ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች በየመን የባሕር ዳርቻ በሦስት ወር ውስጥ ሁለተኛውን ነዳጅ ጫኝ መርከብ አገቱ
የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ኃይል ደኅንነት ድርጅት እና የሶማሊያ የደኅንነት ባለሥልጣናት የባሕር ላይ ወንበዴዎች በኤደን ባሕረ ሰላጤ ከየመን የባሕር ዳርቻ አካባቢ አንድ የጭነት መርከብ ማገታቸውን አስታወቁ።
የዩኬ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት መርከቡ ወደ ምሥራቅ እየተጓዘ በነበረበት ወቅት "ያልተፈቀደላቸው ግለሰቦች ተሳፍረዋል" ሲል ገልጾ፣ ሌሎች መርከቦችም "በጥንቃቄ እንዲጓዙ ምክር ተሰጥቷቸዋል" ብሏል።
የሶማሊያ ከፊል ራስ ገዝ ግዛት የሆነችው የፑንትላንድ ባለሥልጣናት አጥቂዎቹ ሶማሊያውያን መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህ ከግንቦት ወር ወዲህ በየመን የባሕር ዳርቻ ላይ የተፈጸመ ሁለተኛው የመርከብ እገታ ሲሆን የመጀመርያዋ ኤምቲ ዩሬካ የታገተችው በቃና ወደብ አቅራቢያ ነበር።
በሚያዝያ ወር ሌሎች ሁለት መርከቦች በሕንድ ውቅያኖስ ላይ በባሕር ወንበዴዎች ታግተዋል።
የባሕር ላይ ወንበዴዎች ሌሎች ያልተሳኩ በርካታ የእገታ ሙከራዎች እያደረጉ መሆናቸውን እና ይህም በዚህ የውሃ ክፍል ላይ ዳግም እያንሰራሩ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
በአንድ ወቅት በተከታታይ እገታ ይፈጸምባቸው በነበሩ የውሃ ክፍሎች ላይ እስከ ዛሬ ሦስት ዓመት ድረስ የተለያዩ አገራት የባሕር ኃይል አባላትን ያካተተ የተቀናጀ የጸጥታ ዘመቻ ከተደረገ በኋላ ሊጠፉ ተቃርበው ነበር።
ሦስት የፑንትላንድ የደኅንነት ባለሥልጣናት ለቢቢሲ እንዳስረዱት አርብ ዕለት የታገተችው መርከብ ኤምቲ አሳና የተባለች የጭነት መርከብ ናት።
ወደ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ከመሄዳቸው በፊት ከፑንትላንድ የወደብ ከተማ ጋራካድ አቅራቢያ ካለ ሩቅ አካባቢ የተነሱ ሰባት ታጣቂዎች በእገታው ላይ መሳተፋቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
የኤምቲ አሳና መርከብ የታንዛኒያን ባንዲራ የምታውለበልብ ሲሆን ወደ ፑንትላንድ ቦሳሶ ወደብ እየተጓዘች እንደነበር ተገልጿል።
የሕንድ ውቅያኖስ በሶማሊያ የሚካሄደውን የፀረ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ዘመቻ በሚቆጣጠረው የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ኃይል ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት ሲሆን በኤደን ባሕረ ሰላጤ በኩል ያለው ጥበቃ ግን የላላ ነው።
እንደ ፑንትላንድ ባለሥልጣናት ገለጻ ከሆነ ይህ አሁን የባሕር ላይ ወንበዴዎች በተደጋጋሚ እገታ ለመፈጸማቸው አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል።