ፑቲን ዩክሬንን በከባድ ሚሳኤል መደብደብ ለጊዜው አስፈላጊ እንዳልሆነ ተናገሩ

ታትሟል

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን አሁን ለጊዜው ዩክሬንን በሚሳኤል መደብደብ አቁመናል አሉ።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በዩክሬን ዋና ዋና መሠረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ ተደብድበዋል በሚል ነው።

ፑቲን በዚህ ንግግራቸው ዩክሬንን የማጥፋት ግብ እንደሌላቸውም ተናግረዋል።

ቪላድሚር ፑቲን ከአካባቢው አገራት ጋር ለሚደረግ ቀጠናዊ ስብሰባ በካዛኪስታን ዋና ከተማ አስታና በተገኙበት ወቅት ነው ለጋዜጠኞች ይህን የተናገሩት።

አዳዲስ ምልምል ወታደሮችን በተመለተከ ተጠይቀው ሲመልሱም "እኛ 300ሺህ ወታደር ለማዘጋጀት ሁለት ሳምንት በቂያችን ነው" ብለዋል።

ፑቲን ይህን ይበሉ እንጂ አዳዲስ ምልምል ወታደሮችን ለማዘጋጀት በሚደረግ ጥረት በርካታ ሩሲያዊያን ከአገር ተሰደዋል።

የክተት ጥሪያቸውን በአገር ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ፑቲን የክሪሚያ ድልድይ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ የበቀል ባሉት እርምጃ በርካታ ሚሳኤሎችን ወደ ዩክሬን ከተሞች እንዲተኮሱ አዘው ነበር።

ይህን በተመለከተ ሲናገሩም፣ "29 ተቋማት ላይ ዒላማ አድርገን 22 የሚሆኑትን አውድመናል" ብለዋል።

የቀሩትን ሰባት ተቋማትም አንለቃቸውም እናገኛቸዋለን ብለዋል።

ይሁንና ዩክሬንን በሚሳኤል መደብደቡ ለጊዜው አስፈላጊ ሆኖ ስላላገኘነው አናደርገውም ብለዋል።

 "አሁን ባባድ የሚሳኤል ጥቃት ዩክሬን ላይ ማድረስ አስፈላጊ አይደለም፤ ሌሎች ብርቱ ሥራዎች አሉብን" ብለዋል ለጋዜጠኞች።

ፑቲን ከዚህ ባሻገር ዘመቻ ላይ ስለሚገኙ ወታደሮቻቸው የተናገሩ ሲሆን አሁን ለጊዜው 220ሺህ ሠራዊት መንቀሳቀሱን ከዚህ ውስጥ ግን 16ሺህ ብቻ ወደ ውጊያ መግባቱን አብራርተዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ተጨማሪ ሠራዊት ማንቀሳቀሱ አስፈላጊ አይደለም ብለዋል ፑቲን።

ቢቢሲ ባገኘው መረጃ ፑቲን አዳዲስ ዜጎች ለክተት ጥሪው ምላሽ እንዲሰጡ አዋጅ ማስነገራቸውን ተከትሎ በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ሩሲያዊያን አገር ለቀው ወጥተዋል።

ቢቢሲ ባገኘው ሌላ ሁነኛ መረጃ ደግሞ አዳዲስ ምልምል ወታደሮች ወደ ግንባር ከመላካቸው በፊት የሚሰጠው ምልመላ የለብለብ መሆኑን ተረድቷል።

ይህ በእንዲህ ሳለ የቢቢሲ ሩስክ አገልግሎት በዚህ የዩክሬን ጦርነት በሞት የተለዩ ከ7ሺህ 500 በላይ የሩሲያ ወታደሮች ማንነትን ማወቅ የሚያስችል መረጃን አግኝቷል።

በጦርነቱ የሞቱ ሩሲያዊያን አሐዝ ከዚህ በብዙ ቁጥር ሊልቅ እንደሚችል ግምቶች አሉ።

ይህ በእንዲህ ሳለ በዩክሬን ጥቃት ከባድ ጉዳት ደርሶበታል የተባለው የክሪሚያ ድልድይ በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ሙሉ በሙሉ ተጠግኖ ወደ ሥራ ይመለሳል ተብሏል።

ቢሊየነሩ ኤሎን መስክ በበኩሉ የሮኬት ኩባንያው ስፔስ ኤክስ ለዩክሬን የሚያቀርበውን ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት በዘላቂነት ሊቀጥል እንደማይችል ፍንጭ ሰጥቷል።

በዩክሬን የኢንተርኔት አገልግሎት በማይደርስባቸው አካባቢዎች ይህን አገልግሎት እየሰጠ ያለው የኤሎን መስክ ኩባንያ ነው።

በሌላ ዜና የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን ሩሲያ ያቀረበችውን አዲስ የጋዝ መስመር ማዕከል ሐሳብ ደግፈዋል።

ምክረ ሐሳቡ ቱርክ ወደ አውሮፓ ለሚተላለፈው የጋዝ መስመሮች  ማዕከል እንድትሆን ትልምን የያዘ ነው።

በሌላ ዜና የዩኬ የወታደራዊ ስለላ ድርጅት የሩሲያው ዋግነር የግል ወታደራዊ ተዋጊ ኩባንያ በዶኔስክ ክልል የሚገኙ ሁለት ገጠር ቀበሌዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ደርሶበታል።

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ላለፉት ስምንት ወራት አላባራም።