የቢቢሲ ሩሲያዊ ጋዜጠኛ በአገሩ የፍትሕ ሚኒስቴር “በውጭ ወኪልነት” ተፈረጀ

ታትሟል

የሩሲያ የፍትሕ ሚኒስቴር ሁለት ታዋቂ ጋዜጠኞችን፣ የቢቢሲ ሩሲያ ዘጋቢ ኢሊያ ባርባኖቭ እና የሳይንስ ዘጋቢ አስያ ካዛንቴሴቫን “የውጭ ወኪሎች” ሲል ፈረጀ።

የቢቢሲ ሩሲያዊ ጋዜጠኛ ባርባኖቭ ስለ ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እንዲሁም ስለ ቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን ቫግነር በሰፊው ዘገባዎችን ሰርቷል። ቢቢሲ ሚኒስቴሩ በጋዜጠኛው ላይ የፈጸመውን ፍረጃ አውግዟል።

“ቢቢሲ ውሳኔውን አጥብቆ አይቀበለውም” ሲል የቢቢሲ መግለጫ አትቷል።

“የውጭ ወኪል” የሚለው መለያ በሩሲያ ውስጥ የከፋ አሉታዊ ትርጓሜዎች አሉት።

መንግሥት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ የሚያወግዙትን ብቻ ሳይሆን የክሬምሊን ፖሊሲዎችን የሚተቹ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ የሚዲያ ድርጅቶች እና የሲቪል ማኅበረሰብን ጸጥ ለማሰኘት ተጠቅሞበታል በሚልም ይተቻል።

በሩሲያ ውስጥ በጣም ታዋቂ ከሆኑት ደራሲዎች አንዱ ቦሪስ አኩኒን በጥር ወር ላይ በዚህ የውጭ ወኪል ተብለው በተፈረጁ ዝርዝር ውስጥ ተካቷል። ደራሲው ፕሬዚዳንት ፑቲንን ለረዥም ጊዜ በሰላ በመተቸት ይታወቃል።

“የውጭ ወኪል” የሚለው ቃል በሶቪየት ኅብረት ዘመን “የሕዝብ ጠላቶች” ተብለው የተፈረጁ ግለሰቦችን ዘመቻን ያስታውሳል።

“የውጭ ወኪሎች” በማኅበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች ህትመቶች ላይ ራሳቸውን በዚህ ለይተው መጥራት የሚገባቸው ሲሆን ገንዘባቸውን በተመለከተም ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።

ሁለቱም ጋዜጠኛች ባርባኖቭ እና ካዛንቴሴቫ በአሁኑ ወቅት የሚኖሩት በውጭ አገራት ነው።

የሩሲያ ወታደሮች ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ የሩሲያ ሳይንቲስቶች እና የሳይንስ ጋዜጠኞች የጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ፈራሚዎች መካከል የሳይንስ ጋዜጠኛዋ ካዛንቴሴቫ አንዷ ናት።

ጋዜጠኛዋ በሩሲያ ጦርነት ደጋፊዎች በመዋከቧ እንዲሁም የምትሰጣቸው ትምህርቶች እና ሌሎች ፕሮግራሞቿ በመሰረዙ አገሪቱን ለቃ ለመውጣት መገደዷን ተናግራለች።

የሩሲያ የፍትሕ ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት መቀመጫውን በላቲቪያ ያደረገውን ባርባኖቭ ስለ ሩሲያ መንግሥት ውሳኔ እና ፖሊሲዎች “የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት” እና “በዩክሬን ያለውን ጦርነት በመቃወም” ከሶታል።

ቢቢሲ በበኩሉ የፍትሕ ሚኒስትሩ ያሳለፈውን ውሳኔ አውግዞ “ቢቢሲ ታማኝ፣ ገለልተኛ የዜና ምንጭ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ይህ አቋሙ ይታወቃል” ሲልም አጽንኦት ሰጥቷል።