በቀጥታ ስርጭት ወቅት አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ንብረት የተዘረፈው አሜሪካዊ ፓስተር ተከሰሰ

ታትሟል

በአሜሪካ ኒው ዮርክ የቀጥታ ስርጭት ወቅት ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ጌጣጌጦች የተዘረፈው አሜሪካዊው ሰባኪ በማጭበርበር እና በማስገደድ ወንጀል ክስ ተመሰረተበት።

ፓስተር ላሞን ዋይትሄድ ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ ውድ ሰዓቶች፣ አልማዞች እና ሌሎች የከበሩ ድንጋዮች ነበር የተዘረፉበት።

አሁን ግን ፓስተሩ የወንጀል ክስ እንደተመሰረተበት የፍርድ ቤት ሰነዶች አመልክተዋል።

የአንዲት ምዕመንን የጡረታ ቁጠባን በማጭበርበር፣ ከአንድ ነጋዴ ደግሞ ገንዘብ በጉልበት ለመውስድ በመሞከር እና ኤፍቢአይን በመዋሸት ነው ክስ የቀረበበት።

ፓስተሩ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የታሰረ ሲሆን የፌዴራል ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

ከምዕመናን ተወስዷል የተባለው ገንዘብ ወደ 90 ሺህ ዶላር እንደሚጠጋ እና “ቅንጡ እቃዎች እና አልባሳትን ለመግዛት እንደዋለ” የፍርድ ቤት ሰነዱ አመልክቷል።

ፓስተሩ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 20 ዓመት ሊታሰር ይችላል።

ሰባኪው ማክሰኞ ዕለት በኢንስታግራም ገጹ ላይ “ጥፋተኛ አይደለሁም” የሚል ጽሁፍ ያሰፈረ ሲሆን፣ ለተከታዮቹ  በቀጥታ ስርጭት መልዕክትም አስተላልፏል።

ፓስተሩ ባለፈው ሐምሌ መዘረፉ ከተሰማ በኃላ “ባለጌጡ ፓስተር” የሚል ስያሜን በኒው ዮርክ መገናኛ ብዙኃን ተሰጥቶታል። በወቅቱም ዘራፊዎቹ “አያመልጡኝም” ሲል ተደምጦ ነበር።

ኒው ዮርክ ፖስት እንደዘገበው ከፓስተሩ በሌቦች ከተዘረፉት መካከል የእሱ እና የባለቤቱ የሆኑ ሮሌክስ እና ካቫሊየር የተሰኙ ወድ ሰዓቶች እንዲሁም እያንዳንዳቸው 25 ሺህ ዶላር የሚገመቱ የአልማዝ ቀለበት እና የጆሮ ጌጥ ይገኙበታል።