ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዛሬ የሚከበረው የአባቶች ቀን እንዴት ተጀመረ?
ዛሬ የአባቶች ቀን ነው። የአባቶች ቀን የፈረንጆቹ ሰኔ [ጁን] ወር በገባ በሶስተኛው ሳምንት ዕሁድ ይከበራል።
ይህ ቀን በዚህ ዓመት ዛሬ ላይ ውሏል። በፈረንጆቹ ጁን 19 በኢትዮጵያውን አቆጣጠር ደግሞ ሰኔ 12 ማለት ነው።
ቀኑ የአባቶች ነው። እንደአባት የሚታዩ አሳዳጊዎች ወይም አያቶችም ይከበሩበታል። ይህ ቀን በተለያዩ ሀገራት በተለያየ አኳኋን ይከበራል።
የአባቶች ቀን እንዴት ተጀመረ?
የእናቶች ቀን መከበር የጀመረው ከመቶ ዓመታት በፊት ነው። የአባቶች ቀን ግን ይህን ያህል ዕድሜ የለውም። መከበር የጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው።
ቀኑ እንዴት መከበር እንደጀመረ ጥርት ያለ መረጃ የለም።
ሆኖም መነሻው አሜሪካ ሊሆን እንደሚችል የሚገመት ሲሆን ‘እንዴት ተጀመረ?’ የሚለው ጥያቄ ሲነሳ በርከት ያሉ ምላሾሽች ይከተላሉ።
በጣም ታዋቂው እና ለእውነቱ ይጠጋል ተብሎ የሚታሰበው ግን ሶኖራ ሉሲ ስማርት በዋሽንግተን ጀመረችው የሚለው ነው።
እንዴት ጀመረችው?
6 ልጆች የነበሯት የሶኖራ ሉሲ ስማርት እናት በወሊድ ምክንትያት ሞተች። ይህን ጊዜ አባቷ ቤተሰቡን ማስተዳደር ጀመረ።
ሷሮና እንደእናት በሚያሳድጋቸው የአባቷ ሁኔታ ልብ ተነካ። እናም በ1909 በቤተክርስቲያን ውስጥ ስለ እናቶች ቀን ሰማች። የአባቶች ቀን መከበር አለበት የሚል ሀሳብ በልቧናዋ ተጠነሰሰ። ይሄንን ሀሳቧን ለሌሎች አጋራች።
በርከታ የአከባቢዋ ቀሳውስት ሀሳቡን ወደዱት። ተቀበሉት። ታዲያ በተከታዩ ዓመት [በፈረንጆቹ 1910] በጁን 19 ወይም ሰኔ 12 የመጀመሪያ እና ይፋዊ ያልሆነው የአባቶች ቀን እንደተከበረ ይታመናል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ1966 የአሜሪው ፕሬዝዳንት ሊንደን ጆንሰን የሰኔ ወር ሶስተኛ ሳምንት ዕሁድ የአባቶች ቀን ነው ሲሉ አወጁ።
ሀገራት እንዴት ያከብሩታል?
ታይላንድ
በታይላንድ የአባቶች ቀን የሚከበረው በፈንጆቹ ታህስሳ 5 ነው። ይህ ቀን በሀገሪቱ ትልቅ ከፍ ያለ አድናቆት የሚሰጠው ንጉስ ቡምቢል አይዱላዴጅ የልደት ቀን ነው። ንጉሱ የታይላንድ አባት ተብሎ ይጠራል።
ቀኑን በባህላዊ መንገድ ቢጫ ቀለማት ያላቸው ልብሶች በመልበስ ይከበራል።
በእለቱ አባቶች እና አያቶች አሁንም ብዙም የማይዘወሩት ካና የተሰኙ የአበባ አይነት ይበርከትላቸዋል።
ሜክሲኮ
በሜክሴኮ የአባቶች ቀን አሜሪካ እና በርካታ ሀገራት በሚያከብሩበት ተመሳሳይ ቀን ይከበራል።
በዕለቱ ‘የአባቶች ቀን ሩጫ’ በሚል 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የሩጫ ውድድር ይካሄዳል። ልጆችም ከአባታቸው ጎን በውድድሩ ይሳተፋሉ።
ጀርመን
በጀርመን አባቶች ቀኑን ከልጆቻቸው ጋር አያሳልፉትም። ይልቅ እርስ በእራሳቸው ይገናኛሉ። ተገናኝተው የጋራ የእግር ጉዞ ያደርጋሉ። አንዳንደድ ጊዜ ደግሞ ምግብ እና መጠጥ የተሞሉባቸውን ጋሪዎች በመጎተት ያሳልፋሉ።
ኔፓል
በኔፓል ጣፋጭ ነገሮችን ያበረክታሉ። አልፎ አልፎ አባቶች ልጆቻቸውን በመመረቅ ይከብሩታል።
አባቶቻቸው የሞቱባቸው ልጆች ደግሞ በአንድ ቅዱስ እንደሆነ በሚታመን ስፍራ በመገኘት ጸሎት እና ምስጋና ያደርሳሉ።
ፈረንሳይ
በፈረንሳይ የአባቶች ቀን በባህላዊ መንገድ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይከበር ነበር። ሆኖም በ1900 ለውጥ ተደርጎበታል።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ለአባቶች ጽጌሬዳ አበባን ጨምሮ የተለያዩ ስጦታዎች ይበርከታሉ።
በሀገሪቱ በህትይወት ላሉ አባቶች ቀይ ጽጌሬዳ አበባ መስጠት የተለመደ ነው። አባታቸው የሞቱባቸው ደግሞ ነጭ ጽጌሬዳ አበባ በመቃብራቸው ላይ ያኖራሉ።
መልካም የአባቶች ቀን!