የትራምፕ አስተዳደር ሰኞ ዕለት በተካሄደው ለክትባት "ቃል የመግባት" ጉባዔ ላይ አልተገኘም። ይህም አሜሪካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት ዓለም አቀፋዊ መሪነቱን ለመውሰድ አለመፈለጓን ያሳያል እየተባለ ነው።
በርግጥ በጉባዔው ላይ ያልተገኘችው አሜሪካ ብቻ አይደለችም። ሩሲያም ተወካይዋን አልላከችም። በአውሮፓ ሕብረት የቻይና አምባሳደርም ቢሆኑ ስብሰባውን ቢካፈሉም ክትባቱና ሕክምናው ላይ ለሚደረገው ምርምር ለሚያስፈልገው ገንዘብ ምንም ዓይነት ቃል አልገቡም።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግሥትና የግል ፈንድ የኮቪድ-19 ክትባትን ለመስራት እንደሚውል ገልፀዋል።
ነገር ግን ሁለቱ የአሜሪካና የቻይና ግዙፍ መድሃኒት አምራች ኩባንያዎችን ለብቻቸው ተጉዘው ክትባቱን ለማምረት የሚያደርጉት ጥረት ለቀሪው ዓለም ጥሩ ምልክት አይደለም።
ይህ የአውሮፓውያን አመለካከት በሌሎች አገራትም ድጋፍ ያገኘ ሲሆን ማንኛውም ክትባት እንደ ዓለም አቀፍ ንብረት መታየት አለበት ወይስ የአንድ አገርና ኩባንያ ብቻ ነው የሚለው መወያያ ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት ክትባቱን ለማምረት ሩጫ ላይ ያሉ ኩባንያዎች ከተስፋ ይልቅ ስጋት የሚያጭሩ እየሆኑ ነው።
ፍርሃቱ አሜሪካ ወይንም ቻይና ክትባቱን ለቀሪው ዓለም ይከለክላሉ የሚል አይደለም።
ከዚያ ይልቅ በመላው ዓለም በቫይረሱ ለተያዙም ሆነ አንዳይያዙ የሚያስፈልገው መድሃኒትን ለማምረት የተባበረ የምርምር ናጥናት ሥራ፣ ማምረትና ማከፋፈል ስለሚያስፈልገው ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "አሜሪካ ትቅደም" መፈክር ብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሲሆን ይህ አሜሪካን ብቻ ከፊት የማስቀደም አዝማሚያ በምርጫ ቅስቃሳቸው ወቅትም ጎላ ብሎ ተደምጧል።
ስለዚህ አሜሪካ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ክትባትና ሕክምና ምርምር ሥራዎች ላይ ከሌሎች ጋር ትተባበራለች የሚለው ጥያቄ ውስጥ ነው።