በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ነገር ግን በኮቪድ-19 ተይዘው የሚገኙ ሰዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው። ይህም ቫይረሱ ቀስ በቀስ እግሩን በማህበረሰቡ ውስት እያስገባ መሆኑን ያሳያል። ለዚህ ግን ትልቁ መፍትሄ የሕክምና ባለሙያዎችና መንግሥት የሚሰጧቸውን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ነው። ስለዚህ በእጃችን ላይ ያሉትን የመከላከያ መንገዶች በመጠቀም ራሳችንንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን ከበሽታው መጠበቅ ብቸኛው መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፤ እጃችንን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ እንታጠብ። ስለወረርሽኙ የሚቀርቡ የቀጥታ ዘገባዎችንና መረጃዎችን ከዚህ ገጽ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኢራን አየር መንገድ በመካከለኛው ምስራቅ ኮቪድ-19 እንዲሰራጭ አድርጓል ተባለ

    ማሃን የተሰኘው የኢራን አየር መንገድ በመካከለኛው ምስራቅ ለኮቪድ-19 መሰራጭት ምክንያት እንደነበረ ተረጋገጠ።

    ከኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ጋር ግንኙነት ያለው ማሃን አየር መንገድ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ከኢራን ወደ ሌባኖስ እና ኢራቅ አጓጉዟል።

    በሌባኖስ እና ኢራቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጡት ሰዎች በዚህ አየር መንገድ ከኢራን የመጡ ናቸው።

    በማሃን አየር መንገድ ውስጥ የሚገኙ የቢቢሲ ምንጮች እንዳሉት፤ የአየር መንገዱ የበረራ አስተናጋጆች ስለቫይረሱ ስርጭት ስጋታቸውን እንዳይናገሩ ተደርገዋል።

    ከዚህ በተጨማሪም የበረራ ሠራተኞች በቂ የመከላከያ ቁሶችም አያገኙም ነበር።

    የበረራ መከታተያ መረጃ እንደሚያሳየው ምንም እንኳን አገሪቱ የበረራ እገዳ ብትጥልም አየር መንገዱ በተደጋጋሚ ወደ ቻይና ጉዞዎችን አድርጎ ነበር።

    ማሃን ኤር በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

  2. ጸጉር ቤቶችና ኮሮናቫይረስ በአውሮፓ

    ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥለው ከነበሩት አገራት መካከል አንዳንዶቹ እገዳውን ማላለት ጀምረዋል።

    በመላው አውሮፓ የእንቅስቃሴ ገደቡ ቀስ በቀስ መላላት የጀመረ ሲሆን ወደስራቸው ለመመለስ ከፈጠኑት መካከል ጸጉር ቤቶች ይጠቀሳሉ።

    በጸጉር ቤቶቹ ውስጥም ከሁለት በላይ ደንበኞች መጠበቅ አይችሉም፣ ጋዜጣ ማንበብ አይቻልም፣ የጸጉር ባለሙያው ለእያንዳንዱ ደንበኛ የተለያዩ ጓንቶችን መጠቀም አለበት እንዲሁም ደንበኛውም ሆነ ባለሙያው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ አለባቸው።

    ከወርሃ መጋቢት በኋላ በጀርመን የሚገኙ አንዳንድ ጸጉር ቤቶች መከፈት ጀምረዋል።በስፔን የሚገኙ ጸጉር ቤቶችም ከትናንትናው ሰኞ ዕለት ጀምሮ ለደንበኞቻቸው ክፍት ሆነዋል።

  3. አሜሪካ ከአንድ ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝቅተኛውን የሞት መጠን አስመዘገበች

    አሜሪካ ባለፉት 24 ሰዓታት ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ ዝቅተኛውን የሞት መጠን እንዳስመዘገበች አስታውቃለች። የሟቾች ቁጥር 1015 ሲሆን ይህም ከአንድ ወር በኋላ ዝቅተኛው መሆኑ ተጠቁሟል።

    በአሜሪካ እስካሁን ከ 1.1 ሚሊየን በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል። ይህ ቁጥር በስፔን ከተመዘገበው በአምስት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን ከቻይና ደግሞ በ 14 እጥፍ ይበልጣል።

    እስካሁን ደግሞ 200 ሺ የሚሆኑት ከቫይረሱ አገግመዋል።

    የአሜሪካ መንግስት በሰራው ጥናት መሰረት በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎች ቁጥር ከዚህም በላይ በፍጥነት የሚጨምር ሲሆን የሟቾች ቁጥር ግን በመጪው ሰኔ መቀነስ እንደሚያሳይ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

  4. ካምቦዲያ ለሳምንታት በቫይረሱ የተያዘ ሰው አላገኘሁም አለች

    የደቡብ ምስራቅ እሲያዋ አገር ካምቦዲያ ባለፉት ሶስት ሳምንታት በቫይረሱ የተያዘ ሰው ስለመኖሩ ሪፖርት አላደረገችም።

    ይህም ብቻ ሳይሆን ካምቦዲያ በቫይረሱ ከተያዙ 122 ሰዎች 120ዎቹ በፍጥነት እንዲያገግሙ በመርዳት አመርቂ ውጤት አስመዝግባለች።

    ይሁን እንጂ የአገሪቱ መንግሥት የሚፈለገውን ያክል ምርመራ ባለማካሄዱ ተጨማሪ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለ።

    ከአጠቃላይ 16 ሚሊዮን የካምቦዲያ ህዝብ የኮቪድ-19 ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር ከ760 አይበልጥም።

    የአገሪቱ መንግሥት ምንም እንኳ ባለፉት ሶስት ሳምንታት በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ባናገኝም ተጥለው የሚገኙት ገደቦች ይቆያሉ ብሏል።

    በአሁኑ ወቅት በካምቦዲያ ትምህርት ቤቶች፣ ቲያትር እና መዝናኛ ቤቶች ዝግ ናቸው።

  5. ሕንድ የመጠጥ ሱቆችን መክፈቷን ተከትሎ ረጃጅም ሰልፎች እየታዩ ነው

    በሕንድ ሰኞ አመሻሹን አንዳንድ አነስተኛ ሱቆች መከፈት መጀመራቸውን ተከትሎ ዜጎች አልኮል ለመግዛት ሲጣደፉ ተስተውሏል። ረጅም የሚባሉ ሰልፎችም በሱቆች በር ላይ ታይተዋል።

    በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጩት ተንቀሳቃሽ ምስሎችና ፎቶዎች መሰረት የተሰለፉት ሰዎች ማህበራዊ ርቀታቸውን መጠበቅ ላይ ግድ እንደሌላቸው ማሳያ ነው ተብሏል።

    የሕንዷ ኒው ዴልሂ ከተማ ማንኛውም አልኮል መጠጥ ላይ ለኮሮና መከላከያ የሚውል 70 በመቶ ጭማሪ ብታደርግም ሰዎች ከመግዛት ሊቆጠቡ አልቻሉም።

    ሱቆች መከፈታቸውን ተከትሎ በታየው ሰልፍ ምክንያት ደግሞ በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች የሚገኙ ሱቆች ተመልሰው እንዲዘጉም ተወስኗል።

  6. የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርጉ ያለው ጥበቃ ተገደለ

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ባለማድረጋቸው ወደ ሱቅ ውስጥ እንዳይገቡ የከለከላቸውን የጥበቃ ሰራተኛ ነፍስ ያጠፉት የቤተሰብ አባላት ክስ ተመሰረተባቸው።

    ሟች የ43 ዓመቱ ካልቪን ሙንርሊይን በአሜሪካዋ ሚቺጋን ግዛት ነው ጀርባው ላይ በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ያለፈችው።

    የቤተሰቡ አባል የሆነች ሴት ልጅ ማስክ ባለማድረጓ ወደሱቁ መግባት እንደማትችል ሲነግራት በተፈጠረ አለመግባባት ነው ወንጀሉ የተፈጸመው።

    እናት ሻርሜል ቲግ በቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን ባለቤቷ እና ወንድ ልጇ ግን አሁንም እየተፈለጉ እንደሆነ ተገልጿል።

    ማስክ ባለማድረጓ ወደ ውስጥ እንዳትገባ የተከለከለችው ሴት ደግሞ የግዛቲቱን ሕግ በመተላለፍ ክስ ቀርቦባታል።

  7. አሜሪካ ሪኮርድ የሆነ 3 ትሪሊየን ዶላር ልትበደር ነው

    አሜሪካ ኮሮናቫይረስ ያስከተለውን ከፍተኛ ጫና ለመቋቋም በአገሪቱ ታሪክ ሪኮርድ የሆነ 3 ትሪሊየን ዶላር ልትበደር መሆኑ ተገለጸ።

    ከዚህ ቀደም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እና በኮቪድ-19 ምክንያት ዜጎችን ለመደገፍ የትራምፕ አስተዳደር ብድር ወስዶ ነበር።

    አሜሪካ ብድር የምትወስደው የመንግሥት ቦንድ በመሸጥ ነው።

    በብድር የሚገኘው 3 ትሪሊየን ዶላር በዋናነት በቫይረሱ የተጎዱትን በገንዘብ ለመደጎም እና የጤና ስርዓቱን ለማጠናከር የሚውል ነው ተብሏል።

    በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ አጠቃላይ እዳ ወደ 25 ትሪሊዮን ዶላር ተጠግቷል።

  8. በኒው ዚላንድ ለሁለተኛ ቀን በቫይረሱ የተጠቃ ሰው አልተገኘም

    ኒው ዚላንድ ለሁለተኛ ቀን በቫይረሱ የተጠቃ ዜጋ አላገኘሁም አለች።

    ኒው ዚላንድ ጥላ የነበረውን ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብም እያላላች ትገኛለች። ጠቅላይ ሚንስትር ጃኪንዳ አርደረን ባስመዘገብነው ድል ሁላችንም ልንኮራ ይገባል ካሉ በኋላ የአገሪቱ ዜጎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

    ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚንስትሯ በማህብረሰብ ውስጥ ከአንድ ሰው ወደሌላ በሽታው እየተዛመተ እንዳልሆነ በመግለጽ ኮቪድ-19ን 'ድል ነስተነዋል' ብለው ነበር።

    በአሁኑ ወቅት በኒው ዚላንድ 1137 በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ያሉ ሲሆን 20 ደግሞ መሞታቸው ተገልጿል።

  9. እንዴት አደራችሁ ውድ የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች

    ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ ኮሮናቫይረስን የተመለከቱ ዜናዎችን ከአገር ውስጥና ከመላው ዓለም በቀጥታ ዘገባችን ወደ እናንተ ማድረስ እንጀምራለን።

    አብራችሁን እንድትቆዩ ጋበዝናችሁ።