በጣሊያን በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቻይና በለጠ

በዓለማችን ላይ በአሁኑ ሰዓት ከ200ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቀ ሲሆን አብዛኞቹ ሰዎች የሚገኙትም በአውሮፓና በእሲያ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ በርካታ የዓለማችን አገራት የተለያዩ እርምጃዎች የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማገድ ይገኝበታል። ዛሬስ በአገራችንና በዓለማችን ላይ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተገናኙ ምን አዳዲስ መረጃዎች አሉ? ቢቢሲ አማርኛ በዚህ የቀጥታ ዘገባው ወደ እናንተ ያደርሳል።

የቀጥታ ሽፋን

ኬንያዊው ኮሮናቫይረስ አለብህ በሚል ጥርጣሬ ተደብድቦ ተገደለ

ኬንያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ሰዎች ኮሮናቫይረስ ይዞታል ብለው የጠረጠሩትን አንድ ግለሰብ ደብድበው መግደላቸውን የአካባቢው ፖሊስ ለቢቢሲ አስታወቀ። የፖሊስ አዛዡ ነህሚያ ቢቶክ እንዳሉት እስካሁን በግለሰቡ ግድያ ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው የሌለ ሲሆን ምርመራ ግን እየተካሄደ ነው።

ግድያው የተፈፀመው በኬንያዋ ክዋሌ ግዛት በአሳ ምርት በምትታወቀውና ምሳምብዌኒ በተባለች መንደር ነው። ቦታው በባህር ዳርቻውና በነጭ አሸዋው ውበት በቱሪስቶችም በእጅጉ የሚዘወተር ነው።