በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ነገር ግን በኮቪድ-19 ተይዘው የሚገኙ ሰዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው። ይህም ቫይረሱ ቀስ በቀስ እግሩን በማህበረሰቡ ውስት እያስገባ መሆኑን ያሳያል። ለዚህ ግን ትልቁ መፍትሄ የሕክምና ባለሙያዎችና መንግሥት የሚሰጧቸውን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ነው። ስለዚህ በእጃችን ላይ ያሉትን የመከላከያ መንገዶች በመጠቀም ራሳችንንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን ከበሽታው መጠበቅ ብቸኛው መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፤ እጃችንን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ እንታጠብ። ስለወረርሽኙ የሚቀርቡ የቀጥታ ዘገባዎችንና መረጃዎችን ከዚህ ገጽ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በየደቂቃው በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን የሚያሳይ ካርታ

  2. ሩሲያ ወደ ጣሊያን ልካ የነበረው የጦር ሃኪሞችን እንዲመለሱ ወሰነች

    በጣሊያን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ተልከው የነበሩት የሩሲያ የጦር ሃኪሞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተወሰነ።

    የሩሲያ መከላከያ ሚንስትር ሩሲያዊያኑ ሃኪሞች ከነገ ጀምሮ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ ብለዋል።

    ከ6 ሳምንታት በፊት ሩሲያ በኮቪድ-19 እጅጉን ተጠቅቶ ወደነበረው ሰሜናዊ ጣሊያን 100 የጤና ባለሙያዎችን ልካ ነበር።

    በወቅቱ የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ጁሴፔ ኮንቴ የሩሲያ መንግሥት የጤና ባለሙያዎችን ወደ ጣሊያን መላኩን "ከሩሲያ በፍቅር" ሲሉ አድናቆታቸው ገልጸው ነበር።

    የሩሲያ የጦር ሃኪሞች በጣሊያን የነበራቸው ተልዕኮ ምን ያክል ስኬታማ እንደሆነ ባይታወቅም፤ በሩሲያ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ተከትሎ የጤና ባለሙያዎቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተወስኗል።

  3. በዩናይትድ ኪንግደም በኮሮናቫይረስ የሞቱት ቁጥር ከ30ሺህ በላይ ሆነ

    በኮሮናቫይረስ የሟቾች ቁጥር ከአውሮፓ ቀዳሚ በሆነችው ዩናይትድ ኪንግደም 30ሺህ 76 ደርሷል።

    በዛሬው ዕለት 649 ሞቶች እንደተመዘገቡም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ኃላፊ ሮበርት ጄንሪክ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

    በዩኬ በማህበረሰቡ ያለውን የቫይረሱን ስርጭት መጠን ለማወቅ በቀን 100 ሺህ ሰዎችን የመርመር እቅድ ቢያዝም ለአራት ቀናት ያህል ሳይሳካ ቀርቷል። እስካሁን ባለውም በቀን ውስጥ ከፍተኛ የተመረመረው ሰው ቁጥር 69ሺህ 463 ነው።

    በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተጠቃችው አሜሪካ ከ1.2 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ የሟቾችም ቁጥር ከ70 ሺ በላይ መድረሱ ከአለም ቀዳሚ አድርጓታል።

    አሁን ባለው አሃዝ በሟቾች ቁጥር ከአሜሪካ በመቀጠል ዩኬ ትከተላለች።

  4. ጀርመን ሱቆች ይከፈቱ፤ እግር ኳስም ይጀመር አለች

    መራሄተ መንግሥት አንጌላ መርክል ጀርመን የቫይረሱን የስርጭት ፍጥነት ለመቀነስ የወጠነችው ግብ በመሳካቱ የንግድ ቦታዎች እንዲከፈቱና ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ ይችላሉ ብለዋል።

    ከዚህም በተጨማሪ ቡንደስሊጋውም እንዲጀመር የተወሰነ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶችም በቀጣይ ወራት ይከፈታሉ ተብሏል።

    የጀርመን መሪ አንጌላ መርክል መንግሥታቸው ይህን የሚያስፈጽመው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው ብለዋል።

    16ቱም የጀርመን ግዛቶች ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በመጣመር የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር አመርቂ ውጤት ማምጣታቸው ይነገራል።

    ባቫሪያን የተሰኘው ግዛት መሪ ማርኩስ ሶደር ጀርመን የተሻለ ስትራቴጂ በመንደፏ ከየትኛውም አገር በተሻለ ሁኔታ ቫይረሱ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ችላለች ብለዋል።

    አንጌላ መርኬል ጀርመናዊያን ከመንግሥት የሚተላለፉ ምክረ ሃሳቦችን በመከተላቸው ምስጋና አቅርበዋል።

    ስፋታቸው እስከ 800 ካሬ ሜትር የሆኑ የንግድ ቦታዎች እንዲከፈቱ ግዛቶቹ እና ፌደራል መንግሥቱ ተስማምተዋል። ባለሱቆችም ሆኑ ገበያተኛው የፊት እና አፍንጫ ጭምብል ማድረግ እና ማህበራዊ እርቀት መጠበቃቸውን መቀጠል አለባቸው ተብሏል።

    በተጨማሪም ቡንደስሊጋው በባዶ ስታዲያም ከ10 ቀናት በኋላ እንዲጀምር ተስማምተዋል።

  5. ኬንያ የወረርሽኙ ማዕከል ያለቻቸውን ሁለት ሰፈሮች እንዲዘጉ ወሰነች

    የኬንያ መንግሥት የወረርሽኙ ማዕከል ያላቸውን ሁለት ስፍራዎች ለሁለት ሳምንታት ያህል ከማንኛውም እንቅስቃሴ እንዲታገዱ ውሳኔ ላይ ደርሷል።

    በመዲናዋ ናይሮቢ የምትገኘው የንግድ ሰፈር ኢስሊና በሞምባሳ ከተማ ውስጥ 'ኦልድ ታውን' ተብለው የሚጠሩ ሰፈሮች በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ ተጠቅተዋል።

    የበርካታ ሱማሌዎች የንግድ መናኸሪያ በሆነችው ኢስሊ 68 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ በሞምባሳዋ 'ኦልድ ታውን' ደግሞ 63 ሰዎች መያዛቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።

    በአገሪቷ ውስጥ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 582 ደርሷል።

    በሁለቱ ሰፈሮች ውስጥ ማንኛውም እንቅስቃሴ የተከለከለ መሆኑንም የጤና ሚኒስቴር በትዊተር ገፁ አስታውቋል።

    ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ድንበር ተሻጋሪ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎችም በየጊዜው የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲያደርጉ ውሳኔ አስተላልፏል።

    ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ቫይረሱን በተለያዩ አገራት ያዛምቱታል የሚሉ ስጋቶች በተደጋጋሚ ይሰማሉ።

  6. ናይጄሪያዊው በኢንተርኔት አማካኘነት የሞት ቅጣት ተፈረደበት

    የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመቀነስ በሚል ፍርድ ቤት መሄድ በቀረባት ናይጄሪያ፤ የፍርድ ሂደቶች ኢንተርኔትን በመጠቀም የሚወሰኑ ሆነዋል።

    ከሰሞኑም አንድ ግለሰብ 'ዙም' በተባለው መተግበሪያ የሞት ቅጣት ተፈርዶበታል።

    ይህንንም ተከትሎ በመብት ዙሪያ የሚሰራው አለም አቀፉ ሂውማን ራይትስ ዋች የናይጄሪያ ፍርድ ቤቶች በኢንተርኔት ላይ በሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎችም "ፍትሃዊ፣ ግልፅና፣ ሚዛናዊነት" ይጠበቅባቸዋል የሚል መግለጫን አውጥቷል።

    በአገሪቷ ውስጥ ሁሉም ወንጀሎች በፍርድ ቤት የማይታዩ ሲሆን፤ አስቸኳይ የፍርድ ሂደት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔም የሚተላለፈው።

    በኢንተርኔት በነበረው የፍርድ ሂደት ዳኛ ሞጂሶላ ዳዳ ኦላሊካን ሃሚድ የተባለውን ተጠርጣሪ የአሰሪውን እናት በመግደል ወንጀልም ታንቆ እንዲሞት ውሳኔ ተላልፎበታል።

    ሂደቱ ሶስት ሰአታት የፈጀ ሲሆን የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግን ጨምሮ፣ በርካታ ጠበቃዎችና ዳኛዎች ተከታትለውታል።

    ተጠርጣሪውም ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል።

    በናይጄሪያ ሕግ መሰረት የሞት ቅጣቱ ተፈፃሚ የሚሆነው በተለያዩ ግዛት አስተዳዳሪዎች ዘንድ ተቀባይነት ሲያገኝ ነው።

    ሂዩማን ራይትስ ዋች በወረርሽኙ ወቅት የፍርድ ሂደቶች በተለየ መንገድም መቀጠላቸውም የፍትህ አቅርቦቱን ያፋጥነዋል ካለ በኋላ ታንቆ የመሞትን ቅጣት ግን "ጨካኝነትን የተላበሰና ኢ-ሰብአዊ ነው" ብሎታል።

  7. ደቡብ ኮርያ ኪም የልብ ቀዶ ህክምና ስለማድረጋቸው 'ምንም ምልክት የለም' አለች

  8. የፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ይፋ አለመደረግ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል

    የላይቤሪያው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል? ውጤታቸውስ ምን ሆነ? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች ከላይቤሪያውያን ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰሙ ነው።

    የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ኡጂን ናግቤ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ የፕሬዚዳንቱን ውጤት ለማወቅ ጉጉቶች ቢኖሩም ባለስልጣናቱ ግን ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል።

    ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ ጋር በአንድነት ተቀምጠው ከታዩ ከሶስት ቀናት በኋላ በተመረመሩበት ወቅት ነው ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው የታወቀው።

    ፕሬዚዳንቱ ራሳቸውን አግልለው ይቀመጣሉ ተብለው ቢጠበቁም ለህዝቡ የፊት ጭምብል ሲያከፋፍሉ ታይተዋል።

    ከሰሞኑም የላይቤሪያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊ ዶክተር ሞሶካ ፋላህ በአንድ ሬድዮ ፕሮግራም ላይ ቀርበው ከህዝቡ ለሚቀርብላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ ባሉበት ወቅት አንድ ግለሰብ ፕሬዚዳንቱ ተመርምረዋል ወይ የሚል ጥያቄን አቅርቦላቸዋል።

    ኃላፊውም በምላሹ ጥያቄው ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ጠቅሰው በኮቪድ-19 ምርመራ ይፋ አይደረግም ብለዋል።

    የፕሮግራሙ አዘጋጅ ክሌራንስ ጃክሰን ጣልቃ በመግባት ኃላፊው ለጥያቄው ቀጥተኛ መልስ እንዲሰጡም ብትጠይቅም አድፈንፍነው ማለፋቸው በርካታ ጥያቄዎችን አጭሯል።

    ከኃላፊው ጋር የነበረውን የሬድዮ ፕሮግራም የፈጠረውንም ግራ መጋባትም ለማረጋጋት የፕሬዚዳንቱ ምክትል ፀሐፊ ስሚዝ ቶቢ ፕሬዚዳንቱ አለመመርመራቸውን ተናግረዋል።

  9. የደቡብ አሜሪካ ሃገራት እንዴት ዋሉ?

    ብራዚሉ ፕሬዚዳንት ጄይር ቦልሶናሮ በትናንትናው እለት "የወረርሽኙ አስከፊ ወቅት መቋጫ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ" ቢሉም ከሳቸው ንግግር በኋላ የወጣው መረጃ ግን ተስፋቸውን አመላካች አልነበረም። በትናንትናው እለትም 600 ግለሰቦች በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ተከትሎ የሟቾችን ቁጥር ስምንት ሺህ እንዲጠጋ አድርጎታል።

    በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቁት ከተሞች አንዷ የሆነችው ማናውስ ከንቲባ ለእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወረርሽኙን መከላከል ይቻል ዘንድ የህክምና ቁሳቁስ እንዲረዱ በመማፀን ደብዳቤ ፅፈዋል።

    ኡራጓይ በመዲናዋ ሞንቴቪዶ የሚገኙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን እንዲሁም የንግድ ቦታዎችን መክፈት ጀምራለች። ስራ ቦታ መሄድ የማያስፈልጋቸውን ዜጎቿንም በቤታቸው እንዲቀመጡ ትእዛዝ አስተላልፋለች። መንግሥት አገሪቷ ወደነበረችበት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንድትመለስ ያበረታታው አራት መቶ የሚሆኑ የግንባታ ሰራተኞችን መርምሮ ሁሉም ከኮሮናቫይረሱ ነፃ ሆነው በመገኘታቸው ነው። በኡራጓይ 670 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ 17 ግለሰቦች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

    ኮሎምቢያ አስገዳጁ የቤት መቀመጥ ውሳኔ ለሁለት ሳምንታት ያህል የተራዘመ ሲሆን አንዳንድ ዘርፎች ግን ወደቀደመ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። ፕሬዚዳንት ኢቫን ዱኬ እድሜያቸው ከ6-17 የሆኑ ታዳጊዎች በሳምንት ለሶስት ቀናት ያህል ለሰላሳ ደቂቃ እንዲወጡ ፈቅደዋል። በአገሪቷ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 8ሺህ 613 ሲሆን፣ 378 ግለሰቦች ደግሞ ሞተዋል።

  10. በእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት በርካታ አፍሪካውያን የምግብ እጥረት ያጋጥማቸዋል

  11. "ኮሮናቫይረስ ቦምብ የሌለበት ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ነው"- ራይላ ኦዲንጋ

    የኮሮናቫይረስ የአለም ስጋት መሆኑን ተከትሎ ከቫይረሱ ጋር የሚደረጉ ትግሎች የተለያየ ስያሜ እየተሰጣቸው ነው።

    ከሰሞኑም የአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት እንዲሁም የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ኮሮናቫይረስን ከጦርነት ጋር አመሳስለውታል።

    በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የመሰረተ ልማት ግንባታን በተመለከተ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ ወረርሽኙን "ቦምብ የሌለበት ሶስተኛው የአለም ጦርነት ነው" ብለውታል።

    "በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ይህን ያህል ቁጥር ያለው ህዝብ አልሞተም፤ ያውም በእዚህ አጭር ጊዜ ወቅት" በማለት ለደቡብ አፍሪካው ኤስ ኤ ቢሲ ተናግረዋል።

    የኮሮናቫይረስ ጫና አህጉሪቷ ላይ የከፋ እንደሚሆን የገለፁት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በተለይም በወረርሽኙ ማግስት አፍሪካ እነዚህን ችግሮች ብቻዋን የምትጋፈጠው ይሆናል ብለዋል።

    "የአፍሪካ ሃገራት ማንም እንደማይረዳቸውና ከጎናቸው እንደማይቆም በመረዳት ከአሁኑ እውነታውን ሊጋፈጡት ይገባል። ወረርሽኙ አውሮፓ፣ አሜሪካን እንዲሁም ቻይናን አንበርክኳል" ብለዋል።

    አክለውም "የአፍሪካን የንግድ እንቅስቃሴዎች በምናጤንበት ወቅት 85 በመቶ የሚሆነው ከአህጉሪቷ ውጭ የሚደረግ ነው። ይህ ወቅት በአህጉሪቷ ውስጥ ንግድን የምናሳልጥበትን መንገድ የምንቀይስበትን እድል የምንፈጥርበት ነው"

    ከአፍሪካ በሽታዎች ቁጥጥርና ማዕከል በተገኘው መረጃ መሰረት በአህጉሪቷ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 48 ሺህ 22 የደረሰ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል 16ሺህ 19 አገግመዋል፣ 1ሺህ 878 ቱ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

  12. በፌዴሬሽኑ ውሳኔ ላይ የክለብ አመራሮች ምን ይላሉ?

  13. በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከ120 ሚሊዮን በላይ ህንዳውያን ስራቸውን አጡ

    ህንድ የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመግታት እንቅስቃሴን መገደብ ጨምሮ አስገዳጅ የቤት መቀመጥ መመሪያዎችን ማስተላለፏን ተከትሎ 122 ሚሊዮን ህንዳውያን ስራቸውን ማጣታቸው ተገልጿል።

    የህንድን ምጣኔ ኃብት የሚቆጣጠረው ማዕከል ባወጣው መረጃ የሃገሪቷንም የስራ አጥ ቁጥር 27.1 ፐርሰንት አድርሶታል ተብሏል።

    ይህ አሃዝም ክፉኛ በኮሮናቫይረስ ከተጠቃችው አሜሪካ ስራ አጥ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር አራት እጥፍ ነው።

    ህንድ ከመጋቢት 16፣ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴዎችን መገደቧን ተከትሎ በርካታ ዜጎቿ ከስራ ተሰናብተዋል።

    በተለያየ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ትልልቅ ኩባንያዎችን ጨምሮ ጥቃቅን፣ አነሰስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ቀጥ ማለት በርካቶች ስራ እንዲያጡ ምክንያት ሆኗል።

    በተለይም የግንባታ ስራዎችን የህዝብ ትራንስፖርቶች መቆም ብዙዎችን የእለት ጉርሳቸውን እንዲያጡ አድርጓቸዋል ተብሏል።

    የኮሮናቫይረስ ኢኮኖሚያዊ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ተፅእኖ ያደረሰባቸው ከተለያዩ ከተሞች የመጡ የቀን ሰራተኞችን እንዲሁም መደበኛ ባልሆኑ የስራ ዘርፎች ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን ነው። ከ122 ሚሊዮኖቹ ውስጥ 91.3 ሚሊዮኖቹ በአነስተኛ ንግድና በቀን ሰራ የሚተዳደሩ ናቸው።

    እስካሁን ባለው መረጃ በሃገሪቱ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ ደርሷል።

  14. የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የፖላንድ ምርጫን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል

    በአውሮፓ ከሚገኙ ሃገራት መካከል በኮሮናቫይረስ በተያዙ ሰዎችም ሆነ በሟች ቁጥር ፖላንድ ዝቅተኛውን አሃዝ ብታስመዘግብም፤ በዚህ ወር ሃገሪቷ ልታካሂደው ይዛው የነበረው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይካሄድ አይካሄድ የሚለው ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።

    በፖላንድ ህግ መሰረት የመጀመሪያው ዙር ምርጫ በመጪው እሁድ ግንቦት 2፣ 2012 ዓ.ም ለማካሄድ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በምርጫ ጣቢያዎች ሄዶ መምረጥ ችግር ሊሆን ይችላል ተብሏል።

    ከስልሳ አመት በላይ ላሉት ድምፃቸውን በፖስታ ቤት እንዲልኩ በማድረግ መምረጥ ይችሉ ዘንድ ስርአት ተዘርግቷል።

    ገዢውን ጨምሮ የተለያዩ ፓርቲዎች ደህንነቱ በተጠበቀና ህጋዊ በሆነ መልኩ ምርጫው ፖስታን በመጠቀም መሆን አለባቸው የሚሉ አስተያየቶችን እየሰነዘሩ ነው። አራት ቀናት በቀሩት የሃገሪቱ ምርጫ የፓርላመንቱ የታችኛው ምክር ቤት ምርጫው እንዴት ይካሄድ የሚለው ላይ ሚያዝያ 29፣ 2012 ዓ.ም ውሳኔ ላይ መድረስ አለበት።

    ፓርላማው ፕሬዚዳንታዊው ምርጫው በፖስታ መካሄድ የለበትም የሚል ውሳኔም ላይ ከደረሰ ህዝቡ የምርጫ ጣቢያ ላይ በመገኘት ድምፁን መስጠት ይኖርበታል፤ ይህም ላይፈጠር ይችላል እያሉ ነው ምክንያቱም የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን የምርጫ ጣቢያዎችን ለማዘጋጀት ጊዜ የለም እያለም ነው። ይሄም ሁኔታ ምርጫውን ሊያራዝመው ይችላል።

    ፓርላማው በፖስታ ምርጫ ይደረግ ብሎ ቢወስንም ምርጫው መሆን የሚችለው ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነው።

    ተቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው የተፈጥሮ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ምርጫ መደረግ ግዴታ ስላልሆነ እስከ ነሐሴ ሊራዘም ይገባል እያሉ ነው።

    የወረርሽኙ ስጋት ባለበት ወቅት ገዢው ፓርቲ ምርጫ ማካሄድም ያስፈለገው ምናልባትም ከወራት በኋላ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሚደርሰው ኢኮኖሚያዊ ጫናና ስራ አጥነት የመመረጥ እድሌን ያመነምነዋል በሚል ነውም በማለት ትችቶችን የሚሰነዝሩ አልታጡም።

  15. በአሜሪካ በስጋ ኢንዱስትሪ ከተሰማሩት ሠራተኞች ግማሹ የኮሮናቫይረስ አለባቸው ተባለ

    በአሜሪካ በስጋ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከተሰማሩት ሰራተኞች መካከል ግማሾቹ የኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

    በአይዋ በሚገኘው 'ታይሰን ፉድስ' የስጋ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው ከሚሰሩት መካከል 730ዎቹ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ይህም ቁጥር 58 በመቶ የፋብሪካው ሰራተኞች እንደሚሸፍን የአይዋ የህብረተሰብ ጤና ኃላፊዎች በጋዜጣዊ መግለጫቸው ተናግረዋል።

    በሚያዝያ ወር ላይ በአሜሪካ ውስጥ ከሚገኙ 22 የስጋ ፋብሪካዎች ውስጥ ተዘግተው ከነበሩት አንዱ ታይሰን ፉድስ ነበር።

    የኩባንያው ቃለ አቀባይ ዴስ ሞይንስ እንደተናገሩት ፋብሪካው ከመከፈቱ በፊት "ከፍተኛ የሆነ ፅዳት ተከናውኗል" ብለዋል።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ እያጠቃት ባለችው አሜሪካ የሚገኙ የስጋ ፋብሪካዎች አገልግሎታቸውን አለማቆማቸውም ከፍተኛ ትችትን እንዲያስተናግዱ በር ከፍቷል።

    ባለፈው ወር የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የምግብ አቅርቦት ለሟሟላት እነዚህ ፋብሪካዎች ክፍት መሆን አለባቸው የሚል ውሳኔን አስተላልፈው ነበር። በወቅቱ 3ሺህ 300 ስጋ የሚያሽጉ ሰራተኞች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን 20 ግለሰቦችም ህይወታቸውን ያጡበት ወቅት ነበር።

    ባለፈው ወር እንዲሁ በደቡብ ዳኮታ በሚገኝ ስሚዝፊልድ በሚባል የአሳማ ስጋ ማምረቻ ከሚሰሩ ሰራተኞች መካከል 600ዎቹ በቫይረሱ ተይዘው ነበር።

    • በናይጄሪያ አንድ ዶክተር በቫይረሱ ሕይወቱ ሲያልፍ በርካቶች መያዛቸው ተረጋገጠ

      በናይጄሪያ ሰሜናዊ ግዛት ካኖ የሚገኘው የህክምና ማህበር አንድ ዶክተር በኮሮናቫይረስ መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን አስታውቋል፡፡

      የማህበሩ ሊቀመንበር ዶ/ር ሳኑሲ ሞሃመድ ባላ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሌላ 33 ዶክተሮች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጅ ዶክተሮቹ በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡

      በናይጄሪያዋ ካኖ ግዛት ያሉት ዶክተሮች 1 ሺህ 500 ናቸው፡፡

      በግዛቷ በብዛት የጤና አገልግሎቱን የሚሸፍኑት የግል ሆስፒታሎች ቢሆኑም በወረርሽኙ ስጋት ምክንያት በመዘጋታቸው ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሯል፡፡

      በአካባቢው የሚገኙ የመቃብር ቆፋሪዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከተለመደው እየጨመረ መምጣቱን መግለጻቸውን ተከትሎ የናይጄሪያ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከልም ወደ ካኖ ግዛት ድጋፍ ሰጭ ቡድን ልኳል፡፡ ይሁን እንጅ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው ተብሏል፡፡

      በካኖ ግዛት እስካሁን 397 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በናይጄሪያ ካሉ ሌሎች ግዛቶች በቫይረሱ ክፉኛ በመጠቃት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ባለፉት 24 ሰዓታትም 32 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል፡፡

    • የስፔን ጠቅላይ ሚኒስቴር አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተወሰኑ ሳምንት እንዲራዘም ጠየቁ

      በስፔን ባለፉት 24 ሰዓታት በኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ244 ከፍ ማለቱ ተገለፀ።

      በአገሪቱ እስካሁን ድረስ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 25,857 ሲደርስ በቫይረሱ የተያዙት ደግሞ 220,325 ሆኗል።

      ይህም ከማክሰኞ ጋር ሲነፃፀር በ996 ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል።

      ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ምክር ቤታቸውን የአስቸኳይ ጊዜውን ለተወሰነ ሳምንት እንዲያራዝም ጥያቄ አቅርበዋል።

      ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄያቸውን ባቀረቡበት ወቅት "ወደ ግባችን እየተቃረብን ቢሆንም አልደረስንም" ብለዋል።

    • ቻይና ውስጥ ታዳጊዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እያነጋገረ ነው

      በርካታ ቻይናውያን ተማሪዎች ቦርሳቸውን አነግተው አፍና አፍንጫቸውን ሸፍነው ወደ ትምህርት ቤት አምርተዋል።

      ነገር ግን ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እንደ ከዚህ ቀደሙ በሰላም ተመለሱ ብቻ ብሎ የሸኘ ቻይናዊ ወላጅ የለም፤ ይልቅስ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የማይቻልባቸው ምክንያቶች አሉ የሚል መከራከሪያ ያቀረቡ ወላጆች አሉ።

      ለዚህም ምክንያታቸው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ተማሪዎች ራሳቸውን ስተው መውደቃቸውንና በኋላም መሞታቸው መሰማቱ ነው።

      በተለይ ሁለቱ ተማሪዎች የመነጋገሪያ ርዕሱ ማዕከል ናቸው።

      የ15 ዓመቱ እና የ14 ዓመቱ ታዳጊ በተለያየ ግዛት የሚኖሩ ተማሪዎች ቢሆኑም ሁለቱም አሟሟታቸው ተመሳሳይ ነው።

      ሁለቱ ተማሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው አካላዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ራሳቸውን ስተው በመውደቅ ነበር ሕይወታቸው ያለፈው።

      በርግጥ የሁለቱም ተማሪዎች ሞት ካደረጉት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጋር ይገናኛል ብሎ ማረጋገጫ የሰጠ አካል የለም። ቤተሰቦቻቸውም ቢሆን የአስከሬን ምርመራ እንዲደረግ ፈቃድ አልሰጡም።

      ነገር ግን የአንዱ ተማሪ ወላጅ ለመገናኛ ብዙኀን ቃለ መጠይቅ በሰጡበት ወቅት ልጃቸው በሞተበት ወቅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጉን በመግለፅ ጥርጣሬያቸውን ተናግረዋል።

      ይህ ታዲያ ለቻይና ወላጆች በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ መነጋገሪያ ሆኗል። ትምህርት ቤቶችንም በስፖርት ክፍለ ጊዜ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን በማስገደዳቸው ተችተዋል።

      በቻይና መገናኛ ብዙኀን ላይ የቀረቡ አንዳንድ ባለሙያዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲሰራ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ በቂ አየር እንዳያገኙ ሊከለክል ይችላል ማለታቸው ተሰምቷል።

      ለረዥም ጊዜ በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት ቤት ተቀምጠው የነበሩ በመሆኑም ምንም እንኳ ጤነኛና ወጣት ቢሆኑም የጤና ሁኔታቸው ሊወርድ ይችላል ብለዋል።

      እነዚህ ምሁራን ለተወሰነ ወቅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አቁመው የነበሩ ተማሪዎች ወዲያውኑ ወደ ቀድሞ ቁመናቸው ላይመለሱ ይችላሉ ያሉ ሲሆን የቀደመ ብቃታቸውን ለመመለስ ከሶስት እስከ አራት ሳምንት እንደሚፈጅም ገልፀዋል።

    • ሰበር, በኢትዮጵያ 17 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋገጠ

      ዛሬ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ከተደረጉ 1382 ምርመራዎች መካከል 17 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ገልፀዋል።

      ከዚህ ቀደም በተደርጉ ምርመራዎች በየዕለቱ ከአስር ያነሱ ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።

      በዚህም የዛሬው ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች አሃዝ ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ ከታወቀ ወዲህ በአንድ ቀን በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ከፍተኛው ቁጥር ነው።

      ይህም በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን 162 አድርሶታል።

      ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል ሰባቱ ከጅቡቲ የተመለሱና በአፋር በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ መሆናቸው ሲገለጽ ስድስቱ ደግሞ ከሶማሊያ የተመለሱና በሶማሌ ክልል በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ መሆናቸው ተገልጿል።

      አራቱ ምንም አይነት የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ሲሆን አንዱ በስራ ባህሪው ምክንያት ተጋላጭ ነበር ተብሏል።

      በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 93 መድረሱንም መግለጫው አስታውቋል።

    • የኮሮናቫይረስ ተማራማሪው አሜሪካ ውስጥ ተገደሉ

      በኮሮናቫይረስ ላይ ምርምር ሲያደርጉ የነበሩት እና አዲስ ግኝቶችን ለማውጣት ጫፍ ላይ ደርሰው የነበሩት ተመራማሪ መገደላቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡

      በፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት ተመራማሪ የነበሩት ዶ/ር ቢንግ ሊኡ፤ በፔንሲልቫኒያ በሰሜን ፒትስበርግ ሮስ ታውንሽፕ ሕይወታቸው አልፎ እንደተገኙ ባለፈው ቅዳሜ የአካባቢው የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

      ፖሊስ የተማራማሪው አስክሬን ከተገኘበት ቦታ አንድ ማይል ርቀት ላይ ወዲያውኑ የሁለተኛውን ሟች ሃኦ ጉ አስክሬን መኪና ውስጥ ማግኘቱን ገልጿል፡፡

      መርማሪዎች ለኤንቢሲ እንዳሉት ሃኦ ጉ፣ ዶ/ር ሊኡን ገድለው ከዚያም ራሳቸው ላይ በመተኮስ ሕይወታቸው ሳይልፍ እንዳልቀረ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

      የህክምና ትምህርት ቤቱ በድረገጹ ላይ ባስነበበው መግለጫ ዶ/ር ሊኡ በሲንጋፖር ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው የተከታታሉ ሲሆን ለሳይንሱ ዘርፍ የተለየ አስተዋጽኦ ያደረጉ ጎበዝ ተመራማሪ ነበሩ ሲል ገልጿቸዋል፡፡

      አክሎም ዶ/ር ሊኡ ከኮሮናቫይረስ ጀርባ ያለውን ዑደት ለመረዳት የሚያስችል ወሳኝ የሆነ የምርምር ውጤት ለማግኘት ጫፍ ላይ ደርሰው ነበር ብሏል፡፡

      በመሆኑም ተመራማሪው የጀመሩትን ምርምር ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡