በኮሮናቫይረስ የተያዙ 8 ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ የህሙማኑ ቁጥር 82 ደረሰ

የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ እንደሚጠቁመው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1.9 ሚሊዮን ደርሷል። ከእነዚህ መካከል ሲሶ ያክሉ የሚገኙት ደግሞ በአሜሪካ ነው። ፕሬዝደንት ትራምፕ ግን አሁንም ቫይረሱን እንቆጣጠራለን እያሉ ነው። ወደ የቀጥታ ዘገባችን ገጽ ቢያመሩ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃዎችን ታገኛላችሁ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በትሪፖሊ የኮሮናቫይረስ ሆስፒታል በተደጋጋሚ የቦምብ ጥቃት ሳቢያ ተዘጋ

    ትሪፖሊ ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠው መንግሥት በተደጋጋሚ በሚሰነዘረው የቦምብ ጥቃት ምክንያት ትሪፖሊ የሚገኘውን የኮሮናቫይረስ ሆስፒታል ለመዝጋት ተገደድኩ አለ።

    የጤና ባለሙያዎች እንዳሉት አል-ካሃደራ የተባለው ሆስፒታል ባሳለፍነው ሐሙስ ዕለትም የቦምብ ጥቃት አስተናግዷል። ይህም በጥቂቃት ቀናት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ ነው ተብሏል።

    ትሪፖሊን ተቆጣጥሮ የሚገኘው መንግሥት ሆስፒታሉ ላይ ለሚሰነዘሩት ተደጋጋሚ የቦምብ ጥቃቶች በጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራውን ታጣቂ ቡድን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

    በተባባሩት መንግሥታት እና በጀነራል ሃፍታር ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ውጊያ ከሰሞኑ ጠንክሮ እየተካሄደ መሆኑ ተነግሯል።

    ጀነራል ሃፍታር የሚመሩት የሊቢያ ብሔራዊ ጦር፤ ምስራቃዊ የሊቢያ ክፍልን ተቆጣጥሮ ይገኛል።

    ሊቢያ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ 19 ሰዎች ያገኘች ሲሆን እስካሁን የመረመረችው ሰው ቁጥር ግን ከ400 አይዘልም ተብሏል።

  2. ፑቲን በቫይረሱ ክፉኛ ልንጠቃ እንችላለን ሲሉ አስጠነቀቁ

    ሩሲያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ልትጠቃ ትችላልች ሲሉ አስጠነቀቁ።

    በሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ አገሪቱ በአንድ ቀን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ማስመዝገቧን ተከትሎ ፑቲን አስጠንቅቀዋል።

    "አሁን እንደምናየው ከሆነ፤ ሁኔታዎች በየቀኑ እየተለዋወጡ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ፤ ነገሮች የሚቀያየሩት እኛ በምንፈልገው መልኩ አይደለም" ሲሉ ቭላድሚር ፑቲን ለባለስልጣናት ተናግረዋል።

    ፕሬዝደንቱ ጨምረውም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ተሳትፎ ላይ የአገሪቱ ጦር ሊሰማራ እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት በሩሲያ 2550 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሪፖርት ተደርጓል። ይህም በአገሪቱ በጠቅላላው በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥርን ወደ 18328 ከፍ አድርጎታል።

    በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት 2/3 የሚሆኑት በመዲናዋ ሞስኮ ይገኛሉ።

  3. ሰበር, የዩኬ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ11 ሺህ አለፈ

    በዩናይትድ ኪንግደም በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 11,329 መድረሱ ተነገረ።

    ይህ ቁጥር በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ በሆስፒታል የሞቱ ሰዎች ቁጥር ብቻ የሚመለከት መሆኑ ተነግሯል።

    የአገሪቱ መንግሥት ባለፉት 24 ሰዓታት በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 717 መሆኑንም አስታውቋል።

  4. ልደት፣ ሠርግ እና ሞት በኮሮና ዘመን

    የኬንያ ጥንዶች

    የፎቶው ባለመብት, FRANCIS GITONGA

    ዶ/ር ሺላ አቲኖ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሟ ተቀይሯል) ብዙ ልጆች አዋልዳለች።

    በቅርቡ ህክምና መስጫ ውስጥ ያገኘቻት ነፍሰ ጡር ግን ከሌሎቹ ትለያለች። የ32 ሳምንት ነፍሰ ጡር የነበረችው ሴት ኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው ኬንያውያን አንዷ ናት።

    ናይሮቢ የሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ሴቲቱን ለማዋለድ ከተመረጡ ዶክተሮች አንዷ የሁለት ልጆች እናቷ ሺላ ናት።

    “ቫይረሱ ያለባትን ሴት አንደማዋልድ ማወቅ እጅግ ከባድ ነው” ትላለች።

    ነፍሰ ጡሯን ለማዋለድ ቀዶ ህክምና ማድረግ ነበረባት። ህክምናውን ስታደርግ ሰውነቷን ብትሸፍንም፤ ከነፍሰ ጡሯ ሴት ሰውነት ፈሳሽ እንደሚወጣና ንክኪ ሊኖር እንደሚችል ማሰብ አስጨንቋታል።

  5. በኢኳዶር በኮሮና የሞቱ ሰዎች አስክሬን በየመንገዱ እየተጣለ ነው

    የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, Coronavirus: Ecuador struggles to bury its victims

    በኢኳዶር በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች አስክሬን በየመንገዱ እየተጣለ ነው።

    በኢኳዶሯ ትልቋ ከተማ ጉዓያኪል ነዋሪዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ዘመዶቻቸውን ሳይቀብሩ ለቀናት መቆየት ግድ ሆኖባቸዋል።

    የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ መንግሥት የሚሞቱ ሰዎችን አስክሬን ለመቅብር ከአቅሙ በላይ ሆኗል።

    ባሳለፈው ሳምንት በኢኳዶር ጉዓያኪል ከተማ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች አሰክሬን በየመንገዱ ተጥሎ የሚያሳይ ምስል የበርካቶችን ትኩረት ስቦ ነበር።

  6. የኮሮና ዘመን ‘ሮሚዮ እና ዡልየት’ የተባሉት ጣልያናውያን

    ሚካኤል እና ፓውላ የዘመናችን ሮሚዮ እና ዡልየት እየተባሉ ነው።

    ሚካኤል ዲአልፓስ 38 ዓመቱ ሲሆን ፖውላ አግኔሊ ደግሞ 39 ዓመት ሆኗታል። ጣልያናውያኑ በፍቅር የወደቁት፤ አገራቸው የዜጎችን እንቅስቃሴ በገደበችበት ወቅት ነው።

    ሚካኤልና ፓውላ በየበረንዳቸው ሳሉ ተያይተው ነበር የተዋደዱት።

    የቬሮና ነዋሪ የሆኑት ሚካኤልና ፓውላ በየቀኑ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ የሚለቀቅ ዘፈን ለመስማት ከቤታቸው ወጥተው በየበረንዳቸው ቆመው ሳለ ተያይተው፤ ተዋደዋል።

    ሙዚቃውን የምታሰማው ቫዮሊን ተጫዋቿ የፖውላ እህት ናት።

    “እህቴ ቫዩሊን ስትጫወት ለመስማት ወደ በረንዳ ወጣሁ። ከኛ ቤት ፊት ለፊት የሚገኝ በረንዳ ላይ ሚካኤልን አየሁት። የጓደኛዬ ወንድም ነው። እንዳየሁንት ‘ምን አይነት ቆንጅዬ ልጅ ነው’ አልኩኝ” ስትል ፓውላ ለቢቢሲ ተናግራለች።

    ሙዚቃው ሲያልቅ ፓውላ ኢንስታግራም ላይ መልዕክት ተላከላት። ላኪው ሚካኤል ነበረ። ‘ፍቅር በዘመነ ኮሮና የሚል መጽሐፍ ልጽፍ እችላለሁ’ ሲል ነበር የጻፈላት።

    የዛን እለት እስከ ንጋት ሲጻጻፉ ነበር። ብዙ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች እንዳሉና የፍቅር ግንኙነት መጀመር እንደሚችሉም ፓውላ ትናገራለች።

  7. ሰበር, የቦሪስ ጆንሰን የምርመራ ውጤት 'ነፃ' ሆነ

    ጠቅላይ ሚንስትር ቦረስ ጆንሰን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚንስትር ቦረስ ጆንሰን

    በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጦ የነበረው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተነግሯል።

    ቦሪስ ጆንሰን ትናንት ከሆስፒታል ከመውጣቸው በፈት በተደረገላቸው ምርመራ ከኮሮናቫይረስ ነፃ መሆናቸውን ተከትሎ ነው ከሆስፒታል እንዲወጡ የተደረጉት ሲሉ የመንግሥት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ ጨምረውም "ጠቅላይ ሚንስትሩ ትኩረታቸው ወደ ቀደመ ጤናቸው መመለስ ላይ ነው እንጂ ለጊዜው ሥራ ላይ አይገኙም" ብለዋል።

    ቦሪስ ጆንስን በኮቪድ-19 መያዛቸው ተከትሎ ለ7 ቀናት በሆስፒታል ቆይታ አድርገው ትናንት ከሆስፒታል መውጣታቸው ይታወሳል።

  8. የአፍሪካ ሕብረት ልዩ የልዑካን ቡድን አቋቋመ

    የአፍሪካ ሕብረት ልዩ የልዑካን ቡድን አቋቋመ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የአፍሪካ ሕብረት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ የሚያስተባብሩ ልዩ ልዑካን መድቧል።

    የሕብረቱ ሊቀ መንበር ሲሪል ራማፎሳ፤ ኮሮናቫይረስ የአህጉሪቱን ምጣኔ ኃብት እንዳያላሽቀው አስፈላጊው እርምጃ ሁሉ የሚወሰድበት ጊዜ ነው ብለዋል።

    እየተፈተነ ያለውን የአፍሪካ ምጣኔ ኃብት ለመታደግ፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት በረዥም ጊዜ የሚከፈል ብድር በመስጠትና በሌሎችም መንገዶች መደገፍ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

    በልዑካን ቡድኑ ውስጥ ከሚገኙት መካከል የቀድሞ የናይጄሪያ እና የደቡብ አፍሪካ የገንዘብ ሚንስትሮች እንዲሁም የቀድሞው የአፍሪካ ልማት ባንክ የሩዋንዳ ቅርንጫፍ መሪ ይጠቀሳሉ።

    የአፍሪካ ሕብረት ባወጣው መግለጫ፤ የልዑካን ቡድኑ በጂ-20 አገራት፣ በአውሮፓ ሕብረት እንዲሁም በሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ቃል የተገባውን ድጎማ ከግብ እንደሚያደርስ ይጠበቃል ብሏል።

    ሀብታም አገራት አቅመ ደካማ አገራት እዳ የሚከፍሉበትን ጊዜ እንዲያራዝሙና እስከነጭራሹ እዳ እንዲሰርዙም እየተጠየቀ ነው። ይህ ገንዘብ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ይውላልም ተብሏል።

    በቅርቡ ይፋ የሆነ ጥናት እንደሚያሳየው፤ 64 ድሀ አገራት ለጤና ዘርፍ ከሚያውሉት ገንዘብ ይልቅ እዳ ለመክፈል የሚያወጡት ይበልጣል።

    ጋምቢያ፣ ጋና፣ ዛምቢያ፣ ላዎስ፣ ሊባኖስ እና ፓኪስታን ከእነዚህ አገራት መካከል ናቸው።

  9. በዩኬ አስክሬን መሸፈኛ ላስቲክ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል ተባለ

    በዩኬ አሰክሬን መሸፈኛ ላስቲክ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል ተባለ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ቀብር አስፈጻሚዎች ለሽያጭም ሆነ አገልግሎት ለመስጠት አስክሬን መሸፈኛ ወይም 'ቦዲ ባግ' ክምችት እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

    አገልግሎት አቅራቢዎቹ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኘ ምክንያት ሰዎች ከሚፈልጉት በላይ እየገዙ ማስቀመጣቸው ለላስቲኩ እጥረት ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።

    ከአገር ውጪ ለማስመጣት በርካታ ሳምንታትን እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።

    ኩባያዎች አስክሬን መጠቅለያ ላስቲኩን ለማምረትም ጥሬ ግብዓት የሚሆነው ፕላስቲክ ፋይበር ከአገር ውስጥ አቅራቢዎች ማግኘት አለመቻላቸው ተጠቅሷል።

    የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤን ኤች ኤስ) የአስክሬን መሸፈኛ በቂ ክምችት አለኝ ቢልም፤ የጤና ባለሙያዎች ግን የሞቱ ሰዎችን በአንሶላ ለመጠቅለል መገደዳቸውን ተናግረዋል።

  10. ቦሪስ ጆንሰንን ያከመችው ነርስ ወላጆች በልጃቸን ኮርተናል አሉ

    New Zeland Tv

    የፎቶው ባለመብት, New Zeland Tv

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን በኮሮናቫይረስ ከተያዙ በኋላ ለ7 ቀናት ያክል በሆስፒታል መቆየታቸው ይታወሳል።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ በሆስፒታል ቆይታቸው የህክምና እርዳታ ላደረጉላቸው ባለሙያዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ከእነዚህም መካከል ነርስ ጄኒ ማክጊ ትገኝበታለች።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ 'ከኒው ዚላንድ አና ከፖርቹጋል የሆኑ ጄኒ እና ሉዊስ የተባሉ ነርሶች ለ48 ሰዓታት ሳይለዩኝ አብረውኝ ቆይተዋል' ሲሉ ተናግረዋል።

    የጄኒ ወላጆችም ልጃቸው ባሳየችው ሙያዊ ብቃት የተሰማቸው ደስታ ገልጸዋል። ማይክ እና ካሮሊን ማክጊ "በልጃችን ኮርተናል" ብለዋል።

    የጄኒ እናት ካሮላይን "ጠቅላይ ሚንስትሩ ጄኒ ወደምትሰራበት ሆስፒታል መወሰዳቸውን ስንሰማ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እንደምታክማቸው ተረድተናል" ብለዋል።

  11. የኒካራግዋ ‘መዘናጋት’ የበሽታውን ስርጭት እንዳያሰፋው ተሰግቷል

    ኒካራግዋ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    መላው ዓለም በኮሮናቫይረስ በተጨነቀበት ወቅት ሕይወት በኒካራግዋ እምብዛም አልተቀየረም። የእግር ኳስ ጨዋታዎች፣ ፌስቲቫሎችም እየተካሄዱ ነው።

    በእርግጥ በአገሪቱ ዘጠኝ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። አንድ ሰውም ሞቷል። የአገሪቱ መንግሥት ግን አንዳችም እርምጃ አልወሰደም።

    ጎረቤት አገሮች ድንበር ዘግተው የዜጎችን እንቅስቃሴ ቢገድቡም፤ የኒካራግዋ ምክትል ፕሬዘዳንት ራዛሪዮ ሙሪሎ ግን ዜጎች የእለት ከእለት ሕይወታቸውን እንዲገፉበት ፈቅደዋል።

    ይህ ብቻ ሳይሆን፤ የምክትሏ ባለቤት የሆኑት ፕሬዘዳንት ዳንኤል ኦርቲጋ ከሳምንታት በፊት ስብሰባ አካሂደዋል።

    ‘ፓን አፍሪካን ኸልዝ ኦርጋናይዜሽን’ የኒካራግዋን መዘናጋት ተችቷል። በሽታውን ለመከላከል እርምጃ አለመወሰዱንም ኮንኗል።

    ቫይረሱ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣም ተሰግቷል።

  12. የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ አዲሱ የህይወት ዘዬ

    አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያደረጉ እስያውያን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ በቅርቡ በሁሉም ስፍራዎች የሚለመድ ነገር መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ዴቪድ ናቦሮ አስታወቁ።

    ናቦሮ ከቢቢሲ ሬዲዮ 4 ጋር በነበራቸው ቆይታ ከኮቪድ-19 ጋር ስንኖር የምንለምደው አዲሱ የህይወታችን ዘዬ ነው ብለዋል።

    ቫይረሱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጥሎን አይሄድም ያሉት ኃላፊው፣ "በቫይረሱ ተይዘው ያገገሙ ሰዎችም የመከላከል አቅም ማዳበራቸውን እናም ክትባቱ መቼ እንደሚገኝ አናውቅም ብለዋል"

    እንደ ኃላፊው ገለፃ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ በመላው ዓለም እንደሚለመድና አብሮን እንደሚዘልቅ እርግጠኛ ነኝ ሲሉ ተናግረዋልል።

  13. በኢትዮጵያ ሦስት ተጨማሪ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው፤ 4 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል

    ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ እንዳስታወቀው ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከተደረገላቸው 247 ሰዎች መካከል ሦስት ሰዎች ኮቪድ-19 ተገኝቶባቸዋል።

    በተጨማሪም ሚኒስቴሩ እስካሁን ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጡት መካከል አራቱ አገግመዋል ብሏል።

    ቫይረሱ የተገኘባቸው ሦስቱም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ የውጪ አገር ጉዞ ታሪክ የሌላቸውና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው ተብሏል።

    ዛሬ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠው ሦስት ሰዎች መካከል ሁለቱ ወንዶች ሲሆኑ ሁለቱም ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር የነበራቸው ንክኪ ገና አለመረጋገጡን የሚኒስቴሩ መግለጫ ገልጿል።

    እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ኮቪድ-19 የተገነባቸው ሰዎች ቁጥር 74 ደርሷል። በተጨማሪም በቫይረሱ የተያዙና ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 14 ደርሷል።

  14. ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን የገቡበት አጣብቂኝ

    ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን

    የፎቶው ባለመብት, Social media

    ዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት በሳኡዲ አረቢያና የመን ድንበር በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለኮሮናቫይረስ ለአደጋ ተጋልጠዋል ሲል አስታወቀ።

    ቢቢሲ ባለፈው ሳምንት ያናገራቸውና በየመንና ሳኡዲ ድንበር አቅራቢያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ባገኘው መረጃ መሰረት ከሁውቲ ታጣቂዎች በደረሰባቸው ጥቃት በየበረሃው መበተናቸውን ገልፀው ነበር።

    የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ሄዶን ኦሊቪያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ድርጅታቸው ስለሁኔታው እንደሚያውቅ አረጋግጠው ይህም እንደሚያሳስበው እና ስጋት እንደገባው ገልፀዋል።

    እነዚህ ስደተኞች ስጋት ውስጥ የወደቁት በጦርነቱ ምክንያት ብቻ ሳይሆን የኮሮናቫይረስ ወረርሽንን ታዛምታላችሁ በሚል ስጋት እንደሆነ ይናገራሉ።

    ኃላፊዋ በመሆኑም በየመን አማፂያንና በሳኡዲ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም አሁን ያለው ስጋት የጦርነት ብቻ ሳይሆን የቫይረሱ መስፋፋት በመሆኑ የስደተኞቹን ስጋት አይቀንሰውም ብለዋል።ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በየመን የሚገኙ ኢትዯጵያውያን ስደተኞች ለኮሮናቫይረስ እንዳይጋለጡ ስጋት አለኝ አለ

  15. የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መምጣት መንግሥታት ከማወቃቸው አስቀድመው ቢልጌትስ እንዴት ሊያውቁ ቻሉ?

    ቢል ጌትስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቴድቶክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች በሰዓት የተገደበ ንግግር የሚያደርጉበት ዓለም አቀፍ መድረክ ነው። ቢል ጌትስ ከአምስት ዓመት በፊት ያደረጉትን ይህን ንግግር ከ25 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በዩቲዩብ መስኮት ተመልክተውታል።

    እርግጥ ነው ይህ በፈረንጆች ማርች፤ 2015 በካናዳ ቫንኩቨር ቢል ጌትስ ያደረጉት ንግግር "እኚህ ሰው ነብይ ነበሩ እንዴ?" የሚያስብል ነው፤ ያለማጋነን።

    ያኔ ማንም ልብ ያላለው ይህ አስገራሚ ንግግራቸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ሚሊዮኖች በድጋሚ እየተመለከቱት ነው።

    የዚህ ንግግራቸው ጭብጥ በመጪው ጊዜ የዓለም ስጋት ኑክሌር ቦምብ ሳይሆን ቫይረስ ነው የሚል ነው።

    በቅርብ ዓመት አንዳች የቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ ሺዎችን እንደሚገድልም ይተነብያሉ። ይህን ለማስረዳትም አንድ በርሜል እያንከባለሉ ነበር ወደ መድረኩ የወጡት።

    "ልጅ ሳለሁ ዋንኛው ስጋት የኒውክሌር ጦርነት ነበር፤ በቤታችን ጓሮ ምድር ቤት ውስጥ ውሃና ምግብ ማጠራቀሚያ እንዲሆነን ይህንን በርሜል እናስቀምጥ ነበር" ሲሉ ንግግራቸው ጀምራሉ።

    አሁን ግን ኒውክሌር ሳይሆን ቫይረስ ነው የዓለም ስጋት ሲሉ ትንቢታቸውን ይቀጥላሉ። ተጨማሪ ለማንበብቢሊየነሩ ቢልጌትስ የኮሮናቫይረስ ሊከሰት እንደሚችል እንዴት ቀድመው ሊያውቁ ቻሉ?

  16. የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ ነው

    ክትባት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኮሮናቫይረስ ክትባት ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡ መስከረም ወር ላይ ዝግጁ እንደሚሆን በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑ ፕሮፌሰር ለቢቢሲ አስታወቁ።

    ፕሮፌሰር ሳራ ጊልበርት ከቢቢሲ ሬዲዩ 4 ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት በክትባቱ ላይ በክሊኒክ ደረጃ የሚደረገው ሙከራ በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል።

    ከዚያም ክትባቱን የማምረቱ ተግባር በፍጥነት ይቀጥላል ሲሉ አስታውቀዋል።

    "በርካታ ቁጥር ያለው ክትባት ማምረት መጀመር አለብን" ካሉም በኋላ "ኩባንያዎች መስራት አለመስራቱን ሳያረጋግጡ አዲስ ክትባት ማምረት ሊጀምሩ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ያልተለመደ አይደም" ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

    በተጨማሪም ፈዋሽ የሆነ ክትባት እንዳለ እየታወቀ ማንም ሰው ሳይጠቀምበት እንዲቀር ደግሞ ማንም አይፈልግም ብለዋል።

    "በፍትነት ማምረት ከጀመርን በቢሊየኖች ማቅረብ እንችላለን" ሲሉ የሚገልፁት ፕሮፌሰር ሳራ፤ "በዚህ ዓመት ላይሆን ይችላል ነገር ግን አሁን ካልጀመርን የሚቀጥለውም ዓመት የምንፈልገው ላይ መድረስ አንችልም" ብለዋል።

  17. የትግራይ ክልል ወደ ክልሉ የሚገቡ መንገደኞችን ለይቶ ማቆያ ማስገባት ጀመረ

    Mekele

    የትግራይ ክልል ከትናንት ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በአሉላ አባነጋ የአውሮፕላን ማረፊያ በኩል ወደ ክልሉ የሚገቡ መንገደኞች ወደ ተዘጋጀላቸው ለይቶ ማቆያ ማዕከል ማስገባት መጀመሩን አስታወቀ።

    በትናንትናው ዕለት ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የተደረጉት ተጓዦች በቁጥር 47 ሲሆን፤ ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ ማዕከሉ ውስጥ እንደሚቆዩ ተነግሯል።

    በማቆያው የሚኖራቸውን ወጪ ሙሉ በሙሉ መንገደኞቹ ይሸፍናሉ ተብሏል።

    አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በቫይረስ የተያዙ ሰዎች እንደተገኙ ከተገለፀበት ጊዜ ጀምሮ፤ ወደ ክልሉ በአውሮፕላን ሲገቡ የቆዩት ሰዎች ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ አልተደረገም ነበር።

    ተጓዦቹም ቢሆን ራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡ አለመደረጉ ይታወሳል።

    ይሁን እንጂ፤ የክልሉ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባካሄደው የቪድዮ ኮንፈረንስ፤ ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ የተተገበረው ራስን ለይቶ የማቆየት ውሳኔን ጨምሮ ቀደም ብሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት አራዝሟል።

    ክልሉ ባራዘመው የአስቸኳይ አዋጅ መሰረት ማናቸውም ወደ ክልሉ የሚገቡ መንገደኞች በሚሄዱበት ከተማ ላይ መንግሥት ባዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ውስጥ ለአስራ አራት ቀናት እንዲቆዩ ያዛል።

    የፌደራል መንግሥቱ ባለፈው ሳምንት ለአምስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል። ይህም ውሳኔ ክልሎች ካወጧቸው የተለያዩ መመሪያዎች ጋር ተጣጥሞ እንሚሄድ መነገሩ ይታወሳል። ተጨማሪ ለማንበብ ፡ልናውቃቸው የሚገቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዝርዝር ይዘቶች

  18. ስፔን አንዳንድ ተቋማት ሥራ እንዲጀምሩ ፈቀደች

    የስፔን ፖሊስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ስፔን ለሳምንታት ጥላው የነበረውን የእንቅስቃሴ እገዳ ከዛሬ ጀምሮ በማላላቷ ብዙም አስፈላጊ አይደሉም ተብለው የተዘጉ ተቋማት ሠራተኞች ወደሥራቸው እንዲመለሱ ፈቀደች።

    መንግሥት የሽታውን መስፋፋት ለመግታት የጣለውን ጥብቅ የደኅንነት መመሪያዎችን እስካከበሩ ድረስ ፋብሪካዎችና የግንባታ ተቋማት ሥራ እንዲጀምሩ ከተፈቀደላቸው መካከል ይገኛሉ።

    ነገር ግን የግድ አስፈላጊ አይደሉም የተባሉ መደብሮች፣ ምግብ ቤቶችና የመዝናኛ ቦታዎች ግን ዝግ ሆነው ይቆያሉ ተብሏል።

    በዚህ ሳምንት ሰዎች ወደ ሥራ መመለስ ስለሚጀምሩ በሕዝብ ትራንስፖርት ለሚጠቀሙ ሠራተኞች የሚሆኑ 10 ሚሊዮን የአፍና የአፍናጫ መሸፈኛ ጭንብሎች ለተጓዦች ይሰጣሉ።

    ስፔን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ ከተመቱ የዓለማችን ቀዳሚ አገራት መካከል የምትገኝ ሲሆን፤ ነገር ግን ከቅርብ ቀናት ወዲህ በበሽታው አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ይገኛል።

    እስከ ትናንት እሁድ ድረስ ስፔን ውስጥ ከ166 ሺህ ሰዎች በላይ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 17ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በወረርሽኙ ህይወታቸው አልፏል።

  19. የተባበሩት መንግሥታት የዱር እንስሳት ገበያዎች እንዲታገዱ ጥሪ አቀረበ

    የዱር እንስሳ ስጋ ገበያ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የተባበሩት መንግሥታት የብዝሃ ሕይወት ኃላፊ ወደፊት የሚኖርን ወረርሽኝ ለማስቀረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የዱር እንስሳት ንግድ እንዲከለከል ጥሪ አቀረቡ።

    ኤልዛቤት ማሩማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የዱር እንስሳትን መግዛትና መሸጥ የሰውን ልጅ ጤና እንዲሁም የዱር እንስሳት ዝርያን አደጋ ላይ የጣለ ተግባር ነው ብለዋል።

    "ላለፉት 60 ዓመታት የተከሰቱ አዳዲስ ወረርሽኞች የመጡት በሰው ልጅ ተግባር ምክንያት ነው። ይህም የዱር እንስሳትን ወደ ሰው ልጅ ማስጠጋት የበሽታዎችን መተላለፍ መጠን ይጨምረዋል" ብለዋል ማሩማ።

    "ስለዚህ እነዚህ የእንስሳ ገበያዎች በአግባቡ ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል፤ ንፁህና ከሕገወጥ የዱር እንስሳ ንግድ ጋር አለመያያዛቸውንም ልናረጋግጥ ይገባል" ብለዋል።

    በእርግጥ ይላሉ ኃላፊዋ "በርካታ በገጠር የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ከኢኮኖሚና ከምግብ ዋስትና ጋር በተያያዘ ከዱር እንስሳ ንግድ ጋር የተገናኘ ህይወት ይመራሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዱር እንስሳት በህይወታቸውና ታርደው ከሚሸጡበት የዉሃን ግዛት የገበያ ስፍራ ነው የተነሳው መባሉን ተከትሎ ቻይና የዱር እንስሳት ንግድ ላይ ጊዜያዊ ገደብ ጥላለች።

    ነገር ግን አሁንም ይህ ገበያ ለወረርሽኙ መነሻ መሆኑ የተጨበጠ ማስረጃ የለም።

  20. የኮሮቫይረስ ወረርሽኝና ሐሰተኛ ወሬዎችን የመቆጣጠር እርምጃ

    ዋትስአፕ ተጠቃሚዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ታንዛኒያ ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሞታለች ተብሎ በስፋት የተወራባት ጋዜጠኛ በህይወት መኖሯን ለማረጋገጥ ተገደደች።

    የታዋቂዋ ጋዜጠኛ ሞት ሐሰተኛ ወሬ ከተነዛ በኋላ በርካታ አድናቂዎቿ ሃዘናቸውን ለቤተሰቦቿ፣ ለጓደኞቿና ለሥራ ባልደረቦቿ ሲገልጹ ነው በቪዲዮ መልዕክት በህይወት መኖሯን ለማረጋገጥ የተገደደችው።

    የታንዛኒያ የኮምዩኒኬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የዋትስአፕ ቡድኖችንን የሚመሩ ሰዎችን ጨምሮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አሉቧልታዎችን፣ የአመጽ መልዕክቶችንና ሐሰተኛ ወሬዎችን የሚያሰራጩ ሰዎችን ተጠያቂ እንደሚያደርግ አስጠንቅቋል።

    የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ አሳሳች መረጃዎችን በሚያሰራጩ ሰዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ በቅርቡ አስጠንቅቀዋል።

    ከእነዚህም መካከል በሕዝብ ትራንስፖርት ውስጥ የኮሮናቫይረስ መንግሥት ከለጋሾች ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲል የፈጠረው ነገር ነው በማለት ሲናገሩ የነበሩ ባልና ሚስት ላይ ክስ መስርቷል።

    በተጨማሪም አንድ ኮሜዲያን ስለኮሮናቫይረስ በመቀለዱ ሐሰተኛ ወሬ በመንዛት ባለስልጣናት ጠርተው አነጋግረውታል።

    እስካሁን ታንዛኒያ ውስጥ 32 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ የተረጋገጠ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም ሦስቱ ሲሞቱ አምስቱ ደግሞ ከበሽታው ድነዋል።