ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያና ዩክሬን ሴት ምርኮኞችን ተለዋወጡ
ሩሲያ 108 ሴት የጦር ምርኮኞችን ለዩክሬን አስረከበች።
ዩክሬን በበኩሏ 110 ሩሲያዊያንን ለሩሲያ ሰጥታለች።
ከነዚህ መሀል 37 የሚሆኑት ዩክሬናዊያን እጃቸውን የሰጡት በግንቦት ወር በማሪዮፖል አዞቭስቶል ብረት ፋብሪካ ከበባ ውስጥ ለሳምንታት በቆዩበት ወቅት ነበር።
ብዙዎቹ ሩሲያዊ ሴት ምርኮኞች ደግሞ በንግድ ጫኝ መርከብ ውስጥ ባሕርተኛ የነበሩ ናቸው።
አንዳንዶቹ ሴት ምርኮኞች በሩሲያ የሚደገፉ የዶንባስ ክልል ተገንጣይ ቡድን አባላት ናቸው።
በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ ምሥሎች ለጊዜው በውል ካልታወቀ ቦታ ሴት ምርኮኞቹ አገር አቋራጭ አውቶቡስ ሲሳፈሩ የሚያሳዩ ናቸው።
በኋላ ላይ የወጡ ፎቶዎች ደግሞ ምርኮኞቹ በመንግሥት ሥር ባለው ዛፖሬዥያ ደቡብ ዩክሬን ከአውቶቡስ ሲወርዱ ታይተዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት የቮላድሚር ዘለንስኪ ረዳት አንድሪይ የርማክ በማኅበራዊ ሚዲያ 108 ሴት የጦር ምርኮኞች መለቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል።
ከነዚህ ውስጥ አብረው ምርኮኛ የሆኑ እናቶችና ሴት ልጆቻቸው ይገኙበታል ብለዋል።
ከነዚህ ምርኮኞች ዐሥራ ሁለቱ ብቻ የሠራዊት አባላት እንዳልሆኑም አንደሪያ የርማክ ተናግረዋል።
ዴኒስ ፑሽሊን የተባሉ የሩሲያ ባለሥልጣን በበኩላቸው ይህ ሙሉ በሙሉ የሴቶች ብቻ የሆነ የምርኮኞች ልውውጥ በእርግጥም መደረጉን ጠቅሰው ይሁንና ሁለት ዩክሬናዊያን ግን በሩሲያ መቆየትን መርጠዋል ብለዋል።
ኪየቭ ይህን የባለሥልጣኑን ንግግር አላረጋገጠችም፤ አላስተባበለችም።
ዴኒስ ፑሽሊን እንደሚሉት በዩክሬን ከተለቀቁት ውስጥ 80 የሚሆኑት ሩሲያዊያን መርከበኞች ሲሆኑ 30ዎቹ ብቻ የሠራዊት አባላት ነበሩ ብለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ‘ልዩ ዘመቻ’ በሚል ወረራ መፈጸም ከጀመረች አሁን ስምንተኛ ወር ሊይዝ ነው።