ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዋይት ሐውስ የአርጀንቲና ቡድን የፎክላንድን ባነር በማሳየቱ የተነሳነውን ውዝግብ ተከላከለ
ዋይት ሐውስ የአርጀንቲና እግር ኳስ ቡድን አባላት እንግሊዝን አሸንፈው የአገራቸውን የፎክላንድ ይገባኛል ጥያቄ በመደገፍ ባነር በማውለብለባቸው ውዝግብ ከተነሳ በኋላ የመናገር ነጻነት አላቸው ሲል ተከላከለ።
ፊፋ የአርጀንቲና ቡድን ድርጊትን ተከትሎ ፖለቲካዊ ይዘት ያለውን ሃሳብ በማንጸባረቃቸው መመሪያ ጥሰዋል በሚል ቅጣት ሊጥል ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
አርብ ዕለት የዋይት ሐውስ የፊፋ ግብረ ኃይል ኃላፊ አንድሪው ጁሊያኒ ተጫዋቾቹ ያደረጉት ስህተት እንደሆን ሲጠየቁ፣ ቡድኑ በአሜሪካ ውስጥ "ያንን ዓይነት ሃሳብ የማንጸባረቅ" ዕድል እንዲሁም አቅም ነበረው በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ፊፋ ምርመራ እንዲያደርግ ጥሪ ካቀረበ በኋላ የሚሰጡ አስተያየቶች በጉዳዩ ላይ የተፈጠረውን ውዝግብ የበለጠ ሊያባብሱት ይችላሉ።
ፎክላንድስ የተባለው የእንግሊዝ የባሕር ማዶ ግዛት በደቡብ ምዕራብ አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በእንግሊዝ እና በአርጀንቲና መካከል የሉዓላዊነት ውዝግብ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።
የአርጀንቲና ተጫዋቾች ረቡዕ ዕለት በተደረገው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ "ላስ ማልቪናስ ሰን አርጀንቲናስ" የሚል ባነር ይዘው ነበር፤ ትርጉሙም "ፎልክላንዳውያን አርጀንቲናዊ ናቸው" ማለት ነው።
ጁሊያኒ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ በአሜሪካ ሕገ መንግሥት ውስጥ የተካተቱትን የመናገር ነፃነት ጥበቃዎች ጠቅሰው "እዚህ በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በሕገመንግሥታችን ላይ በተቀመጠው የመናገር ነጻነት እናምናለን" ብለዋል።
ዳውኒንግ ስትሪት ፊፋ ክስተቱን እንዲያጣራ የቀረበውን ጥሪ ደግፏል፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋዊ ቃል አቀባይ "የዓለም ዋንጫው የእኛ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን የፎክላንድ ደሴቶች በእርግጠኛነት የእኛ ናቸው። ለፎክላንድ ያለን ቁርጠኝነት ፈጽሞ አይናወጥም" ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ባነሩን ባሳዩት የአርጀንቲና ተጫዋቾች ላይ ሊወሰድ የሚችል ማንኛውም እርምጃ "የፊፋ ጉዳይ ነው" ሲል አክሏል።
ነገር ግን የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል መመርመር እንዳለበት በመግለጽ የንግድ ሚኒስትሩ ፒተር ካይልን አመለካከት አስተጋብቷል።
የፎክላንድ ደሴቶች መንግሥት በበኩሉ ባንዲራው "እንዳሳዘነው፤ ነገር ግን እንዳልገረመው" ገልጿል። ፊፋም "ይህንን ባህሪ በራሱ ደንብ መሰረት እንደሚያጸድቅ" ተስፋ ያደርጋል።
"ፖለቲካ ወደ ስፖርት ሲገባ ማየት አንፈልግም" ሲልም መግለጫው አክሏል።
የአርጀንቲናው ፕሬዚዳንት ሀቪየር ሚሌይ አርጀንቲና፣ እንግሊዝን 2 ለ 1 ባሸነፈችበት ታሪካዊ ጨዋታ ማግስት በሰጡት መግለጫ ተጫዋቾቻቸውን በፅኑ ተከላክለዋል።
የአርጀንቲና ተጫዋቾች ከድሉ በኋላ "ማልቪናስ (ፎክላንድ) የአርጀንቲና ናቸው" የሚል ባነር በማሳየታቸው ፊፋ ምርመራ ሊጀምር ሲል የአርጀንቲና ፕሬዚዳንት ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንቱ "ይህ ሙሉ በሙሉ የስፖርት ስሜት ነው። ጉዳዩ የገንዘብ ቅጣት የሚያስከትል ከሆነ አርጀንቲና ቅጣቱን በደስታ ትከፍላለች። ሊዮኔል ሜሲም የምንጊዜም ምርጡ መሆኑን በድጋሚ ያረጋገጠበት እለት ነው" በማለት በቡድናቸው ያላቸውን ኩራት ገልጸዋል።
ፊፋ በስፖርት ሜዳ ላይ የፖለቲካ መልዕክቶችን በጥብቅ ይከለክላል።
አርጀንቲና ከብሪታንያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ያለባትን ደሴት በመጥቀስ ባነር ማሳየቷ የዲሲፕሊን ደንብ ጥሰት በመሆኑ፣ ማኅበሩ ከ5,000 እስከ 20,000 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ይጥላል ተብሎ ይገመታል።
ይሁንና ቅጣቱ የገንዘብ ብቻ በመሆኑ አርጀንቲና እሁድ ዕለት ከስፔን ጋር የምታደርገው የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ የመሳተፍ መብቷ የተጠበቀ ነው።
"ደሴቶቹና ሕዝቦቻቸው ስለእንግሊዝና አርጀንቲና በሚያደርጉት እያንዳንዱ ውይይት እንደ የፖለቲካ እግር ኳስ ጥቅም ላይ እንዲውሉ አንፈልግም"
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 የፎክላንድ ደሴቶች ሕዝብ የዩኬ የውጭ አገር ግዛት ሆነው እንዲቀጥሉ ከፍተኛ ድምጽ ሰጥቷል።
የአርጀንቲና ምክትል ፕሬዝዳንት ቪክቶሪያ ቪላርሩኤል ረቡዕ ዕለት ቡድኑ ካሸነፈ በኋላ በኤክስ ገጻቸው ላይ "ሌላ ጨዋታ ብቻ አልነበረም" ሲሉ የአርጀንቲና ወታደሮች የሚመስሉ ቪዲዮዎችን አስፍረዋል።