በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 5175 ሲደርስ ሟቾች 81 ሆኑ

የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት እየተስፋፋ ባለባት ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት 141 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ቁጥሩን 5175 አድርሶታል። በዛሬው ዕለት በህክምና ማዕከል የነበሩ የሶስት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ አገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥርም 81 ሆኗል። በአጠቃላይ ከበሽታውም 1ሺህ 544 ሰዎች ማገገማቸውንም የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጋራ ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል። ታሞ ለከፋ ጉዳት ከመዳረግና ከህመሙ ከማገግም ይልቅ ባለሙያዎች እንደሚመክሩት በሽታውን አስቀድሞ መከላከል ዋነኛው መፍትሄ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብና አፍና አፍንጫን መሸፈን ዋነኞቹ ናቸው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የሐሙስ ሰኔ 18/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    ጤና ይስጥልን፤ እንደምን አድራችኋል?

    ዛሬ ዕለቱ ሐሙስ ሰኔ 18/2012 ዓ.ም ነው።

    ቢቢሲ አማርኛ ከመላው ዓለምና ከኢትዮጵያ የሚገኙ ኮሮናቫይረስን የሚመለከቱ ትኩስ ዜናና መረጃዎችን በዚህ የቀጥታ ዘገባ ገጽ ላይ ያቀርባል።

    ስለወረርሽኙ ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት ይህንን የቀጥታ ዘገባ ገጻችንን እንድትጎበኙ በአክብሮት እንጋብዛለን።

    መልካም ቀን ይሁንላልችሁ!

  2. ምርጫ ቦርድ ከትግራይ ክልል የቀረበለትን ጥያቄ እንዳልተቀበለው አስታወቀ

  3. የ'114 ዓመት' የእድሜ ባለጸጋ ከኮሮናቫይረስ አገገሙ

    በኮሮናቫይረስ ተይዘው በአዲስ አበባ በሚገኘው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ የ114 የእድሜ ባለጸጋ ከበሽታው አገግመው መውጣታቸውን የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ያሬድ አግደው በፌስቡክ ገጻቸው አስታወቁ፡፡

    አዛውንቱ ለተጨማሪ ህክምና የካቲት 12 ሆስፒታል እንደሚገኙም ሥራ አስኪያጁ አክለዋል፡፡

    አዛውንቱ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ ለዚህ ስኬት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ የጤና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

  4. የዘንድሮው ኒውዮርክ ማራቶን እንደማይካሄድ ተገለጸ

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ በኒውዮርክ የሚካሄደው የዚህ ዓመት የማራቶን ውድድር መሰረዙን አስተባባሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡

    በጉጉት የሚጠበቀውና የዓለማችን ታላቁ የሩጫ ውድድር በጎርጎሮሳውያኑ ህዳር 1 ላይ ይካሄዳል፤ 50ኛ ዓመቱንም ያከብራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ ወደሚቀጥለው ዓመት ተሻግሮ ህዳር 7/2021 ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል፡

    በከተማዋ ባለሥልጣናትና ለትርፍ ባልተቋቋመው 'ኒውዮርክ ሮድ ራነር' ድርጅት በሚዘጋጀው በዚህ ውድድር በየዓመቱ ከ500 ሺህ በላይ ሯጮች፣ 10 ሺህ በጎ ፈቃደኞች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች ይሳተፋሉ፡፡

    የድርጅቱ ኃላፊ ማይክል ካፒራሶ በሰጡት መግለጫ "ውድድሩ መሰረዙ የሚያናድድ ነበር፤ ነገር ግን ከጤናና ከደህንነት አንጻር መከተል ያለብን አካሄድ ነው" ብለዋል፡፡

  5. በአሜሪካ ደቡባዊና ምዕራባዊ ግዛቶች ቫይረሱ እየተስፋፋ ነው

    በአሜሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በሁለት ወራት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ያሳያል፡፡

    እንደ አሶሺየትድ ፕሬስ ከሆነ ማክሰኞ ዕለት አሜሪካ 34 ሺህ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን የአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር የተባለውን 36 ሺህ 400 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡት ግን ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በነበሩ ሁለት ቀናት ነበር፡፡

    አሪዞና፣ ካሊፎርኒያ፣ ሚሲሲፒ፣ ኔቫዳ፣ ቴክሳስ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እየተመዘገቡ ነው፡፡

    የጤና ባለሥልጣናትም ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚቀጥሉት ሳምንታት ወሳኝ ናቸው ብለዋል፡፡

    ማክሰኞ ዕለት የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ በደቡብና ምዕራባዊ ግዛቶች ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ እንደነበርና በማህበረሰቡ ውስጥ እንደተስፋፋ ተናግረው ነበር፡፡

    ከሁለት ቀናት በፊት በአንድ ቀን 30 ሺህ አዲስ በቫይረሱ ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡ "ይህም ለእኔ በጣም አስደንጋጭ ነው" ብለዋል፡፡

    በመሆኑም አሜሪካዊያንን አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም "ህዝብ ወደ ተሰበሰበባቸው ቦታዎች አትሂዱ፣ ከሄዳችሁ ደግሞ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋችሁን አረጋግጡ" ሲሉ አሳስበዋል፡፡

  6. አይኤምኤፍ የዓለም ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ከተነበየው የከፋ እንደሚሆን ገለፀ

    ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ፣አይ ኤም ኤፍ ቀደም ሲል ለዚህ ዓመትና ለሚቀጥለው ዓመት አስቀምጦት የነበረው የዓለም አኮኖሚ እድገት ከተነበየው የከፋ እንደሚሆን ገለፀ፡፡

    ተቋሙ በተያዘው ዓመት የዓለም ኢኮኖሚ 5 በመቶ እንደሚቀነስ የተነበየ ሲሆን ከ10 ሳምንታት በፊት ከተነበየው በእጅጉ የከፋ ነው፡፡

    የዩናይትድ ኪንግደም ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት ከ10 በመቶ በላይ እንደሚቀንስ የሚጠበቅ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ግን በግማሽ መሻሻል እንደሚያሳይ ተቋሙ አመልክቷል፡፡

    ይህም ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ውድቀት ቢሆንም ጣሊያን ፣ ፈረንሳይ ወይም ስፔን ይገጥማቸዋል ተብሎ ከሚታሰበው ጋር ሲወዳዳር ግን ያን ያህል የከፋ አይደለም፡፡

    የተቋሙ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጅቫ ሚያዚያ ወር ላይ የዩናይትድ ኪንግደም ኢኮኖሚ 6.5 በመቶ፤ በዓለም ደግሞ 3 በመቶ እንደሚቀነስ መተንበዩን በአዲሱ ትንበያቸው ላይ አስታውሰዋል፡፡

    ·ዩናይትድ ኪንግደም በዚህ ዓመት 10.2 በመቶ ሲያሽቆለቁል፤ በሚቀጥለው ዓመት በ6.3 በመቶ ያንሰራራል፡፡

    ·በአሜሪካ በዚህ ዓመት 8 በመቶ ሲቀንስ፤ በሚቀጥለው ዓመት በ4.8 በመቶ መሻሻል ያሳያል፡፡

    ·ጣሊያንና ስፔን ደግሞ በዚህ ዓመት ኢኮኖሚያቸው 12.8 በመቶ ሲቀንስ ፤ በሚቀጥለው ዓመት 6.3 በመቶ ያንሰራራል፡፡

    ·ሩሲያ በዚህ ዓመት 6.6 በመቶ ሲቀንስ በሚቀጥለው ዓመት በ4.1 በመቶ ይሻሻላል፡፡

    ·ቻይና በዚህ ዓመት በአንድ በመቶ ኢኮኖሚዋ ሲያድግ፤በሚቀጥለው ዓመትም 8.2 በመቶ ያድጋል፡፡

    ·ህንድ በዚህ ዓመት 4.5 በመቶ ሲቀንስ፤በሚቀጥለው ዓመት 6 በመቶ ይሻሻላል፡፡

    ·ብራዚል በዚህ ዓመት በ9.1 በመቶ ሲቀንስ፤በሚቀጥለው ዓመት በ3.6 በመቶ መሻሻል ያሳያል፡፡

  7. በኢትዮጵያ ተጨማሪ 186 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ

    ባለፉት ሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ በተደረገው 4034 የላብራቶሪ ምርመራ 186 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል። ይህንንም ተከትሎ በሃገሪቱ ውስጥ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 5034 ደርሷል።

    ከዚህም በተጨማሪ በዛሬው ዕለት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉንም የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል። ሃገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎችም ቁጥር 78 ደርሷል።

    በሌላ መልኩ በትናንትናው ዕለት ሰባ አራት 74 ሰዎች፤ 63 ከአዲስ አበባ፣ 6 ከትግራይ ክልል፣ 2 ከሶማሊ ክልል፣ 2 ከደ/ብ/ብ/ሕ ክልል፣ እና 1 ሐረሪ ክልል ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 1486 መሆኑንም መግለጫው አመላክቷል።

  8. በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር አሁንም እየጨመረ ያለው የት ነው ?

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ወደ 188 የዓለም አገራት የተዛመተ ሲሆን ከ9 ሚሊየን በላይ ሰዎችም በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ 500 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

    አንዳንድ አገራት የጣሏቸውን ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደቦች ተከትሎ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም በሌሎች አገራት ደግሞ ቁጥሩ አሁንም እየጨመረ ነው፡፡

    በላቲን አሜሪካ በግንቦት ወር አጋማሽ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት አሜሪካ የወረርሽኙ ማዕከል እንደምትሆን አስጠንቅቆ ነበር፡፡

    በአፍሪካ፣ እስያና መካከለኛው ምስራቅም አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡

    ብራዚል ማክሰኞ ዕለት ብቻ ከ39 ሺህ በላይ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን፤ ይህም ከዓለም አገራት ከ1 ሚሊየን በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡባትን አሜሪካን በመከተል በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል፡፡

    በቀጠናው ሜክሲኮ ክፉኛ በቫይረሱ የተጠቃች አገር ናት፡፡ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አሁንም እየጨመረ ነው፡፡

    እሁድ ዕለት ብቻ ከ15 ሺህ ሰዎች በላይ በቫይረሱ የተያዙባት ህንድም ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡

    በጎረቤቷ ፓኪስታንም በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ጭማሬ ያሳየ ቢሆንም ከቅርብ ቀናት ወዲህ ግን አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በመጠኑም ቢሆን ቀንሷል፡፡ በሁለቱ አገራት ያሉ የጤና አገልግሎት ሥርዓትም ተጨናንቋል፡፡

  9. 37 የኮሮናቫይረስ ታካሚዎች ከቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል አገግመው ወጡ

    በኮሮናቫይረስ ተይዘው በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ማዕከል ህክምናቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 37 ታካሚዎች አገግመው መውጣታቸውን ሆስፒታሉ በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።

    በቫይረሱ ተይዘው የመጡ ህሙማን ቁጥር በአጠቃላይ 178 መሆኑን ያስታወቀው ሆስፒታሉ በመጀመሪያው ዙር 44 ታካሚዎች አገግመው መውጣታቸውን ተከትሎ፤ በአጠቃላይ ከማዕከሉ አገግመው የወጡ ሰዎች ቁጥርም 81 ደርሷል።

    ከዚህም በተጨማሪ ሆስፒታሉ በፌስቡክ ገፁ ላይ እንዳሰፈረው የኮሮናቫይረስ ሊኖርባቸው ይችላል ተብለው የተጠረጠሩ 205 ግለሰቦች መካከልም 144ቱ ነፃ ተብለው ወደ ቤታቸው ተሸኝተዋል።

    በሃገሪቱ ውስጥ በቫይረሱ ከተያዙት 4 ሺህ 848 ሰዎች መካከል1 ሺህ 412 አገግመዋል።

  10. ኢትዮጵያ የሚገኙ ጋናውያን ተጫዋቾች "ወደ አገራችን መልሱ" እያሉ ነው

    ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የእግር ኳስ ክለቦች የሚጫወቱ ጋናውያን የአገራቸው መንግሥት ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል።

    ከእነዚህ መካከል በ2010 የዓለም ዋንጫ የጋና ቡድን አባል የነበረው ሊ አዲ እና ግብ ጠባቂ የነበረው ሙንታሪ ታጎ ይገኙበታል።

    ተጨዋቾቹ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የጋና ኤምባሲ በማቅናት መንግሥታቸው ወደ አገራቸው እንዲመልሳቸው መጠየቃቸውን ሶከርኢትዮጵያ ዘግቧል።

    ተጫዋቾቹ የሆቴልና የምግብ ወጪ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ኤምባሲው አካባቢ ሆነው የተቀረፁት ተንቀሳቃሽ ምስል ያሳያል።

    ሙንታሪ የጅማ አባጅፋር ግብ ጠባቂ ሲሆን፤ እርዳታ ሲማፀኑ ከነበሩት መካከል ሌላኛው ሪችሞንድ አዶንጎ ለድሬዳዋ ከነማ ይጫወታል።

    የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከወራት በፊት መቋረጡ ይታወሳል።

  11. የአውሮፓ ሕብረት ድንበሩን ለአሜሪካውያን ላለመክፈት እያቀደ ነው

    የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደሮች ስብሰባ ላይ ናቸው። የስብሳበው አጀንዳ ደግሞ ድንበሮቻቸውን በቀጣዩ የፈረንጆቹ ወር መባቻ መክፈት የሚለው ነው።

    ነገር ግን ከአሜሪካ ለሚመጡ ተጓዦች በራቸውን ላይከፍቱ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።

    በርካታ የአውሮፓ ሕብረት ሃገራት በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ድንበሮቻቸውን ለቱሪስቶች ለመክፈት በመዘጋጀት ላይ ናቸው። ወረርሽኙ ድጋሚ ሊስፋፋ ይችላል የሚል እምነት ያላቸው ሃገራት ደግሞ ውሳኔያቸውን በማጤን ላይ ይገኛሉ።

    27 አባል ሃገራት ያሉት ሕብረቱ ሌሎች ሃገራት ድንበር የሚከፈትላቸው የተቀመጠውን መመዘኛ ሲያሟሉ ነው ብለዋል።

    በኮሮናቫይረስ ተያዦችና ሟቾች ቁጥር ዓለምን እየመራች ያለችው አሜሪካ አሁን በርካታ ዜጎች በቫይረሱ እየተያዙባት እንደሆነ አሳውቃለች።

    ብራዚል፣ ሩስያና ሌሎች በርካታ የኮሮናቫይረስ ሪፖርት ያለባቸው ሃገራትም ወደ አውሮፓ ሕብረት እንዳይበሩ ሊለከሉ ይችላል ተብሏል።

  12. የላባቸውን ዋጋ ተነጥቀው ቤሩት ጎዳና ላይ የወደቁት ኢትዮጵያውያን

  13. የላይቤሪያው ሚኒስትር በኮሮና ሳቢያ ሆስፒታል ገቡ

    የላይቤሪያው ትምህርት ሚኒስትር በኮቪድ-19 ምክንያት ሆስፒታል መግባታቸው ተነገረ።

    የላይቤሪያ ትምህርት ሚኒስቴር በሚቀጥለው ሳምንት ትምህር ቤቶች እንዲከፈቱ ዝግጅት እያደረገ ባለበት ወቅት ሚኒስትሩ ሆስፒታል የገቡት።

    ሚኒስትር አንሱ ሶኒ ብቻ ሳይሆን ምክትላቸው ላቲም ዳ-ቶንግም ሆስፒታል ገብተዋል።

    ፍሮንት ፔጅ አፍሪካ የተሰኘው የላይቤሪያ ጋዜጣ ሚኒስትር ዴኤታው ሕመማቸው ሲፀና ወደ ጋና ሄደው እንዲታከሙ መደረጋቸውን ዘግቧል።

    የላይቤሪያ መረጃ ሚኒስትር ሌን ዩጂን ናግቤ ለጋዜጣው እንደተናገሩት ዴኤታው ጤናቸው ሰላም ነው። ዋና ሚኒስትሩም ወደ ጋና ለሕክምና ሄደዋል የሚባለው ውሸት ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

    ላይቤሪያ 652 ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው አረጋግጫለሁ ብላለች። 34 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል።

    በላይቤሪያ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና ይዘጋጁ ዘንድ በሚቀጥለው ሳምንት ትምህርት ይከፈታል ተብሎ ይጠበቃል።

  14. ናይጄሪያ ውስጥ የዱር እንስሳት ገበያው አሁንም እንደደራ ነው

    ምንም እንኳ የተባበሩት መንግሥታት የብዝሃነት ተወካይ የዱር እንስሳት ለምግብነት አይዋሉ ቢልም በናይጄሪያዋ የንግድ ከተማ ሌጎስ የዱር እንስሳት ገበያ አሁንም እንደደራ ነው።

    ኦሎዉ የተሰኘው የከተማዋ ታዋቂ የዱር እንስሳት ገበያ በየቀኑ የተለያዩ የዱር እንሳስት ስጋ ይቸበችችብበታል።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መነሻው የቻይናዋ ዉሃን ከተማ ከሚገኝ የዱር እንስሳት ገበያ ነው የሚል ጥርጣሬ ቢኖርም ናይጄሪያውያን የዱር እንስሳት ነጋዴዎች ግን ስጋው ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ይላሉ።

    ለገበያ ከቀረቡ የዱር እንስሳት መካከል በእንግሊዝኛው ኬን ራት [የዱር አይጦች]፣ እባብ፣ አጋዘን፣ አዞ ይገኙበታል።

    የናይጄሪያ መንግሥት ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በወሰዳቸው እርምጃዎች ሳቢያ ገበያችን ቀዝቅዟል ሲሉ ነጋዴዎቹ ምሬታቸውን ያሰማሉ።

    ናይጄሪያው ውስጥ የዱር እንስሳት ገበያዎች ቡሽሚት የሚል መጠሪያ አላቸው። በእነዚህ ገበያዎች የዱር እንስሳት ለበርካታ አሥርት ዓመታት እየሸጡ ኑሯቸውን የገፉ ነጋዴዎች ይገኛሉ።

    «የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከመምጣቱ በፊት በቀን 100 የተለያዩ እንስሳትን እንሸጥ ነበር። አሁን ግን 20 እንኳ ከሸጥን እሰየው ነው» ይላል ለ20 ዓመታት በዚህ ንግድ ኑሮውን የገፋው ላቱፋት ኦሎዉ።

    የሌጎስ ሃገረ ገዥ ቃል አቀባይ የሆኑ ግለሰብ ከተማዋ የዱር እንስሳት ንግድን ለማገድ ሃሳቡ የላትም ይላሉ።

  15. በመላው ዓለም በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር 477,000 ደረሰ

    በመላው ዓለም በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 9.2 ሲደርስ ከእነዚህ መካከል 477,000ዎቹ መሞታቸው ተገለፀ።

    የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በላቲን አሜሪካ ብቻ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 100 ሺህ ደርሷል።

    ከዚህ ሞት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው የተመዘገበው ብራዚል ውስጥ መሆኑን የዩኒቨርስቲው መረጃ ያሳያል።

    ሜክሲኮ 23 300 ዜጎቿን በኮሮና ምክንያት ስታጣ ፔሩ 8404 እንዲሁም ቺሊ 4505 ሰዎች ሞተዋል።

  16. አውስትራሊያ ከአንድ ወር በኋላ አንድ ሰው አጣች

    አውስትራሊያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ያጣቻቸው ሰዎች ቁጥር 103 ደርሷል። ቁጥሩ በአንድ የጨመረው የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ ሰው በኮቪድ-19 ሳቢያ ቪክቶሪያ ውስጥ መሞታቸውን ተከትሎ ነው።

    አውስትራሊያ በቫይረሱ ሳቢያ ሰው ሲሞትባት ከአንድ ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    በሜልቦርን ከተማ ቫይረሱ እንደ አዲስ ማንሰራራት አሳይቷል እየተባለ ነው።

    በከተማዋ ባሉ ስድስት መንደሮች አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተመዝግበዋል። እኒህ መንደሮች አብዛኛዎቹ ስደተኞች የሚኖሩባቸው ናቸው ተብሏል።

    አውስትራሊያ ውስጥ እንግሊዝኛ ለማይናገሩ የሃገሪቱ ነዋሪዎች ስለቫይረሱ በቂ መረጃ አልተሰጠም እየተባለ ነው። ባለሥልጣናት ግን ይህን አስተባብለዋል።

    ከትላንት ምሽት ጀምሮ ስምንት ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል ተብሏል። ነገር ግን ቁጥሩ ከዚህ በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ነው።

    የሜልቦርን ግዛት ሰዎች ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ወደ ሌሎች ግዛቶች እንዳይስፋፋ ለማድረግ እየሠራን ነው እያሉ ነው።

  17. ሞንጎሊያ በኮሮናቫይረስ ዘመን ምርጫ እያካሄደች ነው

    የሞንጎሊያ ዜጎች ወደ ምርጫ ጣብያዎች እየተመሙ ነው።

    ሞንጎሊያ ከደቡብ ኮሪያ በመቀጠል ሃገር አቀፍ ምርጫ ያካሄደች ሁለተኛዋ የዓለማችን ሃገር ሆናለች።

    ዜጎች ራሳቸው ከቫይረሱ እንዲጠብቁ የተለያዩ መመሪያዎችን ተላልፈዋል። ባለሙያዎች የሰውነት ሙቀት በመለካት፣ የምርጫ ጣብያዎችን ፀረቫይረስ በመርጨት፣ እና ለመራጮች የእጅ ጓንት በማደል ሥራ ተጠምደዋል።

    የሃገሪቱ አበይት ሁለት ፓርቲዎች ሥልጣን ለመቆናጠጥ እየተፋለሙ ነው። ፓርቲዎቹ በርካታ ሕዝብ መሰብሰብ የለበትም የሚለውን ሐሳብ ሲቃወሙ ነው የከረሙት።

    ገዢው የሞንጎሊያ ሕዝቦች ፓርቲ ሥልጣን ለተቀናቃኝ ፓርቲው አሳልፎ ላለመስጠት ይፋለማል።

    ገዢው ፓርቲ 76 መቀመጫዎች ያሉትን የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የተረከበው ከአራት ዓመታት በፊት ነበር።

    እስያዊቷ ዴሞክራሲያዊት ሃገር ሞንጎሊያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ጠበቅ ያለ እርምጃ ወስዳለች።

    እስካሁን 200 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ሲታወቅ በበሽታው ምክንያት የሞተ የለም።

    • ኮሮናቫይረስ በአሜሪካ በአስደንጋጭ ሁኔታ ሊያንሰራራ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል

    • የሜዳ ቴኒሱ ኮከብ ሰርቢያዊው ጆኮቪች በኮሮናቫይረስ ተያዘ

    • እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች!

      እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ከሆነ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ 9,240,398 በላይ ሆኗል። አሜሪካ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚዋ ስትሆን ብራዚል ደግሞ ትከተላለች።

      እስካሁን ድረስ በዓለማችን ላይ ከ 476,945 በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

      በአገራችን በኢትዮጵያም ቢሆን እስካሁን ድረስ በተደረጉ ምርመራዎች 4663 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

      ይህንን የቫይረሱን ስርጭት ለማስቆም እና በቁጥጥር ስር ለማዋል በሕክምና ባለሙያዎችና በመንግሥት የሚሰጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑ ይነገራል።

      እናንተም የቢቢሲ ቤተሰቦች አካላዊ ርቀታችሁን በመጠበቅ፣ አፍና አፍንጫችሁን በመሸፈን እንዲሁም እጃችሁን በተደጋጋሚ በሳሙና በመታጠብ ራሳችሁንና ወዳጆቻችሁን ከቫይረሱ ተከላከሉ።

      ከዚህ ሰአት ጀምሮ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተገናኙ የተለያዩ ዘገባዎችን ይዘንላችሁ እንቀርባለን።

      መልካም ቀን!