ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
‘ዩኒቨርስቲዬ ዲግሪዬን ወስዶ ብሬን ይመልስልኝ’ ያለው ወጣት እያነጋገረ ነው
አንድ የ36 ዓመት ናይጄሪያዊ ተመርቆ ሥራ ማጣቱ አበሳጭቶት ለተማረበት ዩኒቨርስቲ ያልተመለደ ጥያቄ አቅርቧል።
ኦሉዳሬ አላባ የተባለው ይህ ሰው ለዩኒቨርስቲው ያቀረበው ጥያቄ ለትምህርት የከፈለው ገንዘብ እንዲመለስለት ነው።
በፈረንጆቹ 2015 የተመረቀው ይህ ግለሰብ ዲግሪውን ይዞ ሥራ ለማግኘት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም።
ሆኖም ዲግሪው ሥራ ሊያስገኝለት ስላልቻለ 'በቃ እንዲያውም ዲግሪውን ወስዳችሁ ብሬን መልሱልኝ' ብሏል።
ይህ ናይጄሪያዊ ለ5 ዓመታት ተምሮ ዲግሪ ያገኘው በእርሻና የገጠር ልማት ዘርፍ ነበር።
ይህ ያልተመለደ ጥያቄ የቀረበለት ዩኒቨርስቲ ለጊዜው ምላሽ ባይሰጥም የኦሉዳሬ አላባ ጥያቄ የብዙዎችን ስሜት በመንካቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገንዘብ እየተዋጣለት ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት ይህ ናይጄሪያዊ ባለ ዲግሪ ወደተማረበት የመንግሥት ዩኒቨርስቲ ሲያቀና በቪዲዮ ተቀርጾ ነበር።
በደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ የሚገኘው ላዶኬ አኪንቶላ የሚባለው ዩኒቨርስቲ ተመልሶ በመግባት አስተምራችሁ የጫናችሁልኝ ዲግሪ ምንም አልረባኝም፤ ዲግሪውን ውሰዱ ብሬን መልሱ ብሏል።
ይህ ያልተመለደ ጥያቄ በማኅበራዊ ሚዲያ ከተጋራ በኋላ ሰፊ መነጋገሪያ ሆኖ ብዙዎች ለሥራ አጡ ከንፈር መጠውለታል።
ከንፈር መምጠጥ ብቻም ሳይሆን ገንዘብ ተዋጥቶለታል።
ይህ ባለ ዲግሪ ኋላ ላይ ለቢቢሲ ዩሩባ እንደተናገረው ዲግሪውን ለማግኘት 5 ዓመታት እንደለፋና ብዙ የብድር ገንዘብ እንደከሰከሰ አብራርቷል።
‘አባቴ 90 ዓመቱ ነው። ስሞት ልትቀብረኝ ብር ትበደራለህ ወይ ብሎ አሳስቦት ጠየቀኝ። ተበድሮ ከፍሎ ያስተማረኝን አባቴን እንኳ ለመቅበር ዲግሪዬ አልታደገኝም’ ብሏል።
ይህን የአባቱን ስሜት የሚነካ ንግግር ሰምቶ ከተረበሸ በኋላ በቀጥታ ወደ ዩኒቨርስቲው እንደሄደ ነው የተናገረው።
‘በዚህ ስሜት ከቤት ወጥቼ ነው የሄድኩት። ሙሉ ወንድ የመሆን ስሜት አይሰማኝም ነበር’ ብሏል።
ምንም እንኳ ዩኒቨርስቲው ገንዘቡን ሊመልስለት ባይችልም አብረውት የተማሩት እና ሌሎች በነገሩ ስሜታቸው የተነካ ናይጄሪያዊያን ወደ 1200 ዶላር ገንዘብ አሰባስበው ሰጥተውታል።
በዚህ ገንዘብ ላፕቶፕና ተያያዥ ቁሳቁሶችን ገዝቶበታል።
ዓላማውም በበይነ መረብ ለኦንላይን የሚሆኑ ቪዲዯዎችን በመሥራት ራሱን ለመቻል መሞከር ነው።
ምናልባትም ዩቲዩበር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።