በኢትዮጵያ የዘጠኝ ወር ህፃንን ጨምሮ ተጨማሪ ስምንት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት በባለፉት 24 ሰዓታት የላብራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 264 ሰዎች መካከል ስምንቱ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ከእነዚህም መካከል አንደኛው የዘጠኝ ወር ህፃን ሲሆን በተደረገላቸው ምርመራ እሱም እናቱም ተገኝቶባቸዋል። ምርመራ ከተደረገላቸው መካከል አንዱ ኤርትራዊ ሲሆን ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ይህም በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 52 አድርሶታል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።
በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠ ስምንቱ ሰዎች መካከል አምስቱ ከዱባይ የመጡና በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል ሲደረግላቸው የነበሩ ናቸው።
ከእነዚህም ውስጥ አንድ የ25 ዓመት ሴት ኢትዮጵያዊት ከታይላንድ መጥታ በለይቶ ማቆያ ክትትል ስታደርግ የነበረች ሲሆን፤ አንድ የ19 ዓመት ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ጉዞ ታሪክ የሌለው ሲሆን የንክኪ ሁኔታውም በመጣራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ወጣቱ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳለው ተጠርጥሮ በለይቶ ማቆያ የነበረ ነው።
ሌላኛዋ የ30 ዓመት ሴት ኤርትራዊት ስትሆን ከእንግሊዝ ለንደን መጥታ አዲስ አበባ ውስጥ በለይቶ ማቆያ ክትትል እያደረገች የምትገኝ ነበረች።
በአዲስ አበባ እና በሌሎች የክልል ከተሞች የኮሮናቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ አቅም እየጨመረ መጣቱም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መካከል አንድ ግለሰብ በጽኑ ህሙማን ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ።
አራት ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፤ ሁለት ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
ሌላ ሁለት ግለሰቦች ደግሞ ወደ ሀገራቸው ተሸኝተዋል።