ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራን ፖሊሶች አንዲት ተቃዋሚ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ማድረሳቸው ሌላ ቁጣ ቀሰቀሰ
በኢራን አድማ በታኝ ፖሊሶች በአንዲት ሴት ተቃዋሚ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ሲያደርሱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል መውጣቱን ተከትሎ ቁጣ ተቀስቅሷል።
ፖሊሶቹ ተቃዋሚዎች ለማሰር እየሞከሩ ሳለ ወሲባዊ ትንኮሳ አድርሰውባታል።
ተንቀሳቃሽ ምሥሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር በርካቶች ቁጣቸውን አስተጋብተዋል።
የፖሊስ ኃላፊው ከሥራ እንዲነሳ፣ ተቃዋሚዋም ፍትሕ እንድታገኝ ጠይቀዋል።
የኢራን መንግሥት ደጋፊዎች ሳይቀሩ ወሲባዊ ጥቃቱን አውግዘዋል።
ተቃውሞውን የሚያሳዩ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ መዘዋወርም አላቆሙም።
ኢራን በአሁኑ ወቅት አንድ ወር ያስቆጠረ በአሥርታት ውስጥ ያላየቸው ሕዝባዊ ተቃውሞ ገጥሟታል።
ባለፈው ወር የ22 ዓመቷ ማሳ አሚኒ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለች መሞቷን ተከትሎ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው።
ፖሊስ ወጣቷ የሞተችው በጤና እክል ነው ቢልም ቤተሰቦቿ ለሕልፈቷ ፖሊስን ተጠያቂ አድርገዋል።
በኢራን ውስጥ እና ውጪም በርካታ የተቃውሞ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እየተዘዋወሩ ይገኛሉ።
ከሰሞኑ በቴህራን በሚገኘው አርጀንቲና አደባባይ፣ ፖሊሶች ራሳቸውን የሚከላከሉበት የደንብ ልብስ አጥልቀው አንዲት ሴትን አውራ ጎዳና ላይ ከበው የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ወጥቷል።
ሴቲቷን ወደ ሞተር ሳይክል እንድትወጣ አንደኛው ፖሊስ ሲያስገድዳት ሌላው ፖሊስ ከኋላዋ መቀመጫዋን ይነካል።
ሴቲቷ መሬት ላይ ስትቀመጥ ተጨማሪ ፖሊሶች ይከቧታል።
ከኋላ ድምጿ የሚሰማ አንድ ሴት “ፀጉሯን እየጎተቱት ነው” ትላለች።
ድርጊቱ በተፈጸመት አካባቢ የነበሩ አሽከርካሪዎች ክላክስ በማድረግ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት አሽከርካሪዎች በዚህ መንገድ ተቃውሞ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ሒጃብም ሆነ ሌላ ፀጉር መሸፈኛ ያላደረገችው ሴት፣ ከፖሊሶቹ ሮጣ ስታመልጥም በተንቀሳቃሽ ምሥል ታይቷል።
ከኋላ ድምጿ የሚሰማው ሴት “አያችሁት ፖሊሱ ሲስቅ” ትላለች።
ይህ ተንቀሳቃሽ ምሥል ትክክለኛነቱ በቢቢሲ የፐርሺያ አገልግሎት ተጣርቷል።
የኢራኑ ዜና ወኪል ኢርና እንደዘገበው የቴህራን ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ድርጊቱ እንደሚመረመር ገልጸዋል።
ፖሊስ ጉዳዩን እንደሚመረምር ቢገልጽም “ጠላቶች የሥነ ልቦና ጦርነት በማወጅ ሕዝቡን ለማወክና ነውጥ ለማነሳሳት አሲረዋል” ብሏል።
ድርጊቱ የተፈጸመው በአደባባይ እንደሆነ እና የፀጥታ ኃይሎች በአደባባይ ይህንን ካደረጉ በስውር ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መታሰብ እንዳለበት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተናግረዋል።
አትፌህ በሚል ስም ያለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ “ምን ያህል አስቀያሚ፣ አስጸያፊ እና ጨካኝ እንደሆናችሁ በአደባባይ ልታሳዩን ብላችሁ ነው በእስር ቤቶች ሴቶች ላይ የምትፈጽሙትን ወሲባዊ ትንኮሳ በግላጭ ያደረጋችሁት?” ተብሎ ተጽፏል።
በኢራን እስር ቤቶች እንግልት፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ ሥነ ልቦናዊ ብዝበዛ እና ሌሎችም ስቃዮች እንደሚደርሱ ለዓመታት ሪፖርት ሲደረግ ቆይቷል።
በአደባባይ ተቃዋሚዋ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ሲደርስ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምሥል ተከትሎ፣ በርካታ ኢራናውያን ድርጊቱ ተቃውሟቸውን እንደሚያቀጣጥለው ተናግረዋል።
በርካቶች ተቃውሟቸውን በአደባባይ መግለጽ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ “ቁጣችንን ወደ ተግባር እንቀይራለን” ብለዋል።