የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ የሚያላሉ የአውሮፓ አገራት እየተበራከቱ ነው
ቼክ ሪፐብሊክ፡ መንግሥት ጥሎ የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ከዛሬ ጀምሮ አንስቷል።
የአገሪቱ የጤና ሚንስትር እንዳሉት እስከ 10 ሰዎች ድረስ በመሆን በቡድን መንቀሳቀስ ይቻላል።
የውጪ አገር ጉዞም ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ይፈቀዳል ተብሏል። የአውሮፓ አባል አገራት ዜጎችን የኮቪድ-19 ምርመራ እየተደረገላቸው ከሰኞ ጀምሮ ወደ ቼክ ሪፐብሊክ መግባት እንደሚችሉ መንግሥት አስታውቋል።
ጣሊያን፡ ከአውሮፓ ክፉኛ በኮቪድ-19 ከተጠቁ አገራት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ጣሊያን፤ ተጥሎ የሚገኘውን ገደብ ደረጃ በደረጃ እያላለች ትገኛለች።
ከዚህ ቀደም ምግብ እና መድሃኒት የሚሸጡ አነስተኛ ሱቆችን ክፍት አድርጋ ነበር። አሁን ደግሞ የህዝብ ትራንስፖርት፣ የግንባታ እና አምራች ተቋሞቿን ከሰኞ ጀምሮ ክፍት ልታደርግ ነው።
ቤልጂየም፡ መንግሥት የጣለውን እገዳ እንዴት መነሳት እንዳለበት የሚያጤን ኮሚቴ ተቋቁሟል። ኮሚቴው ከአንድ ሳምንት በኋላ አነስተኛ ሱቆች፣ ጸጉር ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች ሳይቀሩ ክፍት እንደሚደረጉ ይጠብቃል።