የመጀመሪያዎቹ ቤተ እስራኤላውያን በ"ዘመቻ ሙሴ" በምሥጢር የተወሰዱበት 40ኛ ዓመት ሲታወስ

ቤተ እሰራኤላውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ጊዜው ከዛሬ አርባ ዓመታት በፊት ነው። የወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር አንድ ሃሳብ ለአገሪቱ የስለላ ተቋም ሞሳድ ያቀርባሉ። ይህም በኢትዮጵያ የሚገኙ አይሁዶችን በምሥጢራዊ ተልዕኮ በድብቅ በማስወጣት ወደ እስራኤል መውሰድ ነበር።

ይህ ዕቅድ ሰምሮ ስምንት ሺህ ገደማ ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጰያ በማስወጣት ወደ ሱዳን አሻግሮ ከዚያም ወደ መካከለኛው ምሥራቋ አይሁዳዊት አገር እስራኤል ከደረሱ 40 ዓመት ሆናቸው።

በ1977 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ከነበረው አስከፊ ረሃብ በተጨማሪ ጦርነትም ብዙዎችን አፈናቅሏል። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች መዳረሻቸው ጎረቤት ሱዳን ነበረች።

በዚህ ወቅት ነበር በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ከሚኖሩበት ሰሜናዊ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ተነስተው ሱዳን የደረሱት። እነዚህ ቤተ እስራኤላውያን ሱዳን ውስጥ ወደሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ለመድረስ ለሳምንታት በእግር ተጉዘዋል።

ውጣ ውረዱ የብዙዎችን ሕይወት ቀጥፏል። በስደት ላይ ወላጆች ልጆቻቸውን በሞት ተነጥቀዋል። ልጆችም ያለ ወላጅ ቀርተዋል።

የተስፋይቱ ምድር ወደሚሏት እስራኤል ለመድረስ ጥቂት ንብረታቸውን ሸክፈው በመቶ የሚቆጠር ኪሎ ሜትር በእግር ለመጓዝ ተገደዋል። ይህንን ጉዞ በባዶ እግር ለመጓዝ የተገደዱትም ጥቂቶች አይደሉም።

በጉዞው ወቅት እስከ አራት ሺህ የሚደርሱት ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ ይገመታል።

መጠለያው ውስጥም በቂ ምግብ እና መድኃኒት አልነበረም።

ኢትዮጵያውያኑ መጠለያ ውስጥ ለወራት ከቆዩ በኋላ "ኦፕሬሽን ሞሰስ" (ዘመቻ ሙሴ) ተጠንስሶ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራኤላውያን አይሁዶች ወደ እስራኤል ከተወሰዱባቸው ዘመቻዎች አንዱ ተወለደ።

ቤተ እስራኤላውያኑ ሱዳን ከደረሱ በኋላ ከእስራኤል የደኅነነት ተቋም ሞሳድ ጋር በተደረገ ግንኙነት አንድ ዕቅድ ይወጣል። የዕቅዱ ማጠንጠኛ ደግሞ አሮስ ነበር። ሱዳን በረሀ ላይ በቀይ ባሕር ዳርቻ ተንጣሎ የሚገኝ የመዝናኛ፤ ቅምጥል ሪዞርት ነው።

የሱዳን ቱሪስት ኮርፖሬሽን የሚኩራረበት የመዝናኛ ቦታ ነበር። ተቋሙ ሥፍራውን እያከራየ ረብጣ ገንዘብ ወደ ካዝናው የሚያስገባበት ነበር።

ይህንን የበረሀ ገነት ተጠቅሞ ሞሳድ "ኢትዮጵያዊ ቤተ-እስራኤላዊያንን ለመታደግ" ያሰበውን ሲያሳካ ቆይቷል።

በአውሮፕላን የሚጓዙ ኢትዮጵያውን አይሁዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአውሮፕላን የሚጓዙ ኢትዮጵያውን አይሁዶች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሞሳድ ይህንን ሪዞርት ተጠቅሞ ስምንት ሺህ ገደማ ሰዎችን በድብቅ ወደ እስራኤል ለማስገባት ችሏል።

የቢቢሲው ጋዜጠኛ ራፊ በርግም ይህንን አስደናቂ የስለላ ተልዕኮን ታሪክ የሚያወሳ "ሬድ ሲ ስፓይስ" የተባለ መጽሐፍ ጽፏል

ኔትፍሊክስ ደግሞ "ዘ ሬድ ሲ ዳይቪንግ ሪዞርት" በሚል ሞሳድ ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለመውሰድ የነበረውን አደገኛ እና መስዋዕነት የተሞላበት ተልዕኮን የሚያሳይ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ፊልም ለዕይታ አብቅቷል።

በወቅቱ እስራኤል ከደረሱት ውስጥ አብዛኞቹ ወጣቶች እና ህጻናት ነበሩ።

በዘመቻ ሙሴ እስራኤል ከገቡ በኋላ የወለዷቸውን ልጆቻቸውን እስራኤል፣ አብረሃም፣ ሞሼ እና ማዛል የሚል ስም አውጥተውላቸዋል።

በተጨማሪም ኔታንያ፣ ፔታህ ቲክቫህ፣ አሽኬሎን እና ሃደራን በመሳሰሉ የእስራኤል ከተሞች በስፋት በመኖር ላይ ይገኛሉ። እነሆ ኢትዮጵያውያን አይሁዶችን ወደ እስራኤል ያደረሰው ዘመቻ ሙሴ በዚህ ሳምንት 40 ዓመት ሞልቶታል።

ኢትዮጵያውን አይሁዶችን ከ40 ዓመት በፊት ወደ እስራኤል ለመውሰድ የተደረገውን ዘመቻ በሚመለከት በእየሩሳሌም አንድ ዝግጀት ተካይሂዶ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የስተደኞች ሚኒስትሩ ኦፊር ሶፌር በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

የስተደኞች ሚኒስትሩ ኦፊር ሶፌር ዘመቻ ሙሴን አወድሰው ለስኬቱ የአገሪቱ ጦር፣ ሞሳድ፣ የአይሁድ ተቋማት እና ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ሚናቸው የጎላ እንደነበር አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው የዘመቻ ሙሴ 40ኛ ዓመት ከአስር ዓመት በላይ በሐማስ እስር ስር ቆይቶ ነጻ የወጣው አቬራ መንግሥቱ በተለቀቀ ማግስት መከበሩን ጠቅሰዋል።

"ጦራችን ሐማስ ላይ ላሳደረው ተጽዕኖ እና ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምስጋና ይግባ እና አቬራ መንግሥቱን ጨምሮ በርካታ ታጋቾችን አስለቅቀናል" ብለዋል።

"ሁሌም ዓላማችን አምነን ቆመናል። ምስጋና ለፈጣሪ ይግባውና ተሳክቶልናል። አቬራን ጨምሮ ሌሎች ታጋቾች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ እንደግፋቸዋል" ማለታቸውን ጄሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።

የስደተኞች ሚኒስትሩ በበኩላቸው ከመስከረም 26 የሐማስ ጥቃት ወዲህ (በጋዛ ጦርነት የተሳተፉትን ጨምሮ) 33 ቤተ እስራኤላውያን ሕይወታቸው አልፏል።

ኔታንያሁ ደግሞ በጦር ሜዳ እስራኤልን ለመከላከል ባከናወኑት ተግባር የጀግንነት ሚና ተጫውተዋል ብለውም አወድሰዋቸዋል።

"ሁለተኛው እና ሦስተኛው ትውልድ በእስራኤል ጦር ውስጥ እስከ አመራርነት በመሳተፍ እንዲሁም የአስራኤልን ኢኮኖሚ በማሳደግ አገሪቱ ልዩ መሆኗን አሳይተዋል" ሲሉ አክለዋል።

ኢትዮጵያውያን በአይሁድ መንግሥት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እና ዘረኝነትን እና መድልዎን ለመዋጋት ቃል ገብተዋል።

"የቤተ እስራኤላውያን ማኅበረሰቦችን አስደማሚ ጽዮናዊ ታሪክ ማሠራጨት እንቀጥላለን" ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን አይሁዶች በጀልባ ሲጓጓዙ
የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያውያን አይሁዶች በጀልባ ሲጓጓዙ

ቤተ-እስራኤላውያንን በተመለከተ መላ ምቱ ብዙ ነው።

ስለ ቤተ እስራኤላውያን አመጣጥ ሁለት ማብራሪያዎች ይቀርባሉ። አንደኛው ንግሥት ሳባ በእየሩሳሌም ንጉሥ ሰለሞን ልትጠይቅ ሄዳ ምኒልክ ተወለደ የሚል ሲሆን፣ ይህ ግን ከአፈ ታሪክ ያልዘለለ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ።

ቤተ እስራኤላውያን የሚያምኑት እና መፅሀፍ ላይ የሰፈረው በሰባኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው ቤተ መቅደስ በፈረሰበት ጊዜ ከይሁዳውያኑ መሰደድ ጋር ተያይዞ የመጣውን ነው።

ከአስራ ሁለቱ ነገዶችም መካከል ዳን ተብሎ የሚጠራው ነገድ ወደ ግብፅ ተሰደደ፤ ከግብፅም የናይል ወንዝን በመከተል ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሰፍረዋል።

በኢትዮጵያ በሚኖሩበት ወቅት ፈላሻ ወይም ካይላ የሚል ስያሜ ተሰጥቷዋል። ፈላሻ የሚለው ቃል 'ሊፍሎሽ' ከሚለው የእብራይስጥ ቃል የመጣ መሆኑን እና ትርጉሙም ከቦታ ቦታ የሚዞር ቋሚ ቦታ የሌለው ማለት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ።

ካይላም እንዲሁ 'ክሂላ' የሚለው ከእብራይስጥ የተወሰደ ሲሆን፣ አንድ ላይ የሚሆን በማኅበር የሚሄድ ማለት ቢሆንም ለዘመናት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩባቸው አካባቢ እንደ ስድብ ይውል ነበር።

የእስራኤል መንግሥትን ምሥረታን ተከትሎ ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል የሚያደርጉት ጉዞ የተጀመረ ቢሆንም፣ ለረጅም ዘመናት በተደጋጋሚ ጥናት በማድረግ አይሁዶች ኢትዮጵያ እንዳሉ ከዚያ 50 የሚሆኑ ወጣቶችን ወደ አውሮፓ እንደተወሰዱ ይነገራል።

የደርግ መንግሥት ወድቆ ለውጥ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ በኋላ ኦፐሬሽን ሰለሞን (ዘመቻ ሰለሞን) በአውሮፓውያኑ 1991 ከ14 ሺህ 600 በላይ ቤተ እስራኤላውያን በ36 ሰዓታት ውስጥ ተወስደዋል።

ከዚያ በኋላም አነስ ያሉ ቤተ እስራኤላውያን የተጓጓዙባቸው ዘመቻዎች የነበሩ ሲሆን ክንፈ ዮና፣ ሸአሪት ይሁዲ ኢትዮጵያ (የቀሩ ይሁዲዎችን መውሰድ) የሚሉም ተካሂደዋል።

ከዚያም በኋላ በአዲስ አበባ እና በጎንደር ተመዝግበው ወደ እስራኤል ለመጓዝ የሚጠባበቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራኤላውያን ይገኛሉ።

የእስራኤል የቅርብ ጊዜ ስታትስቲክስ መረጃ እንሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ኑሯቸውን በዘላቂነት አደላድለው የሚገኙ 150 ሺህ ያህል ቤተ እስራኤላውያን ይገኛሉ።