‘የክሪፕቶው ንጉሥ’ ሳም ባንክማን በባሃማስ በቁጥጥር ስር ዋለ  

ሳም ባንክማን ፍራይድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ግዙፉ የክሪፕቶከረንሲ ልውውጥ ኩባንያ 'ኤፍቲኤክስ' መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳም ባንክማን ፍራይድ በባሃማስ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

ኩባንያው መክሰሩን በቅርቡ በይፋ አውጆ ወጣቱ ቢሊየነር ከስልጣኑ ለቅቄያለሁ ማለቱ ይታወሳል።

‘የክሪፕቶው ንጉስ’ በባሃማስ በሚገኘው ፍርድ ቤት ማክሰኞ እለት እንደሚቀርብም ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።

ሳም ባንክማን በቁጥጥር ስር የዋለው የአሜሪካ እና የባሃማስ ህጎችን ተላልፎ “የፋይናንስ ጥፋቶች” በመፈጸሙ መሆኑን ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

ኤፍቲኤክስ በዓለም ላይ ግዙፍ ከሚባሉ የክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት ኩባንያዎች አንዱ የነበረ ሲሆን እንዳልነበር ሆኖም በመንኮታኮቱ ባለፈው ወር ኪሳራ በይፋ መዋጁ ይታወሳል።

በርካታ የክሪፕቶ ደንበኞች ዲጂታል ገንዘባቸውን በአንዳች ቁስ ወይም መደበኛ ገንዘብ ለመቀየር ሳይችሉ ቀልጦባቸው ቀርቷል።

ኩባንያው ኪሳራ ማወጁን ተከትሎ በሚካሄደው የፍርድ ሂደት ምን ያህሎቹ ገንዛባቸውን እንደሚያገኙ ግልጽ አይደለም።

ባለሙያዎች በበኩላቸው ካላቸው ገንዘብ ጥቂት ሊሆን እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።

ኤፍቲኤክስ ክሪፕቶን በመሸጥ፣ ዲጂታል ገንዘብን የማለዋወጥ ሥራን የሚሠራ የዲጂታል ግብይት አሳላጭ ኩባንያ ነው። 

ኤፍቲኤክስ ኪሳራ ከመግጠሙ በፊት ሳም 'የክሪፕቶ ዋረን በፌት' ተብሎ ይወደስ ነበር።

በኪሳራ የተንኮታኮተው ኤፍቲኤክስ የክሪፕቶ ግብይት ኩባንያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እና 15 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት ነበረው።

የ30 ዓመቱ ሳም በዓለም ላይ ሁለተኛውን ግዙፉን የክሪፕቶከረንሲ ልውውጥ ኩባንያን በበላይነት ሲያስተዳድር ነበር። 

“ዛሬ አመሻሽ ላይ የባሃማስ ለስልጣናት በአሜሪካ መንግሥት ጥያቄ ከደቡብ ኒውዮርክ በታሸገ የክስ መዝገብ መሰረት ሳሙኤል ባንክማን ፍራይድን በቁጥጥር ስር አውለዋል። የክስ መዝገቡን ጥዋት ከፍተን የምናየው ይሆናል በወቅቱም የበለጠ የምንለው ነገር ይኖራል” በማለት በማንሃተን የሚገኘው የአሜሪካ አቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት በትዊተር ገፁ አስፍሯል።

የዋል ስትሪት ተቆጣጣሪዎችም እንዲሁ በሳሙኤል ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

ባንክማን ፍራይድ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ በአሜሪካ ኮንግረስ ኤፍቲኤክስ ስላጋጠመው መንኮታኮት ምስክርነቱን ይሰጣል ተብሎ ነበር።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት ምስክርነቱን መስጠት እንደማይችል የምክር ቤት አባሏ ማክሲን ዋተርስ አስረድተው በቁጥጥር ስር መዋሉም እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።

የሳሙኤል ባንክማን ፍሪድ ጠበቃ ቢቢሲ ላቀረባላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።