ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አበባ ምርት፡ በዘንድሮው የፍቅረኞች ቀን ከአበባ ምርት ከፍተኛ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ
በዘንድሮው የፍቅረኞች ቀን ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከላከችው የአበባ ምርት ከፍተኛ ገቢ ማግኘቷ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ኢትዮጵያ በዘንድሮው የፍቅረኞች ቀን 3 ሺህ ቶን አበባ ወደ ውጭ መላኳንና ከዚህም 55 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በዋጋም በመጠንም ጭማሬ ማሳየቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ በዘንድሮው ገበያ የአበባ ዋጋ የ20 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።
ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
በአውሮፓ ባጋጠመው የነዳጅ ዋጋ መጨመር ብዙ አበባ አምራቾች የሚጠበቀውን ያህል ማምረት አለመቻላቸው እንዲሁም ከአፍሪካ በተለይ ከኬንያ የሚላከው አበባ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ በገጠመው የካርጎ ችግር ምክንያት ብዙ አበባ አለመላኩ የኢትዮጵያ አበባ ተጠቃሚ እንዲሆን ካስቻሉ ምክንያቶች ዋና ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ወደ ውጭ ከላከችው የአበባ ምርት 530 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያገኘች ሲሆን ይህም አገሪቷ ወደ ውጭ ከምትልከው አጠቃላይ ገቢ 15 በመቶ የሚሆነውን እንደሚይዝ አቶ ቴዎድሮስ አስታውሰዋል።
በየዓመቱ በአውሮፓውያኑ ፌብሩዋሪ 14 የሚከበረው የቫላንታይንስ ቀን (የፍቅረኞች ቀን) ሰዎች ለፍቅረኛቸው፣ ለትዳር አጋራቸው፣ ለእጮኛቸው አበባ እና ሌሎች ስጦታዎችን በማበርከት ፍቅራቸውን የሚገልጹበት ዕለት ነው።
ይህንን ዕለት ጨምሮ እስከ ሰኔ ያሉት ጊዜያት የእናቶች፣ የሴቶች እና የአባቶች ቀን የሚከበሩበት በመሆኑ ከፍተኛ የአበባ ሽያጭ የሚከናወንበት ወቅት ነው።
በመሆኑም ከፍቅረኞች ቀን በኋላ ባሉት ጊዜያት ከፍተኛ የአበባ ሽያጭ እንደሚከናወን ይጠበቃል ብለዋል ዳይሬክተሩ።
የኢትዮጵያ አበባዎች የሚላኩት ወደየትኞቹ አገራት ነው?
የኢትዮጵያ የአበባ ምርቶች በአጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻ አገራት ይላካሉ።
በአሁኑ የፍቅረኞች ቀን በብዛት የተላኩት ወደ አውሮፓ ነው። ኔዘርላንድስ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን ፣ ጣሊያን እና ሌሎችም አገራት።
ወደ ሰሜን አሜሪካ እና ካናዳ ፣ ወደ ሩቅ ምሥራቅ ደግሞ ጃፓንና ኮሪያ እንዲሁም አውስትራሊያም ተልከዋል።
በዋናነት የኢትዮጵያ የአበባ ምርት ትልቁ መዳረሻ ግን የዓለም የአበባ ንግድ ማዕከል የምትባለው ኔዘርላንድስ እና ጀርመን መሆናቸውን አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።
ኔዘርላንድስ በዓለም አቀፍ ደረጃ አበባ ከሚያመርቱ እና ከሚልኩ አገራት ግንባር ቀደም ናት። ኔዘርላንድስ ብዙ አበባ ባታመርትም ወደ ውጭ በመላክና ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ቀዳሚውን ሥፍራ ትይዛለች።
ከዚያም ኮሎምቢያ፣ ኢኳዶር፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ይከተላሉ።
ኢትዮጵያ ከአምስቱ የአበባ አምራችና ላኪ አገራት ተርታ የገባችው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ ምቹ የግብርና አካባቢ፣ በቂ አምራች ኃይል እና የውሃ ኃብት መኖሩ እንዲሁም ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለአውሮፓ ገበያ ምቹ ቦታ ላይ መገኘቷ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በማጓጓዙ በኩል ትልቅ ሥራ መስራቱ እዚህ ደረጃ ውስጥ እንድትካተት ያስቻሏት ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
አሁን ላይ ያለው የመሬት አቅርቦት ችግር ከተፈታ ከዚህም በላይ የአበባ ምርት ንግዱን ማሻሻል እንደሚቻል ጠቁመዋል። በዚህ ዘርፍ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬም በአገሪቷ ውስጥ ያለውን የወጪ እና የገቢ ንግድ ጉድለት ለመሙላት እንደሚያግዝም አክለዋል።
ለፍቅረኞች ቀን የሚፈለጉት አበባዎች ምን ዓይነት ናቸው?
ለፍቅረኞች ቀን በዋናነት የሚላከው ቀይ አበባ [ ጽጌሬዳ አበባ] ነው። ተፈላጊነቱም ሆነ ዋጋው ከሌሎች የበለጠ ነው። ዘንድሮ 20 በመቶ የዋጋ ጭማሬ አለው።
ካርኔሽን እና የበጋ አበባም በዚህ ወቅት ተፈላጊ ሲሆኑ የእነርሱ ግን ጭማሬያቸው 10 በመቶ ነው።
አሁን አሁን የፍቅረኞች ቀን በኢትዮጵያ በተለይ በከተሞች አካባቢ በድምቀት እየተከበረ ቢሆንም በአገር ውስጥ ያለው የአበባ ገበያ ግን በዋጋም በመጠንም እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።
ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ተቀዛቅዞ የነበረው የኢትዮጵያ የአበባ ንግድ ከግንቦት 2020 ወዲህ ገበያው ተነቃቅቶ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን አቶ ቴዎድሮስ አክለዋል።