በኢትዮጵያ በቫይረሱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው 55 ሰዎች ከማህበረሰቡ ተገኙ

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ከፍተኛ የተባለው፣ 88 ሰዎች ሰዎች በዛሬው ዕለት በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በቫይረሱ ከተያዙት 55ቱ የውጭ ሃገር ጉዞም ሆነ ከህመምተኛ ጋር የታወቀ ንክኪ መኖሩ አለመታወቁ ብዙዎችን አስደንግጧል፤ ይህም ሁኔታ የኮሮናቫይረስ በማህበረሰቡ ውስጥ እየተዛመተ ስለመሆኑ ጠቋሚ ነው ተብሏል። ከነዚህም መካከል 73ቱ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ የቫይረሱ የስርጭት ማዕከል ከሆነችው ከአዲስ አበባ ናቸው። በአጠቃላይ በሃገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 582 የደረሰ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ፤ 152 ሰዎች አገግመዋል።ሃገሪቷም እስካሁን ባለው 81 ሺህ 10 የላብራቶሪ ምርመራ አድርጋለች። የኮሮናቫይረስን ለመከላከል አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ጭምብል ማድረግ እንዲሁም በተደጋጋሚ እጃችንን መታጠብ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮች ናቸው። በተለይም በዛሬዋ ዕለት የኢድ አልፈጥር በዓልን ለምታከብሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ወዳጅ ጋር አብሮ መቋደስ እንዲሁም መጠያየቅን ገታ በማድረግ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ በዓሉ ይከበር።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የሚኒስትሮች ም/ቤት በኮቪድ -19 ህክምና ላይ በቀጥታ ለሚሳተፉ የማበረታቻ ክፍያ ወሰነ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በኦላይን ስብሰባ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, PM Office

    ዛሬ ግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 83ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

    ውሳኔ ካሳለፈባቸው መካከል አንዱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለማከም በቀጥታ ለሚሳተፉ የጤና ዘርፍ ሰራተኞች የማበረታቻ አበል ክፍያ ሥራ ላይ እንዲውል ያሳለፈው ውሳኔ ነው፡፡

    ውሳኔውን ያሳለፈው የጤና ሚኒስቴር፤ ወረርሽኙን ለመከላከል ለጤና ዘርፉ ሰራተኞች የማበረታቻ አበል ክፍያ ለመወሰን ባዘጋጀው መመሪያ ላይ ከተወያየ በኋላ ነው፡፡

    ከዚህም በተጨማሪ የጂኦተርማል ሀብት ልማት አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡ የውሃና መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር የተወሰኑ ድንጋጌዎችን ለማሻሻል ባቀረበው አዋጅ ላይ ምክር ቤቱ ውይይት አድርጎ ለሕዝብ ተወካዮች መርቷል፡፡

    በወረርሽኙ ምክንያት በኢኮኖሚ ላይ የተከሰተውን ጫና ለመቋቋም እና የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ለመሸፈን የ2012 በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የመካከለኛ ዘመን (የ2013-2017) የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ በመወያየትም፤ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ከጨመረ በኋላ አዋጁን እንዲጸድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች መርቶታል፡፡

    ማዕቀፉም በሥራ ላይ ይዋል ብሏል፡፡

    ለሕዝብ ጥቅም መሬት ሲለቀቅ ስለሚከፈል ካሳ እና መልሶ ማቋቋምን በተመለከተም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባወጣው ደንብ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

  2. ሕዝበ ሙስሊሙ ኢድን ለማክበር እየተዘጋጀ ነው

    የማሌዥያ የእስልምና እምነት ተከታዮች

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    በዓለም ዙሪያ የእስልምና እምነት ተከታዮች የረመዳን ፆም ወር መጠናቀቂያን ለማክበር እየተዘጋጁ ነው።

    ነገር ግን የዘንድሮው ኢድ ከሌሎች ጊዜያት ለየት ያለ ነው። ለወትሮው ሰዎች ሰብሰብ ብለው የሚያከብሩት ኢድ ዘንድሮ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ማሕበራዊ ርቀትን ጠብቆ ሊከበር ግድ ሆኗል።

    ማሌዥያ ውስጥ የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ መስጅዶች ሄደው ጁምአን በስግደት አሳልፈዋል። ነገር ግን ለስግደት የተቀመጡት ተራርቀው ነበር።

    ፓኪስታን ደግሞ በታቃራኒው ሰዎች እንደ ወትሮው ሰብሰብ ብለው ሲሰግዱ ተስተውለዋል። ፓኪስታን ከሌሎች ሃገራት በተለየ የአመሻሽ ፀሎትና የኃይማኖት ትምህርት ፈቅዳለች።

    የፓኪስታን ሙስሊሞች

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ያሉ መስጅዶች ከተዘጉ 9 ሳምንታት ተቆጥረዋል።

    የብሪታኒያ ሙስሊም ካውንስል ሙስሊሞች ኢድን ቤታቸው ሆነው እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርቧል።

    በቦስኒያዋ መዲና ሳራጄቮ ያሉ ሙስሊሞች ወደ መስጅድ እንዲሄዱ ተፈቅዶላቸዋል። በርካቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው ወደ መስጅዶች እያቀኑ ነው።

    የቦስኒያ ሙስሊሞች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

  3. በብራዚል በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 20ሺህ ደረሰ

    ማስክ ያደረጉ ሕጻናት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በብራዚል በቂ ምርመራ ስላልተደረገ እንጅ አሃዙ ከተነገረው ሊበልጥ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ

    በብራዚል በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ20 ሺህ በላይ መድረሱ ተነገረ፡፡

    ይህም በዓለም ካሉ አገራት ብራዚልን ስድስተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል፡፡

    ይሁን እንጅ አሁንም ወረርሽኙ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ነው፡፡

    በአገሪቷ እስካሁን ከ310 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከአሜሪካ እና ሩስያ በመቀጠል ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

    ባለሙያዎች በቂ ምርመራ ስላልተደረገ እንጂ ቁጥሩ ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

    በሌላ በኩል የአገሪቷ ፕሬዚደንት ጄር ቦልሶናሮ፤ በቫይረሱ ሳቢያ የደረሱ አደጋዎችን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገውታል፡፡

    ፕሬዚደንቱ ሐሙስ ዕለት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማንሰራራት በግዛት አስተዳዳሪዎችና በከንቲባዎች የተጣሉ ገደቦችእንዲያላሉ በድጋሜ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

    በኮቪድ -19 ዙሪያ የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች በኮቪድ -19 ዙሪያ ለሚሰጧቸው ምክሮች ያላቸው አመለካከትምባለፈው ወር ብቻ ሁለት የጤና ሚኒስትሮች ሥራቸውን እንዲለቁ ምክንያት ሆኗል፡፡

  4. የግብጽ ሰራተኞች በኮሮና ምክንያት ከደመወዛቸው 1 በመቶ ሊቆረጥባቸው ነው

    የግብጽ ፒራሚድ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የግብጽ መንግሥት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ያጋጠመውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለማቃለል ይረዳል ያለውን የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ አስተዋውቋል፡፡

    አዲስ በወጣው በዚህ ረቂቅ ሕግ ማንኛውም የግብጽ ሰራተኛ ከደመወዙ 1 በመቶ የሚቆረጥበት ሲሆን ጡረተኞች ደግሞ ከጡረታ ገንዘባቸው ላይ 0.5 በመቶ ይቀነስባቸዋል፡፡

    ይሁን እንጅ ከ125 ዶላር በታች ወርሃዊ ገቢ ያላቸው ሰዎችን አያካትትም፡፡

    ከዚህም በተጨማሪ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የተሰማሩ ሰዎችና ገቢያቸው በከፍተኛ ሁኔታ የተዳከመባቸው ሰዎችም በሕጉ ላይካተቱ ይችላሉ፡፡

    ሕጉም ከመጭው የፈረንጆቹ ሐምሌ ወር ጀምሮ ለአንድ ዓመት ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡

  5. አቶ ሙስጠፌን የማንሳት ውዝግብና ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው 12ቱ አባላት

  6. በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 429 ደረሰ

    የጤና ሚኒስቴር አርማ

    የፎቶው ባለመብት, Ministry of Health

    የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባወጡት መግለጫ ባለፉት 24 ሰዓታት ለ3645 ሰዎች ምርመራ ተደርጓል።

    ከእነዚህ ምርመራዎች ውስጥ 30 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ይህም በአገሪቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን 429 አድርሶታል።

    ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 18 የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆኑ ሶስት ከአፋር፣ ሶስት ከትግራይ አራት ደግሞ ከኦሮሚያ እንዲሁም ሁለት የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች መሆናቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።

    መግለጫ

    የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Public Health Institute

    መግለጫ

    የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Public Health Institute

  7. ቫይረሱ እንዳለበት የሚገልጽ ሐሰተኛ ማስረጃ ያቅረበው አሜሪካዊ ተከሰሰ

    ኤፍቢአይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከሥራ ለመቅረት በሚል የኮሮናቫይረስ እንዳለበት የገለፀው አሜሪካዊ ተከሰሰ።

    በአትላንታ ነዋሪ የሆነው የ34 ዓመቱ ሳንትዎን አንቶኒዮ ዴቪስ ለቀጣሪዎቹ ሐሰተኛ የሕክምና ማስረጃ አዘጋጅቶ መስጠቱ ተገልጿል።

    በሰውየው ድርጊትም ድርጅቱ ሥራውን አቋርጦ የመስሪያ ስፍራዎቹን በጸረ ተህዋሲያን ያስረጨ ሲሆን የተወሰኑ ሠራተኞችም ራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩ አድርጓል።

    በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁሉ ለሠራተኞቹ ደሞዝ ይከፍል የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ ድርጅቱን 100 ሺህ ዶላር እንዲያወጣ እንዳደረገው አስታውቋል።

    እንደ መግለጫው ከሆነ የአሜሪካ ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢአይ) ጉዳዩን እየመረመረው ይገኛል።

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ከተከሰቱ መሰል ማጭበርበሮች ይህ የቅርብ ጊዜው ነው ተብሏል።

    " ይህ ጉዳይ ምን ያህል ጥንቁቅ መሆን እንዳለብን፣ ምርመራ ማድረግ እንደሚኖርብንና አጥፊዎችን መክሰስ እንደሚያስፈልገን አሳይ ነው" ብለዋል የኤፍቢአይ ስፔሻል ኤጀንት ክሪስ ሃከር።

  8. አረጋውያንና ሕጻናት ላይ የክትባት ሙከራ ሊደረግ ነው

    ክትባት ሙከራ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በሚያደርገው የክትባት ሙከራ ላይ በሁለተኛው ዙር ሕፃናትና አረጋውያን ሊካተቱ ነው።

    የመጀመሪያው ዙር ሙከራ የተደረገው በሚያዚያ ወር ላይ ሲሆን በወቅቱ በሙከራው የተካተቱት እድሜያቸው ከ55 ዓመት በታች የሆኑት ብቻ ነበሩ።

    አሁን እድሜያቸው ከ70 በላይ የሆነና ከአምስት እስከ 12 የሚሆኑ ከ10ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን በመከላከል አቅማቸው ላይ ያለው ለውጥም ይፈተሻል ተብሏል።

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ምርምሩ የሚሳካ ከሆነ በመስከረም ወር 30 ሚሊዮን ክትባቶች ዝግጁ ይሆናሉ ሲል ተናግሯል።

    በክትባቱ ላይ መንግሥት 131 ሚሊየን ፓውንድ የመደበ ሲሆን ግዙፉ የመድሃኒት አምራች አስትራዜኔካ ለማምረት ተስማምቷል።

    ነገር ግን መንግሥት እንደገለፀው ክትባቱ ሙሉ በሙሉ ይሳካል ብሎ መናገር አይቻልም።

    በርካታ ባለሙያዎች ክትባቱን ለማግኘትና ለማምረት ከ12 እስከ 18 ወር ይፈጃል ሲሉ ይናገራሉ።

  9. የኢንዶኔዢያ ፕሬዝዳንት ለኢድ በዓል ቤተመንግሥታቸውን ዘግተው እንደሚቀመጡ ተናገሩ

    የኢንዶኔዢያ ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢንዶኔዢያ ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ ቤተመንግሥታቸውን ለኢድ እንደማይከፍቱ አስታውቀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ይህንን ውሳኔያቸውን ያሳለፉት አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አስቸጋሪ ነው በሚል ነው።

    በኢንዶኔዢያ ምን ግዜም በኢድ በዓል ላይ ፕሬዝዳንቱ ቤተመንግሥታቸውን ከፍተው ለጥቂት ደቂቃዎች በቤተመንግሥቱ የተገኙ ዜጎችን ያገኙ ነበር።

    በዚህ ወቅት ሰዎች ፕሬዝዳንቱንና ባለቤታውን እጅ ይጨብጣሉ፣ ከዚያም በኋላ ቀለል ያሉ ምግቦችን ይመገባሉ።

    ባለፈው ዓመት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢንዶኔዢያውያን በቤተመንግሥቱ ፕሬዝዳንቱን ለማየት ተገኝተው ነበር።

    በቤተመንግሥቱ የተገኙት ሁሉ በድንኳን ተቀምጠው፣ የቀረበላቸውን ጣፋች ምግቦችና መዝናኛ ዝግጅቶች እየኮመኮሙ ፕሬዝዳንቱን ይጠባበቃሉ። በዚህ ወቅት ግለሰቦቹን የሚያስተናግዱት የቤተመንግሥቱ አገልጋዮች ናቸው።

    በዚህ ዓመት ግን ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ራሱ መንግሥት ካወጣው የወረርሽኝ መከላከያ መመሪያዎች ጋር ስለሚጣረስ አይካሄድም ተብሏል።

    ኢንዶኔዢያ እስካሁን ድረስ 20ሺህ 162 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን በምርመራ አረጋግጣለች።

  10. አስር የደቡብ ሱዳን ሚኒስትሮች በኮሮናቫይረስ ተያዙ

    የሃገሪቷ ማስታወቂያ ሚኒስትር ሚካኤል ማኩዌይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አስር የደቡብ ሱዳን ሚኒስትሮች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገለፀ።

    የሃገሪቷ ማስታወቂያ ሚኒስትር ሚካኤል ማኩዌይ ለቢቢሲ እንደገለፁት ከጤና ሚኒስትሩ ውጭ በስተቀር ሁሉም የኮሮናቫይረስ መከላከያ ግብረ ኃይል አባላት በሙሉ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል።

    ሆኖም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል የሚለውን ሪፖርት አጣጥለውታል።

    የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻርና ባለቤታቸው በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ያስታወቁ ሲሆን መከላከያ ሚኒስትሯም አንጀሊና ቴኒም በቫይረሱ ተይዘዋል።

    በቫይረሱ የተያዙት ሁሉም ሚኒስትሮች በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ሲሆን በሙሉ ጤንነትም ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

    ከዚህም በተጨማሪ የባለስልጣናቱ ጠባቂዎችና ሠራተኞችም በኮሮናቫይረስ ተይዘው በለይቶ ማቆያ ውስጥም ይገኛሉ።

    በደቡብ ሱዳን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፤ እስካሁንም ባለው 300 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ ስድስት ሞቶችም ተከስተዋል።

    የሃገሪቷ የጤና ስርአት በርስ በርስ ጦርነት መዳከም እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተፈናቃዮች መጠለያ ማዕከልም መኖራቸው ጉዳዪን አሳሳቢ ያደርገዋል ተብሏል።

  11. ፓርኮች እንስሳትን ለመመገብ አንዳንድ እንስሳትን ለመግደል መገደዳቸውን ተናገሩ

    በኢንዶኔዥያ የሚገኝ ነብር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኢንዶኔዥያ የሚገኝ መካነ እንሰሳ (ፓርክ) እንስሶቹን ለመመገብ አንዳንድ እንስሳቱን ለማረድ መገደዱን መግለፁን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ባንዱንግ ዙ በአመት ከ3.2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከጎብኝዎች የሚያገኝ ሲሆን ከተዘጋም ሁለት ወራትን አስቆጥሯል። በአሁኑ ወቅት በእርዳታ በሚያገኘው ገንዘብ እንስሳቱን ቢመግብም ሁኔታዎች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነ ለክፉ ወቅት መዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል።

    የመካነ እንስሳው ቃለ አቀባይ እንዳሉት ያሏቸውን 85 እንስሳት ለመመገብ በቀን 400 ኪሎግራም ፍራፍሬ፣ 120 ኪሎግራም ስጋ እንደሚያስፈልግ ገልፀው ሆኖም በተቻለ መጠን እንስሳቱ የሚመገቡትን ምግብ እየቀነሱ እንደሆነ አስረድተዋል።

    "በፓርካችን 30 አጋዘኖች አሉን። ከነዚህም ውስጥ ያረጁትንና ብዙም ጠቃሚ ያልሆኑትን መርጠን ስጋ በል ለሆኑት አቦሸማኔዎችና ነብሮች እንመግባቸዋለን" በማለት ሱልሃን ሲያፊ ተናግረዋል።

    ቃለ አቀባዩ እንዳሉት በዚህ ወቅት እንስሳቱ በህይወት ለመቆየት የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ቢያገኙም መጠኑ የቀነሰ ነው ብለዋል።

    "ያለን ምግብ አልቋል ግን አሁንም መመገብ ይፈልጋሉ" በማለት ተናግረዋል።

  12. አዲስ አበባ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ማዕከል ለምን ሆነች?

  13. አሜሪካውያን መንግሥታቸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ስላደረገው ጥረት ምን ያስባሉ?

    የአሜሪካውና የቻይናው ፕሬዝዳንቶች

    የፎቶው ባለመብት, AFP/GETTY IMAGES

    ፒው የምርምርና ጥናት ማዕከል በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ላይ የ11 ሺህ አሜሪካውያንን ምላሽ ሰብስቧል።

    በርካቶቹ ደቡብ ኮሪያ እና ጀርመን የኮቪድ-19 በመከላከል ረገድ ከአገራቸው የተሻለ ማድረጋቸውን ያምናሉ።

    ነገር ግን በጥናቱ የተሳተፉ በርካታ ሰዎች ቻይናና ጣልያን በኮሮና መከላከል ላይ ለሰጡት ምላሽ ዝቅተኛ ነጥብ ሰጥተዋል።

    ምንም እንኳ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከቻይናዋ ዉሃን እንደተነሳ ቢታመንም ቫይረሱን በመቆጣጠር ረገድ ግን ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰዷ ይታመናል። ጣሊያን ደግሞ በተቃራኒው በቫይረሱ ክፉኛ ከተጎዱ አገራት መካከል ትገኝበታለች።

    ይህ የዳሰሳ ጥናት ምናልባትም የዶናልድ ትራምፕ ተደጋጋሚ ቻይና ላይ የሚያደርሱት ትችት አስተዋጽኦን ሊያሳይ ይችላል ተብሏል።

    አሜሪካ በአሁን ሰዓት 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲታወቅ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች በቻይናም ሆነ በጣሊያን ከሞቱት ቁጥር አልፋ የሄደችው በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ ነበር።

  14. በግጭት የተጎዱ አገራት የኮቪድ-19 ምርመራ የሚያደርጉት ለጥቂት ሰዎች መሆኑ ተገለፀ

    እጁን የሚታጠብ ግለሰብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢንተርናሽናል ሬስኪዩ ኮሚቴ ባጠናቀረው መረጃ መሰረት ግጭት በሚያጠቃቸው አገራት የሚካሄዱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምርመራዎች አነስተና መሆናቸውን ገለፀ።

    ድርጅቱ በሚሰራባቸው በርካታ አገራት በሀብት ደረጃ የተለያዩ ቢሆኑም አስቀድሞ የመከላከል እርምጃ በመውሰድ ከተጠቀሱት አገራት መካከል ኢትዮጵያ ትገኝበታለች።

    ከኢትዮጵያ ጋር ስማቸው የተጠቀሱ አገራት ዮርዳኖስ፣ ታይላንድ እና ኡጋንዳ ናቸው።

    እነዚህ አገራት በርካታ ሰዎችን በመመርመር፣ ንክኪ በመለየት፣ የአካላዊ ርቀት እንዲጠበቅ በማድረግ ሥራዎችን ቀድመው መስራታቸው የወጣው ሪፖርት ያስረዳል።

    ኮሚቴው ግጭት በሚበዛባቸው አገራት የሚካሄዱ የኮቪድ-19 ምርመራዎች አነስተኛ መሆን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሳይገኙና ሳይታወቁ እንዲኖሩ ስለሚያደርግ በዓለም ደረጃ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አዳጋች እንደሚያደርገው ያለውን ስጋት ገልጿል።

    ድርጅቱ በሚሰራባቸው አገራት ከሚሊየን ሰዎች መካከል አነስተኛ ምርመራ ያደረጉ በሚል የመንን፣ ከአንድ ሚሊየን ሰዎች 31 ብቻ በመመርመር ፣ ቻድ 105 ብቻ በመመርመር፣ ናይጄሪያ ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች 165 ብቻ በመመርመር ፣ ማሊደግሞ 173 ብቻ በመመርመር ጠቅሷቸዋል።

    ድርጅቱ የመመርመር አቅም ባነሰ ቁጥር በቫይረሱ የተያዘን ሰው ለይቶ ማከሚያ አስገብቶ የመከላከል፣ ከእነርሱ ጋር ንክኪ ያላቸውን የመለየት እንዲሁም ስርጭቱን በአጠቃላይ በየመቆጣጠር ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ እንዳለው በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

    አሜሪካ ምን እንኳ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቀዳሚ ብትሆንም ከሚሊዮን ሰዎች መካከል 38,394 ምርመራ በማድረግ፣ ዩናይትድ ኪንግደም41,599እንዲሁም ጀርመን 42,581በማድረግ የተሻሉ መሆናቸው ተጠቅሷል።

    ድርጅቱ በሚንቀሳቀስባቸው አገራት በቂ መረጃ የማይገንባቸው አልያም ያለው መረጃ ሙሉ በሙሉ በአግባቡ ያልተሰነደባቸው በሚል ካስቀመጣቸው አገራት መካከል የመን፣ ታንዛንያና ሶሪያ ይገኙበታል።

    በዚህም ምክንያት ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑት እነዚህ አገራት ውስጥ ወረርሽኙ ምን እንደሚመስል ሙሉ በሙሉ ጥርት ያለ ምስል ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።

  15. ፓኪስታንና ባንግላዴሽ ለኢድ በዓል እየተዘጋጁ ነው

    የኢድ አከባበር

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በመላው አለም የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች በያዝነው ሳምንት መጨረሻ የኢድ በዓልን ለማክበር እየተዘጋጁ ነው። የኢድ በዓልም በሙስሊሞች ዘንድ ቅዱስ ተብሎ የሚጠራው የረመዳን ፆም ማብቂያ ነው።

    በዚህ አመት ግን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አከባበሩ የደመቀ ላይሆን ይችላል እየተባለ ነው።

    ሆኖም በርካታ የእስልምና ተከታዮች ባሉባቸው ፓኪስታንና ባንግላዴሽ ግን ዝግጅቶች ከወዲሁ እየተጀመሩ ነው።

    የፓኪስታን ባለስልጣናት እንዳሳወቁት ሱቆች እንዲሁም ገበያዎች ህዝቡ የሚያስፈልገውን የበዓል ሸመታ እንዲያደርግ ተከፍተው እንዲቆዩ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

    ምንም እንኳን በሃገሪቷ ውስጥ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በሱቆች ላይ ተሰባስበው ታይተዋል።

    በባንግላዴሽም አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ህጉን በመተላለፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዓሉን ከቤተሰቦቻው ጋር ለማሳለፍ ወደየቀያቸው እንዳመሩ የሃገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

  16. በዋይት ሃውስ ለ11 ፕሬዚዳንቶች ያገለገሉት አስተናጋጅ በኮሮናቫይረስ ሞቱ

    የቀድሞው አስተናጋጅ ዊልሰን ሩዝቬልት ጀርማን

    የፎቶው ባለመብት, Courtesy of family

    በዋይት ሃውስ ውስጥ ለ11 የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች፣ ለአምስት አስርት አመታት ያህል ያገለገሉት የቀድሞው አስተናጋጅ በ91 አመታቸው በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው አለፈ።

    የቀድሞው አስተናጋጅ ዊልሰን ሩዝቬልት ጀርማን ስራቸውን የጀመሩት በፕሬዚዳንት አይዘንሃወር አስተዳደር በጎርጎሳውያኑ 1957 ነው።

    በመጀመሪያ በዋይት ሃውስ ውስጥ በፅዳት አገልግሎት ተቀጥረው ይሰሩ የነበረ ሲሆን የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ጃኪ ኬኔዲ ወደ አስተናጋጅነት አሳደገቻቸው።

    በዋይት ሃውስ ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ ያገለገሉት በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመን ሲሆን፤ የአስተናጋጆችም ኃላፊ ተደርገው ነበር።

    "ማንኛውንም ሰው ለማገልገል ቅን ነበር፤ እንዲሁም የሚወዳትን ሃገሩን ለማገልገል የነበረው ፍላጎት ከምንም በላይ ነው፤ ለሰዎችም የነበረው ፍቅር ጥልቅ ነው። ቸር የሆነ መንፈስ ነበረው እሱንም ጥሎልን አልፏል" በማለት የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሚሸል ኦባማ ተናግረዋል።

  17. ቻይና የዚህን ዓመት የኢኮኖሚ እድገት ግምት እንደማታስቀምጥ አስታወቀች

    የቻይና ምክር ቤት ስብሰባ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በቻይና 3000 ተወካዮች የታደሙበት አመታዊ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ተጀምሯል።

    ይህ ብሔራዊ ህዝቦች ኮንግረስ (ኤንፒሲ) የሚፀድቀውን የአገሪቱን በጀት በቅርበት የሚከታተል፣ የምጣኔ ሃብት አድገቱን ይፋ የሚያደርግና የሚወጡ ሕጎችን የሚያሳልፍ ነው።

    ቻይና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዚህ ዓመት የምጣኔ ሃብት እድገቷ ምን ያህል ይሆናል የሚለውን ግምት እንደማታስቀምጥ አስታውቀለች።

    "በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት፣ በዓለም ምጣኔ ሃብትና የንግድ እንቅስቃሴ ላይ በተጋረጠው ትልቅ አደጋ ምክንያት አንዳንድ ጉዳዮች ላይ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል ነው" ብለዋል የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬቂያንግ።

    ከዚያ ይልቅ አገሪቱ ያለባትን የበጀት ጉድለት ከፍ ያደረገች ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ የአገሪቱ ምርት 3.6 በመቶ እንደሚሆን በመተንበይ ከፍ አድርጋለች፤ ይህም በጎርጎሳውያኑ 2019 ከተገመተው 2.8 በመቶ ጋር ሲነፃፀር ልዩነት አለው ተብሏል።

  18. በህንድ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ከፍተኛ እጥረት አጋጠመ

    ከጨርቅ የተሰራ የንፅህና መጠበቂያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ለባለፉት አመታት የአስራ አራት አመቷ ፕሪያ ከትምህርት ቤቷ አስር ጥቅል የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ በየወሩ ትቀበል ነበር።

    ነገር ግን በአሁኑ ሰአት የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመግታት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ የእርሷም የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦት ቀጥ ብሏል።

    "የወር አበባ ወረርሽኝ በመከሰቱ አይቆምም። የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ እንደ ምግብ ለሴቶች መሰረታዊ ጉዳይ ነው። መንግሥት ጥያቄያችንን ችላ ለምን እንደሚል አይገባኝም? " በማለት የሰብአዊ መብት ታጋይዋ ማድሁ ባላ ራዋት ተናግራለች

    ከዚህ ቀደምም በሃገሪቷ ውስጥ ካሉት 355 ሚሊዮን የወር አበባ ከሚያዩ ሴቶች መካከል 36 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦት ያላቸው። አብዛኛው ያረጁ ልብሶች፣ ገለባ፣ አመድ በመጠቀም ደም እንዳይፈስ ለመቆጣጠር ይሞክራሉ።

  19. የቻይናው ፕሬዝዳንት በፓርላማ ላይ ያለ ጭምብል መገኘታቸው ተሰማ

    የቻይና ምክር ቤት ስብሰባ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የቻይና ፕሬዝዳንትን ዢ ጂፔንግንና ምክትላቸውን ሊ ኬቂያንግን ባካተተው የከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንቱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ታይተዋል።

    በርግጥ በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ከፊት የሚታዩት ሁለት መስመሮች በከፍተኛ ሹማምንት የተያዙ ሲሆኑ ሁሉም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አላደረጉም።

    ቀሪዎቹ የምክር ቤት አባላት ግን እንደወትሮው ሁሉ የአፍና አፍንጫ መሸኛ አድርገዋል።

    የቻይና ሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ በኮሮናቫይረስ ወረርሸኝ ምክንያት ለሁለት ወራት ተዘግቶ ቆይቶ በትናንትናው ዕለት ተጀምሯል።

  20. በኢትዮጵያ በቫይረሱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው 55 ሰዎች ከማህበረሰቡ ተገኙ