የዛሬው የቀጥታ ዘገባችን በዚህ ይቋጫል።

የዛሬው የቀጥታ ዘገባችን በዚህ ተቋጭቷል።
ወደ እናንተ ስናደርሳቸው የነበሩትን ዘገባዎች ከዚህ በታች መመልከት ይችላሉ።
ነገ ጠዋት በሌላ የቀጥታ ዘገባ እንመለሳለን።
መልካም ምሽት
በዓለማችን ላይ በአሁኑ ሰዓት ከ200ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቀ ሲሆን አብዛኞቹ ሰዎች የሚገኙትም በአውሮፓና በእሲያ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ በርካታ የዓለማችን አገራት የተለያዩ እርምጃዎች የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማገድ ይገኝበታል። ዛሬስ በአገራችንና በዓለማችን ላይ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተገናኙ ምን አዳዲስ መረጃዎች አሉ? ቢቢሲ አማርኛ በዚህ የቀጥታ ዘገባው ወደ እናንተ ያደርሳል።

የዛሬው የቀጥታ ዘገባችን በዚህ ተቋጭቷል።
ወደ እናንተ ስናደርሳቸው የነበሩትን ዘገባዎች ከዚህ በታች መመልከት ይችላሉ።
ነገ ጠዋት በሌላ የቀጥታ ዘገባ እንመለሳለን።
መልካም ምሽት

ጣሊያን ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 427 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አደረገች።
ይህም የሟቾችን ቁጥር 3,405 በማድረስ ቻይና ውስጥ በኮሮናቫይረስ ከሞቱት በላይ አድርሶታል።
ቫይረሱ የተከሰተባት ቻይና የሞቱት ሰዎች ቁጥር 3,242 ነው።

በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ምልክት ታይቶባቸው ከነበሩ ስድስት ሰዎች መካከል አራቱ ነፃ መሆናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የተቀሩት የሁለቱ ሰዎች ውጤት እንደታወቀ ይፋ እንደሚደረግም ተገልጿል።
ወረርሽኙ ወደ ክልሉ እንዳይገባ ጠንካራ እርምጃዎች እየወስድኩ ነው ያለው የክልሉ ጤና ቢሮ፤ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ከአውሮፕላን ማረፊያዎች እና ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር በተጨማሪ የክልሉ መግቢያ በሆኑት በደጀን፣ ደብረ ብርሃን እና ባቲ የሙቀት መለካት ሥራ ተግበራዊ ማድረግ ይጀመራል ብሏል።
ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ከዚህ በታች ያለውን ማስፈንጠሪይ ይጫኑ።
የእስራኤል የደኅንነት ሰራተኞች በኮሮናቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎችን በጥብቅ እየተከታተሉ ሲሆን እራሳቸውን ለመሰወር የሚሞክሩትን ደግሞ አድነው እየያዙ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእንግሊዝ የሚካሄዱ ሊጎች በጠቅላላ እየጨመረ በመጣው የኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት ቢያንስ እስከ ሚያዚያ 22 ድረስ እንደማይካሄድ ተገለጸ።
ይህን ውሳኔ የተላለፈው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ የእንግሊዝ ቻምፒንሺፕ እና ኤፍኤ ካፕ ባወጡት የጋራ መግለጫ ነው።
የእግር ኳስ ማህበሩ ሊጎቹ አሁንም ቢሆን “ላልተወሰነ ጊዜ ሊራዘሙ ይችላሉ” ብሏል።
ሰኔ ሊካሄድ የነበረው የአውሮፓ ዋንጫ እንዲራዘም መደረጉ፤ የእንግሊዝ እና በአውሮፓ የሚገኙ ሊጎች ወድድሮቻቸውን ሰኔ ላይ እንዲያጠናቅቁ ይረዳል ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, HAMLIN FOUNDATION
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ስንብት ላይ የሚገኙ የሰዎች ቁጥር ውስን እንደሚሆን ተነገረ።
የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ታፈሰ እንዳሉት ከነገ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አድናቂዎች፣ ደጋፊዎችና ከየማዕከላቱ የመጡ ሠራተኞች እየተገኙ ስንብት ይደረጋል ብለዋል።
ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ጨምረውም የዶ/ር ካትሪን ሐምሊን የቀብር ሥነ ሥርዓት ሰኞ ከቀኑ 7፡00 በጴጥሮስ ወ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን አንደሚፈፀም ገልጸዋል።
ለሦስት ሳምንታት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለ61 ዓመታት ስለመኖሩት ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን የህይወት ታሪክ ለማንበብ የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ • ካትሪን ሐምሊን ማናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጤና ሚንስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) የኮሮናቫይረስ በሽታ ዘር፣ ቀለም እና ሃይማኖት የለውም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዶ/ር ሊያ ጨምረውም በሽታው ከየትኛውም አገር እና ዜግነት ጋር አይገናኝም ብለዋል።
ትናንት በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ውስጥ ከኮቪድ-19 [ከኮሮናቫይረስ] ክስተት ጋር በተያያዘ ጸረ የውጪ ዜጋ የሆኑ ስሜቶች እየተንጸባረቁ እና ጥቃቶች እየተሰነዘሩ መሆኑን ማመልከቱ ይታወሳል።
ዶ/ር ሊያ በትዊተር ገጻቸው "በሽታው በሁላችንም ላይ የመጣ የጋራ ፈተና ነውና ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በመተባበርና በመረዳዳት በፍፁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ልናሳልፈው ይገባል" ብለዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የስፔን ጤና ጥበቃ ሚንስቴር በኮሮናቫይረስ አዲስ 209 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አደረገ።
ይህም በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ወደ 767 ከፍ አድርጎታል።
በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ13,716 ወደ17,147 አድጓል።
ስፔን ከቻይና፣ ጣሊያን እና ኢራን በመቀጠል በዓለማችን በርካታ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች የሚገኙባት አገር ሆናለች።
የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ፤ በአሁኑ ወቅት 939 ሰዎች በጽኑ ህሙማን ማከሚያ ክፍል ውስጥ እንደሚገኙ እና 1,107 ከበሽታው መዳናቸውን ጨምሮ አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሩዋንዳ ወደ ግዛቷ የሚገቡም ሆነ ከግዛቷ የሚወጡ በረራዎችን አገደች።
በሩዋንዳ ሦስት ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ይህም በአገሪቱ ያለውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 11 አድርሶታል።
አዲስ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል አንድ የ26 ዓመት ሩዋንዳዊ የሚገኝበት ሲሆን ግለሰቡ በቅርብ ጊዜ ወዴትም አገር ለመሄድ በረራ ተጠቅሞ አያውቅም ተብሏል።
ሁለቱ ግን አንዲት ሕንዳዊት በቅርቡ ቫይረሱ የተገኘበትን ሰው ያገባችና አንድ የ45 ዓመት ጎልማሳ ከቤልጂያም በአዲስ አበባ በኩል አድርጎ የመጣ መሆኑ ተገልጿል።
የሩዋንዳ አየር መንገድ ለመንገደኞቹ በረራቸውን ወደሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍ ካልሆነም ገንዘባቸውን እንደሚመልስ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Education Ethiopia
የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ ዛሬ በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መርሃግብር ወደፊት እንገልፃለን ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ተፈታኞች በተዘጉት የትምህርት ቀናት በቤታቸው ዝግጅታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ክቡር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እስከ መጋቢት 21/2012 ዓ.ም ድረስ ለ15 ቀናት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጉን አስታውሰው በዚህ ወቅት ሳይሰጥ የቀረውን ትምህርት በተመለከተ ማካካሻ ትምህርት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, FBC
የኮሮናቫይረስ የፈጠረውን ስጋት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እስረኞች ለቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ከወዳጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ እግድ ጥሏል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በእገዳው ጊዜ ከፍተኛ የጤና ችግር ካልገጠመ በስተቀር እስረኞቹ ከማረሚያ ቤቱ ውጪ ወደ ሚገኙ ሆስፒታሎች እንዲሄዱ አይደረግም።
ኢትዮጵያ ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በርካታ ሰው የሚገኝባቸው ስብሰባዎችና ስፖርታዊ ውድድሮች እንዳይካሄዱ ከማገዷ በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ለ15 ቀናት እንዲዘጉ አድርጋ ተጨማሪ የበሽታውን መስፋፋት መከላከያ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን አሳውቃለች።

አውስትራሊያ ከአርብ ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ባለችው ውሳኔዋ የውጪ አገር ተጓዦች ሙሉ በሙሉ ወደ አገሯ እንዳይገቡ እገዳ ጥላለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ይህንን ውሳኔያቸውን ኮቪድ-19ን ለመከላከል ወሳኝ ነው ሲሉ ገልፀውታል።
ከዚህ እገዳ ቀደም ብሎ ቫይረሱ ከተገኘባቸው አገራት የሚመጡ ግለሰቦችን ወደለይቶ ማከሚያ ማስገባት በራሱ ወደ ግዛቷ የሚመጡ ዜጎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶት ነበር ተብሏል።
በዚህ አዲስ ውሳኔ ደግሞ ከአውስትራሊያንና የአውስትራሊያ የመኖሪያ ፍቃድ ካላቸው ውጪ ማንም ወደ አውስትራሊያ እንዲገባ አይፈቀድለትም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሪሰን እንደተናገሩት ከሆነ በአውስትራሊያ በቫይረሱ ከተያዙ 80 በመቶ ያህሉ ከሌላ አገር የመጡ ወይም ከእነዚህ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ናቸው ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በትናንትናው ዕለት የሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን ወደሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ የደረሱ አራት ጃፓናዊ አገር ጎብኚዎች በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት መግባት ተከለከሉ።
አገር ጎብኚዎቹ የኬኒያ አየር መንገድ አውሮፕላንን የተሳፈሩት ከላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞኖሮቪያ ነበር ተብሏል።
የሴራሊዮን ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ባወጣው መግለጫ ላይ እንደጠቀሰው የአውሮፕላን ማረፊያው ባለስልጣናት በአውሮፕላኑ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ምልክት የሚያሳዩ መንገደኞች እንዳሉ አስቀድሞ ተነግሯቸው ነበር።
አራቱ አገር ጎብኚዎች "ለሕዝብ ደህንነት ሲባል" እንዳይገቡ ተደርገዋል ካለ በኋላ፤ ይዟቸው የመጣው አውሮፕላን ለጊዜው የት እንደሆነ ወዳልተገለፀ ስፍራ እንዲወስዳቸው ተደርጓል ይላል።
በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎች ለይቶ በማከሚያ ስፍራ እንዲቆዩ መደረጉም ተገልጿል።
በሴራሊዮን እንስካሁን ድረስ አንድም በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው አልተገኘም።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እራሳቸውን "የጦርነት ጊዜ መሪ" በማለት የጠሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ላይ "ሙሉ በሙሉ ድል" እንደምታስመዘግብ ተናግረዋል።
አሜሪካ የወታደራዊ ኃይሏን የሕክምና ቡድን ዝግጁ እያደረገች ሲሆን አስፈላጊ የሕክምና ቁሳቁሶችንም በፍጥነት በማምረት ላይ ትገኛለች።
ሁለት የባህር ኃይል መርከብ ሆስፒታሎች ለህሙማን የአልጋ እጥረት ከተፈጠረ በሚል ዝግጁ መደረጋቸው ተገልጿል።
ሌሎችም የወታደራዊ ኃይሉ የሕክምና ቡድን አባላት በተጠንቀቅ ሆነው እንዲጠብቁ ትዕዛዝ መተላለፉ ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ ሁለት የምክር ቤት አባላት ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
በአሜሪካ እስካሁን ድረስ 9 ሺህ 300 ሰዎች በኮቪድ-19 የተያዙ ሲሆን 150 ሰዎች ሳይሞቱ አልቀሩም ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ ወረርሽኙን ለመከላከል ዝግጁ መሆን አለመሆኗን ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ "ያለንበት ሁኔታ ጦርነት ነው" ካሉ በኋላ "ራሴን የማየው የጦርነት ጊዜ ፕሬዝዳንት አድርጌ ነው" ሲሉ አክለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አክለውም የኮሮናቫይረስን በመከላከል ረገድ ከዓለም ሕዝብ ጋር በጋራ መሆናቸውን ገልፀው "የማይታይ ጠላታችን ነው። ያ ደግሞ ምንጊዜም ጠንካራው ጠላት ነው" ብለዋል።
አክለውም "ነገርግን ይህንን የማይታይ ጠላት እናሸንፈዋለን። እንደማስበው ካሰብነው ጊዜ በፈጠነ ሁኔታ እናሸንፈዋለን። ሙሉ በሙሉ ድል፤ የተረጋገጠ ድል ይኖረናል" ብለዋል።

እነዚህን መልካም ልምዶች ይከተሉ፡
ማድረግ የሌለብዎነገሮች፡

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኬንያ በአገሯ ሰባት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ካገኘች በኋላ በአንዳንድ መስጂዶችና አብያተክርስትያኖች የሚደረግ የአምልኮ ስነስርዓትን ከለከለች።
ይህንን እገዳ ተከትሎ አምስት ትልልቅ አብያተክርስትያናት ምዕመኖቻቸውን በቀጥታ የኢንተርኔት ስርጭት እንደሚያስመልኩ ገልፀዋል።
ፕሬስፔቴሪያን እና አንግሊካን አብያተክርስትያኖች የጋብቻ ስነስርዓታቸውን ለመፈፀም መርሃ ግብር አስይዘው የነበሩ አባላቶቻቸውን ወደሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉ ካልሆነም አነስተኛ ቁጥር ያለው ሰው ብቻ እንዲገኝ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኬንያ መዲና የሚገኘው ጃሚያ መስጂድም የጋራ ፀሎት ስነስርዓት እንደማይኖር ገልጿል።
የመስጂዱ ኃላፊዎች ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን በመግለጽ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ያለውን ሁኔታ በተከታታይ እንደሚያስታውቁ ገልፀዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
የዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ኃላፊ አፍሪካ ለከፋ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እንድትዘጋጅ ተናገሩ።
በአፍሪካ እስካሁን ድረስ 16 በኮሮና የተያዙ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ስድስቱ በግብጽ፣ ስድስቱ በአልጄሪያ፣ ሁለት በሞሮኮ አንድ በሱዳንና በቡርኪናፋሶ መሆናቸው ታውቋል።
እስካሁን ድረስ በአፍሪካ አነስተኛ ቁጥር ያለው ታማሚ የተመዘገበ ሲሆን የጤና ባለሙያዎች ግን ቫይረሱ በድንገት በከፍተኛ ሁኔታ ሊሰረራጭና ያለውን የጤና ስርዓት ፈተና ውስጥ ሊጥለው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
የፈረንሳዩ የዜና ወኪል የዓለም ጤና ድርጅቱ ሃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን ጠቅሶ " አፍሪካ ልትነቃ ይገባል፤...በሌሎች አገራት ቫይረሱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንዴት እንደሚጨምር አይተናል" ማለታቸውን ዘግቧል።
በትናንትናው ዕለት በደቡብ አፍሪካ 116 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በአንዴ ሲመዘገቡ ከእነዚህ መካከል ቫይረሱ ከያዛቸው ጋር ንክኪ የነበራቸው 14 ደቡብ አፍሪካውያን እንደሚገኙበት ባለስልጣናት ገልፀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Alamy
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ልጆች ቤት ውለዋል። ወላጆች በዚህ የእረፍት ወቅት ልጆቻቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ለመወሰን ከራሳቸው ትግል የሚገጥሙበት ወቅት ነው።
ልጅዎ ከሌሎች ልጆች ጋር እንዲጫወት ይፈቅዳሉ? ወይስ ከሌሎች ልጆች ጋር አትቀላቀል ሲሉ ይከለክላሉ?
የጤና ባለሙያዎች ማንኛውም ሰው ከሚያስል ወይንም ከሚያስነጥስ ሰው ቢያንስ ሁለት ሜትር መራቅ አለበት ሲሉ ይመክራሉ? እርስዎስ ለልጅዎ ምን ብለው ነግረውት ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደቡብ ኮሪያ ፣ ሴንጋፖርና ቻይና ሁለተኛ ዙር ኮሮናቫይረስ እያጠቃቸው ካሉ የእስያ አገራት መካከል ናቸው። ይህ በአገራቱ እየታየ ያለው ሁለተኛ ዙር ኮሮናቫይረስ ከውጭ የመጣ እንደሆነ ተገልጿል።
የቫይረሱ መነሻ የሆነችው ቻይና እስከ አሁኑ ሰዓት ድረስ የመዘገበችው ምንም ዓይነት አዲስ የኮሮናቫይረስ ታማሚ የለም። ነገር ግን በቅርቡ ከውጭ ወደ ቻይና የገቡ 34 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል።
ደቡብ ኮሪያም ከትናንት እስከ ዛሬ ድረስ 152 አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙባት ሲሆን ከእነዚህ ምን ያህሉ ከውጭ የመጡ ናቸው የሚለው አልታወቀም።
በትናንትናው እለት ሴንጋፖር ደግሞ 47 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ያገኘች ሲሆን ከእነዚህ 33 የሚሆኑት ከውጭ የመጡ ናቸው ተብሏል።
በሌላ በኩል በቻይና ስምንት ሞት የተመዘገበ ሲሆን ሁሉም ኮሮናቫይረስ በተቀሰቀሰባት ሁቤ ግዛት ውሃን ከተማ የተመዘገቡ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, EPA
በጣሊያን በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች መካከል 475 ሰዎች በአንድ ቀን ብቻ መሞታቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት ተናገሩ።
ይህ ቁጥር ቫይረሱ ከተከሰተ ትልቁ ነው የተባለ ሲሆን በአገሪቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥርንም ወደ 3ሺህ አድርሶታል።
በጣሊያን በአሁኑ ሰአት 35,713 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን እስካሁን ድረስ ከበሽታቸው ያገገሙት 4ሺህ ያህሉ ብቻ ናቸው።
ሎምባርዲ በምትሰኘውና ቫይረሱ በተቀሰቀሰባት ግዛት በአንድ ቀን የሞቱ 319 ሰዎች መመዝገባቸው ይታወሳል።
ከቻይና ቀጥሎ በኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቃች አገር ጣሊያን ናት። በዓለማችን ላይ 8ሺህ 758 ያህል ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከእነዚህም አብዛኛው ሞት የተመዘገበው በቻይና ነው።
በዓለማችን ላይ በአሁኑ ሰዓት ከ200ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቀ ሲሆን አብዛኞቹ ሰዎች የሚገኙትም በአውሮፓና በእስያ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።