ቴሌግራም በአውስትራሊያ "ሽብርን የሚደግፉ" ይዘቶችን ባለማጥፋቱ ተከሰሰ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ቴሌግራም "ሽብርን የሚደግፉ" ይዘቶችን ሳያጠፋ በመቅረቱ በአውስትራሊያ ተከሰሰ።

በክራይስትቸርች የተፈጸመውን የጅምላ ተኩስ የተመለከቱ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን ጨምሮ "ሽብርን የሚደግፉ" ይዘቶች ቴሌግራም አለማጥፋቱን የአውስትራሊያ የበይረ መረብ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ገልጿል።

የበይረ መረብ ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ጁሊ ኢንማን-ግራንት እንደተናገሩት፤ ቴሌግራም እስከ 38 ሚሊዮን ዶላር ሊቀጣ ይችላል።

በቴሌግራም ተሰራጭቷል የተባለው አክራሪ ይዘት ከ2019 የክራይስትቸርች መስጊድ ጥቃት እና ከ2022 የኒው ዮርክ፣ ባፋሎ ጥቃት ጋር የተያያዘ መሆኑ ተገልጿል።

በአውስትራሊያ የአይሁዳውያን ፌስቲቫል ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ "መተግበሪያዎች ድንጋጌዎችን እንዲከተሉ ማድረግ" ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጠው ጁሊ ኢንማን-ግራንት ገልጸዋል።

ለፌደራል ፍርድ ቤት በሚያቀርቡት ክስ አማካኝነት "አገልግሎቱ እንዲቋረጥ" እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ቴሌግራም፣ መሥሪያ ቤቱ ያወጣውን የበይነ መረብ ጥንቃቄ መመሪያዎች አለማክበሩን ገልጸዋል።

"በቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ካሉ በጣም አስከፊ የአክራሪ ጥቃቶች ጋር የሚያያዙ ይዘቶችን" ማኅበራዊ ሚዲያው ሳያጠፋ መቅረቱን ጠቁመዋል።

"የትኛውም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሕግ በላይ አይደለም" ያሉት ጁሊ ኢንማን-ግራንት፤ "ይህ ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።

ከአንድ ቀን በፊት ሩሲያ የቴሌግራም መሥራች ፓቫል ዱኖቭን "የሽብር ድርጊትን በማመቻቸት" ከስሳለች።

ቴሌግራም በዩክሬን የደኅንነት ባልደረቦች ሰዎችን ለመመልመል ውሏል በሚል ተከስሷል።

በአውሮፓውያኑ 2024 ዱኖቭ በፈረንሳይ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እንደተደረገበት ይታወሳል።

በወቅቱ ቀርቦበት የነበረው ክስ መተግበሪያው ወንጀልን እንዲቀንስ ተገቢው ቁጥጥር አልተደረገበትም በሚል ነበር።

የፈረንሳይ ምርመራ ቢቀጥልም ዱኖቭ ከወራት በኋላ ተለቅቋል።

የአውስትራሊያ የበይረ መረብ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ኃላፊዋ እንደተናገሩት፤ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2024 ላይ ቴሌግራም ሽብርተኛነት እና የአክራሪነት ድርጊትን ለመግታት ምን እርምጃ ወስዷል የሚለው ላይ ምርመራ ተደርጓል።

ቴሌግራም "ለአምስት ወራት ያህል ምላሽ አልሰጠም" ሲሉም ተናግረዋል።

ቴሌግራም ቆየት ብሎ አስተያየቱን ቢሰጥም "ጨለምተኛውን አሠራር" ቀጥሏል ብለዋል። በመተግበሪያው ላይ አክራሪ ይዘቶች ማግኘት "በጣም ቀላል" መሆኑንም ገልጸዋል።

"ተጠቃሚዎች አክራሪ ይዘትን እንዲላመዱ እና መደበኛ አድርገው እንዲወስዱ ያደርጋል። አንዳንዴም መተግበሪያው ጥቃት ለማቀነባበር ይውላል" ሲሉም አክለዋል።

የቴሌግራም ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፤ መተግበሪያው "ከፍተኛ" የፀረ ሽብር እርምጃዎችን ይወስዳል። ጥረቶቹ "በአግባቡ የተሰነዱ" መሆናቸውን በመጥቀስም "እነዚህን ክሶች አንቀበልም። በፍርድ ቤት የምንከራከር ይሆናል" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በየካቲት 2025 አውስትራሊያ ቴሌግራምን አንድ ሚሊዮን ዶላር ቀጥታለች።

በወቅቱ የቀረበበት ክስ የሕጻናትን ጥቃት በመከላከል እና አክራሪ ይዘቶችን በመገደብ ረገድ ለቀረበበት ጥያቄ በአፋጣኝ ምላሽ አለመስጠቱን ይመለከታል።