በኮሮናቫይረስ የተያዙ 8 ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ የህሙማኑ ቁጥር 82 ደረሰ

የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ እንደሚጠቁመው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1.9 ሚሊዮን ደርሷል። ከእነዚህ መካከል ሲሶ ያክሉ የሚገኙት ደግሞ በአሜሪካ ነው። ፕሬዝደንት ትራምፕ ግን አሁንም ቫይረሱን እንቆጣጠራለን እያሉ ነው። ወደ የቀጥታ ዘገባችን ገጽ ቢያመሩ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃዎችን ታገኛላችሁ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. አውስትራሊያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ስጋት ሁለት ሆስፒታሎች ተዘጉ

    የታስማኒያ ግዛት አስተዳዳሪ ፒተር ገትዊን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የታስማኒያ ግዛት አስተዳዳሪ ፒተር ገትዊን

    በአውስትራሊያዋ ታስማኒያ ግዛት ውስጥ ከሚገኙት ሁለት ሆስፒታሎች ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘው በመገኘታቸው ሆስፒታሎቹ ተዘጉ።

    ይህንንም ተከትሎ በሁለቱ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚሰሩ 1,200 ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ለሁለት ሳምንት ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ሊደረግ ነው።

    በዚህም ሳቢያ የሆስፒታሉን ሠራተኞች ጨምሮ ከእነሱ ጋር የቅርብ ንክኪ አላቸው የተባሉ 5 ሺህ ቤተሰቦቻቸው ወደ ለይቶ ማቆያ ይገባሉ ተብሏል።

    በተዘጉት ሁለቱ ሆስፒታሎች ውስጥ ህክምና ሲከታተሉ የነበሩት አብዛኞቹ ህሙማን በአቅራቢያ ወደሚገኝ ሌላ ሆስፒታል የሚዘዋወሩ ሲሆን ሆስፒታሎቹም ከፍ ያለ ከተዋህሲያን የማጽዳት ተግባር ይከናወንባቸዋል ተብሏል።

    በታስማኒያ ግዛት ውስጥ እስካሁን በኮሮናቫይረስ ከተያዙት 144 ሰዎች መካከል 60 ያህሉ ከእነዚህ ሆስፒታሎች ጋር የተገናኙ እንደሆኑ ዘገባዎች አመልክተዋል።

    የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ፒተር ገትዊን ስለርምጃው ሲናገሩ “የበሽታውን መስፋፋትን ለማስቆም ይህ ልናደርገው የምንችለው ተመራጭ ነገር ነው” በማለት ትብብር ጠይቀዋል።

  2. ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ የሚመጡ መንገደኞችን በሙሉ ልትመረምር ነው

    ደቡብ ኮሪያ ከባህር ማዶ በሚመጡ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተቸግራለች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ የሚመጡ ተጓዦችን በሙሉ ልትመረምር ነው።

    ይህም ብቻ ሳይሆን ለሦስት ቀን ራሳቸውን ለይተው ይቀመጣሉ ተብሏል።

    የአገሪቱ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ለዮንሃፕ የዜና ወኪል እንደተናገረው ይህ ውሳኔ ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

    ልክ እንደ ቻይና ሁሉ ደቡብ ኮሪያም ከባህር ማዶ በሚመጡ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተቸግራለች።

    መንግሥት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ወደ ደቡብ ኮሪያ ከገቡ የአሜሪካ መንገደኞች መካከል አብዛኛዎቹ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    አሜሪካ በአሁኑ ሰዓት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ የተጠቃች የኣለማችን አገር ነች።

  3. ኢትዮጵያዊው ዶክተር በቻይና

    የሚመረመር ሰው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በቻይና ህክምና ለማጥናት ከአምስት ዓመታት በላይ ቆይቷል። በጥቅሉ በኢትዮጵያና በቻይና ህክምና በማጥናትና በዘርፉ በማገልገልም ጭምር አስር ዓመት ገደማ መቆየቱን ይናገራል።

    ምንም እንኳ እሱ የሚኖርበት የቻይና ከተማ በኮሮናቫይረስ ከተጠቁት የቻይና አካባቢዎች የተሻለ የሚባለው ቢሆንም መንግሥት በአጠቃላይ የወሰደው እርምጃ ቻይና የቫይረሱን ስርጭት መግታት እንድትችል አድርጓል ይላል።

    ስሙን መጥቀስ ያልፈለገው ይህ በቻይና የሚሰራው ኢትዮጵያዊ የህክምና ባለሙያ የሆነው ዶክተር የኮሮናቫይረስን ስርጭት በመቆጣጠር በኩል ኢትዮጵያ ከቻይና የምትማረው በርካታ ነገሮች አሉ ብሎ ያምናል።

    ለዚህም ኅብረተሰቡ እጁን ቶሎ ቶሎ እንዲታጠብ ማሳሰብ፣ የትምህርት ቤቶችን መዘጋት በርካታ ሰው የሚገኝባቸውን ትላልቅ ስብሰባዎች አለመካሄድ ከተካሄዱም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እውቅና እንዲሆኑ ማድረግና ሌሎችም የኢትዮጵያ መንግሥት በአግባቡ መውሰድና ተፈጻሚ ማድረግ ካለበት ወሳኝ እርምጃዎች መካከል ቀዳሚ መሆናቸውን ይጠቅሳል። ተጨማሪ ያንብቡ ቻይና ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ያደረገችውን ፍልሚያ በቅርብ የተመለከተው የኢትዮጵያዊው ዶክተር

  4. የጁሊያን አሳንጄ እጮኛ በኮሮና ይያዛል የሚል ስጋት እንዳላት ተናገረች

    የዊኪሊክስ መስራች ጂሊየን አሳንጅ

    የፎቶው ባለመብት, WIKILEAKS

    የምስሉ መግለጫ, ጁሊያን አሳንጄ (መካከል)፣ ስቴላ ሞሪስ (በቀን በኩል ሁለተኛ) ከሌሎች ህግ ባለሙያዎቹ ጋር ሆኖ

    የዊኪሊክስ መስራች ጂሊየን አሳንጅ በኢኳዶር ኤምባሲ ተጠልሎ ሳለ የወለዳቸው ሁለት ልጆች እንደነበሩ ይፋ ሆነ።

    ይህን ምስጢር ይፋ ያደረገችው ደግሞ የልጆቹ እናት ስቴላ ሞሪስ ናት።

    ይህን ነገር ለማንም ተናግሬው አላውቅም። አሁን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አባታቸው በእስር ቤት እንዳይሞት ስለሰጋሁ ነው ምስጢሩን የዘረገፍኩት ብላለች ስቴላ።

    እሷ እንደምትለው ከጁሊየን አሳንጅ ጋር በፈረንጆቹ 2015 ቀደም ብሎ እውቂያ ነበራቸው። ከ2015 ወዲህ ደግሞ ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርተው ኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ያሳድጉ ነበር። ተጨማሪ ማንበብ ይፈልጋሉ?ጁሊየን አሳንጅ በድብቅ የወለዳቸው ሁለት ልጆች "ተገኙ"

  5. ኮሮናቫይረስ እንዳለብን እንዴት ማውቅ እንችላለን?

    የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን ከሌሎች የበሽታ ምልክቶች የሚለያቸው ምንድን ነው? አንድ ሰው የተወሰኑ ምልክቶችን በማየቱ 'የኮሮናቫይረስ ይኖርብኝ ይሆን?' ብሎ ራሱን ሊጠረጥር ይገባል? ይህ በዋናነት የሚረጋገጠው በምርመራ ቢሆንም፤ የተወሰኑት ምልክቶችን ቀድሞ ማወቁ በፍጥነት ወደ ሕክምና ለመሄድ ያግዛል።

    የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ኮሮናቫይረስ እንዳለብኝ እንዴት ላውቅ እችላለሁ?
  6. ጎልማሳ ወንዶች ለምን በኮሮናቫይረስ በይበልጥ ይጠቃሉ?

    የትልቅ ሰው ስዕል

    ኮሮናቫይረስ እድሜያቸው በ50ዎቹና በ60ዎቹ ክልል ያሉ ወንዶችን በብዛት ሲያጠቃ ተስተውሏል። በሽታው እነሱን ብቻ ያጠቃል ማለት ባይሆንም እስካሁን ጎልቶ የታየው በዚህ እድሜ ክልል ላይ ነው።

    ከዩናይትድ ኪንግደም የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው፤ በፅኑ የታመሙ ሰዎች አማካይ እድሜ 60 ነው። አብዛኞቹ ደግሞ ወንዶች ሲሆኑ፤ እንደ ልብ ህመም ያለ በሽታ ያለባቸውና ከመጠን ያለፈ ውፍረት የገጠማቸው ናቸው።

    በዚያው አገር ከሞቱት 647 ሰዎች 44ቱ ከ45 ዓመት እስከ 65 ናቸው። ይህም ካጠቃላይ ቁጥሩ 7 በመቶ ነው።

    ሴቶችም ይሁን ወንድ አዛውንቶች የመሞት እድላቸው ከወጣቶች ቢበልጥም፤ የወንድ አዛውንቶች የመሞት እድል በየትኛውም እድሜ ካሉ ሴቶች ይልቃል።

    ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ቻይና፣ ዉሃን የተገኘው መረጃም የሚያሳየውም ይህንኑ ነው።

  7. በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1.8 ሚሊዮን ደረሰ፤ የሟቾች ቁጥር መቀነስ አሳየ

    ፓሪስ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ምንም እንኳ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 1.8 ሚሊዮን እያለፈ ቢሆንም ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች አልጠፉም።

    በፈረንሳይ፣ በጣሊያንና በኒው ዮርክ የሟቾች ቁጥር መጠነኛ መሻሻልን አሳይቷል።

    ለምሳሌ በጣሊያን በ24 ሰዓታት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 431 ነው። ይህ ከረዥም ሳምንታት በኋላ የተመዘገበ ትንሽ ቁጥር በመሆኑ ተስፋን አጭሯል። ከትናንት በስቲያ ብቻ የጣሊያን ሟቾች ቁጥር 619 ነበር።

    ፈረንሳይ በበኩሏ ለሁለተኛ ጊዜ ዝቅተኛ ቁጥር አስመዝግባለች። 315 ሰዎች በ24 ሰዓታት እንደሞቱባት የገለጸቸው ፈረንሳይ ከዚያ ቀደም ብሎ በነበረው ቀን 345 ሰዎች ነበሩ የሞቱባት።

    በዓለም አቀፍ ደረጃ እስካሁን የሟቾች ቁጥር 114 ሺህ ደርሷል። 422 ሺህ ደግሞ አገግሟል። አሐዙን ያጠናቀረው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ነው።

  8. ቻይና በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አገኘች, በቻይና ቫይረሱ ዳግም እንዳያገረሽ ተሰግቷል

    ባለሙያዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቻይና የዉሃን ከተማን እንቅስቃሴ ገደብ ካነሳች በኋላ ከፍተኛ የሚባል ቁጥር ያላቸ ውሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ይህም ሌላ ዙር ወረርሽኝ እንዳይፈጥር ስጋትን ፈጥሯል።

    የቻይና ብሔራዊ የጤና ኮሚሽን እንዳስታወቀው ከሆነ ትናንትና 108 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ 98 የሚሆኑት ከሌላ አገር ወደ ቻይና የገቡ ዜጎች ናቸው። አስሩ ብቻ እዚያው ቻይና የነበሩ መሆናቸው ኮሚሽኑ አስታውቋል።

    የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ሁቤይ ግዛት አዲስ የተያዘ ሰው ባይገኝም ሁለት ቀደም ብሎ የተያዙ ሰዎች ግን ሞተዋል።

    በመላው ቻይና በድምሩ 3341 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሞተዋል።