ዶክተር ክሪስቲያን ቸናይ
ይባላሉ፡፡ የ98 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ በሙያቸው ደግሞ ዶክተር ናቸው፡፡ ኗሪነታቸውም ፈረንሳይ ፓሪስ ነው፡፡
ምንም እንኳን በእርሳቸው
እድሜ ላይ ላለ ሰው የኮቪድ-19 በሽታ አስጊ ቢሆንም፤ እርሳቸው ግን ሙያቸው የሚፈቅድላቸውን ሥራቸውን ማከናወን ቀጥለዋል፡፡
አዛውንቱ ዶክተር ክርስቲያን፤
የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ባለችው ፈረንሳይ በየሳምንቱ ጡረተኞች ወዳሉባቸው የእንክብካቤ ማዕከላት እየሄዱ ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡
እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱትም
በፈረንሳይ ያለውን የቤተሰብ ሐኪሞች እጥረት ለማቃለል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
"ሁሉም ሰው ሰግቷል፤
እኔም በጣም እጠነቀቃለሁ። ባለቤቴ ቫይረሱን ወደ ቤት ይዤ እንዳልሄድ ትሰጋለች ፡፡ በእርግጥ ትክክል ናት" ይላሉ፡፡
ዶክተር ክሪስቲያን
አሁን ላይ በፓሪስ የሚሰጡትን የህክምና አገልግሎት ለጊዜው ቢያቆሙም ታማሚዎችን በኢንተርኔት አማካኝነት ያማክራሉ፡፡
በየሳምንቱም ወደ የእንክብካቤ
ማዕከላት ይሄዳሉ፡፡
"በዚህ ወረርሽኝ ወቅት
ልተዋቸው አልችልም፡፡ብቻቸውን መቋቋም አይችሉም" በማለት አረጋውያኑ የእርሳቸውን
ድጋፍ እንደሚሹ ይናገራሉ፡፡
ምንም እንኳን የአረጋውያን ማዕከላት ለቫይረሱ ተጋላጭ ቢሆኑም ክርስቲያን
ግን ስራቸውን ሊያቆሙ አይፈልጉም፡፡
"እድለኞች
ነን፡፡ በእንክብካቤ ማዕከሉ እስካሁን በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው የለም፡፡ አንድ ሰው ከተያዘ ግን የከፋ ነው የሚሆነው፤ ማንም እንዲሞት አንፈልግም" ይላሉ፡፡
አሁን ወደ 99 ዓመት እየተጠጉ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ክርስቲያን "በተለያዩ ምክንያቶች እንቅስቃሴዎችን መቀነስ አለብኝ፡፡ ከዚህ በፊት ከምሰራው በጣም ቀስ ብየ ነው የምሰራው፤ ጥንቃቄ ማድረግ ስላለብኝ" ብለዋል፡፡