በአሜሪካ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1 ሚሊዮን ደረሰ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከዓለማችን ላይ የሚጠፋ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል። እስካሁን ባለው መረጃ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲያዙ በሺዎች የሚቆጠሩም ህይወታቸውን አጥተዋል። አንዳንድ አገራት ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ እያነሱ ቢሆንም አሁንም ግን ዜጎቻቸው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው እየተናገሩ ነው። በእኛም አገር አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ ሊዘነጉ የሚገባቸው አይደሉም። እናንተም ጤና ወዳጆቻችሁም ደህና እንዲሆኑ ምኞታችን ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. አማራ ክልል ሠርግ ላይ በፈነዳ ቦንብ ህይወት ጠፋ

  2. “ለሴቶች ተብለው የተሠሩ የሀኪም መገልገያዎች እንፈልጋለን”

  3. ለዛሬ ያልነውን ጨርሰናል፤ ነገ እንመለሳለን

    Face mask

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች ለዛሬ የያዝነውን አጠናቀናል። ነገ በቀጥታ ስርጭታችን እንመለሳለን። ራሳችሁን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አትዘንጉ።

    መልካም ምሽት!

  4. የስፖቲፋይ ተጠቃሚዎች 130 ሚሊዮን ደረሱ

    ስፖቲፋይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኮሮናቫይረስ የድረ ገፅ ሙዚቃ አድማጮችን ይቀንሳል ተብሎ ተሰግቶ የነበረ ቢሆንም፤ የስፖቲፋይ ተጠቃሚዎች 130 ሚሊዮን መድረሳቸው ተገልጿል።

    የሙዚቃ ማድመጫ ድረ ገፁ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ስድስት ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አፍርቷል።

    ተንታኞች በበኩላቸው የስፖቲፋይ ትርፋማነት ድርጅቱ ያለውን ያህል ላይሆን ይችላል እያሉ ነው።

    ዋና ኃላፊው ዳንኤል ኢክ ለሮይተርስ፤ “በመላው ዓለም የተስተዋለው መመሰቃቀል እንዳለ ሆኖ ግባችንን መተናል” ብለዋል።

    የስፖቲፋይ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየናረ የመጣው ከሁለት ወር ወዲህ እንደሆነ ተናግረዋል። አብዛኞቹ ተጠቃሚዎች በሽታው በስፋት የተሰራጨባቸው የስፔን እና ጣልያን ነዋሪዎች መሆናቸውንም አክለዋል።

  5. ኮቪድ-19፡ የአውሮፓ ውሎ

    አውሮፓ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአውሮፓ አገራት እንቅስቃሴ ላይ ጥለው የነበረውን ገደብ ቀስ በቀስ እያነሱ ነው። የበረራ እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፉም እየተንገዳገደ ነው።

    የስፔን ባለሥልጣኖች የባህር ዳርቻ ላይ ፀረ ተዋሕሲ ኬሚካል በመርጨታቸው ይቅርታ ጠይቀዋል። ኬሚካሉ የተረጨው ሕፃናት በኮሮናቫይረስ እንዳይያዙ ነው ቢባልም፤ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ጉዳቱ ያመዝናል ሲሉ ተችተዋል።

    በሌላ በኩል የስዊዘርላንድ መንግሥት እድሜያቸው ከአስር በታች የሆነ ሕፃናት ከአያቶቻቸው ጋር እንዲተቃቀፉ ፈቅዷል። ታዳጊዎች በሽታውን እንደማያስተላልፉ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

    ግሪክ ዜጎቿ ከቤት ሳይወጡ መንግሥታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ በማለት ብዙ ሂደቶች በኮምፒውተር እንዲታገዙ እያደረች ነው። ለምሳሌ የፋክስ ማሽን ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተወግዶ ዲጂታል አገልግሎት እንዲሰጥ ውሳኔ ተላልፏል።

  6. በዩኬ የሟቾች ቁጥር 26,097 ደረሰ

    በዩናይትድ ኪንግደም የሟቾች ቁጥር 26,097 የደረሰ ሲሆን፤ ቁጥሩ በሆስፒታል እና በእንክብካቤ መስጫዎች ውስጥ የሞቱ ሰዎችንም ያጠቃልላል ተብሏል።

    በእንግሊዝ የሞቱ ሰዎች 3,811 እንደሆኑ የህብረተሰብ ጤና ተቋም አስታውቋል። ከነዚህ 70 በመቶው ሆስፒታል የተቀሩት 30 በመቶው ደግሞ ከሆስፒታል ውጪ እንደነበሩ ተገልጿል።

  7. ኬንያዊው ጳጳስ ጣልያን ውስጥ በኮቪድ-19 ሞቱ

    ጡረታ የወጡት ኬንያዊው ጳጳስ ጣልያን ውስጥ በኮቪድ-19 ሞቱ።

    የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ጳጳሱ ስላስ ንጂሩ በጣልያኗ ቱሪን ከተማ የኮሮናይረስ ሕክምና እየተደረገላቸው ነበር።

    በማዕካላዊ ኬንያ ሜሩ ግዛት በምትገኝ የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ለ38 ዓመታት ያገለገሉት ጳጳስ ትናንት [ማክሰኞ] ነው ሕይወታቸው ያለፈው።

    የሞታቸውን ዜና ለመገናኛ ብዙሃን ያሰሙት ተተኪያቸው ናቸው። ዴይሊ ኔሽን የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው የ92 ዓመቱ ጳጳስ ጣልያን ውስጥ ከሌሎች ሁለት ጳጳሶች ጋር በሚኖሩበት ቤት ነው ቫይረሱ የያዛቸው።

    የኬንያው ምክትል ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ጳጳሱን ለአገልግሎታቸው አመስግነው ሃዘናቸው ገልፀዋል።

    200 ሺህ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙባት ጣልያን በኮቪድ-19 ምክንያት 27 ሺህ ሰዎችን አጥታለች።

  8. የሻይ ፍላጎት ጨምሯል፤ አቅርቦት ደግሞ ቀንሷል

    ሻይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በየቀኑ ሚሊዮኖች ሻይ ይጠጣሉ። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ሰቅዞ ከያዘ ወዲህ ደግሞ ሻይ ቅጠል አምራቾች የአቅርቦት መጠናቸው ከፍላጎት ጋር ሊጣጣም አልቻለም።

    እንቅስቃሴ በመገታቱ ምክንያት የሻይ ቅጠል ምርት መሰብሰብ ባለመቻላቸው ምክንያት ነው የሻይ ቅጠል እጥረት ያጋጠመው ተብሏል። የሻይ ቅጠል ዋጋም እየጨመረ ነው።

    የዓለም 82 በመቶ ሻይ ቅጠል ምርትና ንግድን የሚቆጣጠሩት አምስት ሃገራት ናቸው። እነዚህም ቻይና፣ ሕንድ፣ ኬንያ፣ ስሪ ላንካ እና ቪዬትናም።

    ማሕበራዊ ድር-አምባዎች ላይ ሻይ መጠጣት ከኮሮናቫይረስ ይከላከላል መባሉን ተከትሎ የሻይ ፍላጎት እንደጨመረም ይገመታል። ሻይ መጠጣት ከኮሮናቫይረስ እንደሚከላከል ግን ሳይንስ አላረጋገጠም።

  9. የኡጋንዳ ሕዝብ እንደራሴዎች 2.6 ሚሊዮን ዶላር እንዲመልሱ ታዘዙ

    ምክር ቤቱ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ስለ ኮሮናቫይረስ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በሚል 2.6 ሚሊዮን ዶላር (አስር ቢሊዮን የኡጋንዳ ሽልንግ) የመደቡ የሕዝብ እንደራሴዎች ገንዘቡን እንዲመልሱ ታዘዘ።

    ገንዘቡን አንወስድም ያሉ ቢኖሩም፤ እያንዳንዱ የሕዝብ እንደራሴ 5,000 ዶላር ተመድቦለት ነበር።

    ፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ፤ የሕዝብ እንደራሴዎቹ ለራሳቸው ገንዘብ መመደባቸውን “ህሊና ቢስነት” ብለውታል።

    የኡጋንዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ገንዘቡ እንዲመለስ ውሳኔ አስተላልፏል።

    ኡጋንዳ ውስጥ ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች 79 ደርሰዋል። በአገሪቱ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ የሚቀጥለው ማክሰኞ ይነሳል ተብሏል።

  10. በሕንድ የሟቾች ቁጥር 1 ሺህ አለፈ

    ሕንድ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ መሰረት፤ በሕንድ የሟቾች ቁጥር ከአንድ ሺህ በላይ ሆኗል።

    ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው እሮብ ሲሆን፤ 73 ሰዎች ሞተዋል። 31,000 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተይዘዋል።

    ከሌሎች አገሮች አንጻር ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም፤ በቂ ምርመራ እየተደረገ እንዳልሆነ ተመራማሪዎች ተናግረዋል።

    ቫይሮሎጂስቱ ጃኮብ ጆን ለኤኤፍፒ እንደገለጹት፤ ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

    ሕንድ ካለፈው ወር ማገባደጃ ጀምሮ እንቅስቃሴ እንዲቆም አድርጋለች። ውሳኔው እስከቀጣዩ ወርም ተራዝሟል።

  11. የጊኒ ቢሳው ጠቅላይ ሚንስትር ኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

    ጠቅላይ ሚንስትሩ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የጊኒ ቢሳው ጠቅላይ ሚንስትር ኑኖ ጎሜዝ ናቢአም እንዲሁም ሦስት ካቢኔ አባሎቻቸው ኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው።

    ውጤታቸው ማክሰኞ ከታወቀ በኋላ በሆቴል ለይቶ ማቆያ እንደሚገኙ የአገሪቱ ጤና ጥበቃ አስታውቋል።

    እስካሁን በአገሪቱ 70 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል፤ አንድ ሰው ሞቷል።

  12. የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት 4.8 በመቶ አሽቆለቆለ

    አሜሪካ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እንቅስቃሴ ላይ ገደብ መጣሉን ተከትሎ የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት 4.8 በመቶ ማሽቆልቆሉ ተገለጸ።

    እአአ 2014 ላይ ከታየው ውድቀት ወዲህ የዘንድሮው የመጀመሪያው ነው።

    ዛሬ የወጣ አሀዝ እንደሚያሳየው፤ ከ 26 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሥራ አጥ ሆነዋል። በአሜሪካ ታሪክ ንግድ የተቀዛቀዘበት ወቅት መሆኑም ተመልክቷል።

    የአገሪቱ እድገት 30 በመቶ ወይም ከዛ በላይም ሊገታ እንደሚችል ተገምቷል።

    የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ማርክ ዛንዲ፤ ባልተጠበቀ ሁኔታ ምጣኔ ሀብቱ ደቋል ብለዋል።

    ኮሮናቫይረስ የመላው ዓለምን ምጣኔ ሀብት ሳያናጋው በፊት፤ የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት ዘንድሮ ሁለት በመቶ ያድጋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

  13. ዩኬ፡ ሆስፒታል ከገቡ በሽተኞች መከካል አንድ ሶስተኛ ሞተዋል

    Covid-19

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ ሆስፒታል ካቀኑ የዩናይትድ ኪንግደም በሽተኞች መካከል አንድ ሶስተኛው መሞታቸውን አንድ ጥናት ይፋ አደረገ።

    በኮቪድ-19 ላይ የተሠራው ይህ ሰፊ ጥናት እንደሚጠቁመው ሆስፒታል ከገቡ መካከል ከግማሽ በታች ብቻ ናቸው አገግመው መውጣት የቻሉት፤ የተቀሩት ደግሞ አሁንም በመታከም ላይ ይገኛሉ።

    የሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ካለም ሴምፕል የኮቪድ-19 አጥፊነት ከኢቦላ ጋር ተመሳሳይ ነው ይላሉ፤ ኢቦላ ይዟቸው ሆስፒታል ከገቡ ሰዎች መካከል 40 በመቶው መሞታቸውን በመጥቀስ።

    «ሰዎች ይህንን መስማት አለባቸው። በሽታው እጅግ አደገኛ ነው።»

    166 ሆስፒታሎች ውስጥ ያሉ 17 ሺህ በሽተኞች የተሳተፉበት ጥናት እንደሚያመለክተው ለሞት ምክንያት ከሆኑት መካከል ዕድሜና ከመጠን በላይ ውፍረት ይገኙበታል።

    ጥናቱ አክሎም ወንዶች በበሽታው ክፉኛ የመጠቃት ዕድላቸው ሰፊ ነው ይላል።

  14. ታንዛንያ በየእለቱ መግለጫ ባለመስጠቷ ተወቀሰች

    ታንዛንያ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የታንዛንያ መንግሥት በየእለቱ ስለ ኮቪድ-19 መረጃ አይሰጥም ተብሎ መተቸቱን ተከትሉ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ቃሲም ማጃሊዋ ኮሮናቫይረስ የያዛቸው ሰዎች 480 መድረሳቸውን ተናግረዋል።

    መንግሥት የመጨረሻ መግለጫውን የሰጠው ከሳምንት በፊት ነበር። ያኔ በበሽታው የተያዙ ሰዎች 306 ነበሩ።

    በየጊዜው መረጃ አለመሰጠቱ፤ መንግሥት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ደብቋል የሚል ጭምጭምታ እንዲናፈስ ምክንያት ሆኗል።

    ፕሬዘዳንት ጆን ማጉፉሊ፤ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ዜጎች ወደ ሀይማኖት ተቋሞች እንዲሄዱ ማበረታታቸው ይታወሳል።

    ቫይረሱ የሰይጣን ሥራ ስለሆነ ቤተ ክርስትያን ውስጥ አይኖርም ብለውም ነበር።

  15. ጳጳሱ ለኮሮናቫይረስ መድኃኒት አግኝቻለሁ ማለታቸውን አስተባበሉ

    ጳጳስ ሳሜኤል

    የፎቶው ባለመብት, Facebook/Archbishop Samuel Kleda

    በካሜሩኗ ዶዱላ የሚገኙት ጳጳስ ሳሙኤል ክሌዳ፤ ለኮሮናቫይረስ መድኃኒት አግኝቻለሁ ብለዋል በሚል የተሰራጨውን ዘገባ አስተባበሉ።

    ሆኖም ለረዥም ጊዜ በእፅዋት ላይ ምርምር ሲያደርጉ እንደነበር ጠቅሰዋል።

    ባለፈው ሳምንት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ ጳጳሱ “በማውቃቸው እፅዋት በነጻ ህክምና እሰጣለሁ” ብለዋል።

    ጳጳሱ በቴሌቭዥን በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ፤ የኮሮናቫይረስ የያዛቸው ሰዎች የሚያሳዩትን ምልክት በመመርኮዝ ከዕፅዋት የቀመሙትን መድኃኒት ይሰጣሉ።

    “ይህን መድኃኒት ከሰጠኋቸው በኋላ ይሻላቸዋል” ሲሉም ተደምጠዋል።

    ቢሆንም ግን ጳጳሱ “ለኮሮናቫይረስ መድኃኒት አገኘሁ” አላልኩም ብለዋል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ማንኛውም አይነት በግለሰብ ደረጃ የሚዘጋጅ መድኃኒት ኮቪድ-19ን ለመፈወስ እንደማይውል አስጠንቅቋል።

    በመላው ዓለም ተመራማሪዎች ለበሽታው ክትባት ለማግኘት ቀን ከሌት እየሠሩ ይገኛሉ።

  16. ቦሪስ ጆንሰን ወንድ ልጅ ወለዱ

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንና ዕጮኛቸው ኬሪ ሲመንድስ

    የፎቶው ባለመብት, PA MEDIA

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፤ ዕጮኛ ኬሪ ሲመንድስ ወንድ ልጅ 'ከነቃጭሉ' በሰላም መገላገላቸው ተነገረ።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ አፈ-ቀላጤ ጥንዶቹ ሰላም መሆናቸውንና ልጁም ጤናማ መሆኑን አሳውቀዋል።

    በቅርቡ ከኮሮናቫይረስ ያገገሙት ቦሪስ ጆንሰን ዕጮኛቸው ሲወልዱ ለንደን ባለ ሆስፒታል ተገኝተው ነበር ተብሏል።

    «ጠቅላይ ሚኒስትሩና ዕጮኛቸው የአዋላጅ ሐኪሞቹን ከልባቸው አመስግነዋል» ሲሉ ቃል-አቀባያቸው ለመገናኝ ብዙሃን መልዕክት አስተላልፈዋል።

    የ55 ዓመቱ ቦሪስና የ32 ዓመቷ ሲመንድስ ባለፈው መጋቢት ነበር ወንድ ልጅ በሰላም ለመገላገል እየተጠባበቁ እንደሆነ ያሳወቁት።

  17. “ከ 1.5 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ሥራ አጥ ሊሆኑ ይችላሉ”

    ሠራተኛ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    በመላው ዓለም ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ሥራ አጥ ሊሆኑ እንደሚችሉ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት አስታወቀ። ይህም ዓለም ላይ ካሉት ሠራተኞች ግማሽ ያህሉ ሥራ አይኖራቸውም ማለት ነው።

    በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከ 1.3 ሚሊዮን በላይ ደርሰዋል። ወደ 220,000 ሰዎችም ሞተዋል።

    በተለይም መደበኛ ባልሆኑ ዘርፎች የተሰማሩ ሠራተኞች ተጋላጭ መሆናቸው በድርጅቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም በማምረት፣ በማከፋፈል እና በምግብ ዝግጅት ዘርፍ ያሉ ሰዎችን ያጠቃልላል።

    ቫይረሱ መሰራጨት በጀመረበት የመጀመሪያው ወር ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑ መደበኛ ባልሆነ ዘርፍ የተሰማሩ ሠራተኞች ከደሞዛቸው 60 በመቶ ተቆርጦባቸዋል።

    የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ጋይ ሬይደር፤ “ለብዙ ሚሊዮን ሠራተኞች ገቢያቸው ተቋረጠ ማለት፤ የሚበሉት አጡ፣ የወደፊት ሕይወታቸውም ጨለመ ማለት ነው” ብለዋል።

    እነዚህ ሰራተኞች የቆጠቡት ገንዘብ ወይም ብድር የሚወስዱበት የባንክ ካርድም እንደሌላቸው ገልጸው፤ አፋጣኝ እርዳታ እንደሚያሻቸው አሳስበዋል።

  18. እስራኤል ውስጥ የሚሠሩ ፍልስጤማውያን ፈተና ላይ ናቸው

    ፍልስጤማውያን ወደ እስራኤል ሲሻገሩ

    ለወትሮው ከ100 ሺህ በላይ የሥራ ፈቃድ ያላቸው ፍልስጤማውያን እስራኤል ውስጥ በሠፈራ ጣብያዎች ይሠሩ ነበር። የሚከፈላቸው ገንዘብም ላቅ ያለ ነበር።

    326 ፍልስጤማውያን በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ እስራኤል ውስጥና በሠፈራ ጣብያዎች የሚሠሩ መሆናቸው ታውቋል።

    የፍልስጤም አገዛዝ እነዚህ ሠራተኞች ለሁለት ሳምንታት ራሳቸውን ከሰው ንክኪ አፅድተው እንዲቆዩ አዟል፤ ምንም እንኳ ብዙዎቹ እየሾለኩ ወደ ሥራ ቢሄዱም።

    የፍልስጤም ወታደሮች ሠራተኞቹ ወደ እስራኤል የሚያደርጉትን ሕገ-ወጥ ጉዞ በማገድ ላይ ናቸው።

    ከዚህ ቀደም ሠራተኞቹ እንደልባቸው ድንበር ተሻግረው ሠርተው ይመለሱ ነበር፤ አሁን ግን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ይህ ቀላል አልሆነም።

  19. ቻይና ተቃውሞ ብታሰማም አውስትራሊያ ግን የኮቪድ-19 መነሻ ይጣራ እያለች ነው

    አውስትራሊያ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን፤ የኮሮናቫይረስ መነሾ የትና እንዴት እንደሆነ እንዲጣራ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዓለም በሽታው እንዴት ሆኖ እንደተስፋፋ ማወቅ ስለሚሻ መመርመሩ 'ምክንያታዊ' ነው ብለዋል።

    በአውስትራሊያ የቻይና አምባሳደር በገለልተኛ ወገን ይጣራ የሚባለውን ሐሳብ ነቅፈው ቢዘህ ምክንያት ቻይና የአውስትራሊያን ምርቶች ላትገዛ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።

    የቻይናው ቆንፅላ ፅ/ቤት ኃላፊ ያልተጠሩበትን ስብሰባ ድንኳን ሰብረው ገብተዋል ሲሉ የአውስትራሊያ ጤና ሚኒስትር ግሬግ ሃንት ወቅሰዋል።

    በስብሰባው ላይ አውስትራሊያዊው ሚሊዬነር አንድሪው ፎሬስት 10 ሚሊዮን መመርመሪያ ለሃገራቸው እንደሚገዙ አሳውቀዋል።

    ሳይጋበዙ ተገኙ የተባሉት የቻይናው ቆንፅላ ዙ ሎንግ ቻይና ኮቪድ-19ኝን የቀለበሰችበትን መንገድ አንቆለጳጵሰዋል።

    ሚሊዬነሩ አንድሪው ሁለቱ ሃገራት ውጥረታቸውን እንዲቀንሱ ጥሪ አቅርበዋል።

  20. ናይጄሪያ በሚፈለገው መጠን መመርመር አልቻለችም

    የኮሮናቫይረስ ምርመራ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የናይጄሪያ ‘ሴንተር ፎር ዲዚዝ ኮንትሮል’ ኃላፊ ዶ/ር ቺክዌ ኢህክዌዙ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ድጎማ እንዲደረግላቸው ጠየቁ።

    “የኮቪድ-19 ምርመራን በስፋት እያካሄድን በመሆኑ አርኤንኤ (ሪቦኒውክሊክ አሲድ) እንዲሁም ሌሎችም ለምርመራ የሚውሉ መሣሪያዎች ያስፈልጉናል” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።

    ወደ 200 ሚሊዮን ዜጎች ያሏት ናይጄሪያ እስካሁን መመርመር የቻለችው 11,000 ሰዎችን ብቻ ነው። 1,500 ተመርማሪዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    በአንጻሩ፤ 60 ሚሊዮን ነዋሪ ያላት ደቡብ አፍሪካ 185,000 ሰዎች መርምራለች።

    114 ሚሊዮን ዜጎች ያሏት ኢትዮጵያ ደግሞ እስካሁን ከ15,000 ሰው በላይ መርምራለች።

    በርካታ የአፍሪካ አገሮች፤ መመርመሪያ መሣሪያ በማግኘት ረገድ ከእስያና አውሮፓ አገራት ጋር መወዳደር አልቻሉም።