ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ30 ዓመቱ የጅግጅጋ ነዋሪ የኮሮናቫይረስ ተገኘበት
በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 123 የደረሰ ሲሆን 41 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል። ለአለም ስጋት ለሆነው ኮሮና እስካሁን ድረስ የመከላከያ ክትባትም ሆነ የፈውስ መድኃኒት አልተገኘለትም። ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት በሽታውን መከላከል የሚያስችሉ ቀላል መንገዶች አሉ የእጅን ንጽህና በአግባቡ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ቀዳሚዎቹ ናቸው። ከተቻለም ከቤት አለመውጣትና በርካታ ሰው ከሚገኝባቸው ቦታዎች እራስን ማራቅ በተደጋጋሚ እየተመከረ ነው። ቢቢሲ አማርኛም ስለወረርሽኙ ዜናና መረጃዎችን እዚህ ገጽ ላይ የቀጥታ ዘገባዎችን ያቀርባል፤ ይከታተሉ።
የቀጥታ ሽፋን
እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች
ዛሬ የረመዳን የጾም ወር ተጀምሯል። በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች ይህንን ቅዱስ ተብሎ የሚጠራውን የጾም ወር ከሌላው ጊዜ በተለየ ነው የጀመሩት።
ከዚህ ቀደም የነበሩ መሰባሰቦች አሁን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ታግደዋል። በመስጂዶች የሚደረጉ የጀማ ስግደቶች የተከለከሉባቸው አገራትም አሉ።
በቤት ውስጥ ቀኑን ሙሉ ከተጾመ በኋላ ለማፍጠር የሚሰባሰቡ ሰዎችም ቢሆኑ አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ መጨባበጥ፣ መተቃቀፍን እንዲያስወግዱ የጤና ባለሙያዎች እየመከሩ ነው።
ለመላው የሙስሊም ማኀበረሰብ መልካም የረመዳን የጾም ወር እንዲሆን እየተመኘን ጤናችሁን የምትጠብቁበት፣ እናንተም ወዳጆቻችሁም ደህና የምትሆኑበት ወር እንዲሆን ምኞታችንን መሆኑን እንገልፃለን።
ምንጊዜም በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ቸል አትበሉ ደግሞ የኛ መልዕክት ነው። ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ከመላው ዓለም የምንሰበስባቸውን ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ አበይት ዜናዎች ወደ እናንተ ማድረስ እንጀምራለን። አብረን እንሁን!