በኢትዮጵያ የአንድ ወር ጨቅላ ላይ የኮሮናቫይረስ ተገኘ

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 1257 ደርሷል። እስካሁን ድረስ በኮቪድ-19 ከተያዙት መካከልም 12 ሰዎች መሞታቸውንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። የወረርሽኙ ስርጭት በስፋት የሚታየው አዲስ አበባ ሲሆን በሌሎች ክልሎችም በአነስተኛ ቁጥር ይሁን እንጂ ተከስቷል። እስካሁን ድረስ በአገሪቱ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 209 ሰዎች ማገገም ችለዋል። ማንኛውም ሰው ራሱንም ሆነ ሌሎችን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መታደግ የሚችለው አካላዊ ርቀቱን ሲጠብቅ፣ እጁን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ ሲታጠብ እንዲሁም አፉንና አፍንጫውን ሲሸፍን መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ላስ ቬጋስ ስፖርታዊ ውድድሮችን ማስተናገድ ጀመረች

    በላስ ቬጋስ ስፖርታዊ ውድድሮች መመለስ ጀምረዋል። የብራዚሉ ጊልበርት በርንስ የቀድሞው የአሜሪካ ‘ዌልተርዌይት’ ሻምፒዮኑ ታይሮን ዉድሊን ባሸነፈበት የዩኤፍሲ ግጥሚያ ደግሞ የመጀመሪያው ሆኗል።

    በፍሎሪዳ በቀጥታ በተላለፈው ጨዋታ ምንም አይነት ተመልካች በግጥሚያው ቦታ ያልነበረ ሲሆን አካላዊ ርቀትን በጠበቀ ሁኔታ ውድድሩ መስተናገዱ ተገልጿል።

    የነቫዳ ግዛት አትሌቲክ ኮሚሽን ባሳለፍነው ሳምንት ነበር የፍልሚያ ውድድሮች በላስ ቬጋስ መካሄድ እንዲጀምሩ የፈቀደው።

    የቦክስ ውድድር አዘጋጁ ቶፕ ራንክ ደግሞ ሰኔ ሁለት በሻኩር ስቲቨንሰን እና ፌሊክስ ካራባሎ መካከል የሚካሄድ ሌላ ፍልሚያን ሲያስተዋውቅ ነበር።

  2. ሩዋንዳ በኮሮናቫይረስ የመጀመሪያ ሞት መዘገበች

    ሩዋንዳ በኮሮናቫይረስ የመጀመሪያ ሞት መመዝገቧን የሃገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቀዋል።

    ግለሰቡ የስልሳ አምስት ዓመት አሽከርካሪ ሲሆኑ በጎረቤት ሃገር ይኖሩም ነበር ተብሏል።

    በጠና ሲታመሙ ወደ ሃገራቸው የተመለሱ ሲሆን ከመተንፈሻ ችግሮች መወሳሳብ ጋር በተያያዘ ወደ ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ተወስደውም ህክምና ሲደረግላቸው ነበር።

    የኮሮናቫይረስ መዛመትን ለመግታት ጥሩ እመርታ አሳይተዋል ከሚባሉት አገራት አንዷ የሆነችው ሩዋንዳ 359 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች።

  3. የኢየሩሳሌሙ አል-አቅሳ መስጂድ ተከፈተ

    ኢየሩሳሌም ውስጥ የሚገኘው የአል-አቅሳ መስጂድ በኮሮናናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ለሁለት ወራት ከተዘጋ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምዕመናን ክፍት ተደረገ።

    የአል-አቅሳ መስጂድ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ከሚገኙት የመካ እና የመዲና ቅዱስ ቦታዎች ቀጥሎ ሦስተኛው የእስልምና ቅዱስ ስፍራ ነው።

    መስጂዱ ሲከፈት በመቶዎች የሚቆጠሩና የአፍና የአፍነጫ መሸፈኛ ጭምብል ያደረጉ ምዕመናን ተሰብስበው “አላህ ወ አክበር” እያሉና መሬቱን እየሳሙ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

    የመስጂዱ ኃላፊ ኦማር አል-ኪስዋኒ ለምዕመናኑ ተቀብለው መስጂዱ ዝግ በነበረበት ሁለት ወር ያህል በትዕግስት መጠበቃቸውን ገልጸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

  4. ሳይንቲስቶች በዩኬ የእንቅስቃሴ ገደቡን ማላላት አደጋ አለው እያሉ ነው

    የዩኬ የሳይንስ አማካሪ ባለሙያዎች መንግሥት የእንቅስቃሴ ገደቡ ላይ እያሳየ ያለው የማላላት ሂደት ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅዋል።

    ፕሮፌሰር ጆን ኤድመንድስ እንዳሉት ገደቡን የማላላቱ ውሳኔ ፖለቲካዊ እርምጃ ነው ያሉ ሲሆን ሰር ጄርሚ ፋራር ደግሞ የብሄራዊ ጤና አገልግሎቱ ታማሚዎችን የማፈላለግ ስርአት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ አለበት ብለዋል።

    ከሰኞ ጀምሮ ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ፤ እንግሊዝ ውስጥ እስከ ስድስት የሚደርሱ ሰዎች መሰብሰብ ይችላሉ የተባለ ሲሆን በሌሎች አገራት ደግሞ ቀስ በቀስ ገደቦቹ መላላት ይጀምራሉ።

    መንግሥት በበኩሉ ውሳኔውን ያሳለፈው መረጃና ጥናት ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ገልጿል።

    በመላው ዩኬ ተጨማሪ 215 ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን አጠቃላይ የሟቾችን ቁጥር 38 ሺ 376 አድርሶታል።

    ባለሙያዎቹ እንደሚሉት በእንግሊዝ ብቻ በየቀኑ 8 ሺ ሰዎች በቫይረሱ ይያዛሉ፤ እንዲህ አይነት ከፍተኛ ቁጥር እየተመዘገበ ደግሞ ገደቡን ማላላት ስጋት አለው ብለዋል።

  5. ሕንድ ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ብትመዘግብም የእንቅስቃሴ ገደቡን ለማላላት ወስናለች

    በሕንድ ምንም እንኳን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ ቢሆንም በእንቅስቃሴ ላይ ጥላ የነበረውን ገደብ ማላላቷን እንደምትቀጥል አስታውቃለች።

    ከሰኔ 1 ጀምሮ ሬስቶራንቶች፣ ሆቴሎች፣ የገበያ ማዕከላትና የአምልኮ ቦታዎች ክፍት ይሆናሉ ተብሏል። በሶስት ደረጃዎች በተከፋፈለው ገደቡን የማላላት ሂደት መሰረት ይሄኛው የመጀመሪያው ደረጃ እንደሆነም ተገልጿል።

    ከሳምንታት በኋላ ደግሞ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች መከፈት ይጀምራሉ። ነገር ግን ከፍተኛ የኮቪድ-19 ህሙማን በተገኙባቸው አካባቢዎች አሁንም ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ይጠብቃቸዋል።

    ይህ እቅድ ሕንድ በንድ ቀን ውስጥ ብቻ 8000 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ካገኘች በኋላ መሆኑ ደግሞ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።

    በአገሪቱ በአጠቃላይ 174 ሺ 500 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል።

    መንግስት እንዳስታወቀው ከሁለት ወራት በፊት ተግባራዊ የተደረገው እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ የመደገብ ውሳኔ ከ37 ሺ እስከ 78 ሺ የሚደርሱ ሰዎችን ከመሞት አድኗል።

    ነገር ግን ገደቡን ከዚህ በላይ ማቆየቱ 1.3 ቢሊዮን ህዝብ ላላት አገር ኢኮኖሚ" ከምናስበው በላይ ጎጂ ነው" ብሏል መንግስት በመግለጫው።

  6. በኮሮናቫይረስ ምክንያት በማያቋርጥ የጫጉላ ሽርሽር ላይ ያሉት ሙሽሮች

  7. ሐኪሞችን ግራ ያጋባው የኮሮናቫይረስ ወረርሽንና የሚያስከትለው ጉዳት

  8. እንደምን አደራችሁ?

    ኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ፤ በትናንትናው እለት ከአንድ ሺህ ተሻግሯል።

    በትናንትናው ዕለት 95 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በአብዛኛዎቹም የተገኙት የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረባት ባለችው አዲስ አበባ መሆኑንም የጤና ሚኒስቴር እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሚሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል።

    በሃገሪቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል ከ700 በላይ የሚገኙት አዲስ አበባ ነው።

    ከሰሞኑም የውጪ ሃገር ጉዞም ሆነ ከህሙማን ጋር የታወቀ ንክኪ የሌላቸው ሰዎች በበሽታው እየጨመረ መገኘት በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው ስርጭት እየጨመረ ለመሆኑ አመላካች ነው ተብሏል።

    ኢትዮጵያ የመመርመር አቅሟን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ከመቶዎች በቀን ወደ አምስት ሺህ መመርመር ያሳደገች ሲሆን፤ እስካሁንም 106 ሺህ 615 የላብራቶሪ ምርመራዎች ተደርገዋል።

    በአጠቃላይ በሃገሪቷ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1063 የደረሰ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ 208 አገግመዋል። ሃገሪቷ ሰባት ዜጎቿን በኮሮና አጥታለች፤ አምስት ሰዎችም በፀና መታመማቸው ተገልጿል።

    ቢቢሲ አማርኛ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች መፅናናትን እንዲሁም በፀና ለታመሙትም እንዲያገግሙ ምኞታችንን እንገልፃለን። ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለማግኘት የቀጥታ ዘገባችንን ይከታተሉ መልካም የእሁድ ቀን እንዲሆንላቸሁ ተመኘን

  9. “ዩኬ የዓለም ጤና ድርጅትን መደገፍ የማቆም እቅድ የላትም”

    አሜሪካ ከድርጅቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ብታቋርጥም፤ ዩናይትድ ኪንግደም ለዓለም ጤና ድርጅት የምታደርገውን ድጋፍ የማቋረጥ እቅድ እንደሌላት አስታወቀች።

    የጤናና ማሕበራዊ እንክብካቤ ክፍል ቃል አቀባይ እንዳሉት፤ ኮሮናቫይረስ የመላው ዓለም ትግል ነው። “ድርጅቱ ዓለም አቀፉ የጤና ዘርፍ የሚሰጠውን ምላሽ በመምራት ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው” ብለዋል።

    ቃል አቀባዩ አያይዘውም፤ “የምናደርገውን የገንዘብ ድጋፍ የማቋረጥ እቅድ የለንም” ብለዋል።

  10. የአሜሪካ ምክር ቤት የትራምፕ ውሳኔ የክትባት ምርምን ያደናቅፋል አለ

    የአሜሪካ ምክር ቤት የጤና ኮሚቴ ኃላፊ፤ ዶናልድ ትራምፕ ከዓለም ጤና ድርጅት አሜሪካን ማግለላቸው የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ያደናቅፋል ሲሉ አስጠነቀቁ።

    የሪፐብሊካኑ ሴናተር ለማር አሌክሳንደር፤ የፕሬዘዳንቱ ውሳኔ ቫይረሶች አሜሪካ እንዳይገቡ ከሌሎች አገራት ጋር የሚደረገውን ትብብር ከባድ ያደርገዋል ብለዋል።

    “የዓለም ጤና ድርጀት ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የሠራቸው ስህተቶች ካሉ መፈተሽ ተገቢ ነው። ነገር ግን ያ መደረግ ያለበት ወረርሽኙ ካለፈ በኋላ ነው እንጂ በቀውሱ መካከል አይደለም።”

    የአሜሪካ የጤና ባለሙያዎች ኃላፊ፤ ፓትሪስ ሀሪስ፤ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ግንኙነት ማቋረጥ “ውጤት አልባ ነው። ከዚህ የጤና ቀውስ ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ያከብደዋል” ብለዋል።

  11. ሰበር, በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ከ1 ሺህ በላይ ሆነ

    በኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሺህ በላይ ሆነ።

    ባለፉት 24 ሰዓታት በ5034 ናሙናዎች ላይ ተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ 95 ሰዎች ላይ ቫይረሱ በመገኘቱ በአገሪቱ እስካሁን በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 1063 ደርሷል።

    ቀደም ሲል በሽታው ተገኝቶባቸው የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከልም 11 ሰዎች ከቫይረሱ ማገገማቸው በመገለጹ እስካሁን ያገገሙ ሰዎች አሃዝ 208 ሆኗል።

    የጤና ሚንስቴርና የሕብረሰተብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ ባወጡት ዕለታዊ መግለጫ ቫይረሱ ከተገኘባቸው 95 ሰዎች መካከል 30ዎቹ የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ አላቸው ተብሏል።

    አራት ሰዎች ደግሞ በሽታው ከያዛቸው ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሲሆን 61ዱ ሰዎች ግን የታወቀ የውጪ አገር የጉዞ ታሪክም ሆነ በሽታው ከያዛቸው ሰዎች ጋር የታወቀ ንክኪ የላቸው ተብሏል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን በጠቃላይ 106 ሺህ 615 የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 1063ቱ ወረርሽኙ ተገኝቶባቸዋል።

    ዛሬ በሽታው እንዳለባቸው ከተገለጹት 56 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 3 ሰዎች ከትግራይ፣ 22 ሰዎች ከኦሮሚያ፣ 1 ሰው ከአፋር፣ 3 ከሶማሌ፣ 2 ከድሬዳዋ እና 3ቱ ደግሞ ከሐረሪ ክልሎች ናቸው።

  12. ጀርመናውያን ወደ ቻይና እየተመለሱ ነው

    ወደ 400 የሚጠጉ ጀርመናዊያን ኃላፊዎች፣ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው በቻርተር በረራ ወደ ቻይና እየተመለሱ ነው። በቻይና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋሞችም እየተከፈቱ ነው።

    የመጀመሪያው በረራ የተካሄደው ባለፈው አርብ 200 ጀርመናውያንን አሳፍሮ ነበር ሲል የጀርመኑ ኤአርዲ ዘግቧል። በሚቀጥለው ማክሰኞ ወደ ሻንጋይ በረራ ይካሄዳል ተብሎም እቅድ ተይዟል።

    በቻይና ከ5,200 በላይ የጀርመን ተቋሞች አሉ። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተቀጣሪዎችም አሏቸው።

    በሰሜን ቻይና የጀርመን የንግድ ጉዳዮች ኃላፊ ጄንስ ሂልደብራት “የጀርመን ነጋዴዎች ወደ ቻይና ሠራተኞችን የመመለስ ፍላጎት አላቸው” ብለዋል።

  13. በብራዚል በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ተቃረበ

    በብራዚል በኮሮናቫይረስ የሚያዙ፣ ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥርም ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ነው።

    ብራዚል በበሽታው ሳቢያ ሰዎችን በማጣት በዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ ናት። በአንድ ቀን በበሽታው የተያዙ ወደ 27,000 የሚጠጉ ሰዎችንም አግኝታለች።

    ቁጥሩ አሁን ባለበት ፍጥነት ከጨመረ በቀጣይ ሁለት ቀናት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ተነግሯል።

    ፕሬዘዳንት ዣቪር ቦልሶናሮ ዝምታን መርጠዋል።

    ባለፉት ጥቂት ቀናት ትኩረታቸውን ያደረጉት በከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ ባለው የሐሰተኛ መረጃ ጉዳይ ነው።

  14. ፌደረር የዓለም ቁጥር አንድ ተከፋይ አትሌት ሆነ

    ሮጀር ፌደረር በዓለም ቁጥር አንድ ተከፋይ አትሌት በመሆን ከሜዳ ቴኒስ ተጫዋቾች ግንባር ቀደም ሆነ።

    ፎርብስ በሚያወጣው የዓለም ከፍተኛ ተከፋዮች ዝርዝር ፌደረር፤ ሊዮኔል ሜሲን በልጦ አንደኛነቱን ይዟል።

    የ38 ዓመቱ ፌደረር፤ ባለፈው ዓመት 86.2 ዩሮ ካገኘ በኋላ በሀብታሞች ሰንጠረዡ አራት ደረጃ ከፍ ብሏል።

    ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ያለውን ደረጃ እግር ኳሰኞቹ ክርስቲያኖ ሮናልዶ (85 ሚሊዮን ዩሮ)፣ ሜሲ (84 ሚሊዮን ዩሮ)፣ ኔማር (77.5 ሚሊዮን ዩሮ) እና ቅርጫት ኳስ ተጫዋቹ ለብሮን ጄምስ (71.5 ሚሊዮን ዩሮ) ይዘዋል።

    “ፌደረር እግር ኳስ ተጫዋቾቹን በልጦ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሜሲ እና ሮናልዶ ደሞዛቸው ስለተቆረጠ ነው” ሲል የፎርብስ አርታኢ ከርት ባደንሀውሰን ተናግሯል።

    ጃፓናዊቷ ቴኒስ ተጫዋች ናዮሚ ኦሳካ ከሴት አትሌቶች ከፍተኛ ተከፋይ መሆኗ በያዝነው ወር መባቻ ተገልጾ ነበር። በአጠቃላይ ዝርዝሩ 29ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

  15. ሞዲ የሕንድን ወረርሽኙን ‘የመቋቋም’ አቅም አወደሱ

    ሕንድ ከፍተኛውን በአንድ ቀን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አስመዝግባለች። አስከትሎም ጠቅላይ ሚንስትር ንሬንድራ ሞዲ ለአገራቸው ዜጎች ደብዳቤ ጽፈዋል።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ በድጋሚ የተመረጡበትን አንደኛ ዓመት አስታከው “ቢቻለኝ በመካከላችሁ በተገኘው ነበር። ወቅታዊው ሁኔታ ግን ይህን አይፈቅድም” ብለዋል።

    “ብዙዎች ሕንድ በኮሮናቫይረስ ስትጠቃ፤ የዓለም ችግር ትሆናለች ብለው ፈርተው ነበር። ነገር ግን በራስ መተማመን እና በብርታት ዓለም እኛን የሚያይበትን መንገድ ለውጣችኋል” ብለዋል።

    ሕንድ ባለፉት 24 ሰዓታት በበሽታው የተያዙ 7,964 ሰዎች ስታገኝ፤ 265 ሰው ሞቷል።

    አገሪቱ ብዙ መሰናክሎችና ችግሮች አሉባት ያሉት ሞዲ “ቀን ከሌት እየሠራሁ ነው። ችግሮች ቢኖሩም አገራችን ምንም አላጣችም። በእናንተ እተማመናለሁ። በራሴ ከማምነው በላይ በእናንተ ጥንካሬና ችሎታ አምናለሁ” ብለዋል።

  16. ጀርመን አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት እራሷን ማግለሏኝ አጥብቃ ኮነነች

    ጀርመን የፕሬዝደንት ትራምፕ ውሳኔን አጥብቃ ኮነነች።

    ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት ታደርግ የነበረውን የገንዘብ ድጎማ በማቆም እራሳቸውን ከድርጅቱ ማግለላቸውን ማሳቃቸው ይታወሳል።

    የጀርመን ጤና ሚንስትር ጄንስ ሳፓህ "በጣም አሳዛኝ" እና ለዓለም ጤና ወድቀትና እንቅፋት ነው ብለዋል።

  17. አንጌላ መርክል ትራምፕ በጠሩት ስብሰባ ላይ አልገኝም አሉ

    የጀርመኗ መራሔተ መንግሥት አንጌላ መርክል ትራምፕ በአካል ለመገናኘት በጠሩት የጂ7 ስብሰባ ላይ እንደማይገኙ ተነገረ።

    የአንጌላ መርክል ቃል አቀባይ መራሔተ መንግሥቷ በስብሰባው ላይ በአካል እንደማይገኙ ይፋ አድርገዋል።

    የጂ7 አገራት ሰብሰባ በኢንተርኔት አማካኝነት ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ ፕሬዝደንት ትራምፕ ሰብሰባውን በዋይት ሃውስት እና በካምፕ ዴቪድ በአካል ለማድረግ ለአገራቱ መሪዎች ጥሪ አድርገዋል።

    የአንጌላ ቃል አቀባይ "እስከ አሁን ድረስ የቫይረሱን ስርጭት ከግምት በማስገባት፤ በሰብሰባው ለመሳተፍ ወደ ዋሽንግተን ለመሄድ አልተስማሙም። ፌደራል ቻንስለሯ ፕሬዝደንት ትራምፕ ለጂ7 ሰብሰባ ላቀረቡት ጥሪ ምስጋና ያቀርባሉ" ብለዋል።

    የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ግን "የጤና ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ ወደ ካምፕ ዴቪድ ለማቅናት ተስማምተዋል" ተብሏል።

    አሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ እና የሞቱ ሰዎች ከፍተኛውን ቁጥር በመመዝገብ ቁጥር አንድ ሆና ቀጥላላች።

    102ሺህ ሰዎች ሲሞቱ፤ 1.7 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።

  18. የሌስተር ሲቲ አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ኮሮናቫይረስ ይዞኝ ነበር አሉ

    የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ የሆነው የሌስተር ሲቲ አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ከሁለት ወራት በፊት በኮሮናቫይረስ ተይዘው እንደነበረ አስታወቁ።

    የሰሜን አየርላንድ ዜጋ የሆኑት የ47 ዓመቱ አሰልጣኝ አሁን ላይ ከቫይረሱ ሙሉ ለሙሉ ማገገማቸውን አስታውቀዋል።

    የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ከዚህ በፊት በቫይረሱ መያዛቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ሚኬል አርቴታ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ አገግመው ወደ ሥራ ተመልሰዋል።

    ብሬንዳን ሮጀርስ በቫይረስ ተይዘው በነበረበት ወቅት ትንፋሽ ያጥራቸው እንደነበረ ተናግረዋል።

    "መራመድ አልችልም ነበር። ኪሊማንጃሮ ተራራ ስወጣ የነበረውን ስሜት አስታውሶኛል" ብለዋል ብሬንዳን ሮጀርስ።

    እኒህ ኳስ አዋቂ እአአ 2011 ላይ የበጎ አድራጎት ሥራን ለመደገፍ ኪሊማንጃሮ ተራራን ወጥተው ነበር።

    "ለሶስት ሳምንታት ጣዕም እና ሽታ መለየት አልችልም ነበር። ጥንካሬ አልነበረኝም። ከአንድ ሳምንት በኋላ ባለቤቴም እንደ እኔው ሆነች። ሁለታችንም ቫይረሱ እንደነበረብን በምርመራ ተረጋግጦ ነበር" ብለዋል።

  19. ሕንድ በአንድ ቀን ከፍተኛ የሆነ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥርን መዘገበች

    ሕንድ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 7964 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አገኘች። ይህም እስካሁን በአንድ ቀን በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ሲመዘገብ ይህ ከፍተኛው ነው።

    አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ደግሞ የተገኙት ሙምባይ የምትገኝበት ማሃራሽትራ ግዛት ውስጥ ነው።

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የወጣ ተንቀሳቃሽ ምስል ሙምባይ ከተማ የሚገኙ ሆስፒታሎች በታማሚዎች ተጨናንቀው አሳይቷል።

    ምንም እንኳ በሕንድ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት መጨመሩ ቢቀጥልም፤ የአገሪቱ መንግሥት ጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ እየላላ መጥቷል።

    ለሁለት ወራት ተጥሎ የቆየው የእንቅስቃሴ ገደብ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት እጅጉን የጎዳ ሲሆን፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕንዳውያን ደግሞ ሥራ አጥ እንዲሆኑ አድርጓል።

    እስካሁን 4980 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን ሲያጡ፤ 173ሺህ 763 ሰዎች ደግሞ በሽታው ተገኝቶባቸዋል።

  20. ትራምፕ የአሜሪካና የዓለም ጤና ድርጅትን ግንኙነት አቋረጡ

    ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት እያቋረጡ መሆኑን አስታወቁ።

    ድርጅቱ ቻይናን ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጠያቂ ማድረግ ሳይችል ቀርቷል ሲሉ ወንጅለዋል። ቻይን ለመቅጣት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ይፋ ሲያደርጉ “ቻይና የዓለም ጤና ድርጅትን ሙሉ በመሉ ትቆጣጠረዋለች” ብለዋል።

    አገራቸው ለድርጅቱ ታደርግ የነበረውን ድጋፍ ወደሌሎች አካላት እንደምታዘዋውርም ተናግረዋል።

    አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ አገሮች ግንባር ቀደሟ ናት። ባለፈው ዓመት ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ደጉማለች።