የዓለማችን 1/4ኛ የሚሆነው ሕዝብ እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ ተደርጓል

የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። እስካሁን ድረስ ከ400ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 17ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። በአፍሪካም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዕለት በዕለት እያደገ ነው። እራስዎን ከቫይረሱ ወረርሽኝ ለመከላከል የትኛዎቹን የጤና ባለሙያዎች ምክርን እየተገበሩ ነው። ከዓለማችን የምንሰበስባቸውን ትኩስ መረጃዎች እዚህ በቀጥታ እናደርሳችኋለን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኤርትራ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ 3 ሰዎች ተገኙ

    የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኤርትራ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች ማግኘቷን የኤርትራ ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ከዱባይ ባለፈው ቅዳሜ ወደ ኤርትራ የገቡ የኤርትራ ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።

    በዚህም መሰረት በኤርትራ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አራት ደርሷል።

    ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር በተመሳሳይ አውሮፕላን የመጡና ንክኪ የነበራቸው ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል።

    ይህን ተከትሎም ከዛሬ ዕኩለ ሌሊት ጀምሮ ማንኛውም ወደ ኤርትራም ሆነ ከኤርትራ የሚደረጉ በረራዎች ለሁለት ሳምንታት እንዲቆሙ ይደረጋል ተብሏል።

  2. ኮሮናቫይረስ የወጣቶችንም ነብስ ይነጥቃል

    በ21 ዓመቷ በኮሮናቫይረስ የሞተችው ክሎይ ሚድልተን

    የፎቶው ባለመብት, Facebook

    የምስሉ መግለጫ, በ21 ዓመቷ በኮሮናቫይረስ የሞተችው ክሎይ ሚድልተን

    ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የጤና እክል ያልነበረባት የ21 ዓመቷ ወጣት በኮሮናቫይረስ ከተያዘች በኋላ መሞቷን ወላጆቿ ተናገሩ።

    "ቫይረሱ ልጃችንን ነጠቀን" ያሉት ወላጆች፤ ሁሉም እራሱን ከቫይረሱ ለመጠበቅ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

    ክሎይ ሚድልተን የተባለችው ወጣት ምንም አይነት የጤና እክል ሳይኖርባት በዩናይትድ ኪንግደም በቫይረሱ ከሞቱት መካከል አንዷ ነች ተብሏል።

    የወጣቷ እናት ዲዓን በፌስቡክ ላይ "ይህን ቫይረስ እንደ ቀላል የምትገምቱት፤ እባካችሁ ዳግም አስቡበት። ከእራሴ ልምድ እንደተረዳሁት ይህ ቫይረስ የ21 ዓመት ሴት ልጄን ነጥቆኛል" ብለዋል።

  3. በኬንያ በኮሮናቫይረስ ተይዞ የነበረ አንድ ሰው ዳነ

    ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ

    ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ከደቂቃዎች በፊት ለኬንያ ሕዝብ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ፕሬዝደንቱ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ 3 ሰዎች ዛሬ መገኘታቸውን ተናግረው በጠቅላላው በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ 28 ሰዎች መድረሳቸውን አሳውቀዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ፕሬዝደንቱ “አንድ ከቫይረሱ የዳነ ሰው አስመዝግበናል፤ ይህም ቫይረሱን ድል እንደምንነሳው በትክክል ያሳየ ነው” ብለዋል።

    ፕሬዝደንቱ በመግለጫቸው የሰዓት እላፊም አውጀዋል።

    በዚህ መሠረት ከፊታችን ዓርብ ጀምሮ ከምሽቱ 1 ሰዓት እስከ ንጋት 11 ስዓት ድረስ መንቀሳቀስ ክልክል መሆኑን ገልጸዋል።

    የቫይረሱ ስርጭት በሰዎች ላይ ያሳደረውን ጫና ለመቀነስ፤ መንግሥት የተለያየ መጠን ያለው ታክስ ቅነሳ ማድረጉንም አስታውቀዋል።

  4. በሆላንድ በቫይረሱ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

    Holland

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በሆላንድ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የአገሪቱ ባለስልጣናት አመላከቱ።

    የሆላንድ ባለስልጣናት ባለፉት 24 ሰዓታት 80 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል ያሉ ሲሆን፤ ይህም በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ወደ 356 ከፍ አድርጎታል።

    የ17 ሚሊዮን ዜጎች መኖሪያ በሆነችው ሆላንድ፤ እስካሁን በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 6412 ደርሷል።

    የአገሪቱ ጤና ሚንስትር ብዙ ምርመራዎች አለመደረጋቸውን በማስታወስ፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

    መንግሥት ሰዎች በአንድ ስፍራ እንዳይሰበሰቡ ያስተላለፈውን እገዳ እስከ ግንቦት 24 ድረስ አራዝሞታል።

  5. ጠ/ሚ ዐብይ ኮቪድ-19 በአፍሪካ መቆጣጠር ካልተቻለ ለተቀረው ዓለም ስጋት ሆኖ ይቀጥላል አሉ

    PM Abiy Ahmed

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ፋይናንሻል ታይምስ ላይ ባስነበቡት ጽሑፍ ኮቪድ-19 በአፍሪካ መቆጣጠር ካልተቻለ፤ ቫይረሱ የዓለም ስጋት ሆኖ መቆጠሉ አይቀርም አሉ።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ በወጣው ጽሑፋቸው፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ባለጠጋ አገራት ብዙ ሃብት ፈሰስ እያደረጉ መሆኑን አስታውሰው፤ የአፍሪካ አገራት ግን በድህነት ምክንያት ቫይረሱን ለመከላከል በቂ ዝግጅት አለማድረጋቸውን እና የጤና ስርዓታቸው ይህን እንደማይፈቅድላቸው አመላክተዋል።

    “ኮቪድ-19 ሰው ሰራሽም ይሁን ተፈጥሯዊ ልዩነታችንን ሳይገድበው፤ የቆዳ ቀለማችንን ወይም የምናመልካቸውን አማልክት ሳይለይ በአንድ ቫይረስ የተያያዝን የዓለም ዜጋ መሆናችንን አስተምሮናል” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤በአገራት ድጋፍ በዓለም ጤና ድርጅት በኩል ወረርሽኙን መዋጋት ይኖርብናል ብለዋል።

    ለዚህም የጂ-20 አገራት የአፍሪካ የጤና ስርዓትን ለመታደግ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

    ሙሉ ጽሑፉን እዚህጋር ተጭነው ማግኘት ይችላል።

  6. የዓለማችን 1/4ኛ የሚሆነው ሕዝብ እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ ተደርጓል

    Reuters

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሕንድ 1.3 ቢሊየን ዜጎቿ ከቤት እንዳይወጡ ማዘዟን ተከትሎ ከዓለማችን 7.8 ቢሊዮን ሕዝብ ሩብ ያክሉ እንቅስቃሴው ተገቷል።

    ከሩዋንዳ እስከ ካሊፎርኒያ፤ ከኒው ዮርክ እስከ ኒውዚላንድ ድረስ አዲሱ ወረርሽኝ የሰው ልጆች እንቅስቃሴን አስቁሟል፤ ጎዳናዎችን እንቅስቃሴ አልባ፤ ትልልቅ መገበያያ ህንጻዎችን ደግሞ ኦና አድርጓል።

    የኮሮናቫይረስ ስርጭት መጨመርን ተከትሎ በቤት ውስጥ ሆነው የሚቆዩ ሰዎች ቁጥር ደግሞ እንደሚጨምር ይጠበቃል።

  7. ብልጽግና ፓርቲ "ለተፈጠረው ስጋት እና ጥርጣሬ ይቅርታ እንጠይቃለን" አለ

    የብልጽግና ፓርቲ ቃል አቀባይ አቶ አወሉ አብዲ

    የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Press Agency

    የምስሉ መግለጫ, የብልጽግና ፓርቲ ቃል አቀባይ አቶ አወሉ አብዲ

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል ማህበራዊ እርቀትን መጠበቅ አንዱ ነው።

    ኢትዮጵያም የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ዜጎች በቤት እንዲቆዩ እና ማህበራዊ ግንኙነቶች እንዲቀንሱ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑ ይታወቃል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በተለያዩ የአማራ እና ኦሮሚያ ከተሞች ለፓርቲው አባላት ስልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱ ተዘግቧል።

    ይህም በበርካቶች ዘንድ የቫይረሱን ስርጭት ሊያስፋፋ ይችላል የሚል ስጋትን አሳድሯል።

    የብልጽግና ፓርቲ ቃል አቀባይ አቶ አወሉ አብዲ ለቢቢሲ ሲናገሩ "በስልጠናዎቹ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ከአንድ እስከ ሁለት ሜትር ተራርቀው እንዲቀመጡ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት እየተከናወነ ነው" ብለዋል።

    አቶ አወሉ ጨምረውም "ይሁን አንጂ አንዳንድ ሰዎች ይህን የፖለቲካ አጀንዳ ለማድረግ እየሠሩ ይገኛሉ። ለተፈጠረው ስጋት እና ጥርጣሬ ግን ይቅርታ እንጠይቃለን" ብለዋል።

  8. ኮሮናቫይረስ ባስከተለው የደም እጥረት በአማራ ክልል የቀጠሮ ቀዶ ህክምናዎች በሙሉ ተሰረዙ

    ኮሮናቫይረስ ባስከተለው የደም እጥረት በአማራ ክልል የቀጠሮ ቀዶ ህክምናዎች በሙሉ ተሰረዙ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኮሮናቫይረስ ስርጭት ስጋት ምክንያት በአማራ ክልል በሚገኙ ሆስፒታሎች የደም ለጋሾች ቁጥር በመቀነሱ በቀጠሮ የሚደረጉ ቀዶ ህክምናዎች እንዲሰረዙ መደረጋቸው ተነገረ።

    የባህር ዳር ደም ባንክ ኃላፊ አቶ ምክሩ ሽፈራው ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ለደም ባንኩ በሳምንት እስከ 400 ሰው ደም ይለግስ የነበረ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት አምስት ሰዎች ብቻ ናቸው የለገሱት።

    በዚህ ምክንያት ባንኩ እስከ መጋቢት 20 ደረስ ብቻ የሚያገለግል ደም እንዳለው ገልጸዋል።

    የዚህን ዘገባ ዝርዝር ለማንበብ እዚህ ይጫኑ።

  9. በስፔን የሟቾች ቁጥር ከቻይና በለጠ

    የስፔን ጦር አባላት ቫይረሱን የሚገድል የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ሳሉ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የስፔን ጦር አባላት ቫይረሱን የሚገድል የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ሳሉ

    በስፔን በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቻይና መብለጡ ተነገረ።

    የስፔን ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው አሃዝ መሠረት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 3434 ደርሷል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት በስፔን በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን 738 መሆኑም ተነግሯል።

    እስከ ዛሬ እኩለ ቀን በስፔን በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 47610 መሆኑ ተጠቁሟል።

    አሁን ላይ ስፔን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን በመያዝ ከጣሊያን በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

    እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ከሆነ በጣሊያን 6820 እንዲሁም በቻይና 3285 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል።

  10. በኡጋንዳ የ8 ወር ጨቅላን ጨምሮ ስምንት ተጨማሪ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ተገኙ

    በኡጋንዳ ካምፓላ የሚኖር ግለሰብ ከፎቅ ላይ ሆኖ የኮሮናቫይረስ የሚላለፍባቸውን መንገዶች ለነዋረዎች በድምጽ ማጉያ ሲናገር።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በኡጋንዳ ካምፓላ የሚኖር ግለሰብ ከፎቅ ላይ ሆኖ የኮሮናቫይረስ የሚላለፍባቸውን መንገዶች ለነዋረዎች በድምጽ ማጉያ ሲናገር።

    የኡጋንዳ መንግሥት የ8 ወር ጨቅላን ጨምሮ ስምንት ተጨማሪ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ይፋ አደረገ።

    የጨቅላዋ አባት በቅርቡ ወደ ኬንያዋ ኪሱሙ ግዛት ተጉዞ ነበር ተብሏል።

    በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች መካከል ከለይቶ ማቆያ አምልጠው ወደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ለመግባት ሞክረው የነበሩት ሁለት ቻይናውያን ይገኙበታል።

    ከዚህ በተጨማሪ ከኡጋንዳ ወጥቶ የማያውቅ ሌላ የኡጋንዳ ዜጋ ይገኝበታል።

    በአሁኑ ሰዓት በጠቅላላው በኡጋንዳ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 14 ደርሷል።

  11. ከቤት አትውጡ የሚለውን ትዕዛዝ ተላልፎ የወጣው ሩዋንዳዊ በአዞ ተበላ

    አዞ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በሩዋንዳ መንግሥት የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ጥሶ በመውጣት አሳ ለማስገር የሄደው ግለሰብ በአዞ መበላቱ ተሰማ።

    ግለሰቡ የሚኖርበት የደቡብ ካሞኒ አውራጃ ከንቲባ የሆኑት አሊስ ካይቴሲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ግለሰቡ ቤት ተቀመጡ የሚለውን ደንብ ተላልፎ ወጥቶ ነበር፤ በአካባቢው ከጥቂት ሰዎች ጋር በመሆን ኮሮናቫይረስን ለመግታት የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ አያከብርም ነበር" ብለዋል።

    የሩዋንዳ ባለሰልጣናት ሙሉ በሙሉ የመንቀሳቀስ ገደብ የጣሉት እሁድ ዕለት ነበር።

    በሩዋንዳ እስካሁን ድረስ 40 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ይህም በምስራቅ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታማሚ ያለባት አገር አድርጓታል።

  12. ሰበር, የእንግሊዙ ልዑል በኮሮናቫይረስ ተያዙ

    ልዑል ቻርልስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የ71 ዓመቱ ልዑል ቻርልስ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገለጠ።

    የእንግሊዙ ዘውድ ወራሽ የሆኑት ልዑል ቻርልስ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውንና መጠነኛ ምልክት እንደታየባቸው ከቤተ መንግሥቱ የወጣው መረጃ ያስረዳል።

    ባለቤታቸውም ምርመራ የተደረገላቸው ቢሆንም ከቫይረሱ ነፃ ሆነው ተገኝተዋል።

    ልዑሉ ቫይረሱ ከማን እንደያዛቸው እንደማይታወቅና ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በርካታ ኃላፊነቶችን ሲወጡ እንደነበር ተገልጿል።

  13. የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ኮሮናቫይረስን "የተጋነነ" ሲሉ ተቹ

    የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ዢየር ቦልሶናሮ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ዢየር ቦልሶናሮ የአገራቸው ትልቋ ከተማ ሳኦ ፖሎ በኮሮናቫይረስ የተነሳ የእንቅስቃሴ ገደብ ብትጥልም የቫይረሱን አደጋ ዝቅ አድርገው አቀረቡ።

    በቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት አስተያየት መገናኛ ብዙኀንን "ፍርሃት ቀስቃሾች" ያሉ ሲሆን የግዛቶች አስተዳዳሪዎችና ከንቲባዎችን ደግሞ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ያስቀመጧቸውን ገደቦች እንዲያነሱ ጠይቀዋል።

    ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ምንም እንኳ እድሜያቸው 60ና ከዚያ በላይ የሆኑ ተጋላጭ ቢሆኑም እርሳቸውና እና ሌሎች በርካታ ሰዎች የሚያስፈራቸው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

    "እንደ አትሌት ካለኝ ታሪክ በመነሳት በቫይረሱ ብያዝም የምጨነቅበት ምከንያት አይኖርም። ምንም አይሰማኝም ወይንም ልክ ትንሽ ጉንፋን እንደማለት ነው" ብለዋል።

    የፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ተቺዎች ለኮሮናቫይረስ ተገቢው ትኩረት አልሰጡም ሲሉ ያብጠለጥሏቸዋል።

    ከፕሬዝዳንቱ ጋር ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ አሜሪካ አብረዋቸው የተጓዙ 22 ባለስልጣናት በሙሉ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ግን ሁለቴም ውጤታቸው ነፃ መሆኑን ከመናገር ውጪ በግልጽ ለማሳየት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

    በብራዚል ብቻ 2,200 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን 46 ሰዎችም ሞተዋል።

  14. ፑቲን በሆስፒታል ጉብኝታቸው ወቅት የተለየ የፊት መከላከያ ለብሰው ታዩ

    ፕሬዝዳንት ፑቲን

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በትናንትናው ዕለት ሆስፒታል ተኝተው የሚታከሙ የኮሮናቫይረስ ሕሙማንን ሲጎበኙ የተለየ መከላከያ ጭምብል ለብሰው ታይተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በሩሲያ ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ውሏል ብለው ነበር።

    ይሁን እንጂ መንግሥት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት እንኳ እስካሁን ድረስ 658 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    የሞስኮ ከንቲባ ፕሬዝዳንቱ ሆስፒታሉን በሚጎበኙበት ወቅት በዋና ከተማዋ የሚገኘው የሕሙማን ቁጥር መንግሥት ካለው እንደሚልቅ ነግረዋቸዋል።

    ከንቲባው ሰርጌ ሶቢያኒን "ጫን ያለ ነገር እየተካሄደ ነው" ነበር ያሏቸው።

    በሩሲያ ሲኒማ ቤቶችን፣ የምሽት ክበቦችና የሕፃናት መጫወቻዎች ተዘግተዋል።

    የሩሲያ የሕዝብ እንደራሴዎች ደግሞ ከለይቶ ማቆያ አምልጠው የሚወጡ ሰዎች ላይ እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ ከበድ ያለቅጣት እንዲጣል ሃሳብ እያቀረቡ ነው።

  15. " ...እስኪያልፍ ድረስ ተራራቁ" አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

    አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ሲሆኑ መኖሪያቸው በኒውዮርክ ነው። ትናንት በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕከት ለ24 ሰዓት በማታንቀላፋው ኒውዮርክ ያለውን ሁኔታ ገልፀውታል።

    የሰው ጎርፍ ይተራመስባቸው የነበሩት የኒውዮርክ ጎዳናዎች ጭር ማለት ብቻ ሳይሆን ነዋሪዎቿ ራሳቸውን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመጠበቅ እንዲችሉ አንዳቸው ከሌላኛቸው ተራርቀው እንዲቀመጡ መታዘዙን በማንሳት ከእነርሱ እንማር ብለዋል።

    የኒውዮርክ አገረ ገዢ አንድሪው ኩሞ በግዛቲቱ የኮሮናቫይረስ "እንደ ባቡር በከፍተኛ ፍጥነት እየተምዘገዘገ" በመስፋፋት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

    "ቁጥሩ ከጠበቅነው በላይ ከፍ ብሏል። የቁጥሩ ከፍ ማለትም ከገመትነው ጊዜ ቀድሞ ደርሷል" ብለዋል ለጋዜጠኞች ትናንትና በሰጡት መግለጫ።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  16. በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከተደረገላቸው 576 ሰዎች 555ቱ ነጻ ሆኑ

    የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

    የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Public Health Institute FB

    እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከተደረገላቸው 576 ሰዎች መካከል 555ቱ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው መረጋገጡን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቀ።

    በተጨማሪም 9 ሰዎች የምርመራ ናሙና ሰጥተው የላቦራቶሪ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

    ተቋሙ እንዳለው 1,772 የሚሆኑት ሰዎች በቫይረሱ ተጠርጥረው ለ14 ቀናት ክትትል ሲደረግላቸው ከቆዩ በኋላ የኮሮናቫይረስ በሽታ ምልክት ያልታየባቸው በመሆኑ ክትትላቸው ተቋርጧል።

    ከዚህ ባሻገርም በአሁኑ ጊዜ 1,923 የሚሆኑት ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ሰዎች የ14 ቀናት የጤና ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙ ሲሆን፤ መንግሥት ባዘዘው መሰረት ከውጭ አገር የመጡ ከ519 በላይ መንገደኞች በተመረጡ ሆቴሎች ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል።

    እስካሁን በኢትዮጵያ 12 ሰዎች የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከእነሱም መካከል ሁለቱ ወደሀገራቸው ተመልሰዋል።

    ቀሪዎቹ ታማሚዎችደግሞ በለይቶ የህክምና መስጫ ማዕከል የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን ሁሉም ታማሚዎች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

  17. መንግሥት የከፋ ነገር ቢመጣ ለመቋቋም የሚያስችል በጀት መመደቡን ገለፀ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለኮቪድ-19 ድንገተኛ ዝግጅት የሚውል ገንዘብ እና ሌሎች አቅርቦቶችን የሚያፈላልግ የብሔራዊ አቅርቦት አፈላላጊ ኮሚቴ አዋቀሩ።

    መንግሥት የመጨረሻው አስከፊ ሁኔታ ቢከሰት ለመቋቋም የሚያስችሉ ጠቀም ያለ በጀት መድቦ ግብአቶችን በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው ፌስቡክ ገጽ ላይ እንዳስታወቁት የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ አባላት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለአቅርቦት ማሰባሰቢያ ለግሰዋል።

    አክለውም ግለሰቦችና ተቋማት ይህንን የመንግሥት ጥረት ለመደገፍ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

  18. ሰበር, ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከ4ሺህ በላይ ታራሚዎች ሊለቀቁ ነው, ከሚፈቱት ታራሚዎች መካከል ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኀተመወርቅ እንደሚገኝበት ለማወቅ ተችሏል።

    ጠቅላይ አቃቢተ ህግ አዳነች አቤቤ

    የፎቶው ባለመብት, FDRE Attorney General

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በፌደራል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ከ4ሺህ በላይ ታራሚዎች ሊለቀቁ መሆኑን የጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ።

    አቃቢተ ሕጓ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኀን እንዳስታወቁት እስረኞቹ የሚፈቱት በይቅርታ ነው።

    ከሚፈቱት ታራሚዎች መካከል ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኀተመወርቅ እንደሚገኝበት ለማወቅ ተችሏል።

    በይቅርታው የተካተቱት ታራሚዎች በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ስር ባሉ አምስት ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች እንደሆኑ ጨምረው ማስታወቃቸውን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

    በይቅርታው ከተካተቱት መካከል በግድያ ወንጀል ያልተሳተፉ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዲለቀቁ እና ወደ የመጡበት ሀገሮች እንዲላኩ መወሰኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ መግለጻቸው ተዘግቧል።

    ከእነዚህም ውጪ እስከ ሶስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት የተፈረደባቸው፣ በማረሚያ ቤት ሆነው አንድ ዓመት የአመክሮ ጊዜ የሚቀራቸው እንዲሁም በግድያ ወንጀል ያልተከከሰሱ የሚያጠቡ እና ነፍሰ ጡር እናት ታራሚዎች እንደሚገኙበት አቃቢተ ህጓ በመግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል።

  19. "መጥፎው ነገር ሁላችንም ተጋላጭ ነን፤ ጥሩው ነገር ሁላችንም መፍትሄ ነን" ቦቢ ዋይን

    ቦቢ ዋይን ኡጋንዳዊ ፖለቲከኛና ሙዚቀኛ ነው። የኮሮናቫይረስን ወረርሽኝ ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሙዚቃ ሰርቶ ለአፍሪካውያን ለቅቋል።

    "መጥፎው ነገር ሁሉም ተጋላጭ ነው፤ ጥሩው ነገር ሁሉም መፍትሄ ነው" ይላል በሙዚቃው።

    በዚህ የሙዚቃ ስራው በኢጣሊያ የሆነውን ተመልከቱ እያለ በማስጠንቀቅ፣ እጅን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ መታጠብ እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን ልብ ማለት እንደሚገባ ይገልፃል።

    ሙዚቃውን ስሙትና እየተዝናናችሁ ተማሩበት።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

  20. በደቡብ አፍሪካ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 709 ደረሰ

    ደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 709 መድረሱን ሮይተርስ ዘገበ።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ተናገሩት ብሎ እንደዘገበው በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ማክሰኞ ዕለት ከነበረው ቁጥር በ155 ጨምሯል።

    በፍሪስቴት አውራጃ የሚገኝ ቤተ እምነት የቫይረሱ ስርጭት ማዕከል መሆኑን የጤና ሚኒስትሩ ዝዌሊ ማሂዜ መናገራቸው ተዘግቧል።

    ደቡብ አፍሪካ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሐሙስ ጀምሮ ለ21 ቀናት ሙሉ በሙሉ ማንኛውንም እንቅስቃሴን መገደቧ ይታወሳል።

    ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ከፍተኛ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ያሉባት አገር ናት።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ