በኢትዮጵያ የአንድ ወር ጨቅላ ላይ የኮሮናቫይረስ ተገኘ

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 1257 ደርሷል። እስካሁን ድረስ በኮቪድ-19 ከተያዙት መካከልም 12 ሰዎች መሞታቸውንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። የወረርሽኙ ስርጭት በስፋት የሚታየው አዲስ አበባ ሲሆን በሌሎች ክልሎችም በአነስተኛ ቁጥር ይሁን እንጂ ተከስቷል። እስካሁን ድረስ በአገሪቱ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 209 ሰዎች ማገገም ችለዋል። ማንኛውም ሰው ራሱንም ሆነ ሌሎችን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መታደግ የሚችለው አካላዊ ርቀቱን ሲጠብቅ፣ እጁን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ ሲታጠብ እንዲሁም አፉንና አፍንጫውን ሲሸፍን መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በአፍሪካ ስላለው የኮሮናቫይረስ ዘገምተኛ አካሄድ ምን ማለት ይቻላል?

    የኮሮናቫይረስ ወረረሽኝ ከቻይናዋ ዉሃን ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ በመሻገር በርካቶችን አጥቅቷል፤ ህይወትም ነጥቋል።

    ወረርሸኙ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት መዛመት ሲጀምር 'አፍሪካውያን ሊያልቁ ነው' የሚሉ መላምቶች ተሰምተዋል። በሚያዝያ ወር ላይ ሜሊንዳ ጌትስ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የአፍሪካውያን አስከሬኖች በጎዳናዎች ላይ እንደሚረፈረፉም ታይቷቸው ነበር።

    በአህጉሪቷ ውስጥ እስካሁን ባለው መረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 125 ሺህ 640 ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 51 ሺህ 462ቱ አገግመዋል፤ 3 ሺህ 709 ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል።

    ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት አህጉር ቁጥሩ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ትንሽ ነው የተባለ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ ሌሎች የአህጉሪቷን ሁኔታ የሚተነብዩ ባለሙያዎች በአፍሪካ እንደተፈራው ላይሆን ይችላል እያሉ ነው።

  2. እንዴት አደራችሁ የቢቢሲ ወዳጆች?

    እንዴት አደራችሁ ውደ የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች?

    የቀጥታ ዘገባ ገጻችን ተጀምሯል። ወቅታዊ መረጃዎችን እናደርሳችኋላን።

    አብራችሁን ቆዩ።

    መልካም ቅዳሜ!

  3. የናይጄሪያ አየር ኃይል ተመራማሪዎች አዲስ ቬንትሌተር አስተዋወቁ

    በካዱና የሚገኘው የናይጄርያ አየር ኃይል የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዲስ ቬንትሌተር አስተዋወቀ። ቬንትሌተሩ ከኮሮናቫይረስ ጋር ለሚደረገው ፍልሚያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል።

    “ኮሮናቫይረስ ለያዛቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ሌላ የመተንፈሻ አካል በሽታ ላለባቸው ሰዎችም ይሆናል” ሲሉ ካፕቴን ኦሲቺናካ ኡባዲኬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ቬንትሌተሩ የተሠራው ከአገር ውስጥ ምርቶች መሆኑንም ገልጸዋል።

    በኮቪድ-19 ተይዘው መተንፈስ የተቸገሩ ሰዎች በቬንትሌተር ድጋፍ ነው አየር የሚያስገቡት። በሽታውን ለመዋጋትም ያግዛቸዋል።

  4. ስፔን ለድሀ ዜጎቿ በየወሩ 462 ዩሮ ልትሰጥ ነው

    የስፔን ግራ ዘመም መንግስት በአገሪቱ ለሚገኙ እጅግ ድሃ ለሚባሉ ቤተሰቦች በየወሩ 462 ዩሮ ለመስጠት የሚያስችለውን እቅድ አጽድቋል።

    አምስትና ከዛ በላይ ብዙ አባላት ያላቸው ቤተሰቦች ደግሞ እስከ 990 ዩሮ በየወሩ እንደሚያገኙ ተገልጿል።

    እቅዱ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከባድ ችግር ውስጥ የሚገኙ ስፔናውያንን እንደሚያግዝ ይገመታል።

    እስከ 850 ሺ የሚደርሱ ቤተሰቦች በዚህ እቅድ ለመካተት መስፈርቶቹን እንደሚያሟሉ የሚገመት ሲሆን ስፔን ውስጥ ከአንድ ዓመት በላይ የኖሩ ስደተኞችም ይካተታሉ።

    በዚህም መሰረት የስፔን መንግስት በዓመት 3 ቢሊየን ዩሮ የሚደርስ ገንዘብ እንደሚያስወጣው ተገምቷል።

    "በወረርሽኙ ምክንያት የተቸገሩ ቤተሰቦችን ወደተሻለ የማህበረሰብ ክፍል እንዲቀላቀሉ ማድረግ ከቻልን ተሳክቶልናል ማለት ነው’’ ብለዋል የማሕበራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ጆሴ ሉዊስ ኢስክሪቫ።

  5. ግሪክ ከዩኬ፣ ስፔን፣ ጣልያን እና ፈረንሳይ ውጪ ቱሪስቶችን ልትቀበል ነው

    ግሪክ ከሰኔ 15 በኋላ ከ29 አገሮች ጎብኚዎች በመቀበል የቱሪዝም ዘርፏ እንዲያንሰራራ ልታደርግ ነው።

    ሆኖም ግን በወረርሽኙ ክፉኛ ከተጠቁት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጣልያን፣ ስፔን እና ፈረንሳይ ቱሪስቶች እንደማትቀበል አስታውቃለች።

    ግሪክ እንቅስቃሴ ላይ ጥብቅ ገደብ የጣለችው በሽታው መሰራጨት ሲጀምር ነበር። ይህም በወረርሽኙ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ረድቷል።

    የእንቅስቃሴ ገደቡ መላላቱን ተከትሎ፤ ለአገሪቱ ቁልፍ የምጣኔ ኃብት ምንጭ ለሆነው የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል።

  6. የናይጄሪያ ሆስፒታሎች በኮቪድ-19 ስጋት ሌላ ህመም ያለባቸውን እያስተናገዱ አይደለም

    በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ከሚሞቱ ሰዎች ይልቅ ሌላ ህመም ያለባቸው ሰዎች እየሞቱ መሆኑን የናይጄሪያ ጸረ- ኪቪድ-19 ግብረ ኃይል አስታወቀ።

    ሰዎቹ ሕይወታቸውን እያጡ ያሉት የህክምና አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ነው ተብሏል።

    የግብረ ኃይሉ ኃላፊ ቦስ ሙስጠፋ ለመገናኛ ብዙሀን እንደተናገሩት፤ የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎችም በኮቪድ-19 ስጋት ሳቢያ ሌላ ህመም ያለባቸው ሰዎችን አንቀበልም ማለታቸው አሳዛኝና ተቀባይነት የሌለው ነው።

    “ከኮቪድ-19 ውጪ ላሉ ህመሞች የሚሰጠው ትኩረት እየቀነሰ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። እውነቱን ለመናገር፤ ለሌሎች ህመሞች ህክምና እየተደረገ ባለመሆኑ ከኮቪድ-19 በባሰ በሌሎች በሽታዎች ሳቢያ ሰዎች እየሞቱ ነው” ብለዋል።

    ኃላፊው በቂ ህክምና ባለማግኘት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ አልተናገሩም።

    አንዳንድ ሆስፒታሎች በቂ የሀኪም መገልገያ (ፒፒኢ) የለም ብለው ሥራ አቁመዋል። የሀኪሞች ማኅበርም፤ የኮቪድ-19 ምልክት ያለባቸውን ህሙማን ያለ ህክምና መገልገያ አታክሙ ሲል አባላቱን መክሯል።

    ኮሮናቫይረስ ሊኖርባቸው ይችላል በሚል አንዳንድ ህሙማንን ሆስፒታሎች አንቀበልም ማለታቸው ሪፖርት ተደርጎ ነበር።

    በናይጄሪያ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች 9,000 ናቸው። ባለሙያዎች እንደሚሉት ደግሞ ሰፊ ምርመራ ቢደረግ የህሙማን ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል።

  7. “የናሙና ውጤት በፍጥነት አለመታወቁ ሥራችንን አጓቶታል”

    የደቡብ አፍሪካ ሀኪሞች የናሙናዎች ውጤት በሚፈለገው ፍጥነት እየደረሰ አይደለም አሉ። ይህም የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት እያጓተተው መሆኑን ገልጸዋል።

    በቂ መሣሪያ ባለመኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ናሙናዎች ውጤታቸው ሳይታወቅ ከሳምንት በላይ ቆይተዋል።

    ሀኪሞቹ እንዳሉት፤ ከረዥም ጊዜ በፊት የተወሰዱ ናሙናዎች ውጤታቸው ቢታወቅም ዋጋ ቢስ ስለሆነ፤ ናሙናዎቹን ማስወገድ ይሻላል።

    ከተወሰዱ ናሙናዎች መካከል ኮቪድ-19 ያለባቸው ቢኖሩም እንኳን እስካሁን በሽታውን ወደሌሎች ሰዎች አስተላልፈዋል።

    አዳዲስ ናሙና ከሆስፒታሎች፣ ከአረጋውያንና ሌሎችም ለበሽታው ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች ተወስዶ ምርመራ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

    ደቡብ አፍሪካ የበሽታውን ሥርጭት በመቆጣጠር ረግድ በመጠኑም ቢሆን ውጤታማ ብትሆንም፤ የናሙና ውጤት መዘግየት ነገሮችን እያጓተተ ነው።

    አሁን ላይ የበሽታው ሥርጭት እጅግ እየተስፋፋ ነው። የኬፕ ታውን ሆስፒታሎች ከአቅማቸው በላይ ታማሚ ሊገጥማቸው እንደሚችልም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

  8. የፈረንሳዩ መኪና አምራች 15 ሺ ሠራተኞችን ሊቀንስ ነው

    ታዋቂው የፈረንሳይ መኪና አምራች ድርጅት ሬኖ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ባጋጠመው ከፍተኛ የሽያጭ መቀነስ ሳቢያ በመላው ዓለም የሚገኙ 15 ሺ ሠራተኞቹን እንደሚቀንስ አስታውቋል።

    በዚህ ውሳኔም ድርጅቱ እስከ 1.8 ቢሊየን ፓውንድ የሚደርስ ወጪ መቀነስ እንዳሰበ ተገልጿል።

    "እቅዱ አስፈላጊ ነው’’ ብለዋል የድርጅቱ ጊዜያዊ ኃላፊ ክሎቲልድ ዴልቦስ።

    ፈረንሳይ ውስጥ የሚገኙ 6 ሺ የድርጅቱ ሠራተኞችም የሚቀነሱ ሲሆን ሌሎች ስድስት ማምረቻዎች ላይ ደግሞ የክለሳ ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል።

    የፈረንሳይ መንግስት ከዚህ መኪና አምራች ድርጅት 15 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን 8 ቢሊየን ዩሮ ለማበደር ድርድር ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።

    ድርጅቱ በዓመት 4 ሚሊየን መኪናዎችን ያመርት የነበረ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2024 ደግሞ ቁጥሩን ቀንሶ ወደ 3.3 ሚሊየን ዝቅ የማድረግ እቅድ አለው።

    በዛውም የቤተሰብ መኪናዎችና የኤሌክትሪክ መኪናዎች ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ ተገልጿል።

  9. የስፔን ላሊጋ ሰኔ አራት ይጀመራል

    የስፔን ላሊጋ የፊታችን ሰኔ 4 ሪያል ቤቲስ እና ሲቪያ በሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚጀመር እና የሚቀጥለው ዓመት ውድድር ደግሞ መስከረም ላይ እንደሚጀመር የሊጉ ፕሬዝዳንት ሃቪዬር ቴባስ ገልጸዋል።

    ባለፈው ሰኞ ፕሬዝዳንቱ የስፔን ላሊጋ ሪያል ቤቲስ እና ሲቪያ በዝግ ስቴድየም በሚያደርጉት ጨዋታ ሊጀመር እንደሚችል አስታውቀው ነበር።

    "እኛ ተዘጋጅተናል፤ ዋናው ነገር የሊጉን ውድድሮች የምንጨርስበት ቀን ነው’’ ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ከስፔኑ ማርካ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ።

    ፕሬዝዳንቱ አክለውም ተመልካቾች የፈለጉትን አይነት ድምጽ መርጠው ጨዋታዎቹን መከታተል የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱንም ገልጸዋል።

    "ደጋፊዎች እቤታቸው ሆነው ጨዋታዎቹን ሲከታተሉ ከፈለጉ ጸጥ ያለ ስቴድየሙን ድባብ አልያም ደግሞ ተቀድቶ የተዘጋጀ የተመልካቾች ድምጽ እየሰሙ መከታተል ይችላሉ።‘’

  10. በሩስያ በአንድ ቀን ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር ተመዘገበ

    በሩስያ በአንድ ቀን 232 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። ይህም በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 4,374 አድርሶታል።

    ባለሥልጣኖች እንዳሉት፤ 8,572 አዲስ የኮሮናቫይረስ ኬዞች ተመዝግበዋል። በአገሪቱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 387,623 ደርሷል።

    ይህም ሩስያን ከአሜሪካና ከብራዚል በኋላ በበሽታው በርካታ ሰዎች የሞቱባት አገር አድርጓታል።

  11. በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች 968 ደረሱ

    በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከተገኙት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች አሃዝ ከፍተኛው መመዝገቡን የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት አስታወቀ።

    ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ 5015 የላብራቶሪ ምርመራ 137 ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው 20ዎቹ ናቸው።

    ስምንት ሰዎች በሽታው ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሲሆን፤ የተቀሩት 109 ሰዎች የውጪ አገር የጉዞ ታሪክም ሆነ በሽታው ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ የሌላቸው ናቸው።

    መግለጫው ጨምሮም ከዚህ በፊት በቫይረሱ ተይዘው በለይቶ ማከሚያ ውስጥ ክትትል ላይ ከነበሩ ሰዎች መካከል ስድስት ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸው ተገልጿል።

    በተጓዳኝ ህመም ምክንያት ህክምና ላይ የነበሩ የ62 ዓመት ሰው የኮሮናቫይረስ ምርመራ ቢደረግላቸውም፤ ውጤቱ ሳይደርስ ሕይወታቸው እንዳለፈ ተገልጿል።

    ግለሰቡ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ በመረጋገጡ በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ስምንት አድርሶታል።

    በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በበሽታው የተያዙ ሰዎች 968 ሲሆኑ፤ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 197 ደርሷል።

  12. የዶናልድ ትራምፕን ምክር ተከትሎ ሳሙና የዋጠው አሜሪካዊ

  13. ዶናልድ ትራምፕ ለማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰጠውን ከለላ አነሱ

  14. የአውሮፓ ሃገራት እንዴት ዋሉ?

    ሩሲያ በሃያ አራት ሰአት ውስጥ ከፍተኛ የተባለውን፣ 232 ሟቾችን መዝግባለች። በሃገሪቱም በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎችን 4ሺህ 374 አድርሶታል።

    በቫይረሱ የተያዙ ተጨማሪ 8ሺህ 572 ያገኘች ሲሆን፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ቁጥር ጣራ ደርሷል ተብሏል። ሩሲያ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚ ብትሆንም የሟቾች ቁጥር ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። ከዚህም ጋር የተያያዘ ዘገባችንን ለማንበብ በሩሲያ 380ሺ ሰዎች በኮሮና ተይዘው ሟቾች እንዴት 4ሺ ብቻ ሆኑ?

    ኦስትሪያ በቤትም ሆነ ከቤት ውጭ ዋና የተፈቀደ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ እስከ 100 ሰዎች ያሉበት የሰርግ ስነ ስርአትም ማካሄድ ይቻላል ተብሏል። በኮሮናቫይረስ 645 ዜጎቿን ያጣችው ኦስትሪያ የተለያዩ መመሪያዎቿን በማላላትም የከተሞቿን እንቅስቃሴ ለመመለስ ጥረት እያደረገች ነው።

    በኔዘርላንድ የሚገኝ የስጋ ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ ወረርሽኙ የተነሳ ሲሆን ከ130 ሰራተኞቹ መካከልም 21ዱ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተጠቃችው ስፔን በተለያዩ ዙሮች መመሪያዎቿን እያላላች ሲሆን፤ ከሰኞ ጀምሮም ሁለተኛው ዙር ይጀመራል። በዚህም መሰረት ሲኒማና ቲያትር ቤቶች፣ የሙዚቃ አዳራሾች እንዲሁም የመገበያያ መደብሮችም በተወሰነ መልኩ ይከፈታሉ ተብሏል።

    ክሮሺያ ድንበሯን ለአስር የአውሮፓ ህብረት አባላት ክፍት እንደምታደርግም አስታውቃለች።

    • ክትባት እንዴት ሊሰራ ይችላል?

    • ዓለም ለአዲስ ወረርሽኝ መዘጋጀት አለባት-የዓለም ጤና ድርጅት

      ኮሮናቫይረስ "ገና ጥሎን አልሄደም"፤ የሰዎች እንቅስቃሴ በጨመረ ቁጥር "አዲስ ወረርሽኝ ሊከሰት ስለሚችል መዘጋጀት አለብን" ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ናቸው።

      ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ ለቢቢሲ ሬዲዩ 4 ቱዴይ ፕሮግራም እንደተናገሩት የእንቅስቃሴ ገደብ በተነሳ ወቅት ሰዎች በተቻላቸው አቅም አካለዊ ርቀታቸውን መጠበቅ እንዲሁም ከታመሙ ወዲያውኑ ራሳቸውን ለይተው መቀመጥ አለባቸው ብለዋል።

    • ቱርክ የወረርሽኙን መዛመት እንዴት ልትቆጣጠረው ቻለች?

      የኮሮናቫይረስ በቱርክ ከሌሎች ሃገር ዘግየት ብሎ መጋቢት 2፣ 2012 ዓ.ም ነው የተመዘገበው። ሆኖም በአንድ ወር ውስጥ መላው ሃገሪቷን አዳረሳት። በ81 ግዛቶቿም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ተገኙ።

      በአለም ላይ በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቁት እንደ እንግሊዝ ሃገራት ካሉትም ቀድማ በቫይረሱ ከፍተኛ ጫና ደርሶባት ነበር።

      የሟቾችም ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል፤ እንዲሁም በወቅቱ ብዙ ዜጎች እንደተቀጠፉባት ሁለተኛ ጣልያን ትሆናለች የሚሉ ግምቶችም ነበሩ።

      ከሶስት ወራት በኋላ ግን በቱርክ የተፈራው አልደረሰም። ምንም እንኳን የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች ቢገደቡም፤ እንደሌሎች ሃገራት ሙሉ በሙሉም አልተዘጋችም።

      ሃገሪቱ የኮሮናቫይረስ በቀላሉ ሊዛመትባቸው ይችላል ያለቻቸውን ሬስቶራንቶች፣ የገበያ ቦታዎች እንዲሁም በመስጊዶች ሰብሰብ ብሎ መፀለይን አግዳ ነበር።

      ከዚህም በተጨማሪ ከህሙማኑ ጋር ንክኪ አላቸውን ተብለው የተጠረጠሩትን ጥብቅ ክትትል ማድረግ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ በርካቶችን መመርመር የጀመረች ሲሆን የላብራቶሪ ውጤቱም በሰአታት ውስጥ እንዲደርስ መንገዶችን አመቻቸች። በርካታ የለይቶ ማቆያ ማዕከላትን መገንባት እንዲሁም በጠና ለታመሙት ሃይድሮክሲክሎሮኪን እንዲሰጥ አዛለች።

      በሃገሪቱ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥርም 4ሺህ 397 ነው። አንዳንድ ዶክተሮች ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችል አስተያየታቸውን ቢሰጡም 83 ሚሊዮን ህዝብ ላላትና በኮሮና ከፍተኛ ጫና ደርሶባት ለነበረ ሃገር ቁጥሩ ትንሽ ነው ተብሏል።

    • አሜሪካ ለናይጄሪያ ቃል የገባችው ቬንትሌተር አልላከችም

      የናይጄሪያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቃል የተገባውን ቬንትሌተር እስካሁን ድረስ አለመቀበላቸውን ገለፁ።

      ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ለምዕራብ አፍሪካ አገራት 1000 ቬንትሌተር መላኩን ቢገልፁም ላይ መሐመድ ግን እንዳልደረሳቸው አስታውቀዋል።

      አክለውም የቬንትሌተሮቹ እርዳታ ከደረሰ ለሕዝብ በይፋ እንደሚገለፅ አስታውቀዋል።

      ፕሬዝዳንት ትራምፕ የዛሬ ወር ከናይጄሪያው አቻቸው ሙሐመዱ ቡሃሪ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ነበር ቬንትሌተሮቹን ለመላክ ቃል የገቡት።

      በወቅቱ ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ ናይጄሪያ የኮቪድ-19 ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ቁርጠኛ ነች ብለው ነበር።

      ባለፈው ሳምንት በሚቺጋን የሚገኘውን የፎርድ ሞተር ፋብሪካ በጎበኙበት ወቅት አሜሪካ ለናይጄሪያ 1000 ቬንትሌተር መላኳን ተናግረው ነበር።

      ናይጄሪያ እስካሁን ድረስ 8915 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን በምርመራ ስታረጋግጥ ከእነዚህም መካከል 259 ሰዎች ሞተዋል።

    • በደቡብ ኮሪያ ወረርሽኙ አገርሽቷል ተባለ

      በደቡብ ኮሪያዋ መዲና ሴውል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኙ ማገርሸቱን ተከትሎ ወደ ቀውስነት ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል ያላቸውን ስጋት የጤና ባለሙያዎች አስታውቀዋል።

      በባለፉት ሃያ አራት ሰአታት ውስጥ 79 አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ ይህም ቁጥር በአገሪቱ በሁለት ወራት ውስጥ ከተያዙት መካከል ከፍተኛ ነው ተብሏል።

      በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎችም መነሻ ነው የተባለው በሃገሪቷ ምዕራብ ግዛት የሚገኝ ቡቸን የተባለ ትልቅ የዕቃዎች ማከፋፈያ ማዕክል ነው። በማዕከሉ ውስጥ የሚሰሩ በርካታ ሰራተኞች ጫማና አልባሳትም ላይ የኮሮናቫይረስ ተገኝቷል ተብሏል።

      የጤና ባለሙያዎችም አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ካላቸው አካባቢዎች አቅራቢያ መገኘታቸው ስጋትን ፈጥሯባቸዋል።

    • ቢቢሲ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ሊያስተላልፍ ነው

      የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዳግም ሲጀምር አራት ጨዋታዎችን ቢቢሲ ስፖርት በነፃ እንዲያስተላልፍ ፈቃድ አገኘ።

      ቢቢሲ የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታዎች እንዲያስተላልፍ ፈቃድ ሲያገኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

      ሐሙስ እለት ይፋ እንደተደረገው ከሆነ ምንም እንኳ የመንግሥት ፈቃድ እየተጠበቀ ቢሆንም ጨዋታው ሰኔ 10 2012 ዓ.ም እንደሚጀመር ተገልጿል።

      " ይህ እድል ለቢቢሲና ለተመልካቾቹ ትልቅ እድልን ይፈጥራል"ያለችው የቢቢሲ ስፖርት ዳይሬክተር ባርባራ ስላተር ናት።

      የመጀመሪያው ጨዋታ በአስቶን ቪላ እና በሼፊልድ ዩናይትድ ፣ ማንቸስተር ሲቲ ከአርሴናል ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል።