በሱዳን የተኩስ አቁሙ ቢራዘምም ውጊያው እንደቀጠለ ነው ተባለ

ታትሟል

የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የደረሱትን የተኩስ አቁም ስምምነት ለተጨማሪ ሦስት ቀናት ማራዘማቸውን አስታወቁ።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለ72 ሰዓታት የተራዘመው ጎረቤት አገራት፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የተባበሩት መንግሥታት ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተከትሎ ነው።

ይሁን እንጂ በዋና መዲናዋ ካርቱም አሁንም ከባድ ውጊያ መቀጠሉ ተሰምቷል።

ተፋላሚ ኃይሎቹ የተኩስ አቁምም ስምምነት ላይ ሲደርሱ ይህ ቢያንስ ለአራተኛ ጊዜ ቢሆንም ስምምነቶቹ አልጸኑም።

ሆኖም ቀደም ብሎ የነበሩ የተኩስ አቁም ስምምነቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ያስቻሉ ሲሆን በርካታ አገራትም ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ሙከራ አድርገዋል።

በጦሩ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ለሁለት ሳምንታት የቀጠለው ውጊያ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።

በሱዳን ቀድሞ የተገባው የተኩስ አቁም ስምምነት ዛሬ እኩለ ሌሊት ላይ ያበቃል።

በመሆኑም ትናንት ምሽት የሱዳን መደበኛ ጦር የተኩስ አቁሙ እንዲራዘም የተስማማ ሲሆን ተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ከሰዓታት በኋላ ስምምነቱን ተቀብሏል።

በሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት አገራት የማሸማገል ጥያቄ እያቀረቡ ነው።

ደቡብ ሱዳንም የሰላም ስምምነቱን ለማዘጋጀት ሃሳብ ያቀረበች ሲሆን ጦሩም ለንግግሩ ተወካዮችን ለመላክ ተስማምቷል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን፣ ዋሽንግተን የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም በትጋታ እየሰራች እንደነበር ገልጸው፣ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባይሆን እንኳን ግጭትን ይቀንሳል ብለዋል።

ሆኖም በኋላ ላይ የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሪን ጂን ፔሬ፣ ውጊያው በማንኛውም ሰዓት ሊባባስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አርኤስኤፍ እና የዓይን እማኞች ጦሩ በካርቱም አቋሙን መለወጡን ተናግረዋል።

የሲቪል አስተዳደሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርያም አል ሳዲቅ፣ የተኩስ አቁም ቢደረግም ነዋሪዎች አሁንም ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ካርቱም ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሆነው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የተኩስ አቁም የሚሉት ስምምነት እየሆነ ላለው ነገር የፈየደው ነገር የለም። የአየር ድብደባው ቀንም ሌሊትም በሚባል ሁኔታ እየተፈፀመ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ራዲዮ 4 ተናግረዋል።

ዋና መዲናዋን ማዕከል አድርጎ የቆየው ውጊያው በምዕራብ ዳርፉር ክልል እና ሌሎች ግዛቶች እንደተስፋፋም ተዘግቧል።

በውጊያው እስካሁን ቢያንስ 512 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 4 ሺህ 200 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ተጎድተዋል። ነገር ግን ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ተነግሯል።

የዓለም ጤና ድርጅት የበሽታዎች መቀሰቀስ እና የጤና አገልግሎት እጦት ምክንያት የሟቾቹ ቁጥር በርካታ ሊሆን ይችላል ብሏል።

ውጊያ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በርካታ ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ እና በካርቱም ከ60 በመቶ በላይ የጤና ተቋማት አገልግሎት ማቆማቸውን የጤና ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ ነፍስ አድን ድርጅት (አይአርሲ) ኃላፊ እና የቀድሞው የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ዴቪድ ሚሊባንድ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የውጭ ዜጎችን ለማውጣት እየተጣደፉ በሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ግን ችላ ብለዋል ሲሉ ወቅሰዋል።

“በእርግጥ መውጣት የሚፈልጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ማውጣት አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን የቀሩት 45 ሚሊዮን ሕዝቦችስ ?” ሲሉም ጠይቀዋል።

“በሱዳን 15 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታ ይፈልጋል። እንደ አይአርሲ አሁን ጥሪ የማቀርበው በሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎች ወጥተዋል ማለት ችግሩ ተፈትቷል ማለት እንዳልሆነ ነው” ሲሉም አክለዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የጠቀሰው የጦሩ መግለጫ ጦሩ አብዛኞቹን የሱዳን ክልሎች መቆጣጠሩን ፤ነገር ግን በተወሰነ የዋና መዲናዋ አካባቢዎች ነገሮች አሁንም ውስብስብ መሆናቸውን ገልጿል።

ቢቢሲ ጦሩ አገኘሁት ያለውን ድል ማረጋገጥ አልቻለም።

ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ የውጭ አገራት ዜጎቻቸው በቻሉት ፍጥነት አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ እያሳሰቡ ነው።

የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጄን-ፒዬር አሜሪካውያን በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ሐሙስ ምሽት ላይ አሳስበዋል።

የውጭ አገራት ዜጎችን የማስወጣት ሒደት እንደቀጠለ ቢሆንም አሁንም በርካታ የውጭ አገራት ዜጎች በሱዳን እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ይገኛሉ።

የሱዳን ዜጎችም ዋና መዲናዋን ለቀው እየወጡ ሲሆን የምግብ አቅርቦት፣ ውሃ እና ነዳጅ እጥረት አጋጥሟቸዋል።

በሱዳን መደበኛ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ውጊያ የተቀሰቀሰው በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 15 ነበር።

የጦሩ መሪ ጀነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀነራል መሐመድ ሃምዳን ደጋሎ ወይም ሄምቲ አገሪቷ ወደ ሲቪል አስተዳዳር በምትገባባት ሒደት በተለይም 100 ሺህ የሚሆኔት የአርኤስኤፍ አባላት ወደ ጦሩ በሚቀላቀልበት የጊዜ ሰሌዳ ላይ አልተስማሙም።

ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች፣ ከ20 ዓመታት በፊት በዳርፉር በተፈፀመ የጦር ወንጀል በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሊጠየቁ የሚችሉበት አድል በመኖሩ በሱዳን ሥልጣን እናጣለን የሚል ስጋት ውስጥ ናቸው።