ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምሥራቅ ጎጃም ታጣቂዎች በ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች መኪና ላይ በከፈቱት ተኩስ አምስቱን አቆሰሉ
በአማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈትነው በሚመለሱ ተማሪዎች ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ አምስት ተማሪዎች መጎዳታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በወረዳው የሚገኙ እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የቢቢሲ ምንጮች ሐሙስ ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም. ከምሽቱ 12፡30 አካባቢ በቢቡኝ ወረዳ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ወደ ቀያቸው በመኪና በሚመለሱ ተማሪዎች ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
የወረዳው ባለሥልጣናት ጥቃት ከደረሰባቸው ተማሪዎች መካከል ሁለቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ቀሪዎቹ ሦስቱ ግን ቀላል የሚባል ጉዳት እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል።
በጥቃቱ የተጉዱት እና ቀላል እና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በቢቡኝ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆናቸውንም ጨምረው አስረድተዋል።
ቢቢሲ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን በጥቃቱ ዙሪያ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
ጥቃቱ የደረሰው በወረዳው በወይኗ ቀበሌ ሞሰባ ሽሜ አቦ "ግርገራድ" የሚባል አካባቢ መሆኑን የሚገልጹት የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ ታጣቂዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት በዞኑ እና በወረዳው ውስጥ በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ ጨምረው ተናግረዋል።
አካባቢው ሙሉ በሙሉ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር መሆኑን የተናገሩት አንድ የወረዳው ኃላፊ ተማሪዎቹ ባለፈው ሳምንት ለፈተና በሚሄዱበት ወቅትም ተኩስ ተከፍቶባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
"ሲመለሱ ደግሞ ከመደበኛ የመከላከያ ኃይል ጋር መጋፈጥ ያቃተው ጽንፈኛ ቡድን ራሱን አደራጅቶ የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ተማሪዎችን ነው ወደ ቤተሰቦቻቸው እየተመለሱ ባሉበት ተኩስ ከፍቶ ከአምስት ያላነሱ ተማሪዎች ላይ ጉዳት ያደረሰው።"
ከተማሪዎቹ በተጨማሪ መኪናው ላይም ጉዳት መድረሱን ባለሥልጣናቱ ጨምረው አስረድተዋል።
በቢቡኝ ወረዳ 19 ቀበሌዎች መኖራቸውን የገለጹት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ኃላፊዎች፣ ከእነዚህ መካከል በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኙት ስድስቱ ብቻ ናቸው ብለዋል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ ነው የሚሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ኃላፊ "ሐሙስ ዕለት የተፈጸመው ጥቃት አጠቃላይ ማኅብረሰቡን ተስፋ ያስቆረጠ ነው" ብለዋል።
በወረዳው ከሚገኙ 43 ትምህርት ቤቶች መካከል "ከስምንት ያልበለጡ ትምህርት ቤቶች ናቸው ትምህርት ሲሰጡ የነበረው" ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል።
ተማሪዎቹን አሳፍሮ የነበረው መኪና በተለምዶ አይሱዙ ቅጥቅጥ የሚባለው መሆኑን የገለጹት ባለሥልጣኑ ከደብረ ማርቆስ ወደ ድጎ ጽዮን ከተማ እየተመለሱ ባሉበት ወቅት ጥቃቱ መፈጸሙን ገልጸዋል።
ከቢቡኝ ወረዳ ወደ ደብረ ማርቆስ ለመሄድ በእያንዳንዱ ቀበሌ ታጣቂዎች መኖራቸውን የሚናገሩት የአካባቢው ባለሥልጣናት ከዚህ በፊትም ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ አስታውሰዋል።
"የአሁኑን የከፋ የሚያደርገው ምንም የፖለቲካ ትርጉም የማይገባቸው የ12ኛ ክፍል ፈተናን አጠናቅቀው እየተመለሱ ያሉ ተማሪዎች ላይ መፈጸሙ ነው፤ ማኅበረሰቡ ጋር ጭምር ቁጣ እየፈጠረ ያለው በእነዚህ ምንም በማያውቁ ሕጻናት ላይ የተከፈተ ጥቃት መሆኑ ነው።"
በመኪናውን የተሳፈሩት ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን የሚናገሩት ኃላፊው በመኪናው ውስጥ 44 ተማሪዎች ተሳፍረው ነበር።
ከደብረ ማርቆስ ወደ ቢቡኝ የሚሄዱት ተማሪዎች በሰባት አውቶብስ ሆነው መንቀሳቀሳቸውን የጠቀሱት ኃላፊው ይህ ጥቃት የደረሰበት መኪና ከመጨረሻ ላይ እንደነበር ተናግረዋል።
ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው ተማሪዎች ለፈተና ወደ ማርቆስ ሲሄዱም ጉዳት ባይደርስም ተኩስ መከፈቱን ጨምረው ገልጸዋል።
የወረዳው አመራሮች ከዚህ በፊት በአካባቢው ለመንቀሳቀስ በእጀባ መሆኑን ገልጸው ተማሪዎቹ ለፈተና ሲሄዱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እጀባ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
ተማሪዎቹ ፈተናቸውን አጠናቅቀው ሲመለሱ ግን እጀባ እንዳልነበር ገልጸው፤ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ የመንግሥት ታጣቂዎቸ ቢኖሩም ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ ግን አልነበሩም ብለዋል።
ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ በቦታው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መድረሳቸውን እና ታጣቂዎቹም መሸሻቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
ከሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀሰቀሰው የአማራ ክልል ግጭት የበርካቶችን ሕይወት ሲነጥቅ በርካቶችን ለማኅበራዊ ሕይወት መመሰቃቀል መዳረጉን ነዋሪዎች ይነገራሉ።
የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በክልሉ ውስጥ ከፍርድ ውጪ ግድያ፣ በሲቪሎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ ከሕግ ውጪ እስራት፣ አስገድዶ ስወራ፣ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ እንደሚፈፀም ይገልፃሉ።
በክልሉ እየተካሄደ ባለው ግጭት የተነሳ አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው።
በበርካታ የክልሉ አካባቢ ባለው የፀጥታ ስጋት ምክንያት በተሽከርካሪዎች እና በተጓዦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጸም ቆይቷል።