በኢትዮጵያ 91 ሰዎች ከኮቪድ-19 ሲያገግሙ 63 አዲስ ህሙማን ተገኙ

የኮሮናቫይረስ የማኅበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየገሰገሰ ባለባት ኢትዮጵያ ዛሬ 63 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በአገሪቱም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 4532 አድርሶታል፤ ከእነዚህም ውስጥ 1213 አገግመዋል። ተጨማሪ ሁለት ሰዎች የሞቱ ሲሆን የሟቾች ቁጥር 74 ደርሷል። እስከ ዛሬ [እሁድ] ድረስ የተከናወኑ የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራዎችም 216 ሺህ 328 ደርሷል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኬንያ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው በርካታ ታዳጊዎች አርግዘዋል

    ታዳጊ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመግታት ሲባል ከመጋቢት ወዲህ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ በርካታ ታዳጊዎች ማርገዛቸውን የኬንያ ባለሥልጣኖች ተናገሩ።

    የጤና ሚንስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ዘንድሮ በአንድ ግዛት ብቻ ወደ 4 ሺህ ታዳጊዎች አርግዘዋል። አብዛኞቹ ታዳጊዎች ዘመዶች ለዚህ ተጠያቂ መሆናቸው እንዳሳሰባቸውም ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።

    ያረገዙ ታዳጊዎች ትክክለኛ ቁጥር ሪፖርት ስለማይደረግ፤ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።

    በ47ቱም የኬንያ ግዛቶች ያሉ የፖለቲካ ኃላፊዎች መንግሥት ጉዳዩን እንዲመረምር ጠይቀዋል።

    ኬንያ በታዳጊዎች እርግዝና በዓለም ከሚጠቀሱ አገሮች አንዷ ናት። ከ1,000 ነፍሰ ጡር ሴቶች 82 ያህሉ ታዳጊዎች ናቸው።

  2. በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ4 ሺህ አለፈ

    ቢቢሲ

    ባለፉት 24 ሰዓታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተሰባሰቡ 4 ሺህ 809 ናሙናዎች ላይ በተደረገ ምርመራ 116 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ተገለጸ።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዛሬ ባወጡት ዕለታዊ የወረርሽኙ ሁኔታ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው በሽታው ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 40ው ሴቶች ሲሆኑ 76ቱ ወንዶች ናቸው።

    ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 102 ከአዲስ አበባ፣ 6 ከኦሮሚያ፣ 4 ከደቡብ፣ 1 ከጋምቤላ፣ 1 ከአማራ፣ 1 ከትግራይ፣ 1 ድሬዳዋ፣ 1 ከአፋርና ክልሎች ናቸው።

    ዕለታዊው መግለጫ ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ በፊት በወረርሽኙ መያዛቸው ተረጋግጦ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል ተጨማሪ 93 ሰዎች ከበሽታው በማገገማቸው እስካሁን በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርን 1027 አድርሶታል።

    በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥርም በ7 የጨመረ ሲሆን ስድስቱ በህክምና ላይ የነበሩ ሲሆንና ቀሪ አንዱ ደግሞ በአስከሬን ምርመራ የታወቀ ነው። በዚህም በአገሪቱ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 72 ደርሷል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን 207 ሺህ 023 ናሙናዎች ላይ ምርመራ በማድረግ በአጠቃላይ 4 ሺህ 070 ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች አግኝታለች።

  3. ዩናይትድ ኪንግደም ኪራይ መክፈል ላልቻሉ ነጋዴዎች ከለላ መስጠቷን አላቋርጥም አለች

    ዩኬ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ኪራይ መክፈል ላልቻሉ የንግድ ተቋማት ከለላ ማድረጉን እንደሚቀጥልበት አስታወቀ።

    ነጋዴዎቹ በመጪው ክረምት ከተከራዩበት መደብር እንዳይባበሩ ነው መንግሥት ከለላ የሚሰጠው።

    መንግሥት የመደብር፣ የመጠጥ ቤትና የምግብ ቤት ባለቤቶች ኪራይ እንዳይከፍሉ የሦስት ወር ከለላ ለመስጠት ውሳኔ ያስተላለፈው የካቲት ላይ ነበር።

    ከለላው ሰኔ 30 ያበቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በሦስት ወር ተራዝሟል።

    የአገሪቱ የመስተንግዶ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ኬት ኒኮልስ በውሳኔው መደሰታቸውን ገልጸዋል። ዘርፉ እንዲያገገም ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያሻም ተናግረዋል።

    ወረርሽኙ ጫና ያሳደረባቸው የመደብር አከራዮች እንዲሁም ተከራዮቻቸው የሚከተሉት አዲስ ደንብ በመንግሥት ይፋ ተደርጓል።

    ተከራዮች የኪራይ ገንዘብ ሙሉውን ወይም በቻሉት መጠን እንዲከፍሉ፤ አከራዮችም እንዲደግፏቸው ያበረታታል።

  4. ኮሮናቫይረስ ውሸት ነው ያሉ የሩሲያ ቄስ አንድ ገዳምን ተቆጣጠሩ

  5. ኢትዮጵያ ዴክሳሜታዞንን እንደ ድንገተኛ ህክምና ለመጠቀም ወሰነች

    ዴክሳሜታዞን

    የፎቶው ባለመብት, NURPHOTO

    ኢትዮጵያ ኦክስጂን ወይም የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው በጠና ለታመሙ የየኮሮናቫይረስ ህሙማን ዴክሳሜታዞንን ለመጠቀም መወሰኗን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ከሰሞኑ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ዴክሳሜታዞን በተባለው መድኃኒት ላይ በተደረገው ሙከራ በኮሮናቫይረስ በጽኑ ከታመሙ ሰዎች የአንድ ሦስተኛውን ሕይወት መታደግ እንደሚችል እና በወረርሽኙ ሰበብ ኦክስጂን በሚያስፈልጋቸው ሰዎች ላይ የሚያጋጥምን ሞት በአንድ አምስተኛ ሊቀንስ እንደቻለ ተነግሯል።

    ሚኒስቴሩ የዚህን ጥናትና ሪፖርት በዝርዝር እንደተመለከተው በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የገለጹት ጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የህክምና ጉዳዮች አማካሪ ቡድን እና የጤና ባለሙያዎች አማካሪ ምክር ቤትን በማማከር ዴክሳሜታዞን እንደ ድንገተኛ ህክምና ለመጠቀምም መወሰኑ አመልክተዋል።

  6. "ከየካቲት እስከ ሰኔ ድረስ በረራ በመከልከሉ 1 ቢሊዮን ዶላር አጥተናል"

  7. በኤርትራ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 142 ደረሰ

    አንዲት ሴትዮ ተቀምጠው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኤርትራ ትናንት 11 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ማግኘቷን ተከትሎ በአገሪቱ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 142 መድረሱን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

    መግለጫው አክሎም ሁሉም ቫይረሱ የተገኘባች ሰዎች በቅርቡ ከሱዳን የመጡ ናቸው ብሏል።

    በኤርትራ እስካሁን ድረስ 39 ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሲሆን 103 ደግሞ አስፈላጊውን ሕክምና እያገኙ መሆኑ ተገልጿል።

    ኤርትራ የምትዋሰናቸው አገራት የኮሮናቫይረስ ወርሽኝ ለመከላከል የእንቅስቃሴ ገደብ የጣሉ ቢሆንም ዜጎች ግን በባህርና በየብስ ተደብቀው ወደ አገሪቱ እንደሚገቡ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

  8. የኮቪድ--19 ክትባትና የዓለም ጤና ድርጅት ተስፋ

    ክትባት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዓለም ጤና ድርጅት በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮቪድ-19 ክትባቶች በጎርጎሳውያኑ ዓመት መጨረሻ ላይ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ህብረተሰቦች ይመረታሉ ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

    እስካሁን ድረስ ቫይረሱን ለመከላከልም ሆነ ለማዳን የሚረዳ አንድም ክትባት አለመኖሩ ይታወቃል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ተመራማሪ የሆኑት ሶዩመያ ስዋሚናታን በመላው ዓለም የሚገኙ ሳይንቲስቶች የኮሮናቫይረስ ክትባት ሊሆኑ የሚችሉ ከ200 በላይ ምርምሮች ላይ እየሰሩ ነው ብለዋል።

    በአሁን ሰዓት ከአስር በላይ የሚሆኑ ክትባቶች ደግሞ በሰው ላይ እየተሞከሩ ነው።

    ተመራማሪዋ " ተስፋ አለኝ፣ እንደሚሳካ ተስፋ አደርጋለሁ" ሰሉ ተናግረዋል።

    ሳይንቲስቷ አክለውም " ክትባት መስራት ወሰብሰብ ያለ ነገር አለው፤ ከበርካታ እርግጠኛ አለመሆን ጋር የሚመጣ ነው። በርካታ ክትባቶችን እየሞከርን ነው፤ አንዱ እንኳ ባይሳካ ወይንም ሁለተኛው ባይሆንልን ተስፋ መቁረጥ፣ እጅ መስጠት የለብንም" ብለዋል።

    እንዲሁም " እድለኞች ከሆንን፣ ከዚህ ዓመት መጨረሻ በፊት አንድ ወይንም ሁለት ክትባቶች ለምርጫ ይኖሩናል" ብለዋል።

    ክትባቱ ዝግጁ ቢሆንም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦች ሲሆኑ እነርሱም የሕክምና ባለሙያዎች፣ በእድሜ እና በሕመም ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ ግለሰቦች እስረኞች እና የአረጋውያን ተንከባካቢዎች ሊሆኑ እንሚችሉ ይጠበቃል።

  9. በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 202ሺህ 214 ናመናዎች ላይ የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጓል

    ምርመራ ሲደረግ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከ200ሺህ በላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች ተደርገዋል። ከእነዚህም ምርመራዎች ውስጥ 2ሺህ 953 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ከነዚህም መካከል አብዛኞቹ ሰዎች የሚገኙት የማህበረሰብ ስርጭት በከከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለባት አዲስ አበባ ውስጥ ነው። በኢትዮጵያ በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ከተረጋገጠው ሰዎች መካከል አንድ ሺህ ያህሉ መያዛቸው ሪፖርት የተደረገው ባለፉት ስድስት ቀናት ውስጥ ነው።

    ከሰኔ 6 እስከ ሰኔ 11 2012 ዓ.ም ድረስ ብቻ ማለት ነው።

    በዚህም የተነሳ ኮቪድ-19 በማህበረሰብ ውስጥ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑንና ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

    ስለዚህ ራስዎን እና የሚወዷቸውን ከኮሮናቫይረስ ለመጠበቅ በሕክምና ባለሙያዎችና በመንግሥት የሚነገሩ ምክሮችን ተግባራዊ ማድረግ በብርቱ አስፈላጊ መሆኑን የህብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች የዘወትር ማሳሰቢያ ነው።

  10. እንደምን አደራችሁ

    ያገገሙ ሰዎች ከሚሊኒየም አዳራሽ ሲወጡ

    የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Broadcasting Corporation

    የኮሮናቫይረስ ስጋት በቀጠለባት አለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ ማገገማቸው ተስፋን ሰንቋል።በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች አራት ሺህ መጠጋቱ በትናንትናው ዕለት ተገልጿል። ከነዚህም ውስጥ 934ቱ አገግመዋል።ከህመሙ ሙሉ ለሙሉ ለመዳን የተወሰኑ ወራት እንደሚወስድ የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።በርካቶች ያገገሙ ሰዎችም ድካሙ፣ የጡንቻ መዛሉ እንዲሁም በተወሰነ መልኩ ትንፋሽ መቆራረጥ እንዳጋጠማቸውም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።ከዚህም በተጨማሪ በበርካታ አፍሪካ ሃገራት ውስጥ ከህመሙ አገግመው ማህበረሰቡን የተቀላቀሉ ሰዎች መገለልና መድልዎ እየደረሰባቸው እንደሆነም እየተናገሩ ነው።በርካቶች እንደሚጠቋቁማቸውብና በፍራቻም እንደሚያዩዋቸው በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል።በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰብ፣ ወዳጅ፣ ዘመድ መፅናናትን እንዲሁም በጠና ለታመሙትም ከበሽታቸው ይፈውሳቸው ዘንድ እንመኛለን።ከኮሮና ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለማግኘት የቀጥታ ዘገባችንን ይከታተሉ