያደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያ ክፉኛ ይወቀሳል።

    በኬንያ ሰዓት እላፊ የታወጀው በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

    ያሲን በጎርጎሳውያኑ መጋቢት 30 በቤተሰቦቹ ቤት በረንዳ ላይ ሆኖ ፖሊስ ጎዳና ላይ ያሉ ሰዎችን ሲያባርር እየተመለከተ እንደነበር እናቱ ከድጃ አብዱላሂ ለቢቢሲ ተናግራለች።

    ኒዴማ የአገሪቱን ፖሊስ በሚከታተለው ገለልተኛ ባለስልጣን ምርመራ ከተደረገ በኋላ ነው ክስ የተመሰረተበት።

    በአሁን ሰዓት እስር ቤት የሚገኘው ፖሊስ፣ ነገው ፍርድ ቤት ቀርቦ የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት እንደሚጠይቅ ለማወቅ ተችሏል።

    ኬንያ የሰዓት እላፊ በጣለችበት የመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት ብቻ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን አምንስቲ ኢንተርነናሽናል ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

    ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ፖሊስ ከተገቢው በላይ ኃይል በመጠቀሙ ይቅርታ ጠይቀዋል።

  8. ከ መጋቢት 4 2012 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት መቶ ቀናት 32 ሚሊዮን ሰዎች በቤት ለቤት ዳሰሳ ታይተዋል

    ኢትዮጵያ ከመጋቢት መጋቢት 4 - ሰኔ 14 2012 ዓ.ም ባሉት መቶ ቀናት በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጡት አሃዛዊ መረጃ ያስረዳል።

    እስከ ሰኔ 14 2012 ድረስ ብቻ 216 ሺህ 328 የላብራቶሪ ምርመራዎች ተደርገው 4 ሺህ 532 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ ተረጋግጧል።

    32 ሚሊዮን ሰዎች በቤት ለቤት ዳሰሳ መታየታቸው የተገለፀ ሲሆን 13 ሺህ 859 የማከምያ አልጋዎች ተዘጅተዋል ተብሏል።

    ከጥር 15 ጀምሮለ764 ሺህ 948 ተጓዦች ልየታ እና ክትትል መደረጉን ይኸው መረጃ ይገልጻል።

    በእነዚህ መቶ ቀናት ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው 31 ሺህ 573 ሰዎች ተለይተው 708 ሰዎች የኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው ይኸው መረጃ በተጨማሪ ያሳያል።

  9. በደቡብ አፍሪካ አንድ ግዛት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት 196 ትምህርት ቤቶች ዳግም ተዘጉ

    የደቡብ አፍሪካ የጤና ባለስልጣናት በአገሪቱ ምስራቃዊ ኬፕ አውራጃ የኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ጥረት ውጤት አለማምጣቱ ተገለፀ።

    በአውራጃው ምርመራ ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል 180ዎቹ በቫይረሱ ተይዘው ተገኝተዋል።

    ማካኡላ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማክሰኞ እለት ጸረ ተዋህሲያን ለመርጨት በሚል የተዘጋ ሲሆን ከተማሪዎቹ ጋር ንክኪ የነበራቸውን የመለየት እና ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል።

    ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከ20 ቀን በፊት ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራቸውን እንዲቀጥሉ የተናገሩ ቢሆንም ምስራቅ ኬፕ አውራጃ ግን 196 ትምህርት ቤቶቹን ከዚህ ውሳኔ በኋላ ዘግቷል።

    በደቡብ አፍሪካ ይህች የውቅያኖስ ዳርቻ አውራጃ በደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ ከተጠቁ ግዛቶች መካከል ሁለተኛዋ ናት።

    በግዛቲቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከ300 ሰዎች በላይ መሞታቸው ተገልጿል።

  10. ከኮቪድ-19 ያገገሙ ሰዎች ስጋት ምን ይሆን?

    በኮቪድ-19 ተይዘው ሆስፒታል ከገቡ በኋላ አገግመው የሚወጡ ሰዎች በሳንባቸው ላይ ዘላቂ የሆነ ጉዳት ሊከሰት እንደሚችል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

    ሳንባን የሚጎዳውና በሽታ ፑልሞናሪ ፋይብሮሲስ ይሰኛል። ይህ በሽታ ከኮሮናቫይረስ የሚያገግሙ ሰዎችን በምን ያህል ደረጃ እንደሚያጠቃ ገና በእንጭጩ ያለ ጥናት ነው ተብሏል።

    ይህ በሽታ በሳንባ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ዘላቂ ሲሆን የመተንፈስ ችግር፣ ሳል እንዲሁም ድካም እንዳለው ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

    ቻይና ውስጥ በተደረገና በታተመ ጥናት ከ70 ያገገሙና ከሆስፒታል የወጡ በሽተኞች መካከል 66ቱ የተወሰነ የሳንባ መጎዳት ገጥሟቸዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም ራዲዮሎጂስቶች ኮሮናቫይረስ የተያዙና ያገገሙ ሰዎች ውጤትና ተከትሎ በተደረጉ ምርመራዎች ለዘለቄታው የሚቆይ አደገኛ ኢንፌክሽን ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

  11. በአፍሪካ የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ ሊደረግ ነው

  12. በጀርመን አንድ ግዛት ውስጥ የእንቅስቃሴ ገደብ በድጋሚ ተጣለ

    በጀርመን ሰሜን ሪሂኔ ዌስትፋሊያ ግዛት አስተዳዳሪ በግዛቲቱ ውስጥ በምትገኘው ጉተርስሎህ በድጋሚ የእንቅስቀሴ ገደብ ሊጣል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

    እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ቶኒስ በተባለ የሥጋ ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ወረርሽኙ በመቀስቀሱ ነው፡፡ 1ሺህ 553 የፋብሪካው ሠራተኞችም በኮቪድ -19 መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡

    በመሆኑም አስተዳዳሪዋ አርሚን ላስቼት ተግባራዊ የሚደረጉ ገደቦችን በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡

    በዚህም አካላዊ ርቀትን የመጠበቅ ሕጉም መጋቢት ላይ እንደነበረው ጥብቅ ይሆናል፡፡

    የአካባቢው ነዋሪዎችም ከሰዎች ጋራ መገናኘት የሚችሉት በራሳቸው ግቢ ብቻ ሲሆን በግቢ ውስጥ የሚደረጉ የቡድን እንቅስቃሴዎችም ይታገዳሉ፡፡

    የሙዚቃ ድግሶች፣ ፊልም ቤቶች፣ ቤተ መዘክሮችና ጋለሪዎች ይዘጋሉ፡፡

    ዝግ በሆኑና በቂ አየር በማይገባባቸው ቦታዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግም አይቻልም፡፡

    ጂም፣ መዋኛዎችና የሳውና አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲሁም የምሽት ክለቦችና ካፍቴሪያዎችም እንዲዘጉ ይደረጋል፡፡ ምግብ ቤቶች ብቻ ወደ ቤት መወሰድ የሚችሉ ምግቦችን የማቅረብ አገልግሎት እንዲሰጡ ተፈቅዷል፡፡

    ለተቋሙ 7 ሺህ ሠራተኞች ራሳቸውን ለይተው መቆየታቸውም ግድ ነው ተብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ቦታው በብረት አጥር የተከለለ ሲሆን በፖሊሶችም ይጠበቃል፡፡

    ባለሥልጣናት ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለሠራተኞቹ እያቀረቡ ነው፡፡

    በጉተርስሎህ በአጠቃላይ 360 ሺህ ሰዎች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡

  13. "ወንዶች ከሴቶች የተሻለ ፕላዝማ መለገስ ይችላሉ"

    በዩናይትድ ኪንግደም በኮሮናቫይረስ ተይዘው የነበሩና ከበሽታው ያገገሙ ወንዶች ከደማቸው ፕላዝማ እንዲለግሱ ተጠይቀዋል፡፡

    ፕላዝማው ለኮቪድ-19 ህክምና ምርምር የሚውል ነው ተብሏል፡፡

    ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወንዶች ከሴቶች በበለጠ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ለከፋ ሕመም ይዳረጋሉ፡፡ በመሆኑም ከሴቶች በተሻለ ከፍተኛ መጠን አንቲቦዲ ያመርታሉ፡፡

    ይህ ማለት ደግሞ ከእነርሱ የሚወሰደው ፕላዝማ የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

    የአገሪቷ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት እንዳለው ሙከራው የሚሳካ ከሆነ ሆስፒታል ውስጥ ያሉ ህሙማንን ለማከም ይረዳል፡፡

    ተቋሙ ከኮቪድ ያገገሙ ሰዎች ደምና ፕላዝማ እንዲለግሱ መጠየቅ የጀመረው በሚያዚያና እና ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ሲሆን 600 የሚጠጉ ሰዎች ፕላዝማቸውን ለግሰዋል፡፡

    ከወንዶች ከተለገሰው ፕላዝማ 43 በመቶ የሚሆነው ከፍተኛ መጠን አንቲቦዲ ያለው ሲሆን ለምርምር ሙከራው ይውላል ተብሏል፡፡ ከሴቶች የተገኘው 29 በመቶ ሲሆን በንጽጽር የወንዶቹ ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡

    ከፍተኛ መጠን ያለው አንቲቦዲ አንዳንዴ እድሜያቸው ከገፉ ሰዎች፣ በሆስፒታል የኮቪድ -19 ህክምና ከሚከታተሉና እስያዊያን ህሙማን ይገኛል፡፡

    አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ ሲያዝ የተፈጥሮ በሽታን የመከላከያ ሥርዓቱ በሽታን አምጪ ተህዋስን የመከላከያ ዘዴን ያዘጋጃል፤ ይህም ቫይረሱን በማጥቃት ወደ በሽታ እንዳይሸጋገር ያደርጋል።

    ይህ ሂደትም ፕላዝማ በተባለውና በደም ውስጥ ባለው ፈሳሽ ክፍል ውስጥ የሚገኝ ነው።

  14. የህክምና ባለሙያዎች ስጋት

    ከሳምንታት በፊት በኮቪድ-19 የተያዙ የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር መጨመሩን የኢትዮጵያ ጤና ሚንስር ዶ/ር ሊያ ታደሰ መናገራቸው ይታወሳል። በተጨማሪም ቢቢሲ ያነጋገራቸው በተለያዩ የሕክምና ተቋማት የሚሰሩ ባለሙያዎችም የሕክምና መከላከያ ቁሳቁሶች (ፒፒኢ) እጥረት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

    ከእነዚህም መካከል ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ማቆያ የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ተብሎ በሚጠራው ጤና ጣቢያ ውስጥ ያሉት ይገኙበታል።

    ወረዳ 10 ጤና ጣቢያ ተብሎ በሚጠራው ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ ለቢቢሲ የተናገሩ ሁለት የጤና ባለሙያዎች፤ በሚገኙበት ለይቶ ማቆያ መሠረታዊ የሚባሉ ግልጋሎቶችን በአፋጣኝ ማግኘት አልቻሉም።

    ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ስናነጋግራቸው በጣቢያው ውሃ እና መብራት እንዳልነበረ ገልጸውልናል። ሰኞ፣ ሰኔ 9 ቀን 2012 በድጋሚ ስናናግራቸው ግን ለሳምንት ያክል ያልነበረው የመብራት እና ውሃ እገልግሎት እንደመጣ ተናግረው ሌሎች ጥያቄዎቻቸው አሁንም ምላሽ እንዳላገኙ ግን ጨምረው አስረድተዋል። ተጨማሪ እዚህ ያንብቡ የጤና ባለሙያዎች መሠረታዊ ፍላጎታችን እየተሟላ አይደለም አሉ

  15. የኢቦላ እና የኤችአይቪ ተመራማሪው በመጨረሻ ለኮቪድ- 19 እጅ ሰጥተው እንደነበር ተናገሩ

    ፕሮፌሰር ፒተር ፒዎት በለንደን የንጽህናና 'ትሮፒካል'ህክምና ትምህርት ቤት ተመራማሪ ናቸው፡፡

    ፕሮፌሰሩ በዓለማችን ካሉ እውቅ የተላላፊ በሽታዎች ምሁራን መካከል አንዱ ሲሆኑ የጉልምስና ሕይወታቸውን ያሳለፉትም ቫይረሶች ላይ ምርምር ሲያደርጉ ነው፡፡

    ተመራማሪው በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1976 የኢቦላ ቫይረስን ያገኘው የምርምር ቡድን አባል ነበሩ። ከዚህም ባሻገር በኤችአይቪ /ኤድስ ምርምርም ፈር ቀዳጅ ናቸው፡፡

    ፕሮፌሰር ፒተር እድሜ ልካቸውን ሲታገሏቸው በነበሩት በእነዚህ ገዳይ ቫይረሶች ግን ተይዘው አያውቁም፡፡

    ይሁን እንጂ ፕሮፌሰሩ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፈው ኮቪድ- 19 አላመለጡም፡፡

    ፕሮፌሰር ፒተር ፒዮት በቫይረሱ ተይዘው የነበረ ሲሆን አሁን ላይ እንዳገገሙ ተነግሯል።

    በቫይረሱ መያዛቸውን ያወቁት ትኩሳት፣ የሰውነት መድከም፣ ራስ ምታትና የጡንቻ ህመም ካጋጠማቸው በኋላ ወደ አንድ ሆስፒታል አምርተው ከተመረመሩ በኋላ ነው፡፡

    ከዚያም በሽታው ተባብሶባቸው ሆስፒታል ገብተው በኦክስጅን እየታገዙ እስከመተንፈስ ደርሰው ነበር፡፡

    በእርግጥ ህመሙ ሲጀምራቸው ቀላል ጉንፋን ሊሆን ይችላል በማለት አቃለው እንደተመለከቱትና ያም ስህተት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

    ቫይረሱ ማንንም እንደማይምርና በጤና ላይ ዘላቂ ጠባሳ ጥሎ እንደሚያልፍ የገለጹት ፕሮፌሰሩ፤ ቅድመ ዝግጅት ቢደረግ ኖሮ በቫይረሱ ሳቢያ ያጣናቸውን ሰዎች ቁጥር መቀነስ ይቻል ነበር ይላሉ፡፡

  16. በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር 4 ሚሊየን ሊደርስ ይችል ነበር- ትራምፕ

    በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ120 ሺህ በላይ መሆኑ ተዘግቧል።

    ይሁን እንጂ ፕሬዚደንት ትራምፕ ከአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ቁጥሩ ከ150 ሺህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

    ፕሬዚደንት ትራምፕ ስፔክትረም ኒውስ ከተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ከ2 ሚሊየን እስከ 4 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎችን በቫይረሱ ሳቢያ ልናጣ እንችል ነበር ማለታቸው ተዘግቧል።

    መጋቢት ወር ላይ ከለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ የወጣ ሪፖርትም በአሜሪካ 2.2 ሚሊየን ሰዎች ህክምና ሳያገኙ ሊሞቱ ይችላሉ ብሎ ነበር።

    ምንም እንኳን በአሜሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ የነበረ ቢሆንም፤ አሁንም ግን ካሊፎርኒያ፣ ቴክሳስና ፍሎሪዳን ጨምሮ በ23 ግዛቶች ቁጥሩ እየጨመረ ነው።

  17. ኡጋንዳ 'አደገኛ ወደሆነ የወረርሽኙ ደረጃ' እያመራች ነው ተባለ

    የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አገሪቷ ወደ ባሰና አደገኛ ወደ ሆነ የወረርሽኙ ደረጃ እያመራች ነው ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡

    ፕሬዚደንቱ በተወሰኑ የአገሪቷ ክፍል የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደገና መጀመሩን ተከትሎ ከሕብረተሰቡ ውስጥ ንክኪያቸው በውል ሊለይ የማይችል ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

    ከዚህ ቀደም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በአብዛኛው ከውጭ አገር የተመለሱና ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች እንደነበሩ ፕሬዚደንቱ አስታውሰዋል፡፡

    ፕሬዚደንቱ አክለውም በሕዝብ እና የግል ትራንስፖርት አገልግሎት የተጣለው እገዳ በትንሹ በ33 ድንበር ላይ በሚገኙ አካባቢዎች እንደሚነሱ ተናግረዋል፡፡

    ነገር ግን ከፍተኛ የስደተኛ ቁጥር ያለባቸው ወይም ዋና መተላለፊያ የድንበር አካባቢዎች በትራንስፖርት ላይ የተጣሉ ደንቦችን ተግባራዊ ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡

    የምሽት ሰዓት እላፊን ባለበት የሚቀጥል ሲሆን ትምህርት ቤቶችና የአምልኮ ሥፍራዎችም እንደተዘጉ ይቆያሉ፡፡

    በኡጋንዳ እስካሁን 774 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 631 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል፡፡ በአገሪቷ እስካሁን በቫይረሱ የሞተ ሰው የለም፡፡

  18. ከአንድ እናት በአንድ ጊዜ ከተወለዱ ሦስት ጨቅላ ህጻናት ኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

    በሜክሲኮ ከአንዲት እናት በአንድ ጊዜ አዲስ የተወለዱ ሦስት ጨቅላ ህጻናት በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ።

    ጨቅላ ህጻናቱ በቫይረሱ አንዴት ሊያዙ እንደቻሉ በጤና ባለሙያዎች ላይ ግርታን የፈጠረ ሲሆን፤ የጤና ባለሥልጣናትም ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ነገር ሰምተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

    ጨቅላ ህጻናቱ ምርመራ የተደረገላቸው ከተወለዱ በኋላ በሰዓታት ውስጥ ሲሆን ቫይረሱ እንዳለበት ከታወቀ ማንኛውም ሰው ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ አልነበራቸውም ተብሏል።

    ጉዳዩ ተመራማሪዎችንም አስገርሟል። ነገር ግን አጋጣሚው ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ በእንግዴ ልጅ አማካኝነት መተላለፍ መቻል አለመቻሉን ለማየት ሊረዳ ይችላል ብለዋል።

    በሳን ሊዩስ ፖቶሲ የኅብረተሰብ ጤና ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት ሚጌል አንጀል፤ "ይህ ከዚህ ቀደም በሳይንስ የማይታወቅ ነው" ብለዋል።

    ከጨቅላ ህጻናቱ መካከል ሁለቱ በጥሩ ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን ሌላኛው ግን የመተንፈሻ አካል ህመም ህክምና እየተደረገለት ይገኛል።

    የጤና ባለሥልጣናት ወላጆቻቸው በቫይረሱ ተይዘው፤ ነገር ግን የበሽታው ምልክት ያልታየባቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ።

    ወላጆቻቸውም ራሳቸውን አግልለው የምርመራ ውጤታቸውን እየተጠባበቁ ነው።

  19. ሳዑዲ ዘንድሮ አለም አቀፍ የሐጅ ተጓዦችን እንደማታስተናግድ አስታወቀች

    ሳኡዲ አረቢያ ከየትኛው አገር ለሐጅ ሥነሥርዓት የሚመጡ ምዕመናንን ዘንድሮ እንደማታስተናግድ ይፋ አደረገች።

    ምክንያቱ ደግሞ ቫይረሱን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመቆጣጠር ባላት ፍላጎት ነው ተብሏል።

    ሆኖም አሁን በሳኡዲ የሚኖሩ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ በሐጅ ሥነሥርዓት ላይ ሊካፈሉ እንደሚችሉ በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርጋለች።

    በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከመላው ዓለም ወደ መካና መዲና ለሐጅ ሥነሥርዓት ይጎርፋል።

    የሐጅ ሥነሥርዓት በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መንፈሳዊ ተግባር ነው።

    ሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ማድረግ ከእስልምና አምስት መሰረቶች አንዱ ሲሆን ማንኛውም የገንዘብና የጤና አቅም ያለው ምዕመን በሕይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ ሐጅ የማድረግ ግዴታ አለበት።

    በዚህ ዓመት በሐጅ ሥርዓት ሊካፈሉ የሚችሉት በተለያየ ክፍለ ዓለም ነዋሪ ሆነው ነገር ግን የሳኡዲ የመኖርያ ፍቃድ ያላቸው ብቻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

    ሳኡዲ አረቢያ እስከዛሬ በዚህ ወረርሽኝ 161,005 ሰዎችተ ይዘውባት 1ሺህ 307 ዜጎች ሞተውባታል።

  20. በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ9 ሚሊዮን አለፈ

    ከተቀሰቀሰ ስድስት ወራት የሆነው ኮሮናቫይረስ መላውን ዓለም አዳርሶ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሆኗል።

    በሽታው በወረርሽኝት የተከሰተባት ቻይና በሦስት ወራት ውስጥ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር ብትችልም ቫይረሱ በፍጥነት ወደ አውሮፓ ከዚያም ወደ ሰሜን አሜሪካ ተሻግሮ በአስር ሺህዎች ከፍ ብሎም በመቶ ሺህዎች በበሽታው ሲያዙ ቆይተው አሁን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የበሽታው ታማሚ ሆነዋል።

    በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አሃዝ በዓለም ዙሪያ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ተሻግሮ 9 ሚሊዮን 79 ሺህ 452 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል።

    ከዓለም አገራት ውስጥ ከፍተኛው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ያሏት አገር ኃያሏ አሜሪካ ስትሆን 2,289,168 ህሙማንን እንዳገኘች እስከ ሰኞ ምሽት ድረስ የመዘገበች ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የደቡብ አሜሪካዋ ብራዚል 1,083,341 ዜጎቿ በበሽታው ተይዘዋል።

    በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ አውሮፓንና እስያን የምታካልለው ታላቋ ሩሲያ 591,456 ሰዎች በሽታው እንዳለባቸው ያሳወቀች ሲሆን፤ ከአንድ ቢሊየን በላይ ሕዝብ ያለት የእስያ አገር ሕንድ 425,282 ሰዎች ላይ በሽታውን አግኝታለች።

    በእነዚህና በሌሎችም አገራት በበሽታው መያዛቸው የሚረጋገጥ ሰዎች ብዛት በየደቂቃው እየጨመረ እንደሚሄድ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ያመለክታል።