ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፈረንሳይ ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች የተጣለው የማኅበራዊ ሚዲያ ክልከላ በፍርድ ቤት ታገደ
የፈረንሳይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ላይ የተጣለውን የማኅበራዊ ሚዲያ እገዳ "ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ይጥሳል" ሲል ውድቅ አደረገ።
የአገሪቱ ሕግ አውጭዎች ባለፈው ሐምሌ ወር ነበር ማኅበራዊ ሚዲያ በሕፃናት የአዕምሮ ጤና ላይ ጎጂ ተፅዕኖ ያስከትላል የሚሉ ስጋቶች መነሳታቸውን ተከትሎ ለሕጉ ድጋፋቸውን የሰጡት።
ይህም ፈረንሳይ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ በመከልከል የመጀመሪያዋ አውሮፓዊት አገር እንድትሆን አድርጓት ነበር።
ሆኖም አርብ ዕለት የሕገ መንግሥታዊ ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከመስከረም ጀምሮ ደረጃ በደረጃ እንደሚተገበር ቃል የገቡለትን እገዳ ውድቅ አድርጎታል።
ፕሬዚደንቱ ለፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስቲን ሌኮርኑን የምክር ቤቱን ሁሉንም ነጥቦች ግምት ውስጥ የሚያስገባ አዲስ ረቂቅ እንዲያዘጋጁ ጠይቀዋል።
ባለፈው ወር ሕግ አውጭዎች በሕጉ ላይ ድምጽ ከሰጡ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕጉን የተወሰኑ ክፍሎች ዘጠኝ አባላት ላሉት እና የሚወጡ ሕጎች ሕገ መንግሥቱን ያከበሩ እንደሆኑ ለሚያረጋግጠው ምክር ቤት ልከው ነበር።
ሕገ መንግሥታዊው ምክር ቤቱም ሕጉ "የሐሳብ ልውውጥን እና የመናገር ነፃነትን የሚጥስ" መሆኑን እንዳረጋገጠ ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የኦንላየን አገልግሎት ለማግኘት የዕድሜ ማረጋገጫ ማቅረብ እንዳለባቸው በሚጠይቀው መስፈርት ላይ ያለውን ስጋት አንስቷል። " ሕጉ አስፈላጊ የሆኑ የሕግ ከለላዎችን አላዘጋጀም" ብሏል።
የፕሬዚዳንት ማክሮን ቢሮ በበኩሉ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ካሳለፈ በኋላ " መንግሥት አዲስ ረቂቅ ለማዘጋጀት በሚቻለው ፍጥነት እንደሚሰራ" ጠቅሶ፣ ፕሬዚደንቱ ማሻሻያውን በ2027 መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጿል።
ከመስከረም ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የነበረው ሕግ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንት መክፈት እንዳይችሉ የሚከለክል ሲሆን ለሁሉም አዲስ አካውንቶች ማረጋገጫዎች እንዲቀርቡም ይጠይቃል።
ይህም ከጥር ወር ጀምሮ ቀድሞ በተከፈቱ ሁሉም አካውንቶች ላይ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር ይገልጻል።
ተቃዋሚዎች የሕጉ ተጨባጭነት ላይ ጥያቄ ሲያነሱ የነበረ ሲሆን ግላዊነትን በመጠበቅ ረገድ እንዲሁም የእድሜ ማረጋገጫ መንገዶች ውጤታማነት፣ ታዳጊዎች ሕጉን የመጣስ አደጋዎች እና ሕጉ የተዘጋጀበት እና ተግባራዊ ለማድረግ የታሰበበት ጊዜ ፍጥነት ላይ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አውስትራሊያ ታኅሳስ ወር ላይ ማኅበራዊ ሚዲያን ከ16 ዓመት በታች ላሉ ታዳጊዎች በመከልከል የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች። ሆኖም በርካቶች አሁንም የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን መጠቀማቸውን እንደቀጠሉ በስፋት ይታወቃል።
ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥም ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ሕግ በአውሮፓ እየተስፋፋ መጥቷል።
ግንቦት ወር ላይ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን፣ በኅብረቱ አባል አገራት ውስጥ ላሉ ታዳጊዎች "ማኅበራዊ ሚዲያን ማዘግየት" የሚል ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን አዲስ ሕግ በወራት ውስጥ ሊወጣ እንደሚችል ተናግረዋል።
በዩናይትድ ኪንግደምም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር፣ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ከጥር 2027 ጀምሮ ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም እንደሚከለከሉ ሰኔ ወር ላይ አስታውቀው ነበር።