ሩሲያ ከዩክሬን የብረት ምርትእየሰረቀች ለአፍሪካ እየሸጠች ነው የሚል ወቀሳ ቀረበባት

ታትሟል

የዩክሬን ትልቁ የብረታብረት ኩባንያ ኃላፊ ሩሲያ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ብረት ከወደቦች እና ከፋብሪካዎች ዘርፋለች ሲሉ ከሰሱ።

ሜትኢንቨስት የተሰኘው ኩባንያዋ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዩሪ ራይዘንኮቭ እንደተናገሩት በዩክሬን የተመረቱ ብረቶች ለአፍሪካ፣ ለእስያና እንዲሁም በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች እየተሸጠ ነው ብለዋል።

እየተሸጠ ያለው ብረት በአውሮፓ ባሉ ደንበኞች ቀደም ብሎ የታዘዘ ነው ተብሏል።

ሩሲያ  በቀረበባት ውንጀላ ላይ የተናገረችው ነገር የለም።

በሩሲያ ጦር ለሶስት ወር ተከባ በነበረችው ማሪፖል የሚገኘው የአዞቭስታል ፋብሪካን የሚቆጣጠረው ይህ ኩባንያ ነው።

የሜትኢንቨስት ዋና መቀመጫ የንግድ እና የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል በሆነችው ማሪፖል ሲሆን በሩሲያ ቁጥጥር ስር የገባችውም ግንቦት ወር ላይ ነው።

የአዞቭስታል ፋብሪካ የማሪፖል ከተማ ሙሉ በሙሉ በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ውስጥ ከመግባቷ በፊት ለከተማዋ ነዋሪዎችና ወታደሮች እንደ መጠለያነትም ያገለግል ነበር።

በአዞቭስታል ፋብሪካ በተፈጸመው ጥቃትም 300 ሰራተኞችና 200 የሰራተኞች ዘመዶች መገደላቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

ዩሪ ራይዘንኮቭ እንዳሉት ይህ ፋብሪካ እና በአቅራቢያው ያለ ሌላ ወንድም ፋብሪካ የሆነው ኢሊች 40 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬንን ብረት ያመርታሉ።

በነዚህ ፋብሪካዎች ውስጥ ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ አውሮፖ ውስጥ ያሉ ደንበኞች በሺዎች የሚቆጠር ቶን ብረት አዘው ክፍያም ፈፅመዋል።

ኃላፊው እንደተናገሩት ይህ ክፍያ የተፈጸመበት የብረት ምርት ወደ ሩሲያ እየተጋዘ፣ በአፍሪካ እና እስያ ሃገራት እየተሸጠ መሆኑን ከነዋሪዎች እና ኩባንያው ውስጥ ካሉ ምንጮችን ጠቅሰዋል። 

" የሩሲያ ጦር እየሰራ ያለው በመሠረቱ ዘረፋ ነው።የእኛን ምርት ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ምርቶችም በአውሮፖ ደንበኞች የታዘዙና ክፍያ የተፈጸመባቸው ናቸው።ስለዚህ በመሠረታዊነት ከእኛ ብቻ ሳይሆን እየሰረቁ ያሉት ከአውሮፓውያንም እየሰረቁ ነው” በማለት ራይዘንኮቭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኩባንያው በተቻለ መጠን የተሰረቀውን የብረት ምርት ሰነዶችን እየመዘገበ ሲሆን ወደፊትም ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል።