'ቱፓክ ሻኩር' ስራ ፈትቻለሁ ሲል አመለከተ

የፎቶው ባለመብት, Rapper Tupac Shakur
የአሜሪካዋ ኬንታኪ ግዛት አስተዳዳሪ ቱፓክ ሻኩር ስራ ፈትቻለሁ ሲል ያስገባውን ማመልከቻ በቅርቡ ቀልድ ነው በሚል በማሰባቸው ይቅርታ ጠየቁ።
" በቱፓክ ሻኩር ስም ሥራ መፍታቱን ያመለከተ ሰው አለን። ምናልባት ለጨዋታ ብሎ ይሆናል" ብለው ነበር አንዲ ቤሼይር በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት።
ነገር ግን ስሙን በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ1996 ከሞተው ከዝነኛው የአሜሪካ ራፐር ጋር የሚጋራው ግለሰብ በትክክል ስሜ ቱፓክ ማሊክ ሻኩር ነው ሲል አቤት ብሏል።
" በጣም ነው ያፈርኩት፤ ይህ ስሜ ነው" ሲል በአካባቢው ለሚታተም ጋዜጣ ተናግሯል። ግለሰቡ ለጋዜጣው አክሎ እንደተናገረው ስራ መፍታቱን ያመለከተው ከ1 ቀን በፊት ነው።
በአሜሪካ የኮሮናወረርሽኝን ተከትሎ ሚሊየኖች ስራ መፍታታቸው ይታወቃል።
ሻኩር አክሎም "ባለፈው ወር ያሉብኝን ወጪዎች እንዴት አድርጌ መሸፈን እንዳለብኝ መላ ጠፍቶኝ ነው ያለሁት" ብሏል።






